ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፲፯


ምዕራፍ ፲፯

አልማ የአቢናዲን ቃል አመነ እናም ፃፈ—አቢናዲ በእሳት ተቃጥሎ ሞተ—አቢናዲ በገዳዮቹ ላይ በሽታንና በእሳት ሞትን ተነበየ። በ፻፵፰ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ አቢናዲ ይህን ንግግሩን ሲጨርስ፣ ንጉሱ ካህናት እንዲወስዱትና እንዲገድሉት አዘዘ።

ነገር ግን ከእነርሱ መካከል አልማ የሚባል ሰው ነበር፤ እርሱም ደግሞ የኔፊ ትውልድ ነበር። እርሱም ወጣት ነበር፣ እናም አቢናዲ በተናገራቸው ቃላት ያምን ነበር፣ አቢናዲ ስለጥፋታቸው በእነርሱ ላይ ስለመሰከረው ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ ንጉሱ በአቢናዲ እንዳይቆጣ፣ ነገር ግን በሰላም እንዲሄድ ለመነው።

ነገር ግን ንጉሱ ይበልጥ ተቆጣ፤ እናም አልማ ከመካከላቸው ውጥቶ እንዲጣል አደረገ፣ እናም እርሱን ይገድሉት ዘንድ አገልጋዮችን ላከ።

ነገር ግን ከፊታቸው ሸሸ፣ እናም እንዳያገኙት ተደበቀ። እናም ለብዙ ቀናት ተሰውሮ አቢናዲ የተናገረውን ቃላት ሁሉ ፃፈ

እናም እንዲህ ሆነ ንጉሱ ጠባቂዎቹ አቢናዲን እንዲከቡትና እንዲወስዱት አደረገ፤ እናም አሰሩትና ወደ ወህኒ ቤት ጣሉት።

እናም ከሶስት ቀናት በኋላ ከካህናቱ ጋር በመመካከር፣ በድጋሚ በፊቱ እንዲቀርብ አደረገ።

እናም እንዲህ አለው፥ አቢናዲ፣ በአንተ ላይ ወንጀል አግኝተናልና ለሞት ብቁ ነህ።

አንተ እግዚአብሔር ራሱ በሰው ልጆች መካከል ይመጣል ብለሃልና፤ እናም አሁን፣ በዚህ የተነሳ እኔንና ህዝቤን በተመለከተ የተናገርከውን መጥፎ ቃላት ካላስተባባልክ ትገደላለህ።

አሁን አቢናዲም አለው፥ እልሀለሁ፣ ይህንን ህዝብ በተመለከተ የተናገርኩት ቃላት አላስተባብልም፣ እውነት ናቸውና፣ እናም እውነተኛነቱን ታውቁ ዘንድ በእናንተ እጅ እንድወድቅ ለራሴ ፈቅጃለሁ።

አዎን፣ እናም እስከሞቴም ድረስ እሰቃያለሁ፣ ቃሌንም አላስተባብልም፣ እነርሱም በእናንተ ላይ እንደምስክርነት ይቆማሉ። እናም እኔን የምትገድሉኝ ከሆነ ንፁህ ደም አፍሳችኋልና፤ ይህም በመጨረሻው ቀን ደግሞ በእናንተ ላይ እንደምስክር ይቆማል።

፲፩ እናም አሁን ንጉስ ኖህ እርሱን ሊለቀው ነበር፣ ምክንያቱም ቃሉን ፈርቶ ነበርና፤ የእግዚአብሔር ፍርድ በእርሱ ላይ ይመጣል ብሎ ፈርቶ ነበርና።

፲፪ ነገር ግን ካህናቱ በእርሱ ላይ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ንጉሱን አዋርዷል በማለት ከሰሱት፣ ስለዚህ ንጉሱ በቁጣ በእርሱ ታወከ፣ እናም እርሱ ይገደል ዘንድ አሳልፎ ሰጠው።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ወሰዱትና አሰሩት፣ እስኪሞት ድረስ በእስር ጭሮር አሰቃዩትም።

፲፬ እናም አሁን ነበልባሉ መለብለብ ሲጀምረው፣ እንዲህ በማለት ጮኸባቸው፥

፲፭ እነሆ፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ሁሉ እንዲህ ይሆናል፣ ዘሮቻችሁ እኔ የተሰቃየሁትን ሥቃይ፣ እንዲሁም በእሳት የመሞት ስቃይን፣ ብዙዎች እንዲሰቃዩ ያደርጋሉ፤ እናም ይህ የሚሆነው በጌታ በአምላካቸው ደህንነት በማመናቸው ነው።

፲፮ እናም እንዲህ ይሆናል በክፋታችሁ የተነሳ በሁሉም አይነት በሽታ ትሰቃያላችሁ።

፲፯ አዎን፣ እናም በሁሉም ክንድ ትመታላችሁ፣ እናም የዱር መንጋ በዱርና ኃይለኛ አውሬዎች እንደሚነዱ፣ ወዲህና ወዲያ ትነዳላችሁም ትበተናላችሁም።

፲፰ እናም በዚያ ቀን ትታደናላችሁ፣ በጠላቶቻችሁ ክንድም ትወሰዳላችሁ፤ እናም ከዚያ በኋላ የሞትን ስቃይ በእሳት እኔ እንደተሰቃየሁ ትሰቃያላችሁ።

፲፱ እንደዚህም እግዚአብሔር ህዝቡን በሚያጠፉት ላይ በቀልን ያደርጋል። አቤቱ አምላኬ ነፍሴን ተቀበል።

እናም አሁን፣ አቢናዲ እነኚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ በእሳት ሞቶ ወደቀ፤ አዎን፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ባለመካዱ እንዲሞት በመደረጉ፣ የቃሉን እውነታ በሞቱ አተመው።