ጉድለቶች ያሉበት አጨዳ
አዳኙ የእኛን ትንሽ መሥዋዕት ለመቀበል እና በፀጋው ፍጹም ለማድረግ ዝግጁ ነው። ከክርስቶስ ጋር ሆኖ ፍጹም ያልሆነ ፍሬ የለም።
ልጅ እያለሁ ባደግሁበት ደቡብ ምዕራብ ሞንታና የዓመቱን ወቅቶች አስደናቂ ለውጦች መውደድ ተማርኩኝ። ከሁሉም አስበልጬ የምወደው የአጨዳ ጊዜ የሆነውን የመኸር ወቅትን ነበር። ቤተሰባችን የወራት ልፋታችን በተትረፈረፈ ምርት እንደሚካስ ተስፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን ጸለዮም ነበር። ወላጆቼ ስለአየሩ ሁኔታ፣ ስለእንስሳቱ እና ስለተክሎቹ ደህንነት እንዲሁም ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ ስለሆኑ ስለሌሎች ብዙ ነገሮች ይጨነቁ ነበር።
ሳድግ በጣም አስፈላጊ ነገር መሆኑን ይበልጥ ተገነዘብኩኝ። ኑሯችን የተመሰረተው በምንሰበስበው እህል ላይ ነበር። አባቴ እህል ለመሰብሰብ እንጠቀምበት ስለነበረው መሳሪያ አስተማኝ። የእርሻ መሳሪያውን ወደ እርሻ ውስጥ ሲያስገባ፣ ትንሽ የእህል መደብ ሲያጭድ እና የተቻለውን ያህል ብዙ እህል በማጠራቀሚያው ውስጥ እንዳረፈ እና ከገለባው ጋር አብሮ እንዳልተጣለ ለማረጋገጥ ወደማጨጃ መሳሪያው የኋለኛ ክፍል ሲያይ ተመለከትኩ። በእያንዳንዱ ጊዜ የማጨጃ መሳሪያውን እያስተካከለ ይህንን ድርጊት ብዙ ጊዜ ደጋገመ። ከጎን ጎኑ እየሮጥኩ የሚያደርገውን እንደሚያውቅ ሰው ከእርሱ ጋር ገለባውን ነካ ነካ አደረኩት።
በማሽኑ ላይ በቂ ማስተካከያ እንዳደረገ ካረጋገገጠ በኋላ መሬት ላይ ከወደቀው ገለባ ውስጥ የተወሰኑ የእህል ፍሬዎችን አገኘሁና ይህ ለምን ሆነ የሚል እይታ እያሳየሁ ሰጠሁት። አባቴ ለእኔ ያለኝን አልረሳም፣ “በቂ ነው እንዲሁም ይህ መሳሪያ ማድረግ የሚችለው ይህንን ያህል ነው።” በሰጠው ማብራሪያ ስላልረካሁ ስለዚህ አጨዳ ጉድለቶች አሰላስልኩ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ማታ ማታ አየሩ ቀዝቀዝ በሚልበት ጊዜ ወደ ደቡብ ረጅም ጉዞ እያደረጉ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ስዋኖች፣ ዝይዎች እና ዳክዬዎች ለመመገብ እርሻው ላይ ሲያርፉ ተመለከትኩ። ጉድለቶች ከነበሩበት አጨዳችን የተረፈውን እህል ተመገቡ። እግዚአብሄር ፍጹም አድረጎት ነበር። እንዲሁም አንድም ፍሬ አልባከነም ነበር።
ፍጹም መሆን ላይ ማተኮር አብዛኛውን ጊዜ በዓለማችን እንዲሁም በቤተክርስቲያኗ ባህል ውስጥም እንኳን ፈተና ነው። ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ እውን መሆን የማይችሉ ተስፋዎች እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ የራሳችን ትችት ብቁ ያለመሆን እና መቼም ብቁ ልንሆን አንችልም የሚል ስሜት ይፈጥራሉ። አንዳንዶች “እንግዲህ እናንተም ፍጹማን ሁኑ” የሚለውን የአፋኙን ግብዣ በተሳሳተ መንገድ ይረዳሉ።1
ፍጹም መሆን በክርስቶስ ፍጹም ከመሆን ጋር አንድ እንዳልሆነ አስታውሱ።2 ፍፁም መሆን ሊሳካ የማይችል እኛን ከሌሎች ጋር የሚያወዳድር በራስ ላይ የተቀመጠ መሥፈርት ይፈልጋል። ይህ የጥፋተኝነት ስሜትንና ጭንቀትን ያስከትላል እንዲሁም ራሳችንን ለማግለልና ከሌሎች እንድንለይ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
