ከአራተኛው ቀን በኋላ
በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ወደፊት ስንጓዝ አራተኛው ቀን ሁልጊዜም ይመጣል። እርሱም ሁልጊዜ ሊረዳን ይመጣል።
ጠዋት ላይ እንድናስታውስ እንደተደረገው፣ ዛሬ አዳኙ ወደ ኢየሩሳሌም የገባብት እና የእርሱን ታላቅ የሃጢያት ክፍያ ማለትም ስቃዩን፣ ስቅለቱን እና ትንሳኤውን የሚያስከትለውን ቅዱስ ሳምንት የጀመረበት የሆሳዕና ሰንበት ነው።
እንደተተነበየው ወደ ከተማው ከመግባቱ ብዙም ሳይቆይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከውድ ጓድኞቹ፣ ከማርያም እና ከማርታ፣ ወንድማቸው አልዓዛር መታመሙን ሲሰማ ሙሉ በሙሉ በአገልግሎቱ ላይ ተሰማራ።1
የአልዓዛር ህመም የከፋ ቢሆንም እንኳን፣ ጌታ “ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ። ከዛም ለደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ አላቸው።”2 ቢታንያ ወደሚገኘው ወደጓደኞቹ ቤት ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት፣ “ኢየሱስ [ለደቀመዛሙርቱ] በግልጥ አልዓዛር ሞተ” አለ። 3
ኢየሱስ ወደ ቢታንያ ውስጥ ሲመጣ መጀመሪያ ማርታን ከዛ ደግሞ ማርያምን አገኘ። ምናልባት አርፍዶ በመምጣቱ ምክንያት ተስፋ በመቁረጥ ሁለቱም “ጌታ ሆይ፣ አንት በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” በማለት ሰላምታ ሰጡት።4 ማርታም እንዲህ በማለት ገለጸች፣ “ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል።”5
እነዚህ አራት ቀናት ለማርያም እና ለማርታ አስፈላጊ ነበሩ። እንደ አንዳንድ የረቢዎች አስተሳሰብ፣ የሞቱ ሰዎች ነፍስ በህይውት መኖር እንደሚቻል ተስፋን በመስጠት አካል ውስጥ ለሶስት ቀናት እንደሚቆዩ ይታመን ነበር። ይሁን እንጂ፣ በአራተኛው ቀን ያ ተስፋ ይጠፋል ምክንያቱም አካል መበስበስ እና “[መሽተት]” ስለሚጀምር።6
ማርታ እና ማሪያም በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነበሩ። ። ኢየሱስም [ማሪያም] ስታለቅስ ሲመለከት… በመንፈሱ አዘነ፥ በራሱም ታወከ።
“ወዴት አኖራችሁት? አለም። “ጌታ ሆይ፣ መጥተህ እይ አሉት።”7
በዚህ ወቅት ነው በእርሱ ምድራዊ አገልግሎት ውስጥ ከተአምራቶች ውስጥ አንዱን የምናየው። በመጀመሪያ ጌታ እንዲህ አለ፣ “ድንጋዩን አንሱ።”8 ከዛ አባቱን ካመሰገነ በኋላ፣ “አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ።
“የሞተውም እጆቹ እና እግሮቹ ተገንዘው፣ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፣ ፍቱት እና ይሂድ ተዉት አላቸው።”9
ልክ እንደ ማርያም እና ማርታ፣ ሁሉንም ሟችነት፣ ሃዘንን10 እና ድክመትን11 ለመለማመድ እድል አለን። እያንዳንዳችን የምንወደውን ሰው በማጣት የሚመጣ የልብ ሃዘን ይገጥመናል። የእኛ ምድራዊ ጉዞ ግላዊ ወይም የምንወደው ሰው በሽታን፣ የመንፈስ ጭንቀትን፣ ድብታ ወይም ሌላ የአእምሮ የጤና እክሎችን፤ የገንዘብ ችግርን፤ ክህደትን፤ ሃጢያትን ሊያካትት ይችላል። እናም አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ተስፋ በመቁረጥ ስሜቶች ይታጀባሉ። እኔ የተለየሁ አይደለሁም። እንደ እናንተም፣ በዚህ ህይወት ውስጥ የሚጠበቁ እጅግ በጣም ብዙ ፈተናዎች አጋጥመውኛል። ስለ አዳኙ እና ከእርሱ ጋር ስላለን ግንኙነት በሚያስተምረኝ በዚህ ታሪክ ተስቤአለው።
በታላላቅ ሃዘኖቻችን ውስጥ፣ እንደ ማርያም እና ማርታ አዳኙን እንሻለን ወይም አብን ለእርሱ መለኮታዊ ምልጃ እንጠይቃለን። በህይወታችን ውስጥ ግላዊ ችግሮች ሲገጥሙን የአልዓዛር ታሪክ ተግባራዊ የሚሆኑ መርሆዎችን ያስተምረናል።
