የክህነት መሪ መልዕክት
አገልግሎት፦ በቅዱሳን ልቦች ውስጥ ቤተክርስቲያኗን የማቋቋሚያ መንገድ
የክርስቶስን የመሰለ አገልግሎት ለአዳኙ ካለ ከልብ የመነጨ ፍቅር እና እንድንረዳቸው እድል ለሰጠን ሰዎች ካለ ፍቅር ይነሳል።
የሰማያዊ አባታችን እቅድ የእኛን በምድር ላይ መምጣት፣ መፈተን እና ተመልሰን በእርሱ ፊት እንደገና ለመኖር ብቁ መሆንን ይጠብቅብናል። በምድር ላይ እየኖረ ያለ ወይም በምድር ላይ እስከዛሬ የኖረ ማንኛውም ሰው የመዳን ወይም የዘላለም ሕይወትን የማግኘት ዕድል ይኖረዋል ያም ማለት “እንደ እግዚአብሔር ለመሆን” እንዲሁም ከቤተሰቡ ጋር በእርሱ ፊት ለዘላለም ይኖራል ማለት ነው።
ያለሰማያዊ አባት እርዳታ ህያውነትን እና ዘላለማዊ ህይወትን ማግኘት ከባድ ስለሆነ ነው በሃጥያት ክፍያው አማካኝነት እኛን ሊቤዠን አንድያ ልጁን የላከው። በዮሃንስ 3፥16 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና።”
በአሞፅ 3፥7 ውስጥ እንደሚነበበው ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ሰማያዊ አባታችን ህዝቡን እንዲመሩ ነቢያትን ጠርቷል፦ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም።” በነቢያቱ አማካኝነት መልዕክቱን ለልጆቹ ያስተላልፋል።
ዛሬ ሁላችንም የምንደግፈው ህያው ነብይ አለን። በየካቲት 2018 (እ.አ.አ) ህዝቡ ምን እንዲያደርግ እንደሚፈልግ ለነብዩ ገለጸላቸው። ፕሬዚዳንት ረስል ኤም ኔልሰንም ስለአገለግሎት አፈፃፀም በሚከተሉት ቃላት ተናገሩ፦ “አሁን ለጎረቤቶቻችን ትኩረት እና ጥበቃ ስለምንሰጥበት እንዲሁም ስለምናገለግልበት አዲስ የተቀደሰ መንገድ ልናሳውቅ ነው።” በሚከተሉት መካከል ሁለት ዋና ልዩነቶች እንዳሉ እናውቃለን በአገልግሎት እና በቤት ለቤት ወይም በጉብኝት ትምህርት እንዲሁም ቀድሞ ስናደርጋቸው በነበሩት እነርሱም፦
-
እርስበርስ ከልብ መዋደድ እና
-
መነሳሳት
እርስበርስ ከልብ መዋደድ
ሽማግሌ ዲዬተር ኤፍ. ኡክዶርፍ “ፍቅር የእምነታችን ልኬት፣ የመታዘዛችን መነሳሻ እና የደቀመዝሙርነታችን እውነተኛ ዝንባሌ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።.1
እናም ማገልገል ማለት እርዳታ ለሚፈልጉት እርዳታ መስጠት ማለት ነው። የክርስቶስን የመሰለ አገልግሎት ለአዳኙ ካለ ከልብ የመነጨ ፍቅር እና እንድንረዳቸው እድል ለሰጠን ሰዎች ካለ ፍቅር ይመነጫል።
ይህ ሌሎችን የማገልገል ስራ በሁለቱ ታላላቅ ትዕዛዛት ይመራል፦ በማቴዎስ 22፥37–39 ውስጥ እንደሰፈረው እግዚአብሔርን እና ጎረቤታችንን መውደድ፦ “ኢየሱስም እንዲህ አለው። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።
“ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።
“ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።”
እነዚህን ትዕዛዛት መታዘዝ በዚህች አለም ውስጥ ይበልጥ ሰላም እና ደስታ እዲኖረን ያስችላል። ጌታን ብንወድ እና ብንታዘዝ እንዲሁም ጎረቤታችንን ብናገለግል ፍጹም በሆነ መንገድ ወደ እኛ የሚመጣን የላቀ ደስታ በቀላሉ እናገኛለን።
