ትምህትና ቃል ኪዳኖች 3–9፦‘ለህያውና ለሙታን የደስታ ድምፅ’፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 125–128፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]
“ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 125–128፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
ህዳር 3–9፦ “ለህያውና ለሙታን የደስታ ድምፅ”
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 125–128
በነሐሴ 1840 (እ.አ.አ) በሐዘን የተደቆሰችው ጄኒ ኒይማን ነቢዩ ጆሴፍ በጓደኛው ሲሞር ብረንሰን የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ሲሰጥ አዳመጠች። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው የጄኒ ወጣት ወንድ ልጇ ሳይረስ እንዲሁ በቅርቡ ሞቶ ነበር። ሐዘኗን የጨመረውም ሳይረስ ፈጽሞ ያልተጠመቀ መሆኑ ነበር፣ እናም ጄን፣ ይህ ለዘለዓለማዊ ነፍሱ ምን ትርጉም ይኖረዋል ይሆን ስትል ተጨነቀች። ጆሴፍ የሚወደው ወንድሙ አልቪን ከመጠመቁ በፊት ስለሞተ ተመሳሳይ ሐሳብ ያስጨንቀው ነበር። እናም ነቢዩ የወንጌል ሥርዓቶችን ሳይቀበሉ ስለሞቱት እንዲሁም እነርሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምንችል ጌታ የገለጸለትን በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት ሁሉ ሊያካፍል ወሰነ።
ለሙታን የመጠመቅ ትምህርት ቅዱሳኑን አስደሰታቸው፤ ሀሳቦቻቸው ወዲያውኑ ወደ ሞቱ የቤተሰብ አባላቶቻቸው ተመለሱ። አሁን ለእነሱ ተስፋ አላቸው! ጆሴፍ ደስታቸውን ተጋራ፣ እናም ይህንን ትምህርት ለማስተማር በፃፈው ደብዳቤ፣ ጌታ ስለሙታን ደህንነት ያስተማረውን ለመግለፅ የደስታን እና የጋለ ስሜትን የሚያንፀባርቅ ቋንቋ ተጠቀመ፦ “ተራሮችም በደስታ ይጩሁ፣ እና ሸለቆዎች ሁሉ በጎላ ድምፅ አልቅሱ፤ እና እናንት ባህሮች እና ደረቅ ምድራት ሁሉ የዘለአለም ንጉሳችሁን አስደናቂነት ተናገሩ!” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 128፥23)።
ቅዱሳን 1፥415–27፤ “Letters on Baptism for the Dead [ለሙታን ስለመጠመቅ የሚጠቅሱ ደብዳቤዎች]፣” Revelations in Context [ራዕያት በአገባብ]፣ 272–76 ተመልከቱ።
በቤት እና በቤተክርስቲያን ለመማር የሚረዱ ሃሳቦች
ጌታ ቤተሰቦቼን እንድንከባከብ ይፈልጋል።
ካገለገለባቸው ከብዙዎቹ አንዱ ከሆነው ከእንግሊዝ የሚስዮን አገልግሎቱ ከተመለሠ በኋላ ብሪገም ያንግ ከጌታ ሌላ አስፈላጊ ጥሪ ተቀበለ። ባልነበረበት ጊዜ ተጎሳቁሎ የነበረውን “ቤተሠ[ቡ]ን በልዩ ሁኔታ እን[ዲ]ንከባከባቸው” ቁጥር 3 ተጠይቆ ነበር። ይህንን ክፍል በምታጠኑበት ጊዜ፣ ጌታ አንዳንድ ጊዜ በአገልግሎታችን መሥዋዕትነትን ለምን እንደሚፈልግ አስቡ። ቤተሠባችሁን ለመንከባከብ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?