አዳኙ ቢታንያ ሲደርስ፣ ሁሉም አልዓዛር መዳን አይችልም ብለው ተስፋ ቆርጠው ነበር ምክንያቱም ከሞተ አራት ቀናት አልፈዋልና። አንዳንድ ጊዜ በገዛ ችግሮቻችን ወቅት፣ ክርስቶስ በጣም የዘገየ መስሎ ሊሰማን እንዲሁም ተስፋችን እና እምነታችን የተፈተነ ሊመስለን ይችላል። በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ወደፊት ስንጓዝ አራተኛው ቀን ሁል ጊዜ እንደሚመጣ ምስክርነቴ ነው። እርሱ ሁሌም ሊረዳን ወይም ተስፋችንን ወደ ህይወት ሊመልስ ይመጣል። እንዲህ ሲል ቃል ገብቶልናል፦
“ልባችሁ አይታወክ።12
“ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፥ ወደ እናንተ እመጣለሁ።”13
አንዳንድ ጊዜ ሁሉም ተስፋ የተሟጠጠ እስኪመስል በምሳሌ አነጋገር እስከ አራተኛው ቀን ድረስ ወደ እኛ የማይመጣ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ለምን ያን ያህል ይቆያል? ፕሬዘደንት ቶማስ ኤስ. ሞንሰን እንዲህ አስተማሩ፣ “የሚያስደስቱን ብዙ ነገሮች የሚሰጠን የሰማይ አባታችን መቋቋም ባለብን ፈተናዎች መማር፣ ማደግና፣ መጠናከር እንደምንችል ያውቃል።”14
ነብዩ ጆሴፍ ስሚዝ እራሱ ከባድ የአራተኛ ቀን ልምድ አጋጥሞታል። ልመናውን ታስታውሳላችሁን? “እግዚአብሔር ሆይ የት ነህ? እና የተሰወርክበትን ስፍራ የሚሸፍነው ድንኳን የት ነው?”15 በእርሱ ስናምን፣ እንደዚህ ዓይነት መልስ መጠበቅ እንችላን፦ “ልጄ፣ ለነፍስህ ሰላም ይኑርህ፤ ጭንቀትህ እና ስቃይህ ለጥቂት ጊዜ ቢሆን ነው።”16
ከአልዓዛር ታሪክ ውስጥ መማር የምንችለው ሌላኛው መልዕክት በምንሻው መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ውስጥ የገዛ ሚናችን ምን ሊሆን እንደሚችል ነው። ኢየሱስ መቃብሩን ሲቀርብ፣ እርሱ እዛ ላሉት ስዎች በመጀመሪያ እንዲህ አለ፣ “ድንጋዩን አንሱ።”17 አዳኙ ባለው ኃይል የተነሳ ካለምንም ጥረት እርሱ ድንጋዩን በተአምር ማንቀሳቀስ አይችልም ነበርን? ይህን ማየት አስደናቂ እና የማይረሳ ልምድ ይሆን ነበር፣ ነገር ግን እርሱ ለሌሎቹ እንዲህ አለ፣ “ድንጋዩን አንሱ።”
ሁለታኛ፣ ጌታ “በታላቅ ድምጽ አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ።”18 ድንጋዩ ዞር ሲል በሰዎች በቶሎ እንዲታይ ጌታ፣ እራሱ፣ በተአምር አልዓዛርን መግቢየው ላይ ቢያደርገው ኖሮ የበለጠ አያስደንቅም ነበረን?
ሶስተኛ፣ አልዓዛር በወጣ ጊዜ “እጆቹ እና እግሮቹ ተገንዘው፣ ፊቱም በጨርቅ እንድ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፣ ፍቱት እና ይሂድ ተዉት አላቸው።”19 አልዓዛር ንፁህ ሆኖ እና የመገነዣ ጨርቁ በመልካሙ ታጥፎ ጌታ መግቢያው ላይ ሊያቆመው እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ።
እነዚህን ገጽታዎች የመጠቆም ጠቀሜታ ምንድን ነው? እያንዳንዳቸው እነዚህ ሶስት ነገሮች የጋራ ነገር አላቸው—ማንኛዎቹም የክርስቶስን መለኮታዊ ኃይል መጠቀመም አላስፈለጋቸውም። ደቀመዛሙርቱ ማድረግ የሚችሉትን ነገሮች እነርሱ እንዲያደርጉ አዘዛቸው። በእርግጥ ደቀመዛሙርቱ ድንጋዩን በራሳቸው የማንቀሳቀስ ችሎታ ነበራቸው፤ አልዓዛር ከተነሳ በኋላ በዋሻው መግቢያ ላይ ለመቆም እና እራሱን ለማቅረብ ችሎታ ነበረው እናም የአልዓዛር ወዳጆች መገነዣውን ለማውለቅ መርዳት ይችሉ ነበር።
ይሁን እንጂ፣ አልዓዛርን ከሞት የማንሳት ኃይል እና ሥልጣን የነበረው ክርስቶስ ብቻ ነበር። የእኔ አመለካከት፣ አዳኙ ማድረግ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ይጠብቅብናል እናም እርሱ ብቻ ማድረግ የሚችለውን ነገር ያደርጋል።20
