2021 (እ.አ.አ)
ሌሎችን ውደዱ እንዲሁም አገልግሉ
ጥቅምት 2021 (እ.አ.አ)


የአካባቢ አመራር መልዕክት

ሌሎችን ውደዱ እንዲሁም አገልግሉ

ሌሎችን የማገልገል ተነሳሽነታችንን የምናገኘው እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እና በቤዛው አማካኝነት ህያውነትን እና ዘላለማዊ ሕይወትን ለእኛ ለልጆቹ ለማምጣት ያለውን ዓላማ በመረዳት ነው።.

ሰኔ 6 ቀን 1831 (እ.አ.አ) በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካኝነት በተሰጠው ራዕይ ውስጥ ጌታ እንዲህ ብሏል፦ “እና ደግሞም፣ ለሁሉም ነገሮች ንድፍን እሰጣችኋለሁ” (ት እና ቃ 52፥4)።

ንድፎች አንድ ሰው “ህያውነትን እና ዘላለማዊ ሕይወትን [ከሚያመጣው]” (ሙሴ 1፥39) ከእግዚአብሄር ዓላማ ጋር የተስማማ እንዲሆን ሊከተላቸው የሚገቡት ምሳሌዎች፣ መመሪያዎች፣ ደረጃዎች እና መንገዶች ናቸው።

በመላው ግብረገባዊ አገልግሎቱ አዳኛችን እና ቤዛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎችን እንዴት መውደድ እና ማገልገል እንደሚኖርብን ታላቁን ምሳሌ አሳይቶናል። ማስተማር ብቻም ሳይሆን ኖሮታል። እርሱ እንደወደደው እንድንወድ እና እንዳገለገለው እንድናገለግል “ፍለጋውን እንድ[ንከተል]” ይጋብዘናል (1 ጴጥሮስ 2፥21)።

ፕሬዚዳንት ስፔንሰር ደብልዩ. ኪምባል (1895–1985) አገልግሎት የሌሎችን እንዲሁም የራሳችንን ህይወት ስለሚባርክ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት “በፍቅር እና በአገልግሎት ቀላል ተግባራት” እንዲሳተፉ አበረታተዋል።.1

አንዲት ወጣት እናት በአንድ ሌሊት ልታደርግ በነበረ በረራ ጊዜ በተከሰተው መጥፎ የአየር ጠባይ ምክንያት በቺካጎ አየር ማረፊያ ከአንድ የሁለት ዓመት ሴት ልጅ ጋር ያለምግብ ወይም ለልጇ የሚሆን ንፁህ ልብስ እና ያለገንዘብ ታግዳ ቆይታ ነበር። ነፍሰጡር ነበረች እንዲሁም የውርጃ ስጋት ስለነበረባት የግድ ካልሆነ በስተቀር ልጇን እንዳትሸከም የሃኪም መመሪያ ተሰጥቷት ነበር። ወደ ሚሽገን የሚሄድ በረራ ለማግኘት በመሞከር ለረዥም ሰአታት ያለማቋረጥ ከአንደኛው ሰልፍ ወደሌላኛው ሰልፍ እየተሸጋገረች ትቆም ነበር። ተርሚናሉ በጫጫታ፣ በተዳከሙ፣ ተስፋ በቆረጡ እና ቁጡ በሆኑ መንገደኞች የተሞላ ነበር እንዲሁም ሰልፉ ወደ ፊት ሲጓዝ በልጇ ለቅሶ እና እሷን መሬት ላይ በእግሯ በመግፋቷ ምክንያት የሚተቹ ድምጾችን ትሰማ ነበር። ማንም የበሰበሰችውን፣ የተራበችውን፣ የደከመችውን ልጇን ለመርዳት አልጠየቀም።

