“የዳግም መመለስ ድምጾች፦ ቀደምት ተቀያሪዎች፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]
“ቀደምት ተቀያሪዎች፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
የዳግም መመለስ ድምጾች
ቀደምት ተቀያሪዎች
ቤተክርስቲያኗ ከመቋቋሟ በፊትም እንኳን ጌታ፣ “እርሻው ነጥቷል አዝመራውም ዝግጁ ነው” ሲል ተናግሯል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 4፥4)። ይህ ንግግር በቀጣዮቹ ወራት ብዙ የእውነት ፈላጊዎች በእግዚአብሔር መንፈስ እየተመሩ ዳግም የተመለሰችውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለመፈለግ በመጡ ጊዜ እውነትነቱ ተረጋግጧል።
እነዚህ ብዙዎቹ ቀደምት ተቀያሪዎች ዳግም የመመለስን መሰረት በመጣል ቁልፍ ሚና ነበራቸው፣ እንዲሁም ታሪካቸው እስከ ዛሬም ድረስ ለእኛ በጣም ጠቃሚ ነው። ያሳዩት እምነት እኛም በተመሳሳይ መልኩ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መለወጣችንን ለማሳየት የሚያስፈልገን አይነት እምነት ነው።
አቢጌል ካልኪንስ ለነርድ
አቢጌል ካልኪንስ ለነርድ በእድሜዋ ሰላሳ አጋማሽ ላይ ሳለች ኃጢያቷ ይቅር እንዲባልላት ፈለገች። አልፎ አልፎ መፅሐፍ ቅዱስን ታነባለች፣ ሰዎች ከክርስቲያን ቤተክርስቲያናት ወደቤቷ መጥተው ይጎበኟትም ነበር፣ ነገር ግን አንዱን ቤተክርስቲያን ከሌላው ምን እንደሚለየው ግራ ይገባት ነበር። እንዲህም አለች፣ “በአንድ ማለዳ መፅሐፍ ቅዱሴን ይዤ ወደ ጫካ ወርጄ በጉልበቴ ተንበረከኩ።” ከልቧ ወደ ጌታ ጸለየች። እንዲህም አለች፣ “በቅጽበትም ራዕይ በፊቴ ተገለጸ፣ የተለያዩ ተቋማትም ተራ በተራ በፊቴ አለፉ፣ አንድ ድምጽም ‘እነዚህ ለትርፍ የተገነቡ ናቸው’ ሲል ተናገረኝ። ከዚያም፣ ባሻገር፣ ታላቅ ብርሃንም ለማየት እችል ነበር፣ ድምጽም ከበላይ ‘ህዝብን አስነሳለሁ፣ እነርሱንም የእኔ በማድረግ እና በመባረክ እደሰታለሁ’ ሲል ተሰማኝ።” ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ አቢጌል ስለመፅሐፈ ሞርሞን ሰማች። ምንም እንኳን የመጽሃፉ ቅጂ ገና በእጇ ያልገባ ቢሆንም፣ “በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እና ሃይል የዚህን መጽሀፍ እውነትነት ለማወቅ” ፈለገች፣ ከዚያም “ወዲያውኑ መኖሩን ተገነዘበች።” በመጨረሻም መፅሐፈ ሞርሞንን ማንበብ በቻለችበት ጊዜ፣ “ልትቀበለው ዝግጁ” ነበረች።” እርሷና ባለቤቷ ላይመን በ1831 (እ.አ.አ) ተጠመቁ።
ቶማስ ቢ. ማርሽ
ቶማስ ቢ. ማርሽ ወጣት ሳለ መፅሐፍ ቅዱስን አጥንቶ ነበር፣ እንዲሁም በአንድ የክርስቲያን ቤተክርስቲያንም ተቀላቅሎ ነበር። ነገር ግን እርካታን ስላላገኘ፣ በመጨረሻም ከሁሉም ቤተክርስቲያኖች አባልነት ወጣ። እንዲህም አለ፣ “ጥልቅ የሆነ የትንቢት መንፈስ ነበረኝ፣ እናም ለአንድ [የሃይማኖት መሪ] አዲስ ቤተክርስቲያን እንደሚነሳ፣ ይህም እውነትንም በንጽህና የያዘ እንደሚሆን እንደምጠብቅ ነገርኩት።” ብዙም ሳይቆይ፣ ቶማስ ቦስተን፣ ማሳቹሴትስ ያለውን ቤቱን ትቶ ወደ ምዕራብ መጓዝ እንዳለበት መንፈሳዊ መነሳሳት ተሰማው። ሶስት ወር ያህል በምዕራባዊ ኒውዮርክ ከቆየ በኋላ የሚፈልገውን ባለማግኘቱ ወደቤቱ ጉዞውን ጀመረ። በመንገድ ላይ ሳለ አንዲት ሴት ቶማስን “ጆሴፍ ስሚዝ በተባለ ወጣት ስለተገኘ ወርቃማ መፅሐፍ” ሰምቶ እንደሆነ ጠየቀችው። በዚህ ሀሳብ ቀልቡ ተስቦ፣ ቶማስ ወዲያውኑ ወደ ፓልማይራ ተጓዘ እንዲሁም ልክ የመጀመሪያዎቹ 16 የመፅሐፈ ሞርሞን ገፆች ከማተሚያው እንደወጡ ማርቲን ሃሪስን በማተሚያ ቤቱ ውስጥ አገኘው። ቶማስም