2022 (እ.አ.አ)
“ጌታ ጥሪ ለሚሰጠው ሰው ሁሉ ብቃትን ይሰጠዋል።”
የካቲት 2022 (እ.አ.አ)


የአባላት ድምጽ

“ጌታ ጥሪ ለሚሰጠው ሰው ሁሉ ብቃትን ይሰጠዋል።”

“የጌታን ተልዕኮ በማከናወን ላይ ስንሆን የጌታን እርዳታ እናገኛለን”።

ጌታ በጥሪዎቻችን ሁልጊዜ እንደሚደግፈን ፕሬዚዳንት ቶማስ ኤስ. ሞንሰን (1927–2018) ለቤተክርስቲያኗ አባላት ግልጽ አድርገዋል። “ጌታ ጥሪ ለሚሰጠው ሰው ሁሉ ብቃትን ይሰጠዋል።” ብለዋል።1

በ2018 (እ.አ.አ) ለኬንያ እና ታንዛኒያ የህዝብ ጉዳዮች ዳይሬክተር ተደርጌ ተጠራሁ። በህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ ውስጥ አገልግዬ ነበር፤ ነገር ግን ይህ አዲስ ጥሪ ለእኔ ከአቅም በላይ ነበር። ስራዬ የመሪነት ሚናዎችን ያካትት ነበር፤ ሆኖም ቤተክርስቲያኗ በደንብ ባልታወቀችበት እና አልፎ አልፎም ከተቃዋሚ ሚዲያዎች ጋር በመጋፈጥ የህዝብ ጉዳዮች ዳይሬክተር የመሆን ሚና በእውነት አስፈራኝ።

አዲሱን ጥሪ እንደተቀበልኩኝ በቅርቡ ድጋፍ ያገኙት ነቢይ ረስል ኤም. ኔልሰን አለም ዓቀፍ ጉዞ እንደሚያደርጉና ኬንያም ከሚጎበኟቸው ቦታዎች አንዷ እንደሆነች ተነገረኝ። በተጨማሪም የነብዩን ጉብኝት ዝግጅት የህዝብ ጉዳይ ዲፓርትመንት እንደሚመራው በአካባቢው አመራር መመሪያ ተሰጥቶበት እንደነበር ተነግሮን ነበር።

ወደ ካስማዬ ፕሬዚዳንት በመሄድ ምን ያህል በቂ እንዳልሆንኩ እንደሚሰማኝ ነገርኩት። በጥሞና አዳመጠና እንዲህ አለ፣ “ሥራውን ለማከናወን ብቁ የሆነ ሰው ቢኖር አንቺ እንደሆንሽ አልጠራጠርም፤ እህት ጄፕኬሜ ከጌታ ጋር ተነጋገሪ፤ እርሱም ይመራሻል እንዲሁም ያግዝሻል።” ከዚያም የካስማ ፕሬዚዳንቴ እጅግ የሚያስፈልገውን እና ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረውን በረከት ሰጠኝ።

የመጀመሪያ ስራችን የነበረው የነብዩን መምጣት ለአገሪቱ ለማሳወቅ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ነበር። ይህ ኬንያ ባለችው ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው የሚዲያ ዝግጅት ነበር። በጣም ያስገረመን በዝግጅቱ ላይ ከ15 በላይ ተሳታፊዎች ነበሩን። እንዲሁም ስለቤተክርስቲያኗ እና ስለ ነብዩ ጉብኝት መጥተን እንድንናገር ከማሰራጫ ሚዲያ ተቋማት ግብዣ ተደርጎልናል። የካስማው ፕሬዚዳንት ቤተክርስቲያኗን እንዲወክል ተመድቦ ነበር። በዚህ አጋጣሚ ድንገተኛ ሁኔታ ስለገጠመው መገኘት አልቻለም ነበር። በመጨረሻዋ ደቂቃ በእርሱ ቦታ መተካቴ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። ምን ያህል ፍርሃት እንደሰማኝ መናገር አልችልም፤ ሆኖም ወደ ሬዲዮ ጣቢያው ለመሄድ እንዲሁም ስለማውቀው እና በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ስለነበረኝ ተሞክሮ ብቻ ለመናገር ለራሴ ቃል ገባሁ። በጥዋቱ የሬዲዮ ስርጭት ፕሮግራም ቀርቤ ስለቤተክርስቲያኗ በድፍረት ተናገርኩኝ። ለጥያቄዎቻቸው በልበ ሙሉነት መልስ መስጠት ችዬ ነበር። ስርጭቱ በጥሩ ሁኔታ ተከናወነ፤ እንዲሁም ብዙ ሰዎች እንዴት የቤተክርስቲያኗ አባል መሆን እንደሚችሉ ለመጠየቅ ወደ ስቱዲዮዎቹ ደውለው ነበር።

ፕሬዚዳንት ኔልሰን እና አጃቢዎቻቸው ሲደርሱ አነጋገሩን እናም የእግዚያብሄር ነብይ ፍቅር ተሰማን። በግለሰብ ደረጃ “የጌታን ተልዕኮ በማከናወን ላይ ስንሆን የጌታን እርዳታ እናገኛለን”2 የሚሉት የፕሬዚዳንት ሞንሰን ቃላት እውነትነት ተሰማኝ።

ሳስበው የነብዩ ጉብኝት እቅድ እንደተሳካ ምንም ጥርጥር የለኝም፤ ይህም የሆነው በችሎታችን አይደለም፣ ምክንያቱም አንዳች አልነበረንምና። ጌታ ስራዎቹ እንዲሳኩ ይፈልግ ነበር እናም በኬንያ ያሉ ቅዱሳንን ለመባረክ በእጁ ውስጥ መሣሪያዎች እንሆን ዘንድ እራሳችንን፣ ድክመቶቻችንን እና ሁሉንም አቀረብን።

በዚህ ቅዱስ ተሞክሮ አማካኝነት “ጌታ ጥሪ ለሚሰጠው ሰው ሁሉ ብቃትን ይሰጠዋል።” የሚለውን ዘላለማዊ ትምህርት ተማኩኝ።

ማስታወሻዎች

  1. Thomas S. Monson, “Duty Calls”, Ensign, May 1996, 44.

  2. Thomas S. Monson, “Duty Calls”, 44.