በተጨማሪም፣ “Take Special Care of Your Family [ለቤተሰባችሁ ልዩ እንክብካቤ አድርጉ]፣” Revelations in Context [ራዕያት በአገባብ]፣ 242-49 ተመልከቱ።
በአስቸጋሪ ጊዜያት በጌታ መተማመን እችላለሁ።
የሐሰት ክሶች እና የመታሠር ስጋት ጆሴፍ ስሚዝ እንደገና በነሐሴ 1842 (እ.አ.አ) እንዲደበቅ አስገድደውታል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ለቅዱሳን የፃፋቸው ቃላት (አሁን ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 127) በተስፋና በደስታ ተሞሉ ነበሩ። ቁጥር 2–4 እናንተን ስለ እግዚአብሔር ምን ያስተምሯችኋል? ሹፈትን እና ተቃውሞን ስለመጋፈጥስ? ስደት እየደረሰባችሁ እንደሆነ በሚሰማችሁ ጊዜ ከእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ሊረዷችሁ የሚችሉት የትኞቹ ሀረጎች ናቸው? ጌታ በህይወታችሁ “ጥልቅ ውሀ” ውስጥ እንዴት እንደሚጠብቃችሁ መመዝገብን አስቡ።
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 127፥5–8፤ 128፥1–8
“በምድር የመዘገባችሁት ሁሉ በሰማይ የተመዘገበ ይሆናል።”
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 127፥5–8፤ 128፥1–8ን ስታነቡ፣ ጌታ እንዲህ ያሉ የተለዩ የሙታን ጥምቀቶች ምዝገባን የተመለከቱ መመሪያዎችን ለጆሴፍ ስሚዝ የሰጠበትን ምክንያት ፈልጉ። ስለ ጌታ እና ስለ ስራው ይህ ምን ያስተምራችኋል? ይህ መመሪያ የግል የማስታወሻ ደብተርን በመሠሉ የቤተሰብ መዛግብታችሁ ላይ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ይመስላችኋል?
የቅድመ አያቶቼ መዳን ለእኔ መዳን አስፈላጊ ነው።
በዚህ ህይወት ያልተጠመቁ ቅድመ አያቶቻችን ለደህንነታቸው የእኛን እርዳታ የሚፈልጉት ለምን እንደሆነ እግዚአብሔር በጆሴፍ ስሚዝ በገለጠው በኩል ግልፅ ነው፦ይህንን ሥርዓት ለመቀበል ወይም ላለመቀበል ለመምረጥ ይችሉ ዘንድ ለእነርሱ በውክልና ተጠምቀናል። ነገር ግን ነቢዩ የቅድመ አያቶቻችን መዳን “ለእኛ መዳን” አስፈላጊ እና መሠረታዊ ነው ሲልም አስተምሯል። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 128፥15–18ን ስታነቡ ያ ለምን እንደሆነ አስቡ።
ቁጥር 5 ለሙታን የሚደረግ የጥምቀት ሥርዓት “ከአለም መመስረት በፊት” እንደተዘጋጀ ያስተምራል። ይህ እውነት ስለ እግዚአብሔር እና ስለ እቅዱ ምን ያስተምራችኋል? “Family History and Temple Work: Sealing and Healing [የቤተሰብ ታሪክ እና የቤተመቅደስ ስራ፦ መታተም እና መፈወስ]” የሚለው የሽማግሌ ዴል ጂ. ረንለንድ መልዕክት ምን ግንዛቤ ይጨምርላችኋል? (ሊያሆና፣ ግንቦት 2018 (እ.አ.አ)፣ 46–49)።
ጆሴፍ ስሚዝ ስለ ክህነት ስርዓቶች እና ስለ ሙታን ጥምቀት ሲያስተምር “የማሰር ኃይል”፣ “የመገጣጠሚያ አገናኝ” እና “ፍጹም አንድነት” የመሣሠሉ ሀረጎችን ተጠቅሟል። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 128፥5-25ን በምታነቡበት ጊዜ እነዚህን እና ተመሳሳይ ሐረጎችን ፈልጉ። እነዚህን ሐረጎች በምሳሌ ለማስረዳት ልትጠቀሙባቸው የምትችሏቸው እንደ ሠንሰለት ወይም ገመድ ያሉ ነገሮችን ማሰብ ትችላላችሁ? እነዚህ ይህን ትምህርት ለመግለፅ ጥሩ ሃረጎች የሆኑት ለምንድን ነው?
የሚከተሉትን ጥያቄዎች ግምት ውስጥ ማስገባት የእነዚህን ጥቅሶች ጥናታችሁን ሊረዳም ይችላል፦
-
በእናንተ አመለካከት፣ ለሙታን መጠመቅ “ ከሁሉም ርዕሶች በላይ የከበረ … በዘለዓለም ወንጌል” (ቁጥር 17) ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ምን ዓይነት ተሞክሮዎች እንደዚህ እንዲሰማችሁ ረድተዋችኋል?
