“የዳግም መመለስ ድምጾች፦መንፈሳዊ መገለጦች እና የከርትላንድ ቤተመቅደስ፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]
“መንፈሳዊ መገለጦች እና የከርትላንድ ቤተመቅደስ፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
የዳግም መመለስ ድምጾች
መንፈሳዊ መገለጦች እና የከርትላንድ ቤተመቅደስ
ከዚህ በታች የሚገኙት በከርትላንድ ቤተመቅደስ ምረቃ ላይ እና ያንን ተከትሎ በተደረጉ ሌሎች ስብሰባዎች ውስጥ የነበሩ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ቃላት ናቸው። ብዙዎች ልምዶቻቸውን የጥንቶቹ ቅዱሳን “ከላይ ኃይል [ከለበሱበት]” ከበዓለ ሃምሳ ቀን ወቅት ጋር አነፃፅረውታል (ሉቃስ 24፥49፤ በተጨማሪም የሐዋርያት ሰራ 2፥1–4፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 109፥36–37 ተመልከቱ)።
እላይዛ አር. ስኖው
“የምረቃው ሥነ-ሥርዓቶች ድርጊቶች እንደገና ሊነገሩ ይችሉ ይሆናል፣ ነገር ግን የዚያን የማይረሳ ቀን የሰማይ መገለጦች ምንም ሰብዓዊ ቋንቋ ሊገልጸው አይችልም። ለአንዳንዶች መላዕክት ተገለጡ፣ በተገኙት ሁሉም ላይ መለኮታዊ መገኘት ተረጋገጠ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ልብ ‘በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሴት’ ተሞልቶ ነበር።”
ሲልቭያ ከትለር ዌብ
“ከቀደምት ትዝታዎቼ ውስጥ አንዱ የቤተመቅደሱ ምረቃ ነው። አባቴ በጭኑ ላይ አስቀመጠን እና ለምን እንደምንሄድ እንዲሁም አንድን ቤት ለእግዚአብሔር እንዲሆን መመረቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ነገረን። ምንም እንኳን በወቅቱ በጣም ትንሽ ልጅ የነበርኩኝ ቢሆንም፣ ዝግጅቱን በግልፅ አስታውሳለሁ። ያለፉትን አመታት ወደኋላ መለስ ብዬ መመልከት እና በዚህ የማይረሳ ቀን ላይ ነቢዩ ጆሴፍ እጆቹን ወደ ሰማይ ከፍ አድርጎ፣ ፊቱ እንደ አመድ ነጭ ሆኖ፣ እንባው በጉንጮቹ እየፈሰሱ ሲናገር ማስታወስ እችላለሁ። ሁሉም እያነቡ የነበሩ ይመስላል። ቤቱ በጣም በመሙላቱ ልጆች በአብዛኛው በትላልቅ ሰዎች ጭኖች ላይ ተቀምጠው ነበር፤ እህቴ በአባቴ እኔ ደግሞ በእናቴ ጭን ላይ ተቀምጠን ነበር። የለበስናቸውን ቀሚሶች እንኳ ማስታወስ እችላለሁ። በዚያን ጊዜ የሁሉንም ነገር አስፈላጊነት ለመገንዘብ አዕምሮዬ በጣም ለጋ ነበር፣ ነገር ግን በጊዜ ሂደት የበለጠ እየተገነዘብኩት መጣሁኝ፣ እናም እዚያ የመገኘት እድል በማግኘቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”
ኦሊቨር ካውድሪ
“ምሽት ላይ በጌታ ቤት ውስጥ ከነበሩት የቤተክርስቲያንኗ ኃላፊዎች ጋር ተገናኘሁ። መንፈሱ አብዝቶ ፈሰሰ—የእግዚአብሔር ክብር እንደ ታላቅ ደመና ሲወርድ እና በቤቱ ላይ ሲያርፍ፣ እንዲሁም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ቤቱን ሲሞላው አየሁ። እንዲሁም እሳት በእነርሱ ላይ የሚያርፍ የሚመስል እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖችንም አየሁ፣ … በሌላ ቋንቋ ሲናገሩ እና ትንቢት እየተናገሩ ነበር።”
ቤንጃሚን ብራውን
“ብዙ ራዕዮች ታይተው [ነበር]። አንደኛው ፀሃይ በደመና ላይ ሲያበራ እንደ ወርቅ የሚያንጸባርቅ አይነት ብሩህ የሆነ ትራስ ወይም ደመና በቤቱ ላይ ሲያርፍ አየ። ሌሎች ሁለት ሰዎችም በእጆቻቸው ብሩህ ቁልፎች እና ብሩህ ሰንሰለት የያዙ ሶስት ሰዎች በክፍሉ ውስጥ በአየር ላይ ሲያንዣብቡ ተመለከቱ።”
ኦርሰን ፕራት
“እግዚአብሔር እዚያ ነበር፣ መላዕክቱ እዚያ ነበሩ፣ መንፈስ ቅዱስ በሰዎች መካከል ነበር … እንዲሁም ከጭንቅላታቸው አክሊል እስከ እግሮቻቸው መዳፍ ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እና ምሪት ተሞልተው ነበር።”
ናንሲ ናዮሚ አሌክሳንድር ትሬሲ
“ቤተመቅደሱ ተሠርቶ የተጠናቀቀበት እና የተመረቀበት [ጊዜ] … በህይወቴ በጣም ደስተኛ የሆንኩባቸው ሁለቱ ቀናት ነበሩ። ለበዓሉ የተዘጋጀው ተስማሚ መዝሙር ‘The Spirit of God Like a Fire is Burning’ [የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ እሳት ይነዳል] የሚል ነበር። የሰማይ ተፅእኖ በዚያ ቤት ላይ ማረፉ በእርግጥ እውን ነበር። በምድር ላይ ያለ ገነት እንደሆነ ተሰማኝ።”