በክርስቶስ ፍጹም መሆን ከዚህ በጣም የተለየ ነገር ነው። በፍቅር በመንፈስ ቅዱስ በመመራት—ይበልጥ አዳኙን የመምሰል—ሂደት ነው። መሥፈርቶቹ የተቀመጡት ደግ በሆነው እና ሁሉን በሚያውቅ የሰማይ አባት ነው እንዲሁም እንድንቀበላቸው እና እንድንኖራቸው በተጋበዝንባቸው ቃል ኪዳኖች ውስጥ በግልፅ ተቀምጠዋል። ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እይታ ማን እንደሆንን አጽንኦት በመስጠት ከጥፋተኝነት እና ብቁ ካለመሆን ሸክሞች ነጻ ያደርገናል። ይህ ሂደት የሚያነሳሳን እና የተሻልን እየሆንን እንድንሄድ የሚያበረታታን ቢሆንም፣ የምንለካው በእምነት እርሱን ለመከተል በምናደርገው ጥረት ለእግዚአብሔር ባለን የግል ቁርጠኝነት ነው። አዳኙ ወደ እርሱ እንድንመጣ ያቀረበልንን ግብዣ ስንቀበል፣ ያለን ምርጥ ነገር በቂ እንደሆነ እንዲሁም የአፍቃሪ አዳኙ ጸጋ እኛ መገመት በማንችላቸው መንገዶች ልዩነት እንደሚያመጣ ወዲያው እንገነዘባለን።
አዳኙ አምስት ሺህ ሰዎችን በመገበበት ጊዜ ይህን መርህ በተግባር ማየት እንችላለን።
ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን አለው?…
“ፊልጶስ፦ እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት።
“ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ፣
“አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል አለው?”3
በልጅ እምነት፣ መከናወን ያለበትን ተግባር ታላቅነት ግምት ውስጥ በማስገባት በሚያሳዝን ሁኔታ በቂ እንዳልሆነ የሚያውቀውን ነገር ስላቀረበው ስለዚህ ወጣት ልጅ አዳኙ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስባችሁ ታውቃላችሁ?
“ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፥ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን።
“ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፦ አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ አከማቹ አላቸው።“4
አዳኙ ትንሹን መሥዋዕት በቂ እንዲሆን አደረገው።
ይህ ከሆነ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን በጀልባ አስቀድሞ ላካቸው። ብዙም ሳይቆይ በእኩለ ሌሊት ራሳቸውን በማዕበል በሚናወጥ ባህር ላይ አገኙት። የመንፈስ ምስል በውሃው ላይ እየተራመደ ወደእነርሱ ሲመጣ ባዩ ጊዜ ታወኩ።
“ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና፦ አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው።
“ጌታ ሆይ፣ አንተስ ከሆንህ በውሃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው።
“እርሱም ና፤ አለው። ጴጥሮስም ከጀልባው ወርዶ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በውኃው ላይ ተራመደ።
“ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ።
ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፦ አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው።5
ወንድሞች እና እህቶች፣ ያ የውይይቱ መጨረሻ ላይሆን ይችላል። ጴጥሮስ እና አዳኙ፣ ጴጥሮስ በውሃው እንደረጠበና ምናልባትም በጣም የመሞኘት ስሜት እየተሰማው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ጀልባው ሲመለሱ፣ አዳኙ ይህን የመሰለ ነገር ብሎ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ፡- “ጴጥሮስ ሆይ፣ አትፍራ እንዲሁም አትጨነቅ። እኔ አንተን በማይበት ዓይን ራስህን ብታይ ኖሮ ጥርጣሬህ አክትሞ እምነትህ ያድግ ነበር። ውድ ጴጥሮስ፣ ከጀልባው ስለወረድክ እወድሃለሁ። ተሰናክለህ የነበረ ቢሆንም መሥዋዕትህ ተቀባይነት አለው፤ ማንኛውንም ችግር እንድትቋቋም ልረዳህ ሁል ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እንዲሁም መሥዋዕትህ ፍጹም ይደረጋል።”
ሽማግሌ ዲየትርኤፍ. ኡክዶርፍ አስተማሩ፦
“አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ጥንካሬያችሁ እንደሆነ እንድታዩ፣ እንዲሰማችሁ እና እንድታውቁ። በእርሱ እርዳታ አማካኝነት ማድረግ የማትችሉት ነገር እንደሌለ። አቅማችሁ ወሰን አልባ እንደሆነ። እርሱ በሚያያችሁ መንገድ እራሳችሁን እንድታዩ እንደሚፈልግ። አንዲሁም ያ ዓለም እናንተን ከሚያይበት መንገድ በጣም የተለየ እንደሆነ አምናለሁ“ ሲሉ አስተምረዋል።
“ለደከሙት ኃይልን ይሰጣል፤ እንዲሁም ኃይል እንደሌላቸው ለሚሰማቸው ጥንካሬን ይጨምራል።”6
ምንም ይሁን ምን የእኛ ምርጥ የሆነውን ፍጽምና የጎደለው መስዋዕት አዳኙ ፍጹም ሊያደርገው እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። ጥረቶቻችን ምንም ያህል እዚህ ግባ ሊባሉ የማይችሉ ቢመስሉ የአዳኙን ኃይል በፍጹም ዝቅ አድርገን መመልከት አይገባንም። ቀላል የደግነት ቃል፣ አጠር ያለ ልባዊ የሆነ የአገልግሎት ጉብኝት ወይም በፍቅር የተሰጠ የመጀመሪያ ክፍል ትምህርት፣ በአዳኝ እርዳታ መጽናናትን መስጠት፣ ልቦችን ማራራት እንዲሁም የብዙዎችን የዘላለም ህይወት መቀየር ይችላል። ክህሎት የጎደለው ጥረታችን ወደ ተዓምራት ሊመራ ይችላል እንዲሁም በሂደቱ ፍጹም በሆነ የአጨዳ ሥራ ውስጥ መሳተፍ እንችላለን።
ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ በሆኑ ተሞክሮዎች አማካኝነት በመንፈሳዊ እንድናድግ በሚያደርጉ ሁኔታዎች ውስጥ እንሆናለን። ሥራውን መፈጸም እንደምንችል ላይሰማን ይችላል። አብረናቸው የምናገለግለውን ሰዎች በመመልከት መቼም ብቁ እንደማንሆን ይሰማን ይሆናል። ወንድሞች እና እህቶች እንደዚህ የሚሰማችሁ ከሆነ ከኋላዬ የተቀመጡትን አብሬአቸው የማገለግለውን አስደናቂ ወንዶች እና ሴቶች ተመልከቱ።
ህመማችሁ ይሰማኛል፡፡