“እግዚአብሔርን እና ጎረቤታችንን መውደድ የአገልግሎት ትምህርት፣ በቤተክርስቲያን የተደገፈ ቤት ተኮር ትምህርት፣ በመጋረጃው በሁለቱም ወገን ላለው የማዳን ስራ መሰረት ነው። እነዚህ እግዚአብሔርን እና ጎረቤታችንን እንድንወድ በተሰጡን መለኮታዊ ትዕዛዛት ላይ የተመረኮዙ ናቸው” ብለዋል የአስራሁለቱ ሃዋርያት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት የሆኑት ሽማግሌ ኤም. ረስል ባላርድ።2
ፍቅር ከስሜትም በላይ ነው፤ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንወዳቸዋለን ስንል ልንረዳቸው እንፈልጋለን ማለት ነው። ማቴዎስ 20፥26–27 እንዲህ ይነበባል፦ “ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤
“ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን።”
“እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛመርት የምንሆነው እንዴት ነው?” የሚለውን ጥያቄ ከጠየቁ በኋላ አዳኙ እራሱ እንደሚከተለው በተናገረ ጊዜ ይህንን ጥያቄ እንደመለሰ ሽማግሌ ዲዬትር ኤፍ. ኡክዶርፍ ገልጸዋል፦ “ብትወዱኝ ትዕዛዛቴን ጠብቁ”።3 ይህ ነው እውነተኛ የጌታ ደቀ መዝሙር የመሆን እውነታ።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚቀበሉ ከእርሱ ጋር ይራመዳሉ እንዲሁም ትዕዛዛቱን ይጠብቃሉ። በሞዛያ 15፥14–18 እንዲህ እናነባለን፦ “እናም ሰላምን የተናገሩት፣ መልካሙን የምስራች ዜና ያመጡት፣ ደህንነትን የተናገሩት እናም ለፅዮን፦ አምላክሽ ነግሷል! ያሉት እነዚህ ናቸው፦ አገልግሎት ብቸኛ ለሆኑት እና ለተተውት ሰላም፣ ደስታ እና መልካም የምስራች ዜና ያመጣል። ልጆቻችን ቤተሰብን፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንዲሁም ጎረቤቶቻችንን እንዲወዱ ማስተማር ያስፈልገናል።
መነሳሳት
በተገቢ ሁኔታ ስናገለግል በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ልብ ውስጥ ቤተክርስቲያኗን እንመሰርታለን። አንድ ቀን፣ የሉቡምባሺ ካስማ ፕሬዚዳንት ሆኜ እያገለገልኩኝ በነበረበት ወቅት የጌታ መንፈስ በሉቡምባሺ ሁለተኛ አጥቢያ ለሚገኝ አንድ ጓደኛዬ ስልክ እንድደውልለት አነሳሳኝ። ይህ መነሳሳት ቀኑን ሙሉ ሲሰማኝ ነበር ስለዚህ በመጨረሻ ስራ እንደደረስኩኝ ደወልኩለት። ይህ ነበር የሆነው፦ “እንዲህ ሲል ጮኸ፣ ፕሬዚዳንት በዚህ ቅፅበት በመደወልህ ተደንቂያለሁ! አሁን እያሳመነኝ ከነበረ የፕሮቴስታንት ፓስተር ጋር ውይይት አድርጌ ነበር! የስልክ ጥሪህ አጠናከረኝ፤ ይህ በእውነተኛ የጌታ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለመሆናችን ማስረጃ ነው።” እንዲህ ስል መለስኩለት፦ “ውድ ወንድሜ፣ እኛ የጌታ ቤተክርስቲያን አባላት ነን፤ በህይወታችን ምንም አይነት ችግሮች ቢያጋጥሙን ጠንክረን መቆም ያስፈልገናል። እኛ ከጌታ ቤተክርስቲያን ነን፣ ማንም ከእርሱ ፍቅር ሊለየን አይችልም እንዲሁም ያንን ማንም ሊቀይር አይችልም።”
ይህ የስልክ ጥሪ ወንድሜ በጌታ የላቀ እምነት ጠንክሮ እንዲቆም ረዳው ምክንያቱም በቤተክርስቲያኗ በአባልነት የቆየው ለሁለት አመት ብቻ ስለነበር።
