ምዕራፍ ፰
አሞን የሊምሂን ህዝብ አስተማረ—ስለ ሀያ አራቱ ያሬዳውያን ሰሌዳዎች ተማረ—የጥንት ታሪኮች በባለራዕዮች መተርጎም ይችላሉ—ከባለራዕይነት የበለጠ ስጦታ የለም። ፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ሊምሂ ለህዝቡ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ፣ ብዙ ነገሮችን ተናግሯል እናም እኔ ጥቂቶቹን ብቻ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ፅፌአለሁ፤ በዛራሔምላ ምድር የነበሩት ወንድሞቹን በተመለከተ ለህዝቡ ሁሉንም ነገር ነገራቸው።
፪ እናም አሞን በህዝቡ ፊት ቆሞና፣ ዜኒፍ ምድሪቱን ለቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እራሱም እንኳን ከምድሪቱ እስከወጣበት ድረስ የተከናወኑትን ሁሉ እንዲናገር አደረገ።
፫ እናም ደግሞ ንጉስ ቢንያም ያስተማራቸውን የመጨረሻ ቃላት ነገራቸው፣ እናም እርሱ የተናገራቸውን ቃላት ሁሉ ይረዱት ዘንድ ለንጉስ ሊምሂ ህዝብም ገለፀላቸው።
፬ እናም እንዲህ ሆነ ይህን ሁሉ ካደረገ በኋላ፣ ንጉስ ሊምሂ ህዝቡን አሰናበተ፣ እናም እያንዳንዳቸው ወደየቤታቸው እንዲመለሱ አደረገ።
፭ እናም እንዲህ ሆነ ህዝቡ የዛራሔምላን ምድር ለቀው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን ታሪክ የያዙትን ሰሌዳዎች አሞን ያነባቸው ዘንድ በፊቱ እንዲቀርቡ አደረገ።
፮ አሁን፣ አሞን ታሪኩን እንዳነበበ፣ ቋንቋውን መተርጎም እንደሚችሉ ንጉሱ ጠየቀው እናም አሞንም እንደማይችል ነገረው።
፯ እናም ንጉሱ እንዲህ አለው፥ በህዝቤ ስቃይ በማዘኔ፣ ከህዝቤ አርባ ሶስት የሆኑት የዛራሔምላን ምድር ያገኙ ዘንድ፣ ከባርነትም እንዲያስለቅቁን ለወንድሞቻችን አቤት እንልበት ዘንድ ወደ ምድረበዳው እንዲጓዙ አደረግሁ።
፰ እናም እነርሱ ለብዙ ቀናት በምድረበዳ ውስጥ ጠፉ፣ ነገር ግን ትጉህ ነበሩ፣ እናም የዛራሔምላን ምድር አላገኙትም ነበር፣ ነገር ግን በብዙ ውኃዎች መካከል ባለች ምድር አቋርጠው ተጉዘው፣ በሰዎችና፣ በአውሬዎች አጥንት፣ እናም ደግሞ በሁሉም አይነት የግንብ ፍርስራሽ የተሸፈነች ምድር አግኝተው፣ እንደ እስራኤልም ሰራዊት ብዙ ህዝቦች የነበሯትን ምድር ካገኙ በኋላ ወደዚህች ምድር ተመለሱ።
፱ እናም ለምስክርነት የተናገሯቸው ነገሮች እውነት መሆናቸውን ለማሳየት በፅሁፍ የተሸፈኑ ሀያ አራት ሰሌዳዎችን አቀረቡ፣ እናም እነርሱ ንፁህ ወርቆች ነበሩ።
፲ እናም እነሆ፣ ደግሞ፣ ትልቅ ነሀስ፣ እንዲሁም መዳብ፣ እናም ፍፁም ጥሩ የሆኑትን ጥሩሮች አመጡ።
፲፩ እናም እንደገና፣ እጀታቸው የጠፉና፣ ስለታቸው ዝጎ የተበላሹ ጎራዴዎችን አመጡ፤ እናም በምድሪቱ ቋንቋውንም ሆነ በሰሌዳዎቹ ላይ ያሉትን ፅሁፎች መተርጎም የሚችል ማንም አልነበረም። እናም እንዲህ እልሃለሁ፥ አንተ መተርጎም አትችልምን?
