ሸክማቸውን ማቅለል እንዲችሉ
በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ ያለው ልዩ ሸከም በቅዱስ መሲህ ብቁነትም በሚያሳየው፣ በምህረት፣ እና በጸጋ ላይ እንድንመካ ይረዳናል።
በተጋባበት በመጀመሪያ አመታት ትልቅ መኪና እንደሚያስፈልገው የሚያስብ ውድ ጓደኛዬ ነበር። ባለቤቱ ግን ይህን አዲስ መኪና የሚያስፈልገው ሳይሆን የሚፈልገው እንደሆነ እርግጠኛ ነበረች። በሚያስቀው በዚህ የባል እና ሚስት ንግግር በዚ አይነት ግዢ ላይ ያለውን ጥቅም እና ጉዳትን ለማመዛዘን እንዲጀምሩ አደረጋቸው።
“ውዴ፣ አራቱንም ጎማዎች ማንቀሳቀስ የሚችል የጭነት መኪና ያስፈልገናል።”
እንዲህም ጠየቀችው፣ “አዲስ የጭነት መኪና ለምን እንደሚያስፈልገን ታስባለህ?”
እርሱም ጥያቄዋን መልካም መልስ ነው ብሎ ባሰበበት መለሰላት። “በከፍተኛ መዕበል ውስጥ ለልጆቻችን ወተት ቢያስፈልገንስ፣ እናም ወደ ሱቅ ለመሄድ የምንችለው በጭነት መኪናው ብቻ ቢሆንስ?”
ባለቤቱም በፈገግታ እንዲህ መለሰች፣ “አዲስ የጭነት መኪና ከገዛን፣ ለወተትመግዣ ገንዘብ አይኖረንም---ስለዚህ በመዕበል ወደሱቅ ለመሄድ ለምን ትጨነቃለህ!”
ከጊዜም በኋላ መመካከራቸውን ቀጠሉ እና በመጨረሻም የጭነት መኪናውን ለመግዛት ወሰኑ። አዲሱን መኪና ከገዙ በኋላ፣ ጓደኛዬ የጭነት መኪናው እንዴት ጠቃሚ እንደሆነ እና ለመግዛት የፈለገበትን ምክንያት ለማሳየት ፈለገ። ስለዚህ በቤታቸው የሚጠቀሙበት እንጨት ለመቁረጥ እና ለማምጣት ወሰነ። የመከር ጊዜ ነበር፣ እናም እንጨት ለማግኘት በፈለገበት ተራራ ላይ በረዶ ወርዶ ነበር። በተራራ መንገድ ላይ እየነዳ እያለ፣ በረዶው ጥልቅ እየሆነ መጣ። የሚያንሸራትተው መንገድ አደገኛ እንደሆነ ጓደኛዬ ተገነዘበ፣ ነገር ግን በአዲሱ የጭነት መኪና ተመክቶ መጓዝ ቀጠለ።
በሚያሳዝን ሁኔታም፣ ጓደኛዬ መሄድ በበረዷማው መንገድ ላይ እሩቅ ተጓዘ። እንጨት ለመቁረጥ በወሰነበት ቦታ ላይ ከመንገዱ ወጥቶ ሲሄድ፣ መኪናው መነቃነቅ በማይችልበት ሁኔታ ላይ ሆነ። የመኪናው አራት ጎማዎች መሽከርከር ጀመሩ። ከዚህ አደገኛ ቦታ እራሱን እንዴት እንደሚያድን አላዋቀም ነበር። አፍሮም ተጨንቆም ነበር።
ጓደኛዬም፣ “እዚህ ተቀምጬ አልጠብቅም” በማለት ወሰነ። ከመኪናው ወረደ እና እንጨት መቁረጥ ጀመረ። የመኪናውን የሁዋላ ክፍል በከባድ ጭነት ሞላው። ከዚያም ጓደኛዬ ከበረዶው ለመውጣት እንደገና ለመሞከር ወሰነ። የመኪናውን ሞተር ካስነሳ በኋላ ወደፊት ቀስ በቀስ መሄድጀመረ። በቀስታ የጭነት መኪናው ከበረዶው ወጥቶ ወደ መንገዱ ገባ። በመጨረሻም ወደ ቤትለመሄድ ነጻ፣ ደስተኛ እና ትሁት ሰው ነበር።
የግል ሸክማችን
ከጓደኛዬ፣ ከጭነት መኪና፣ እና ከእንጨት ታሪክ ለመማር የሚቻለውን አስፈላጊ ትምህርት ለማስተማር ስሞክር የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ከእኔ ጋር እንዲሆን እጸልያለሁ። ከበረዶው እንዲወጣ፣ ወደ መንገድ እንዲገባ፣ እና ወደፊት እንዲሄድ ያስቻለው ቢኖር የእንጨቱ ጭነት ነበር። ወደ ቤተሰቡ እና ቤቱ እንዲመለስ ያስቻለውም ጭነቱ ነበር።