ከዚያም “አንድ ሰው ወደ እኛ መጣና ደግነት በተሞላበት ፈገግታ ‘አንቺን ለመርዳት ማድረግ የምችለው ነገር ይኖራልን?’ ሲል እንደጠየቀ ሴትዮዋ ተናግራለች። በረዥሙ ተንፍሼ በአመስጋኝነት እርዳታውን ተቀበልኩኝ። እያለቀሰች የነበረችውን ህጻን ልጄን ከቀዝቃዛው ወለል ላይ አነሳት እና ወደራሱ እቅፍ አድርጎ ጀርባዋን በፍቅር መታመታ አደረጋት። ማስቲካ መብላት ትፈልግ እንደሆነ ጠየቃት። ስትረጋጋም አቅፎ ያዛትና ከፊቴ በሰልፉ ላይ ለነበሩት ለሌሎቹ እርዳታቸው እንዴት እንደሚያስፈልገኝ የሆነ ነገር በትህትና ነገራቸው። የተስማሙ መሰሉ እናም ወደቲኬት መሸጫው [ከሰልፉ ፊት] ሄደና ከትኬት ቆራጯ ጋር በመነጋገር በቅርቡ በሚነሳ በረራ ውስጥ እንድሳፈር አመቻቸልኝ። ከእኛ ጋር ወደ አግዳሚ ወንበር ሄደና ደህና መሆኔን እስኪያረጋግጥ ድረስ ለአፍታ አወራን። መንገዱን ቀጠለ። ወደ ሳምንት ከሚሆን ጊዜ በኋላ የሃዋርያ ስፔንሰር ደብልዩ. ኪምባልን ፎቶ አየሁና በአየር ማፊያው ያገኘሁት የነበረው እንግዳ ሰው እርሱ እንደነበር አወቅኩት።”

ከብዙ አመታት በኋላ ፕሬዚዳንት ስፔንሰር ደብልዩ. ኪምባል በከፊል እንዲህ የሚነበብ ደብዳቤ ደረሳቸው፦

“ውድ ፕሬዚዳንት ኪምባል፦

“የብሬገም ያንግ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነኝ። ከሙኒክ ምዕራብ ጀርመን የሚስዮን አገልግሎቴ ገና መመለሴ ነው። የሚያስደስት የሚስዮን አገልግሎት ጊዜ ነበረኝ እንዲሁም ብዙ ተምሪያለሁኝ።

“ባለፈው ሳምንት የዛሬ ሃያ አንድ አመት በቺካጎ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ስላከናወኑት አንድ ፍቅራዊ አገልግሎት ታሪክ ሲነገር በክህነት ስብሰባ ላይ ተቀምጬ ነበር። ታሪኩ ትኬት ለመግዛት ከአንድ ከምታለቅስ፣ የተጨነቀች ልጅ ጋር ረዥም ሰልፍ ላይ ቆማ ስለነበረች ወጣት ነፍሰጡር ሴት ይናገራል። ውርጃ ያሰጋት ስለነበር ልጇን ለማባበል ማንሳት አትችልም ነበር። ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ውርጃ ስላጋጠማት ዶክተሮች እንዳታጎነብስ ወይም እንዳትሸከም ትዕዛዝ እንዲሰጡ ምክንያት ነበራቸው።

“ስታለቅሰ የነበረችውን ልጅ አባበሏት እንዲሁም ስለችግሩ በሰልፉ ለነበሩት ለሌሎች መንገደኞች አስረዱ። ይህ የፍቅር ድርጊት በእናቴ ላይ የነበረውን ግፊት እና ውጥረት አስወግዷል። ከጥቂት ወራት በኋላ ፍሊንት ሚሽገን ውስጥ ተወለድኩኝ።

“ስለፍቅርዎ ላመሰግንዎ እወዳለሁ። ስለአገልግሎት ምሳሌነትዎ ላመሰግንዎት እወዳለሁ።”2

ከአስራሁለቱ ሃዋርያት የሆኑት ሽማግሌ ጆሴፍ ቢ. ዊርዝሊን እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፦ “ፍቅር የደቀመዝሙርነት መንገድ መጀመሪያ፣ መሃል እና ፍጻሜ ነው። ያጽናናል፣ ይመክራል፣ ያክማል እንዲሁም በመከራ ጊዜም ሰውን ያጽናናል።