-
“በአባቶች እና በልጆች መካከል … የሚያስተሣስር ግንኙነት” (ቁጥር 18) ከሌለ ምድር በእርግማን የምትመታው በምን መልኩ ነው?
-
በቁጥር 19–25 ውስጥ ስላሉት የጆሴፍ ስሚዝ ቃላት ያስደነቃችሁ ምንድነው? እነዚህ ጥቅሶች ስለኢየሱስ ክርስቶስ በሚሰማችሁ ስሜት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው? ለሞቱ ቅድመ ዓያቶቻችሁ ስለሚደረገው የቤተመቅደስ አገልግሎትስ? (በተጨማሪም “Come, Rejoice [ኑ፣ ተደሰቱ]፣” መዝሙር፣ ቁ. 9 ተመልከቱ)።
እነዚህን ጥቅሶች ካጠናችሁ በኋላ፣ ለቅድመ ዓያቶቻችሁ አንድ ነገር እንድታደርጉ መነሣሣት ሊሰማችሁ ይችላል። በFamilySearch.org ላይ ያሉት ሃሳቦች ሊረዱ ይችላሉ።
“ቤተመቅደስ እና የቤተሰብ ታሪክ” አይነት በወንጌል ላይብረሪ ስብስብ ውስጥ ያሉት “የሚያነሣሱ ቪዲዮዎች” ተግባራዊ እርዳታን፣ የሚያነሣሱ ታሪኮችን እና በመሪዎች የተሠጡ የቤተሰብ ታሪክ መልዕክቶችን ሊያቀርቡላችሁ ይችላሉ።
በተጨማሪም ኬቪን አር. ዱንካን፣ “A Voice of Gladness! [የደስታ ድምጽ]፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2023 (እ.አ.አ)፣ 95–97 ተመልከቱ።
“ታላቅ እና ድንቅ ዝግጅት።”
ፕሬዘዳንት ጎርደን ቢ. ሂንክሊ እንዳሉት፦
“ስለሁሉም የተከፈለው የኢየሱስ የኃጢያት ክፍያ፣ ለሌሎች ሊከፈል የሚችልን ታላቅ መስዋዕትነት ይወክላል። ለሰው ልጆች ሁሉ ወኪል የሆነበትን ንድፍ አዘጋጅቷል። አንድ ሰው ሌላ ሠውን ወክሎ መሥራት የሚችልበት ይህ ንድፍ በጌታ ቤት ውስጥ በሚከናወኑ ሥርዓቶች ቀጥሏል። እዚህ የወንጌልን እውቀት ሣያገኙ የሞቱ ሰዎች እናገለግላለን። የተከናወነውን ሥርዓት መቀበል አለመቀበል የእነርሱ ምርጫ ነው። በምድር ላይ ካሉት ጋር እኩል ናቸው። ሙታን በህይወት እንዳሉት ተመሳሳይ ዕድል ተሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም ሁሉን ቻይ የሆነው ጌታ ለነቢዩ በሠጠው ራዕይ በኩል እንዴት ያለ ታላቅ እና ድንቅ ዝግጅትን አደረገ”(“The Great Things Which God Has Revealed [እግዚአብሔር የገለጻቸው ታላቅ ነገሮች]፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2005 (እ.አ.አ)፣ 82–83)።
ልጆችን ለማስተማር የሚረዱ ሀሳቦች
ቤተሰቤን በመንከባከብ መርዳት እችላለሁ።
-
ልጆቻችሁ የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ማገልገልን እንዲማሩ ለመርዳት፣ በChapter 50: The Saints in Nauvoo [ምዕራፍ 50፦ በናቩ ውስጥ ያሉ ቅዱሳን]” (በDoctrine and Covenants Stories [የትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ታሪኮች]፣ 184 ውስጥ ያለውን ስለብሪገም ያንግ የሚያወሳ መረጃ ማካፈልን ወይም ተዛማጅ ቪዲዮውን በወንጌል ላይብረሪ) ወይም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 126ን በራሳችሁ አባባል አሣጥራችሁ መግለፅን አስቡ። “ቤተሰብህን በልዩ ሁኔታ እንድትንከባከባቸው” (ቁጥር 3) በሚለው ሃረግ ላይ ልታተኩሩ እና ቤተሰብን በልዩ ሁኔታ መንከባከብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከልጆቻችሁ ጋር መነጋገር ትችላላችሁ።
