2022 (እ.አ.አ)
አዲስ የተወለደ ሕፃን ተስፋ
ታህሳስ 2022 (እ.አ.አ)


የአካባቢ አመራር መልዕክት

አዲስ የተወለደ ሕፃን ተስፋ

ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማይ አባት ለእርሱ የሰጠውን ተልእኮ ፈጽሟል። እኛ የእሱን ምሳሌ እንድንከተል እና የሰማይ አባት ለእኛ የሰጠንን ተልዕኮ እንድንፈጽም ይጋብዘናል።

ባለፈው ዓመት የተወለዱ ሦስት አዳዲስ የልጅ ልጆችን በማቀፍ በዚህ ባለፈው ዓመት ደስታ አግኝቻለሁ። ዓይኖቻቸውን ስመለከት በንፁህነታቸው፣ በንጽህናቸው እና ምድራዊ ህይወታቸውን ሲጀምሩ ይዘው በሚመጡት ተስፋ ተደንቂያለሁ።

የአዲስ ህጻን መወለድ በተለይም ደስታን እና አድናቆትን፣ በዓልን እና ተስፋን ያመጣል። ተስፋው የሕፃኑ ህይወት አዲስ እድል እና የበለጠ ደስታን እና ፍስሃን ስለሚያመጣ ነው። ለቤተሰብ እና ለጓደኞች—በተለይም ለወላጆች—ንፁህ የሆነው አዲስ ህፃን ምድራዊ ጉዞውን ሲጀምር የአዲሱን ህይወት ተአምር መመልከቱ አስደናቂ ነው።

የንጉሣዊ ልጅ መወለድ ለአዲስ ዕድል ከተሰጠው ተስፋ በተጨማሪ የሚጠበቁ ነገሮችን ያመጣል። የመንግስቱ ህዝቦች ቀጣይነት ያለው ያልተቋረጠ ንግሥናን ማየት ይፈልጋሉ። ይህ በተለይ ጥበበኛ፣ ደግ እና በሕዝባቸው ተወዳጅ ለሆኑ ንጉሥ እና ንግሥት እውነት ነው።

ሁሉን የሚያውቅ፣ አፍቃሪ የሰማይ አባት መንግሥት ዜጎች ለሆኑት፣ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በሥጋ መወለድ መነገሩ ታላቅ አድናቆትንና ተስፋን ይዞ ነበር። የጥንት ነቢያት ስለዚህ የተቀባ፣ የተስፋ ልጅ፣ መሲሕ፣ የዓለም አዳኝ እና ቤዛ ስለሚሆነው ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮ ተንብየዋል።

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳይያስ 9:6)።

መላዕክት በተወለደበት ምሽት እንዲህ ሲሉ አወጁ፦ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤

“ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። . . .

“ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ” (ሉቃስ 2፥10–11, 14)።

ሕፃኑ ኢየሱስ በተስፋ የተሞላ ነበር እንዲሁም ሲወለድ ለዓለም ታላቅ ተስፋን ይዞ መጣ። እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ በርግጥ መለኮታዊ ተልዕኮውን ተወጥቷል።

ያ ተልዕኮ በተለይ ምን ነበር? ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ተልእኮውን አጋርቷል፦

“እኔ የዓለም ብርሃን እና ህይወት ነኝ፤ እናም አብ ከሰጠኝ መራራ ጽዋም ጠጥቻለሁ፣ እናም የዓለምን ሃጢያት በራሴ ላይ በመውሰድም አብን አክብሪያለሁ፣ በዚህም ከመጀመሪያ ጀምሮ በሁሉም ነገሮች የአብን ፈቃድ ፈጽሜአለሁ (3ኔፊ 11:11)።

“እነሆ ወንጌሌን ሰጥቻችኋለሁ፣ እናም ለእናንተ የሰጠኋችሁ ወንጌልም ይህ ነው—ወደ ዓለም የመጣሁት የአባቴን ፈቃድ ለመፈጸም ነው፤ ምክንያቱም አባቴ ልኮኛልና።