እያንዳንዳችን ሸክም አለን። የግላችን ሸክም ማድረግ የሚገቡን ነገሮችና እድሎች፣ ሀላፊነቶች እና እድሎች፣ ስቃዮችና በረከቶች፣ ምርጫዎች እና መገደቢያዎች ያሉት ነው። ሸከማችንን በየጊዜው እና በጸሎት ስናመዛዝነው ሁለት የሚመሩ ጥያቄዎች የሚረዱ ይሆናሉ፥ “ያለኝ ሸከም በክርስቶስ እምነት በቀጥተኛው እና በቀጭን ጎዳና ወደፊት እንድገፋና ወደፊት የምሄድበትን የማይገድብ የመንፈስ ሀይል የሚሰጠኝ ነውን? ሸከሜ ብቁ መንፈሳዊ ሀይል ሰጥቶኝ በመጨረሻም ወደ ሰማይ አባት ቤት ለመመለስ እንድችል የሚያስችል ነውን።
አንዳንዴ በስህተት ደስታ የሸክም አለመኖር ነው ብለን እናስብ ይሆናል። ነገር ግን ሸክም ለደስታ እቅድ አስፈላጊ ክፍል ነው። የግላችን ሸክም መንፈሳዊ ሀይልን ማመንጨት ስለሚገባው በጣም ከሚያስፈልጉ ነገሮች ከሚያውኩ እና ከሚለዩ ብዙ ጥሩ ከሆኑ ግን ጠቃሚ ያልሆኑ ነገሮችን የህይወታችን አካል ማድረግ የለብንም ።
የኃጢያት ክፍያ አጠናካሪ ሀይል
አዳኝ እንዲህ አለ፥
“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።
“ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤
“ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” (ማቴዎስ 11፥28–30)።
ቀንበር በሁለት በሬዎች ወይም ሌሎች እንስሳት መካከል ሆኖ ሸክምን እንዲጎትቱ የሚያስችላቸው የእንጨት ማማ ነው። ቀንበር እንስሳት ጎን ለጎን ሆነው ስራዎችን ለማከናወን አብረው እንዲሰሩ የሚያስችላቸው ነው።
ጌታ ለእየግለሰብ የሰጠውን “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ” በማለት የጋበዘበትን አስቡት። ቅዱስ ቃል ኪዳናትን መስራት እና መጠበቅ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በቀንበር ያስተሳስረናል። በዚህም፣ አዳኝ በእርሱ እንድንመካ እና፣ ምንም እንኳን ጥረታችሁ ከእርሱ ጋር እኩል ያልሆኑ እና ለመመሳሰል የማይችሉ ቢሆኑም፣ ከእርሱም ጋር አብረን እንድንሰራ ይጠራናል። በሟች ጉዞዋችን እርሱን ስናምን እና ከእርሱ ጋር ሸከማችንን ስንጎትት፣ በእውነትም ቀንበሩ ልዝብ ሸክሙም ቀሊል ነው።
በብቻችን አይደለንም እናም በምንም ብቸኛ መሆን አያስፈልገንም። በየቀኑ ህይወታችን ከሰማይ እርዳታ ጋር ወደፊት ለመግፋት እንችላለን። በአዳኝ የኃጢያት ክፍያ “ከእራሳችን በላይ” የሆነ ችሎታ እና ጥንካሬ ለመቀበል እንችላለን (“Lord I Would Follow Thee,” Hymns,, no. 220)። ጌታ እንዳወጀው፣ “ስለዚህ፣ በጉዞአችሁ ቀጥሉ እና ልቦቻችሁ ይደሰቱ፤ እነሆ፣ እና አስተውሉ፣ እኔ እስከመጨረሻም ከእናንተ ጋር ነኝና” (ት. እና ቃ. 100፥12)።
በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ አሙሎን አልማን እና ህዝቡን ያሳደደበትን ምሳሌ አስቡት። የጌታ ድምጽ በዚህ ስቃያቸው ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣ፥ “እራሳችሁን አቅኑም መልካም መፅናኛ ይኑራችሁም፤ ከእኔ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን አውቀዋለሁና፤ ከህዝቤም ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ እናም ከባርነት አስለቅቃቸዋለሁ” (ሞዛያ 24:13).