ሆኖም ፍጹም መሆን በክርስቶስ ፍጹም ከመሆን ጋር አንድ እንዳልሆነ ሁሉ ራስን ማነጸጸር ከመምሰል ጋር አንድ እንዳልሆነ ተምሪያለሁ። እራሳችንን ከሌሎች ጋር በምናወዳድርበት ጊዜ የሚኖሩት ሁለት ውጤቶች ብቻ ናቸው። ወይ ራሳችንን ከሌሎች የተሻልን አድርገን በመመልከት በሌሎች ላይ የምፈርድና ሌሎችን የምንወቅስ እንሆናለን አለበለዚያ ራሳችንን ከሌሎች ያነስን አድርገን በመመልከት እንጨነቃለን፣ ራሳችንን እንወቅሳለን እንዲሁም ተስፋ እንቆርጣለን። ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማነጻጸር ፍሬያማ አያደርግም፣ የተሸለ ሰው አያደርግም እንዲሁም አንዳንዴም ፍጹም የሚያሳምም ነው። በርግጥም እነዚህ ንጽጽሮች የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ እርዳታ እንዳናገኝ እንቅፋት በመሆን ትልቅ መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትሉብን ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የምናከብራቸውን የክርስቶስን የመሰለ ባሕርያትን የሚያሳዩ ሰዎችን መምሰላችን የሚያስተምር እና የሚገነባ እና የተሻለ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንድንሆን ሊረዳን ይችላል።
አዳኙ አብን በመምሰል ልንከተለው የሚገባንን ምሳሌ ትቶልናል። ደቀ መዝሙሩን ፊሊጶስን እንዲህ አዘዘው፣ “አንተ ፊሊጶስ፥ ይህንን ያህል ዘመን ከአንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል፥ እንዴትስ አንተ፥ አብን አሳየን ትላለህ?“7
ከዚያም እንዲሀ ሲል አስተማረ “በእኔ የሚያምን፣ እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል።”8
ጥረቶቻችን ምንም ያህል እዚህ ግባ ሊባሉ የማይችሉ ቢመስሉ፣ ቅን ከሆንን አዳኙ ሥራውን ለመስራት ይጠቀምብናል። በቀላሉ የምንችለውን ሁሉ ካደረግን እና እርሱ ጉድለታችንን እንደሚሞላልን ካመንን በዙሪያችን የከበቡን ተዓምራት አካል ልንሆን እንችላለን።
ሽማግሌ ዴል ጀ. ረንለንድ እንዲህ ብለዋል “ፍጹማን መሆን አያስፈልገችሁም ነገር ግን አንፈልጋችኋለን፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ፈቃደኛ የሆነ ሰው የተወሰነ ነገር ማድረግ ይችላል9
እንዲሁም ፕሬዝዳንት ረስልኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩን “ጌታ ጥረትን ይወዳል።“10
አዳኙ የእኛን ትንሽ መሥዋዕት ለመቀበል እና በፀጋው ፍጹም ለማድረግ ዝግጁ ነው። ከክርስቶስ ጋር ሆኖ ፍጹም ያልሆነ ፍሬ የለም። እርሱ እንደሚረዳን፣ በምንሰናከልበት ጊዜ ከማንኛውንም ችግር እንደሚያድነን እንዲሁም ፍፁም ያልሆነውን ጥረታችንን ፍጹም ያደርግ ዘንድ ጸጋው ለእኛ እንደሆነ ለማመን ድፍረት ሊኖረን ይገባል።
በዘሪው ምሳሌ ውስጥ አዳኙ በመልካም መሬት ላይ ስለበቀሉ ፍሬዎች ይገልጻል። አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሁሉም የእርሱ ፍጹም ፍሬዎች ናቸው።11
ነቢዩ ሞሮኒ ሁሉንም እንዲህ ሲል ጋብዟል፣ “እናም ለራሳችሁ ኃጢአተኝነትን በሙሉ ከካዳችሁ፣ በሙሉ ኃይላችሁ እና አእምሮአችሁ እና ጉልበታችሁ እግዚአብሔርን ከወደዳችሁ፣ ፀጋው ለእናንተ ይበቃችኋል፣ በፀጋው በክርስቶስ ፍፁም ትሆናላችሁ።”12
ወንድሞች እና እህቶች፣ ትንሹን መሥዋዕታችንን እንኳ ፍጹም ለማድረግ ሃይል ስላለው ስለክርስቶስ እመሰክራለሁ። የምንችለውን እናድርግ፣ ማምጣት የምንችለውን እናምጣ እንዲሁም ፍጹም ያልሆነውን መስዋዕታችንን በእምነት በእግሮቹ ስር እናስቀምጥ። የፍጹም መኸር ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።