በት እና ቃ 42፥14 እንዲህ የሚል እናነባለን “እናም በእምነት ጸሎትም መንፈስ ይሰጣችኋል፤ እናም መንፈስን ካልተቀበላችሁ አታስተምሩምና።” መንፈስን መፈለጋችን ግድ ነው ምክንያቱም አገልግሎት የሚሄደው ከጌታ መንፈስ ጋር ነው። እንደ አገልግሎት ወንድሞች እና እህቶች እንነሳሳ ዘንድ ሁላችንም በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ የጌታ መንፈስ ሊሰማን በሚችል መንገድ እንኑር። አልማ እና ወንድሞቹ ዞራማውያንን ወደጌታ ለማምጣት ረዱ እንዲሁም አገለገሏቸው።አልማ ስራው ቀላል እንዳልሆነ ስላወቀ ወንድሞቹን ሰበሰበና የሚከተለውን ጸሎት ጸለየ፦ “ጌታ ሆይ፣ እኛም በድጋሚ እነርሱን ወደ ክርስቶስ በማምጣት ድልን እናገኝ ዘንድ ለእኛ ትፈቅድልናለህ።
“እነሆ ጌታ ሆይ የእነርሱ ነፍስ ውድ ነው፣ እናም ብዙዎቹ ወንድሞቻችን ናቸው፤ ስለዚህ ጌታ ሆይ፣ እነዚህን ወንድሞቻችንን በድጋሚ ወደአንተ እናመጣቸው ዘንድ ሃይልን እና ጥበብን ስጠን” (አልማ 31፥34–35)።
በጸሎት አማካኝነት ከሰማያዊ አባታችን እርዳታ እንቀበላለን እንዲሁም ጌታ ከእኛ ከልጆቹ የሚጠብቀውን ለማከናወን በቂ ጥንካሬ ይኖረናል።
ንግግሬን በ2 ኔፊ 32፥8–9 ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ጽሁፍ መቋጨት እፈልጋለሁ። ጽሁፉ እንዲህ ይነበባል፦ “እናም የተወደዳችሁ ወንድሞቼ አሁንም በልባችሁ አንደምታሰላስሉ አስተውላለሁ፤ እና ይህን ነገር በሚመለከት መናገር ስላለብኝ ያሳዝነኛል። ሰዎችን እንዲጸልዩ የሚያስተምረውን መንፈስ ካዳመጣችሁት መጸለይ እንዳለባችሁ ታውቃላችሁ፤ እርኩስ መንፈስ ሰዎችን ጸሎት አያስተምርምና፣ ነገር ግን መጸለይ እንደሌለባቸው ያስተምራቸዋል።
“ነገር ግን እነሆ፣ ሳትታክቱ ዘወትር መጸለይ እንዳለባችሁ፤ በመጀመሪያ ወደ አብ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ካልጸለያችሁ ምንም ነገር ለጌታ ማከናወን እንደማይገባችሁ፣ እርሱም ስራችሁን ቅዱስ እንደሚያደርግላችሁ፣ ስራችሁም ለነፍሳችሁ ደህንነት እንደሚሆን እነግራችኋለሁ።”
አገልግሎት በመንፈስ ተነሳሽነት እንደሚሰራ እናውቃለን፤ በዚህም ምክንያት እኛ እንደወላጆች ጌታ እንድናደርግ የጠየቀንን ነገር ስናደርግ ጌታ እንዴት ምላሽ እንደሚሰጥ ልጆቻችንን እንድናስተምር ተጋብዘናል። በት እና ቃ 82፥10 እንዲህ የሚል እናነባለን፣ “እኔ ጌታ የምለውን ስታደርጉ በቃሌ እታሰራለሁ፤ ነገር ግን የምለውን ባታደርጉ፣ የተስፋ ቃል የላችሁም።”
ወንድሞች እና እህቶች፣ ፕሬዚዳንት ረስል ኤም. ኔልሰን የእግዚአብሔር ነብይ ነው፣ ጌታ ሁልጊዜ በእጆቹ መሳሪያ እንዲሆን አቆይቶታል። በየካቲት 2018 (እ.አ.አ) ጌታ ለነብዩ አገልግሎትን የተመለከተ ራዕይን ገለጠላቸው እንዲሁም በጥቅምት 2018 (እ.አ.አ) በኑ፤ ተከተሉኝ እና በቤት አምልኮ ላይ ያተኮረ የሰንበት አምልኮን የጊዜ ርዝመት የተመለከቱ ሌሎች ሁለት ራዕዮች ተገለጡ። በዚያን ጊዜ ይህች ዓለም በአለም አቀፍ ወረርሽኝ እንደምትመታ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾቻችን በሮች እንደሚዘጉ እንዲሁም እያንዳንዱ አባት ቅዱስ ቁርባኑን በቤት ሊያዘጋጅ እንደሆነ እንኳን አላወቅንም ነበር። በህያው ነቢዩ በራስል ኤም. ኔልሰን አማካኝነት ዛሬ በምድር ያለችውን ቤተክርስቲያኑን ስለሚመራ ለጌታ ምስጋና እናቀርባለን።
ፑንግዌ ኤስ ኮንጎሎ የአካባቢ ሰባ ሆነው የተጠሩት በየካቲት 2018 (እ.አ.አ) ነበር። ከሳራፊን ሙጎ ንግዌዝያ ጋር ጋብቻ ፈጽመዋል። የሁለት ልጆች ወላጆች ናቸው። ሽማግሌ እና እህት ኮንጎሎ በዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ሉቡምባሺ ውስጥ ይኖራሉ።