አጠቃላይ ጉባኤ
የደስታ ድምፅ!
የሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


የደስታ ድምፅ!

ቤተመቅደሶችን መገንባት ከነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ጀምሮ በሁሉም ነቢያት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነበር ነው።

“አሁን፣ በተቀበልነው ወንጌል ውስጥ ምን እንሰማለን? የደስታ ድምፅ! የምህረት ድምፅ ከሰማይ፤ እና ከምድር ውስጥም የእውነትን ድምፅ፤ …የምስራች ዜና ለሙታን፤ ከህያውና ከሙታን የደስታ ድምፅ፤ የታላቅ ደስታን የምስራች ነው።”1

ወንድሞች እና እህቶች፣ እነዚህን ቃላት ከነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ሰምቶ አለመደሰት ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው!

የጆሴፍ የደስታ አገላለጽ በእውነት በሰማይ አባታችን በእግዚአብሔር ታላቅ የደስታ እቅድ ውስጥ የሚገኘውን ሙሉ እና ግርማ የተሞላውን ደስታ ይዟል፣ ምክንያቱም እንደተረጋገጠልን፣ “ሰዎች የሚኖሩትም ደስታን እንዲኖራቸው ዘንድ” ስለሆነ ነው።2

በቅድመ ምድር ህይወታችን የእግዚአብሔርን የደስታ እቅድ ስንሰማ ሁላችንም በደስታ ጮኸናል፤3 እናም በእሱ እቅድ መሰረት ስንኖር በደስታ መጮህን እንቀጥላለን። ነገር ግን የዚህ የነቢዩ የደስታ መግለጫ አውድ ምን ነበር? እነዚህን ጥልቅ እና ልባዊ ስሜቶች ያነሳሳው ምንድን ነው?

ነቢዩ ጆሴፍ ስለ ሙታን ጥምቀት ሲያስተምር ነበር። ይህ በእውነትም በከፍተኛ ደስታ መቀበልን ያገኘ የከበረ መገለጥ ነበር። የቤተክርስቲያኗ አባላት ለሟች ዘመዶቻቸው መጠመቅ እንደሚችሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያውቁ ተደስተው ነበር። ውልፈርድ ውድረፍ “ይህን በሰማሁበት ቅጽበት ነፍሴ በደስታ ዘለለች!” ብለዋል።4

ጌታ የሚገልጠው እና የሚመልሰው ከዚህ አለም ላለፉት ለምናፈቅራቸው የምንጠመቅበትን ብቻ አልነበረም። እግዚአብሔር ለወንዶች እና ለሴቶች ልጆቹ ሊለግስ የጓጓቸው ሌሎች ብዙ ስጦታዎች ወይም ቡራኬዎች ነበሩ።

እነዚህ ሌሎች ስጦታዎች የክህነት ስልጣን፣ ቃል ኪዳኖች እና ሥርዓቶች፣ ለዘለአለም ለመቆየት የሚችሉ ጋብቻዎች፣ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ልጆችን ከወላጆቻቸው ጋር ማሠር ወይም ማተም፣ እና በመጨረሻም ወደ እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እና ወደ ልጁ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የመመለስን በረከት ያካትቱ ነበር። እነዚህ ሁሉ በረከቶች የተገኙት በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ አማካኝነት ነው።

እግዚአብሔር እነዚህን ከሁሉ የላቀ እና ቅዱስ በረከቶች5 መካከል አድርጎ ስለቆጠረ፣ እነዚህን ውድ ስጦታዎች ለልጆቹ የሚሰጥበት የተቀደሱ ሕንፃዎች እንዲቆሙ አዟል6። እነዚህ ሕንፃዎች በምድር ላይ የእርሱ መኖሪያ ይሆናሉ። እነዚህ ሕንጻዎች በምድር ላይ በስሙ እና በቃሉ የታተመ ወይም የታሰረ በሰማይም የሚታተምባቸው ወይም የሚታሰርባቸው ቤተ መቅደሶች ይሆናሉ 7

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያኗ አባልነት፣ እነዚህን የከበሩ ዘለአለማዊ እውነቶችን እንደ ተራ ነገር መውሰድ ቀላል ሊሆንብን ይችላል። እኛ የለመድነው ነገር ሆነዋል። አንዳንድ ጊዜ ስለ እነርሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተማሩ ሰዎች ዓይን ብናያቸው ጠቃሚ ነው። ይህ በቅርብ ጊዜ ባጋጠመኝ ሁኔታ ግልጽ ሆነልኝ።