“እምነት [በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ] የተግባር መርህ እንደሆነ” እናውቃለን21 እና “ተአምራቶች እምነትን አይፈጥሩም፣ ነገር ግን ጠንካራ እምነት የሚዳብረው ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በመታዝዘ ነው። በሌላ አባባል፣ እምነት የሚመጣው በጽድቅ ነው።”22 ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን በማድረግ እና በመጠበቅ በጽድቅ ለመተግበር እና የክርስቶስን ትምህርት በህይወታችን ውስጥ ለማከናወን ስንጥር፣ እምነታችን ወደ አራተኛው ቀን ሊያሸጋግረን በቂ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ በጌታ እርዳታ ከተስፋ መቁረጥ የመነጩ በመንገዳችን ላይ ያሉ መሰናክሎችን ማንሳት እና የሚያስሩንን ነገሮች መፍታት እንችላለን። “በአቅማችን ያሉትን ነገሮች በሙሉ እንድናደርግ” ጌታ ሲጠብቅብን23 በእርሱ ስናምን በእነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚያስፈልገውን እርዳታ እንደሚሰጥ አስታውሱ።
እንዴት ነው ድንጋዮችን አንስተን በእርሱ አለት ላይ መገንባት የምንችለው?24 የነቢያትን ምክር መጠበቅ እንችላለን።
ለምሳሌ፣ ባለፈው ጥቅምት ፕሬዝዳንት ረስል ኤም. ኔልሰን በአዳኙ እና በወንጌሉ ላይ በገዛ ምስክርነቶቻችንን ሃላፊነትን እንድንወስድ፣ ለእነሱ እንድንሰራ እና እንድንከባከባቸው፣ እውነትን እንድንመግባቸውእና አማኝ ባልሆኑ በተሳሳተ ፍልስፍና እንዳንበክላቸው ተማጽነዋል። ለእያንዳንዳችን እንዲህ ቃል ገባ፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ምስክርነት ለማጠናከር ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ስትሰጡ፣ ተዓምራትን በህይወታችሁ እንዲከሰቱ ጠብቁ።”25
ይህን ማድረግ እንችላለን!
እኛ እንዴት ነው በምሳሌያዊ ሁኔታ ተነስተን መውጣት የምንችለው? በደስታ ንስሃ መግባት እንዲሁም ትዕዛዛትንለመከተል መምረጥ እንችላለን። ጌታ እንዲህ አለ፣ “ትዕዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”26 በየቀኑ ንስሃ ለመግባት መጣር እና ፍላጎት ባለው ልብ በጌታ ፍቅር በመሞላት በደስታ ወደ ፊት መጓዝ እንችላለን።
ይህን ማድረግ እንችላለን!
በጌታ እርዳታ እንዴት ነው ከሚያስሩን ነገሮች እራሳችንን የምንፈታው? በቃል ኪዳኖችአማካኝነት ከሁሉም በላይ በፍቃደኝነት ከሰማይ አባታችን እና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እራሳችንን ማሰር እንችላለን። ሽማግሌ ዲ.ታድ ክርስቶፈርሰን እንዲህ እስተማሩ፦ “የእኛ የስነ ምግባር እና መንፈሳዊ ኃይል ምንጭ ምንድን ነው እናም እንዴት ነው ያገኘነው? ምንጩ እግዚአብሔር ነው። ይህን ኃይል ለመጠቀም የምንችለው ከእርሱ ጋር በገባናቸው ቃል ኪዳኖች በኩል ነው። … በዚህ መለኮታዊ ስምምነት ውስጥ፣ እርሱን በማገልገላችን እና ትዕዛዛቱን በመጠበቃችን በምላሹ ሊደግፈን፣ ሊያነፃን እና ከፍ ሊያደርገን እግዚአብሔር ቃሉን ይጠብቃል።27 ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን መግባት እና መጠበቅ እንችላለን።
ይህን ማድረግ እንችላለን!
“ድንጋዩን አንሱ።” “ወደ ውጭ ና።” “ፍቱት እና ይሂድ ተዉት።”
ምክሮች፣ ትዕዛዛት እና ቃል ኪዳኖች። ይህን ማድረግ እንችላለን!
ሽማግሌ ጀፍሪ አር ሆላንድ እንዳሉት፣ “ አንዳንድ በረከቶች በቶሎ ይመጣሉ፣ አንዳንዶች ዘግይተው፣ አንዳንዶች ከመንግስተ ሰማያት በፊት አይመጡም፣ ነገር ግን የኢየሱስ ከርስቶስን ወንጌልን ተቀብለው ለሚታቀፉ በረከቶቹ ይመጣሉ።”28
እናም በመጨረሻ፣ “ስለዚህ፣ ተደሰቱ፣ እናም አትፍሩ፣ እኔ ጌታ ከእናንተ ጋር ነኝና፣ እናም ከጎናችሁ እቆማለሁ።”29
ሁሌም በሚመጣው ስሙ ቅዱስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ ይህ ምስክርነቴ ነው አሜን።