ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፴፰


አልማ ለልጁ ለሺብሎን የሰጠው ትዕዛዛት

ምዕራፍ ፴፰ አጠቃሎ የያዘ።

ምዕራፍ ፴፰

ሺብሎን ለፅድቅነት ምክንያት ስደት ደረሰበት—ደህንነት የዓለም ህይወትና ብርሃን በሆነው በክርስቶስ ነው—ስሜቶቻችሁን በሙሉ ተቆጣጠሩ። በ፸፬ ም.ዓ. ገደማ።

ልጄ፣ ቃሌን አድምጥ፣ ለሔለማን እንኳን እንደተናገርኩ ለአንተም ተናግሬአለሁ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እስከጠበቅህ ድረስ በምድሪቱ ላይ ትበለፅጋለህ፤ እናም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እስካልጠበቅህ ድረስ ከፊቱ እንድትለይ ትደረጋለህ።

እናም አሁን፣ ልጄ፣ ለእግዚአብሔር ባለህ ፅኑነት፣ እናም ታማኝነት፣ በአንተ ታላቅ ደስታ እንደሚኖረኝ አምናለሁ፤ በአምላክህ በወጣትነትህ ተስፋ መጣልህን በመጀመርህ፣ ትዕዛዛቱን በመጠበቅ እንደምትቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም እስከመጨረሻው የፀና የተባረከ ነውና።

ልጄ፣ እኔ እንዲህ እልሀለሁ፥ በዞራማውያን መካከል በታማኝነትህ፣ እናም በትጋትህና፣ በፅናትህ እንዲሁም በታጋሽነትህ የተነሳ በአንተ ታላቅ ደስታን አግኝቻለሁ።

አንተ ታስረህ እንደነበርህ አውቃለሁ፤ አዎን፣ እናም አንተ ለቃሉ ስትል በድንጋይ መወገርህን አውቃለሁ፤ ጌታም ካንተ ጋር በመሆኑ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በትዕግስት ጸንተሀል፤ እናም አሁን ጌታ እንዳስለቀቀህ አንተም ታውቃለህ።

እናም እንግዲህ ልጄ፣ ሺብሎን፣ እምነትህን በእግዚአብሔር ላይ እስካደረግህ ድረስ ከፈተናህና ከችግርህ፣ እናም ከስቃይህ እንደዚሁ እንደምትላቀቅና፣ በመጨረሻው ቀን ከፍ እንደምትደረግ እንድታስታውስ እፈልጋለሁ።

እንግዲህ፣ ልጄ፣ እነዚህን ነገሮች በራሴ እንዳወቅኋቸው እንድታስብ አልፈልግም፤ ነገር ግን በውስጤ ያለው የእግዚአብሔር መንፈስ እነዚህን ነገሮች እንዳውቅ አደረገኝ፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ባልወለድ ኖሮ እነዚህን ነገሮች ባላወቅሁ ነበር።

ነገር ግን እነሆ፣ ጌታ በታላቅ ምህረቱ በዚህ ህዝብ መካከል የጥፋት ስራን እንዳቆም እንዲነግረኝ መልአኩን ላከ፤ አዎን፣ እናም መልአኩን ፊት ለፊት ተመለከትኩትና፣ ተናገረኝ፣ ድምፁም እንደነጎድጓድ ነበር፣ እናም ምድሪቷን በሙሉ አንቀጠቀጣት።

እናም እንዲህ ሆነ ለሶስት ቀንና ሌሊት ነፍሴ በመሪር ህመምና ስቃይ ውስጥ ነበረች፤ እናም ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምህረት እስከምጮህ ድረስ ለኃጢአቴ ስርየትን በጭራሽ አላገኘሁም ነበር። ነገር ግን እነሆ፣ ወደ እርሱ ጮህኩና፣ ለነፍሴም ሰላምን አገኘሁ።

እናም አሁን ልጄ፣ በክርስቶስ ብቻ ካልሆነ በቀር መዳን የሚቻልበት ሌላ መንገድ እንደሌለ፣ ከእኔ ትማር ዘንድ ጥበብንም እንድትማር ይህን ነግሬሀለሁ። እነሆ፣ እርሱ የዓለም ህይወትና ብርሃን ነው። እነሆ፣ እርሱ የእውነትና የፅድቅ ቃል ነው።

እናም አሁን፣ ቃሉን ማስተማር እንደጀመርህ ደግሞም ማስተማርን እንድትቀጥል እፈልጋለሁ፤ እናም በሁሉም ነገር ትጉህና ራስህን የምትቆጣጠር እንድትሆን እፈልጋለሁ።

፲፩ አንተ በኩራት እንዳልተሞላህ አረጋግጥ፤ አዎን፣ በራስህ ጥበብም ሆነ በጉልበትህ እንደማትመካ አረጋግጥ።

፲፪ ደፋርነትን ተጠቀም፤ ነገር ግን ኃያልነትህን አትጠቀም፤ እናም ደግሞ በፍቅር ትሞላ ዘንድ ስሜትህን በሙሉ ተቆጣጠር፤ ከስራ ፈትነት ራስህን ቆጥብ።

፲፫ እንደ ዞራማውያን አትፀልይ፣ እነርሱ ሰዎች እንዲሰሙአቸው እንደሚፀልዩ እናም ለብልህነታቸው እንዲወደሱ እንደሚፈልጉ አይተሃቸዋልና።

፲፬ አምላክ ሆይ እኛ ከወንድሞቻችን የተሻልን ስለሆንን እናመሰግንሀለን አትበል፤ ነገር ግን ጌታ ሆይ ለከንቱነቴ ይቅር በለኝ፣ እናም ወንድሞቼንም በምህረትህ አስታውስ በል—አዎን፣ በሁሉም ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ከንቱነትህን አረጋግጥ።

፲፭ እናም ጌታ ነፍስህን ይባርክና፣ በመጨረሻው ቀን በሰላም እንድትቀመጥ በመንግስቱ ይቀበልህ። አሁን ልጄ ሂድ፣ እናም ለዚህ ህዝብ ቃሉን አስተምር። ንቃ። ልጄ ደህና ሁን።