፲፪ እናም በድጋሚ እንዲህ እልሃለሁ፣ መተርጎም የሚችልስ ማንንም አታውቅምን? ይህ ታሪክ ወደራሳችን ቋንቋ እንዲተረጎም እፈልጋለሁና፤ ምናልባት እነዚህ ሰሌዳዎች የመጡባቸው ስለጠፉት ህዝቦች ቅሪት እውቀት ይሰጡናልና፤ ወይንም ምናልባት ስለጠፉት እነዚህ ሰዎች ግንዛቤ ይሰጡን ይሆናልና፤ እናም የመጥፋታቸውን መንስኤ ለማወቅ እፈልጋለሁ።
፲፫ አሁን አሞን እንዲህ አለው፥ ንጉስ ሆይ መዝገቡን መተርጎም ስለሚችለው ሰው በእርግጠኝነት ልነግርህ እችላለሁ፤ ምክንያቱም እርሱ የሚመለከትበትና በጥንት ጊዜ የነበሩትን መዛግብት ሁሉ ለመተርጎም የሚችልበት አለው፣ እናም ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ነገሮቹም ተርጓሚዎች ተብለው ይጠራሉ፣ እናም ካልታዘዘ በስተቀር ማንም ሰው በእነርሱ መመልከት አይችልም፣ አለበለዚያ ማድረግ የሌለበትን ይሻልና፣ ይጠፋል። እናም በእነርሱ ለመመልከት የታዘዘ ሰው ባለራዕይ ተብሎ ይጠራል።
፲፬ እናም እነሆ፣ በዛራሔምላ ምድር ያለው የህዝቡ ንጉስ እነዚህን ነገሮች እንዲሰራ የታዘዘ ነው፣ እናም ይህ ታላቅ ስጦታ ከእግዚአብሔር ያገኘው ነው።
፲፭ እናም ንጉሱ ባለራዕይ ከነቢይ የበለጠ ነው አለ።
፲፮ እናም አሞን ባለራዕይ፣ ገላጭና፣ ደግሞም ነቢይ ነው አለ፤ እናም ከዚህ ይበልጥ ታላቅ የሆነ ስጦታ የእግዚአብሔር ኃይል ከሌለው በቀር ማንም ሰው ሊኖረው አይችልም፤ ነገር ግን ሰው ከእግዚአብሔር የተሰጠ ታላቅ ኃይል ሊኖረው ይችላል።
፲፯ ነገር ግን ባለራዕይ ያለፉ ነገሮችን ሊያውቅ ይችላል፣ ደግሞም ሊሆኑ የሚችሉትን ነገሮች ሊያውቅ ይችላል፣ እናም በእነርሱ አማካይነት ሁሉም ነገሮች ይገለጣሉ፣ ወይም ሚስጥሮች ይታወቃሉ፣ የተደበቁ ነገሮች ወደብርሃን ይመጣሉ፣ እናም የማይታወቁ ነገሮች በእነርሱ እንዲታወቁ ይሆናሉ፤ እናም ደግሞ በእነርሱ ካልሆኑ በቀር የማይታወቁትን ነገሮች እንዲታወቁ ይደረጋሉ።
፲፰ በዚህም እግዚአብሔር ሰው በእምነት ታላቅ ድንቅ ነገሮችን ይሰራ ዘንድ ዘዴውን አቅርቦለታል፤ ስለዚህ እርሱም ለእንደእርሱ አይነት ህያው ፍጡር ጠቃሚ ይሆናል።
፲፱ እናም አሁን፣ አሞን እነዚህን ቃላት መናገሩን እንደጨረሰ ንጉሱ እጅግ ተደሰተና፣ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል ምስጋናውን አቀረበ፥ እነዚህ ሰሌዳዎች ታላቅ ሚስጥር እንደያዙ ጥርጥር የለውም፣ እናም እነዚህ ተርጓሚዎች ለሰዎች ልጆች ሁሉንም እንደዚህ አይነት ሚስጥሮች ለማብራራት ሲባል ያለጥርጥር ተዘጋጅተዋል።
፳ አቤቱ የጌታ ስራ እንዴት ድንቅ ነው፤ እናም ከህዝቦቹስ ጋር ምን ያህል ጊዜ ይሰቃያል፤ አዎን፣ የሰው ልጅ ግንዛቤስ እንዴት ዕውርና የማይደረስበት ነው፣ ምክንያቱም ጥበብን አይሹምና፣ እርሷም በእነርሱ ላይ እንድትገዛ አይፈልጉምና!
፳፩ አዎን፣ እነርሱ ከእረኛው እንደሸሸው እንዳልተገራው መንጋ ናቸው፣ ይበተናሉም፣ ይነዳሉም፣ እናም በጫካ አውሬዎችም ይበላሉ።