ምዕርፍ ፪
ክፋትና እርኩሰት በህዝቡ መካከል ተስፋፋ—ኔፋውያን እና ላማናውያን ከጋድያንቶን ዘራፊዎች እራሳቸውን ለመከላከል ተዋሃዱ—የተለወጡ ላማናውያን ነጭ ሆኑ እናም ኔፋውያን ተብለው ተጠሩ። ፭–፲፮ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ ደግሞም ዘጠና አምስተኛው ዓመት እንደዚህ አለፈ፣ እናም ሰዎቹ እነዚያን ምልክቶችና የሰሟቸውን አስገራሚ ነገሮች መርሳት ጀመሩ፣ እናም ከሰማይ በሆነው ምልክት ወይም አስገራሚ ነገር መደነቃቸው መቀነስ ጀመሩ፤ በዚህም ልባቸው መደንደንና አዕምሮአቸው መታወር ጀመረ፣ እናም ያዩአቸውንና የተመለከቱአቸውን በሙሉ አለማመን ጀመሩ—
፪ የሰዎችን ልብ ለመምራትና ለማጭበርበር በሰው እንዲሁም በዲያብሎስ ኃይል በተሰሩት በማለት በልባቸው ጥቂት ከንቱ ነገር አሰላሰሉ፤ እንደዚህም ሰይጣን የሰዎችን ልብ በድጋሚ የራሱ አድርጓል፣ በዚህም የተነሳ አሳውሮአቸዋልና የክርስቶስን ትምህርት በተመለከተ የሞኝ እናም ከንቱ ነገር መሆኑን እንዲያምኑ መርቷቸዋል።
፫ እናም እንዲህ ሆነ ሰዎቹ በክፋቶቻቸውና በእርኩሰቶቻቸው መበርታት ጀመሩ፤ እናም ከእንግዲህ ምልክቶችም ሆኑ አስገራሚ ነገሮች እንደሚሰጡ አላመኑም፤ እናም ሰይጣን የሰዎችን ልብ መምራት፣ መፈተንና በምድሪቱ ታላቅ ክፋትን እንዲሰሩ ማድረግ ቀጠለ።
፬ እናም ዘጠና ስድስተኛው ዓመት፤ ደግሞም ዘጠና ሰባተኛው ዓመት፤ እናም ደግሞ ዘጠና ስምንተኛው ዓመት፣ እንዲሁም ደግሞ ዘጠና ዘጠነኛው ዓመት እንደዚህ አለፉ፤
፭ እናም ደግሞ በኔፊ ህዝብ ላይ ንጉስ ከነበረው ሞዛያ ጊዜ ጀምሮ መቶ ዓመት አለፈ።
፮ እናም ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣ ስድስት መቶ ዘጠኝ ዓመታት አለፉ።
፯ እናም ስለ ክርስቶስ ወደ ዓለም መምጣት ለነቢያቱ የተነገሩት ምልክቶች ከተሰጡ ጊዜ አንስቶ ዘጠኝ ዓመታት አለፉ።
፰ እንግዲህ ኔፋውያን ምልክቱ ከተሰጠበት ወይንም ከክርስቶስ መምጣት ጀምሮ ጊዜአቸውን መቁጠር ጀመሩ፤ ስለዚህ ዘጠኝ ዓመታት አለፉ።
፱ እናም የመዛግብቱ ኃላፊነት የነበረው፣ የኔፊ አባት የነበረው፣ ኔፊ ወደ ዛራሄምላ ምድር አልተመለሰም፤ እናም በምድሪቱም በሙሉ ሊገኝ አልቻለም።