ባለፈው ዓመት፣ የቶኪዮ ጃፓን ቤተመቅደስ ዳግም ከመመረቁ በፊት፣ ከእምነታችን ያልሆኑ ብዙ እንግዶች ያንን ቤተመቅደስ ጎበኙ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ከሌላ ሃይማኖት የመጣ አስተዋይ መሪን ያካተተ ነበር። ለእንግዳችን ስለ የሰማይ አባት የደስታ እቅድ፣ በዚያ እቅድ ውስጥ ስላለው የኢየሱስ ክርስቶስ የማቤዣ ሚና እና ቤተሰቦች በማተም ስነ-ስርዓት በኩል ለዘለአለም አንድ ሊሆኑ እንደሚችሉ ትምህርት አስተማርን።

በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ ወዳጃችን ስሜቱን እንዲገልጽ ጋበዝኩት። ያለፈውን፣ የአሁን፣ እና የወደፊት ቤተሰብን አንድ ስለማድረግ በተመለከተ ይህ መልካም ሰው በቅንነት እንዲህ ሲል ጠየቀ፣ “የእምነትህ አባላት ይህ ትምህርት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ በትክክል ተረድተዋል?” “ምናልባት ይህ እጅግ የተከፋፈለውን ዓለም አንድ ሊያደርጉ ከሚችሉ ትምህርቶች አንዱ ሊሆን ይችላል” በማለት አከለ።

እንዴት ያለ ኃይለኛ ምልከታ ነው። ይህ ሰው የተነካው በቤተመቅደሱ ድንቅ የእጅ ጥበብ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ቤተሰቦች ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለዘለአለም የታሰሩ ይሆናሉ በሚለው ድንቅ እና ጥልቅ ትምህርት ነበር።8

እንግዲያው የእኛ እምነት ያልሆነ ሰው እንኳን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚደረገውን ታላቅነት ሲገነዘብ ሊያስደንቀን አይገባም። ለእኛ የተለመደ ወይም ተራ ሊሆን የሚችለው አንዳንድ ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሰሙ ወይም በሚሰማቸው ሰዎች ግሩም እና አስደናቂ ሆኖ ይታያል።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ ማለዳ ጀምሮ፣ ቤተመቅደሶችን መገንባት ከነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ጀምሮ በሁሉም ነቢያት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ነበር። እና ለምን እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ነው።

ነቢዩ ጆሴፍ ስለ ሙታን ጥምቀት ሲያስተምር ሌላ ታላቅ እውነትን ገለጠ። እንዲህ አስተማረ፣ “ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ደህንነታችንን በሚመለከትም፣ እነዚህ ሙታንንና ህያዋንን የሚመለከቱ መሰረታዊ መርሆች በቀላል እንደማይታለፉ ላረጋግጥላችሁ። መዳናቸው ለእኛ መዳን አስፈላጊ እና መሰረታዊ ነው፣ … ያለ እኛ ፍጹማን ሊሆኑ አይችሉም—ወይም እኛ ያለሙታኖቻችን ፍጹም ልንሆን አንችልም።9

ለማየት እንደምንችለው፣ የቤተመቅደሶች አስፈላጊነት እና ለህያዋንም ሆነ ለሙታን የሚደረገው ሥራ በጣም ግልጽ ይሆናል።

ተቃዋሚው በንቃት ላይ ነው። በቤተመቅደሶች ውስጥ በሚደረጉ ስነስርዓቶች እና ቃል ኪዳኖች ኃይሉ ስጋት ውስጥ ገብቷል፣ እናም ስራውን ለማቆም የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ለምን? ምክንያቱም ከዚህ ቅዱስ ሥራ የሚመጣውን ኃይል ስለሚያውቅ ነው። እያንዳንዱ አዲስ ቤተመቅደስ ሲወሰን የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ኃይል ለእኛ ቤዛ ለመሆን እና ወደ እርሱ ስንመጣ የጠላትን ጥረቶች ለመቋቋም በመላው አለም ይስፋፋል። ቤተመቅደሶች እና ቃል ኪዳን ጠባቂዎች በቁጥር እያደጉ ሲሄዱ፣ ጠላትም እየደከመ ይሄዳል።