“ፍቅር ታላቁ ትዕዛዝ ነው—ሁሉም ሌሎች በእርሱ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው። እንደህያው ክርስቶስ ተከታይነታችን ትኩረታችን እሱ ነው”፣3

ወደ ምድረበዳ ሲሄድ አልማን የተከተሉት ሰዎች የእግዚያብሄርን ቃል ከነብዩ አልማ ከተማረሩ በኋላ ራሳቸውን ትሁት አደረገጉ። ተግዳሮቶቻቸውን እና ሁኔታቸውን ወደጎን በማለት—የእግዚአብሔር ህዝብ ለመባል፣ አንዳቸው የሌላውን ሸክም ለመሸከም፣ ከሚያዝኑ ጋር አብረው ለማዘን፣ መጽናናት የሚሹትን ለማጽናናት እና ሁልጊዜም እንደ እግዚአብሔር ምስክሮች ለመቆም—ቃልኪዳን ገቡ። ህይወታቸው ተቀየረ፦ወደጌታ የተቀየሩ ሆኑ እናም ከቤተክርስቲያኑ ጋር ተዋሃዱ እንዲሁም በአልማ ጊዜ የነበሩት የቤተክርስቲያን መሪዎች “ህዝባቸውን ጠበቁ፣ እናም ከጽድቅነት ጋር የተገናኙ ነገሮችን መገቧቸው” (ሞዛያ 23፥18) ይላል።

በመላው ሕይወቴ አንድ ሰው በጥምቀት የተደረጉትን ቃልኪዳኖች እና በረከቶች ሀይል ሲረዳ በቤተክርስቲያኗ የአባልነት ቆይታው ምንም ያህል ጊዜ ቢሆንም እሱ ወይም እሷ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ያላቸውን የእርሱን[ሷን] ጥሪዎች እና ተግባሮች በከፍተኛ ጉጉት እና ደስታ እንደሚመለከት[ምትመለከት] አስተውያለሁ።

አዲስ ኪዳን በጌታ እራት ወቅት ስለሆኑት ስለሁሉም ክስተቶች አልመዘገበም። አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሳ እና እንደ አገልጋይ ሆኖ ታጥቆ የሐዋርያትን እግር ለማጠብ በተንበረከከበት (ዮሃንስ 13፥3–17) እራት ወቅት አንዳንድ በጣም ጉልህ የሆኑ ክስተቶች ተከስተዋል። ሌሎችን እንዴት እንደምናገለግል ከአዳኝ የምንማረው እንዴት የሚያስደንቅ ምሳሌ ነው። ህይወታችንን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የቤተክርስቲያን አባላት ያልሆኑትንም እንኳን ለማገልገል ቁርጠኛ እና ቀና እንድንሆን ይጋብዘናል።

አዳኙ እንዲህ ሲል አስተምሯል፦ “ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ ይሁን እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ አዳኙ እንዳደረገው ሌሎችን እንድትወዱ እና እንድታገለግሉ እጋብዛችኋለሁ እንዲሁም የአዳኙን ምሳሌ ስንከተል ህይወታችን በብርሃን እና በደስታ እንደሚሞላ ቃል እገባለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ቲየሪ ኬ.ሙቶምቦ እንደሰባዎቹ አጠቃላይ ባለስልጣን ማረጋገጫ ያገኙት በየካቲት 2020 (እ.አ.አ) ከሻዪ ናታሊ ሲንዳ ጋር በትዳር የተቆራኙ ሲሆን የስድስት ልጆች ወላጆች ናቸው።

ማስታወሻዎች

  1. Teachings of Presidents of the Church: Spencer W. Kimball [2006], 79.

  2. Teachings of Presidents of the Church: Spencer W. Kimball, 79–81.

  3. Joseph B. Wirthlin, “ታላቁ ትዕዛዝ,” ሊያሆና፣ ጥቅምት 2007 (እ.አ.አ) ይመልከቱ)።.

አትም