፲ እናም እንዲህ ሆነ በመካከላቸው ብዙ ስብከቶች እንዲሁም ትንቢቶች ቢላኩም፣ ህዝቦች በክፋታቸው እንደቆዩ ነበር፤ ደግሞም አስረኛው ዓመት አለፈ፤ እናም ደግሞ አስራ አንደኛውም ዓመት በክፋታቸው አለፈ።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ በአስራ ሦስተኛው ዓመት በምድሪቱ ላይ ሁሉ ጦርነቶች እንዲሁም ፀብ ተጀመረ፤ የጋድያንቶን ዘራፊዎች እጅግ ብዙ ስለነበሩና፣ ብዙዎችን ስለገደሉ፤ እናም ብዙ ከተሞችንም ስለደመሰሱና፣ በምድሪቱ ላይ ብዙ ግድያና፣ ሞት ስላሰራጩ፣ ኔፋውያንም ሆኑ ላማናውያን በእነርሱ ላይ እጃቸውን ለጦርነት ማንሳታቸው አስፈላጊ ነበር።
፲፪ ስለዚህ፣ ወደ ጌታ የተለወጡት ላማናውያን በሙሉ ከኔፋውያን ወንድሞቻቸው ጋር አንድ ሆኑ እናም ለህይወታቸውና ለሴቶቻቸውና ለልጆቻቸው ደህንነት፣ አዎን፣ ደግሞም ልዩ መብቶቻቸውንና የቤተክርስቲያናቸውን ክብር እናም አምልኮታቸውንና፣ ነፃነታቸውን እንዲሁም ህልውናቸውን እንዲጠብቁ ዘንድ በጋድያንቶን ዘራፊዎች ላይ መሳሪያዎችን እንዲያነሱ ተገደው ነበር።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ከዚህ አስራ ሦስተኛው ዓመት ከማለፉ በፊት ኔፋውያን በዚህ እጅግ መሪር በሆነው ጦርነት የተነሳ ፈፅመው እንዲጠፉ ማስፈራሪያ ተደርጎባቸው ነበር።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ከኔፋውያን ጋር አንድ የሆኑት ላማናውያን ከኔፋውያን ጋር ተቆጥረው ነበር፤
፲፭ እናም እርግማናቸው ከእነርሱ ተወስዶ ነበር፣ እናም ቆዳቸው እንደኔፋውያን ነጭ ሆኖ ነበር፤
፲፮ እናም ወጣት ወንዶቻቸው እንዲሁም ሴት ልጆቻቸው እጅግ መልካም ሆኑ፤ እናም ከኔፋውያን ጋር ተቆጠሩና፣ ኔፋውያን ተብለው ተጠሩ። እናም አስራ ሶስተኛው ዓመት ተፈፀመ።
፲፯ እናም እንዲህ ሆነ በአስራ አራተኛው ዓመት መጀመሪያ፣ በዘራፊዎቹ እናም በኔፊ ህዝብ መካከል የነበረው ጦርነት ቀጠለና፣ እጅግ መሪር ሆነ፤ ይሁን እንጂ፣ የኔፊ ህዝብ በሌቦቹ ላይ ጥቂት ብልጫ አግኝተው ነበር፣ ስለዚህ ከምድራቸው አስወጥተው ወደ ተራራውና ወደ ሚስጥራዊው ስፍራቸው እንዲሸሹ አደረጉአቸው።
፲፰ እናም አስራ አራተኛው ዓመት በዚሁ ተፈፀመ። እናም በአስራ አምስተኛው ዓመት በኔፊ ህዝብ ላይ መጡባቸው፤ እናም በኔፊ ሰዎች ክፋትና፣ ፀብና ተቃውሞዎች የተነሳ፣ የጋድያንቶን ዘራፊዎች በእነርሱ ላይ ብዙ ብልጫ አገኙ።
፲፱ እናም አስራ አምስተኛው ዓመት በዚሁ ተፈፀመና፣ እንደዚህም ሰዎቹ ብዙ ስቃይ ውስጥ ነበሩ፤ የጥፋት ጎራዴም እነርሱን ሊቆርጣቸው እስከሚቃረብ በእነርሱ ላይ ነበር፤ እናም ይህ የሆነው በክፋታቸው የተነሳ ነው።