በቤተክርስቲያኗ የመጀመሪያ ጊዜያት፣ አንዳንዶች አዲስ ቤተመቅደስ መቼ ይታወጃል በማለት ይጨነቁ ነበር ምክንያቱም “የገሃነም ደወሎች መጮህ ሳይጀምር ቤተመቅደስ መስራት አልጀመርንም” ይሉ ስለነበር ነው። ነገር ግን ብሪገም ያንግ በድፍረት “እንደገና ሲደውሉ መስማት እፈልጋለሁ” በማለት መለሰ10

በዚህ ሟች ህይወት ውስጥ ጦርነቱን አናመልጥም ነገር ግን በጠላት ላይ ስልጣን ሊኖረን ይችላል። በቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖችን ስንገባ እና ስንጠብቅ ሃይል እና ጥንካሬ የሚመጣው ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ፕሬዘደንት ራስል ኤም፡ “ለጌታ የማይታዘዙት ከሚታዘዙት የሚለዩበት ጊዜ ይመጣል። የእኛ አስተማማኝ ዋስትና ወደ ቅዱስ ቤቱ ለመግባት ብቁ በመሆን መቀጠል ነው” በማለት አስተምረዋል።11

እግዚአብሔር በነቢዩ በኩል ቃል የገባልን አንዳንድ ተጨማሪ በረከቶች እነሆ፦

ተአምራት ትፈልጋላችሁ? ነቢያችን፣ “በቤተመቅደሶቹ ውስጥ ለማገልገል እና ለማምለክ መስዋዕቶች ስታደርጉ፣ ጌታ እናንተ እንደሚያስፈልጋችሁ የሚያውቀውን ታዕምራት እንደሚያመጣ ቃል እገባላችኋለሁ” ብለዋል።12

የአዳኙን የኢየሱስ ክርስቶስን የፈውስ እና የብርታት ኃይል ትፈልጋላችሁን? ፕሬዘደንት ኔልሰን እንድናረጋገጥ እዳደረጉት፣ “በቤተመቅደስ ውስጥ የምንማራቸው ነገሮች ሁሉ … ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ግንዛቤ ይጨምራሉ። … ከዚያም በኋላ፣ ቃል ኪዳኖቻችንን ስንጠብቅ፣ በእርሱ ፈዋሽ፣ የሚያበረታ ኃይል ይባርከናል። እና አቤቱ፣ የእርሱ ኃይል በመጪዎቹ ቀናት እንዴት እንደሚያስፈልገን።”13

ኢየሱስ ክርስቶስ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት በመጀመሪያው የሆሳዕና እሑድ፣ ብዙ ደቀ መዛሙርት “ደስ አላቸው እናም በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ” እንዲህ አሉ፣ “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው።”14

በሆሳና እሁድ በ1836 (እ.አ.አ) የከርትላንድ ቤተመቅደስ እየተቀደሰ መሆኑ ምንኛ ተገቢ ነበር። በዚያ ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም ደስተኞች ነበሩ። በዚያ የመወሰኛ ጸሎት ላይ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እነዚህን የምስጋና ቃላት ተናግሯል፦

“ጌታ ኤልሻዳይ ሆይ፣ … ስማን፣ እና በግርማ፣ በክብር፣ በሀይል፣ በስልጣን በዙፋንህ ላይ ከምትቀመጥበት ከቅዱስ መኖሪያህ ሰማይም መልስ ስጠን። …

“…እና ከዙፋንህ ዙሪያ ከሚገኙት ከደማቅ፣ አንጸባራቂ ሱራፌሎች ጋር በአድናቆት ምስጋና፣ ለአምላክ እና ለበጉ ሆሳዕና በመዘመር ድምጻችንን እናሰማ ዘንድ በመንፈስህ ሀይልም እርዳን!

“እነዚህ … ቅዱሳንህም በደስታ እንዲጮሁ ፍቀድ።”15

ወንድሞች እና እህቶች፣ ዛሬ በዚህ በሆሳዕና እሑድ፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ቅዱስ አምላካችንን እናመስግን እናም ለእኛ ባለው መልካምነት ደስተኞች እንሁን። “አሁን፣ በተቀበልነው ወንጌል ውስጥ ምን እንሰማለን?” በእውነት “የደስታ ድምፅ!”16

የጌታ የተቀደሰ ቤተ መቅደሶች ውስጥ ስትገቡ ደስታን የበለጠ እንደምታገኙ እመሰክራለው። እርሱ ለእናንተ ያለውን ደስታ እንደምትለማመዱ እመሰክራለው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

አትም