-
የቤተሠብ አባላትን “መንከባከብ” ስለምንችልባቸው መንገዶች ስትነጋገሩ የቤተሠብ ፎቶዎችን መመልከት (ወይም መሣል) ለእናንተ እና ለልጆቻችሁ የሚያዝናና ሊሆን ይችላል። እንደ “Home Can Be a Heaven on Earth [ቤት በምድር እንደሚገኝ ሰማይ ሊሆን ይችላል]፣” መዝሙር፣ ቁጥር 298) ያለ መዝሙርን መዘመርም ትችላላችሁ።
ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች የመጠመቅ እድል ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።
-
የጆሴፍ ስሚዝ አዕምሮ በየትኛው ጉዳይ ተይዞ እንደነበረ ከትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 128፥1 ውስጥ እንዲያገኙ ልጆቻችሁን ጋብዟቸው። የትኛውን ርዕስ “ከሁሉ ታላቅ” እድርጎ እንደሚያስብ ለማወቅ ቁጥር 17ን መመርመርም ይችላሉ። ያገኙትን እንዲያካፍሉ እንዲሁም ይህ ርዕስ ለምን አስደሳች እንደሆነ እንዲናገሩ አድርጉ።
-
ልጆቻችሁ ለራሳቸው የጥምቀት ቃል ኪዳኖች እንዲዘጋጁ (እንዲሁም እንዲኖሯቸው) ከመርዳት በተጨማሪ፣ በህይወት ዘመናቸው እነዚህን ቃል ኪዳኖች ያልገቡ ሰዎችን እንዴት መርዳት እንደሚችሉ እንዲያውቁ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። ሳይጠመቅ ስለሞተ ስለምታውቁት ስለ አንድ ሰው ለልጆቻችሁ መንገርን አስቡ። ከዚያም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 128፥5ን አብራችሁ ልታነቡና የአንድን ቤተመቅደስ የጥምቀት ገንዳ ምስል (በዚህ መዘርዝር መጨረሻ ላይ እንዳለው) ልትመለከቱ ትችላላችሁ። ሁሉም ሰው ከሰማይ አባት ጋር ቃል ኪዳን የመግባት ዕድል ይኖረው ዘንድ ለሞቱ ሠዎች በውክልና በቤተመቅደስ ስለመጠመቅ ምን እንደሚሰማችሁ ለልጆቻችሁ ንገሯቸው።
የሰማይ አባት ስለቤተሰቤ ታሪክ እንዳውቅ ይፈልጋል።
-
የወላጆችን፣ የዓያቶችን፣ የቅድመ ዓያቶችን እና የመሳሰሉትን ስም የያዘ የወረቀት ሠንሰለት መስራት እናንተን እና ልጆቻችሁን የሚያዝናና ሊሆን ይችላል (የዚህን ሣምንት የአክቲቪቲ ገፅ ተመልከቱ)። ከዚያም ስለእነዚህ ቅድመ ዓያቶች የምታውቁትን አንዳችሁ ለሌላችሁ ማካፈል ትችላላችሁ። የቤተሰብ ታሪካችንን “ሙላት እና የተፈፀመ” የሚያደርገው “የሚያስተሣሥር ግንኙነት” ምን እንደሆነ ለማወቅ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 128፥18ን አብራችሁ አንብቡ። “Courage: I Think I Get It from Him [ድፍረት፦ ከእርሱ ያገኘሁት ይመስለኛል]” (የወንጌል ላይብረሪ) የሚለውን ቪዲዮ ልትመለከቱም ትችላላችሁ።
-
ልጆቻችሁ በቤተሰብ ታሪክ እንዲሳተፉ የሚረዱ ተጨማሪ አክቲቪቲዎች በ“The Temple and the Plan of Happiness [ቤተመቅደስና እና የደስታ እቅድ]” በአባሪ ለ ወይም በFamilySearch.org ውስጥ ይገኛሉ።