“አባቴም በመስቀል እሰቀል ዘንድ ልኮኛል፤ እናም በመስቀል ላይ ከተሰቀልኩ በኋላ፣ ሰዎችን ሁሉ ወደራሴ አመጣ ዘንድ፣ እኔ በሰዎች እንደተሰቀልኩ በአብ አማካኝነት ሰዎች ይነሱ ዘንድ፣ መልካምም ይሁኑ መጥፎ በስራቸው እንዲፈረድባቸው በእኔ ፊት ለመቆም ይችሉ ዘንድ፣ ተሰቅያለሁ” (3 ኔፊ 27፥13–14)።

የመጣው የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ነበር።

ከላይ ባሉት ጥቅሰች ውስጥ እንደተገለጸው የአባታችንን ፈቃድ ከመፈጸም በተጨማሪ ክርስቶስ ሌላ ምን አደረገ?

አካላቸው የታመመ፣ የተሰበረ ወይም የሞቱትን ብዙዎችን አድኗል።

የዛሉትን እጆች ከፍ አድርጓል፣ ደካሞችንም አበርትቷል።

ክፉ መናፍስትን አስወጥቷል እንዲሁም ብዙዎችን ከሃጢያት ቀንበር ነጻ አውጥቷል።

ለተከታዮቹ ዘላለማዊ እውነቶችን አስተምሯል።

እንዲሁም የተልዕኮው እጅግ አስቸጋሪ ክፍል የሆነው የጌቴሴማኒ ሥቃይ፣ የጎልጎታ ስቅለት ህመም፣ ሞትን በትንሣኤ ድል የሚያደርግበት ጊዜ በደረሰ ጊዜ፣ ተከታዮቹን በድፍረት እንዲህ ብሏቸዋል፦አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን? (ዮሃንስ 18፥11)።

እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እና የመንግስቱ አባላት፣ እንድናደርግ የተጠየቅነው ነገር የቱንም ያህል ከባድ ቢሆን በግለሰብ ደረጃ ፍቃዱን ለመፈጸም የሰማይ አባታችን የሰጠንን ጽዋ ለመጠጣት የክርስቶስን ምሳሌ እየተከተልን ነው? በዚህ አመት ለክርስቶስ ምን አይነት ስጦታ ልትሰጡት እንደምትችሉ ስታስቡ፣ የሰማይ አባት የሰጣችሁን ተልእኮ እንድትፈጽሙ አሳስባችኋለሁ።

በዚህ ወቅት የአለም አዳኝ የሆነውን የሕፃኑን የኢየሱስን ልደት ስናከብር በህይወታችን ውስጥ ትልቅ ተስፋ ሊኖረን ይችላል። እግዚአብሔር፣ እርሱ እንዲፈጽመው የላከውን ተልዕኮ በድፍረት በፈጸመ ጊዜ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍጹም ምሳሌን አቅርቧል። በእርሱ ምክንያት “ደስታ ለዓለም፣ ጌታ መጥቶአል ምድር ንጉሷን ትቀበል!” የሚሉትን ቃላት በእውነት መግለጽ እንችላለን።1

ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እንደሆነ፣ እንደ ሁላችን ንጹሕ ሕፃን ሆኖ እንደተወለደ እመሰክራለሁ። ፍጹም ህይወት ኖሯል። ተሰቅሏል እንዲሁም ከሞት ተነስቷል። እርሱ ዛሬም ህያው ነው፤ ሁላችንም ወደ እርሱ እንድንመጣ ይጋብዘናል፤ በእርሱ ከታመንን እና ከተከተልነውም ይፈውሰናል እንዲሁም ይለውጠናል።

ማስታወሻዎች

  1. “Joy to the World,” Hymns, no. 201.

አትም