የእነዚያን የ16 ገጾች ቅጂ ይዞ እንዲሄድ ተፈቀደለት እናም ለባለቤቱ ኤሊሳቤጥ ወደ ቤት ይዟቸው ሄደ። “የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ በማመንዋ” በመጽሃፉ “በጣም ተደስታ” ነበር ሲል ያስታውሳል። በኋላም ቶማስ እና ኤሊሳቤጥ ከልጆቻቸው ጋር ወደ ኒውዮርክ ተዛወሩ እና ተጠመቁ። (ስለ ቶማስ ማርሽ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት፣ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 31ን ተመልከቱ።)
ፓርሊ እና ታንክፉል ፕራት
ልክ እንደ ቶማስ ማርሽ፣ ፓርሊ እና ታንክፉል ፕራት ከመፅሐፍ ቅዱስ የተማሩትን ወንጌል እንደተረዱት ለመስበክ ሲሉ በኦሃዮ ያለውን የተትረፈረፈ እርሻቸውን መተው እንዳለባቸው ለተሰማቸው የመንፈስ ግፊት ምላሽ ሰጡ። ፓርሊ ለወንድሙ እንደተናገረው፣ “የእነዚህ ነገሮች መንፈስ በአዕምሮዬ በጣም ከመስፈኑ የተነሳ ምንም ማረፍ አልቻልኩም።” ወደ ምስራቅ ኒው ዮርክ ሲደርሱ፣ ፓርሊ በዛ ስፍራ ለተወሰነ ጊዜ መቆየት እንዳለበት ተሰማው። ታንክፉል ግን ያለእርሱ ጉዞዋን መቀጠል እንዳለባት ተስማሙ። ፓርሊ እንዲህ በማለት ነገራት፣ “በዚህ ሃገር ክፍለግዛት ልሰራው የሚገባኝ ስራ አለኝ፣ እናም ምን እንደሆነ፣ ወይንም ምን ያህል ጊዜ ፈጅቶ መሰራት እንዳለበት አላውቅም፤ ነገር ግን ይህ ሲፈጸም እመጣለሁ።” በዚያ ስፍራ ነበር ፓርሊ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለመፅሐፈ ሞርሞን የሰማው። “ስለመጽሀፉ ለየት ያለ ፍላጎት አደረብኝ” ብሏል። የመጽሃፉን አንድ ቅጂ ጠየቀና ለሊቱን ሙሉ አነበበው። ጠዋትም “በአለም ካለው ሃብት ሁሉ የበለጠ” ዋጋ በመስጠት መጽሃፉ እውነት እንደሆነ አወቀ። በጥቂት ቀናት ውስጥ ፓርሊ ተጠመቀ። ከዚያም እርሷም ተጠምቃ ወደነበረችው ወደ ታንክፉል ተመለሰ። (ስለፓርሊ ፒ. ፕራት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 32ን ተመልከቱ።)
ስድኒ እና ፊቢ ሪግደን
ከኒው ዮርክ ወደ ምዙሪ ሚስዮን በመሄድ ላይ የነበረው ፓርሊ ፕራትና ሌሎች አገልጋይ ባልደረቦቹ ሜንቶር፣ ኦሃዮ ሲደርሱ፣ ፓርሊ ኦሃዮ በነበረ ወቅት ያውቃቸው ወደነበሩት ወደ ስድኒ እና ፊቢ ሪግደን ቤት ጎራ አሉ። ስድኒ የክርስቲያን ሰባኪ ነበር፣ እንዲሁም ፓርሊም የእርሱ ቤተክርስቲያን አባል የነበረ ሲሆን፣ እንደ መንፈሳዊ አማካሪው ይመለከተው ነበር። ፓርሊ ስለመፅሐፈ ሞርሞን እና ዳግም ስለተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ለጓደኞቹ በጉጉት ነገራቸው። ምንም እንኳን በመጀመሪያ ስለመፅሐፈ ሞርሞን ጥርጣሬ ቢገባውም፣ ስድኒ ራሱ በአዲስ ኪዳን ላይ ስለተገለጸው የእውነተኛው ቤተክርስቲያን መመለስ ሲያጠና ነበር የቆየው። “ነገር ግን መጽሃፍህን አነበዋለሁ፣ እናም ይህ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ራእይ ስለመሆኑና ስላለመሆኑ ለማወቅ እጥራለሁ” ብሎ ለጓደኛው ፓርሊ ነገረው። ከሁለት ሳምንታት ጥናትና ጸሎት በኋላ፣ ሁለቱም እርሱና ፊቢ መጽሃፉ እውነት እንደሆነ አረጋገጡ። ነገር ግን፣ በቤተክርስቲያኗ መቀላቀል ቤተሰቡን ትልቅ መስዋዕት እንደሚያስከፍልም ስድኒ አውቆ ነበር። በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ስፍራ ጨምሮ ያለጥርጥር የሰባኪነት ስራውን እንዲሁም ያጣል። እርሱና ፊቢ ሊሆኑ ስለሚችሉት ነገሮች ሲነጋገሩ፣ ፊቢ እንዲህ በማለት ገለጸች፣ “የሚያስከፍለንን ዋጋ አስልቻለሁ፣ እናም … የእኔ ፍላጎት፣ ሞትም ይሁን ህይወት፣ የእግዚአብሔርን ፍቃድ ለማድረግ ነው።”