ለመዳን የተሰጠው የተስፋ ቃል ከቃል ኪዳኖች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተመልከቱ። የተቀበሉ እና በታማኝነት የተከበሩ ቃል ኪዳኖች እና በትክክለኛው የክህነት ስልጣን የተከናወኑ ስርዓቶች በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ሊገኙ የሚችሉ በረከቶችን በሙሉ ለመቀበል አስፈላጊ ናቸው። ከኃጢያት ክፍያ በረከቶች በተጨማሪ፣ በክህነት ስርዓቶች የአምላክነት ሀይል በወንዶች እና በሴቶች በስጋ ይታያልና። (ት. እና ቃ. 84:20–21ተመልከቱ).
ስለአልማ እና ህዝቡ ታሪክ በማሰብ የሚቀጥለውን ቁጥር ስናነብ፣ አዳኝ “ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” (ማቴዎስ 11፥30) ያለበትን አስታውሱ።
“እናም …በጀርባችሁም እንኳን ሊሰማችሁ እንዳይቻላችሁ፣ በትከሻችሁ ላይ ያለውን ሸክም አቀልላችኋለሁ” (ሞዛያ 24፥14)።
ብዙዎቻችሁ ሸከማቸው ወዲያው በድንገት እና በመጨረሻ ይወሰድላቸዋል ብለን እናስብ ይሆናል። የሚቀጥለው ቁጥር ግን እንዴት ሸከማቸው እንደተቃለለ ይገልጻል።
“እናም አሁን እንዲህ ሆነ በአልማና በወንድሞቹ ላይ የሆነው ሸክም ቀለለላቸው፣ አዎን፣ ሸክማቸውን ማቅለል እንዲችሉ እናም በደስታና በትዕግስት ለጌታ ፈቃድ ተቀባይ እንዲሆኑ ጌታ ብርታትን ሰጥቷቸዋል” (ሞዛያ 24፥15፤ ትኩረት ተጨምሮባቸዋል)።
ፈተናዎች እና ችግሮች ከህዝቡ ወዲያው አልተወሰደም። ነገር ግን አልማ እና ተከታዮቹ ተጠናከሩ፣ እናም ተጨማሪ ያላቸው ችሎታ ሸከማቸው ቀላል እንዲሆን አደረገላቸው። እነዚህ መልካም ሰዎች በኃጢያት ክፍያ እንደ ወኪል እንዲሆኑ (ት. እና ቃ. 58፥26–29) እና ጉዳያቸው ላይ ለውጥ ለማምጣት እንዲችሉ አደረጋቸው። እናም “በጌታ ሀይል” (የሞርሞን ቃላት 1፥14፤ ሞዛያ 9፥17፤ 10፥10፤ አልማ 20፥4)፣ አልማ እና ህዝቡ ወደ ዛራሄምላ ምድር ወደ ደህንነት እንዲሄዱ ተመሩል።
የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ የአዳም ውድቀትን ከማሸነፉ በተጨማሪ ለግል ኃጢያቶቻችን እና መተላለፍ ስርየት ይሰጠናል፣ ነገር ግን የኃጢያት ክፍያው ደግሞም መልካም እንድናደርግ እና ከስጋዊ ችሎታችን በላይ የተሻልን እንድንሆን ያስችለናል። ስህተት ስንሰራ እና በህይወታችን የኃጢያትን ውጤት ለማሸነፍ እርዳታ ሲያስፈልገን፣ አዳኝ በሚያድነው ሀይሉ ንጹህ ለመሆን እንድንችል አድርጓል። ነገር ግን የኃጢያት ክፍያው ታዛዥ፣ ብቁ፣ ትዕዛዛትን ለማክበር ለሚጠነቀቁ፣ እና ከሆኑበት የተሻለ ለመሆን እና በታማኝነት ለማገልገል ለሚጥሩ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችም እንደሚሆን ደግሞም እንረዳለን? ይህን የኃጢያት ክፍያ አጠናካሪ አስተያየት በሙሉ ሳንረዳው ሸከማችንን በእራሳችን ቆራጥነት እና ስነ ስርዓት እና ውስን እንደሆነ በምናውቀው ችሎታችን በብቻችን መሸከም እንደምንችል በስህተት እናምናለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደምድር ለእኛ ለመሞት መምጣቱን ማወቅ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ጌታ በኃጢያት ክፍያው በኩል እና በመንፈስ ቅዱስ ሀይል፣ ህይወት ለእኛ ለመስጠት፣ ሊመራን ብቻ ሳይሆን ሊያጠናክረን እና ሊፈውሰን ፍላጎት እንዳለው ማወቅም ያስፈልገናል።
አዳኝ ህዝቡን ይረዳል
አልማ አዳኝ ለምን እና እንዴት ችሎታ እንዲኖረን እንደሚያደርግ ገልጿል፥
“እናም በመከራና በሁሉም ዓይነት ህመምና ፈተናዎች በመሰቃየት ይሄዳል፤ የህዝቡን ህመምና በሽታ በራሱ ላይ ይወስዳል የሚለውን ቃል ይፈፀም ዘንድ ይህ ይሆናል።
“እናም ህዝቡን ያሰረውን የሞት እስር ይፈታ ዘንድ ሞትን በራሱ ላይ ይወስዳል፣ እናም በስጋ አንጀቱ በምህረት ይሞላ ዘንድ፣ በስጋ ህዝቡን ከድካሙ እንዴት እንደሚረዳ ያውቅ ዘንድ ድካማቸውን በራሱ ላይ ያደርጋል” (አልማ 7፥11–12)።
በዚህም አዳኝ የተሰቃየው ለእኛ ኃጢያት እና መተላለፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለስጋዊ ህመማችን እና ስቃያችን፣ ለደካምነታችን እና ለጉድለታችን፣ ለፍርሀታችን እና ለንዴታችን፣ ተስፋ ለምንቆርጥበት፣ ለጸጸታችን፣ ተስፋ ለሚያስቆርጠን፣ ኢ-ፍትሀዊ ድርጊት ለሆኑት እና አግባብ ላልሆኑት በሙሉ ነው።
በሟች ህይወት እናንተ ወይም እኔ የሚያጋጥመን አዳኝ በመጀመሪያ ያላጋጠመው ምንም የስጋ ህመም፣ ምንም የመንፈስ ቁስል፣ ምንም ሀዘን ወይም የልብ መሰበር፣ ምንም አቅመ ደካምነት ወይም ድክመት የለም። በደካምነት “ማንም ይህ ምን እንደሆነ አያውቅም፤ ማንም አይገባውም” በማለት ታለቅሱ ይሆናል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ በፍጹም ያውቀዋል እና ይገባዋል፣ ምክንያቱም ከእኛ በፊት የእኛን ሸክም ተሰምቶታል እናም ተሸክሞታልና። የመጨረሻውን ዋጋ ስለከፈለ እና ያን ሸክም ስለተሸከመ( አልማ 34:14 ተመልከቱ)፣ ፍጹም ሀዘናችን ይሰማዋል እናም የምህረት ክንዱን ወደእኛ ለመዘርጋት ይችላል። ለኛ ለመድረስ፣ ለመንካት፣ ለመርዳት፣ ለመፈወስ፣ እና ለመሆን ከምንችለው በላይ እንድንሆን ለማጠናከር እና በእራሳችን ሀይል በመመካት ማድረግ ከምንችለው በላይ ለማድረግ እንድንችል ለመርዳት ይችላል። በእርግጥም፣ ቀንበሩ ልዝብ ሸክሙም ቀሊል ነው።
ግብዣ፣ የተስፋ ቃል፣ እና ምስክር
የግል ሸከማችሁን ስታመዛዝኑ ስለአዳኝ የኃጢያት ክፍያ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት እንድታጠኑ፣ እንድትጸልዩበት፣ እንድታሰላስሉበት እጋብዛችኋለሁ። በስጋዊ አዕምሮአችሁ የኃጢያት ክፍያን ብዙ ነገሮች በሙሉ ለመረዳት አንችልም። ነገር ግን የኃጢያትክፍያን ብዙ አተያየቶችን መረዳት እንችላለን እንዲሁም ያስፈልገናል።
ለጓደኛዬ፣ የእንጨት ጭነቱ ህይወት የሚያድን ሀይል ሰጠው። ባዶ የነበረው የጭነት መኪና፣ ምንም እንኳን ሞተሩ አራቱን ጎማዎች ለማነቃነቅ የሚችልበት ሀይል ቢኖረውም፣ በበረዶ ውስጥ ለመሄድ አልቻለም። ሀይል ለማግኘት ከባድ ጭነት ያስፈልግ ነበር።
ጭነቱ አስፈላጊ ነበር። ጓደኛዬ ከነበረበት እንዲወጣ፣ ወደ መንገድ እንዲገባ፣ ወደፊት እንዲገፋ፣ እና ወደ ቤተሰቡ እንዲመለስ ሀይል የሰጠው ጭነቱ ነበር።
በእያንዳንዳችህ ህይወት ውስጥ ያለው ልዩ ሸክም በቅዱስ መሲህ ብቁነትም በሚያሳየው፣ በምህረት፣ እና በጸጋ ላይ እንድንመካ ይረዳናል (2 ኔፊ 2፥8)። አዳኝ ሸክማችንን ለመቋቋም እንድንችል (ሞዛያ 24:15ተመልከቱ)እንደሚረዳን እመሰክራለሁ እናም ቃል እገባለሁ። በቅዱስ ቃል ኪዳኖች ከእርሱ ጋር በቀንበር ስንተሳሰር እና በህይወታችን ችሎታ የሚሰጠንን የኃጢያት ክፍያ ስንቀበል፣ ያለንበት ሁኔታ እንዲቀየርልን ለመጸለይ ሳይሆን፣ ካለንበት ሁኔታ ለመማር፣ መቀየር ለመቻል፣ ወይም ለመቀበል እንፈልጋለን እናም እንጸልያለን። የሚሰሩ ወኪሎች እንጂ የሚሰራባቸው እቃዎች አንሆንም (2 ኔፊ 2፥14 ተመልከቱ)። በመንፈስ ሀይል እንባረካለን።
በአዳኝ የኃጢያት ክፍያ በኩል እያንዳንዳችን የተሻለ እንሆን እና እናድርግ። ዛሬ ሚያዝያ 6 ቀን ነው። በራዕይ በኩል ዛሬ አዳኝ የተወለደበት ቀን እንደሆነ እናውቃለን። ሚያዝያ 6ም የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የተመሰረተችበት ቀን ነው። (See D&C 20:1; Harold B. Lee, “Strengthen the Stakes of Zion,” Ensign, July 1973, 2; Spencer W. Kimball, “Remarks and Dedication of the Fayette, New York, Buildings,” Ensign, May 1980, 54; Discourses of President Gordon B. Hinckley, Volume 1: 1995–1999 [2005], 409.)በዚህ ልዩ እና ቅዱስ ሰንበት ቀን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛችን እንደሆነ ምስክሬን አውጃለሁ። ህያው ነው እናም እኛን ያጸዳል፣ ይፈውሳል፣ ይመራል፣ ይጠብቃል፣ እናም ያጠናክራል። ስለእነዚህ ነገሮች የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።