አጠቃላይ ጉባኤ
አስታራቂዎች ይፈለጋሉ
የሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


19:4

አስታራቂዎች ይፈለጋሉ

ከጸብ እና ከእርቅ አንዱን የመምረጥ ነጻነት አላችሁ። አሁን እና ሁሌም አስታራቂዎች ለመሆን እንድትመርጡ አበረታታችኋለሁ።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ከእናንተ ጋር መሆን አስደሳች ነው። በእነዚህ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ያለማቋረጥ በአእምሮዬ እና በጸሎቴ እያሰብኳችሁ ነበር። አሁን ንግግር ሳደርግላችሁ ጌታ እንድትሰሙት የሚፈልገውን መንፈስ ቅዱስ እንዲገልጽላችሁ እጸልያለሁ።

ከብዙ ዓመታት በፊት የቀዶ ጥገና ሕክምና ተማሪ ሰልጣኝ በነበርኩበት ወቅት፣ በጣም ተላላፊ በሆነ ጋንግሪን የተበከለን እግር እየቆረጠ የነበረን አንድ የቀዶ ጥገና ሐኪምን ረድቻለሁ። ቀዶ ጥገናው አስቸጋሪ ነበር። ከዚያም ይባስ ብሎ ውጥረቱን ለመጨመር፣ ከቡድኑ ውስጥ አንዱ ጥሩ ያልሆነ ሥራ ሰራ እናም የቀዶ ጥገና ሐኪሙ በቁጣ ገነፈለ። በቁጣው መሃል በጀርሞች የተሞላውን የቀዶ ህክምና ምላጭ ወረወረው። ይህም እጄ ላይ አረፈ!

ከቁጥጥር ውጭ ከሆነው የቀዶ ጥገና ሀኪም በስተቀር ሁሉም በቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ያሉ ሰዎች በዚህ አደገኛ የቀዶ ጥገና አሰራር ጥሰት ተደናግጠው ነበር። ደግነቱ፣ እኔ በበሽታው አልተያዝኩም። ነገር ግን ይህ ተሞክሮ በእኔ ላይ ዘላቂ የሆነ ስሜት ጥሎብኛል። በዚያው ሰዓት በእኔ የቀዶ ሕክምና ክፍል ውስጥ ማንኛውም ነገር ቢፈጠር ስሜቴን ከቁጥጥር ውጪ ፈጽሞ እንደማላደርግ ለራሴ ቃል ገባሁ። በብስጭት ምንም ነገር፣ የቀዶ ህክምና ምላጭንም ሆነ የቁጣ ቃላትን፣ ላለመወርወር በዚያን ቀን ቃል ገባሁ።

አሁን እንኳን፣ ከብዙ አሥርተ ዓመታት በኋላ፣ በእጄ ላይ ያረፈው የተበከለው የቀዶ ህክምና ምላጭ ከሕዝባዊ ውይይታችን እና ዛሬ በጣም ብዙ ግላዊ ግንኙነቶቻችንን ከሚጎዳው መርዛማ ጸብ የበለጠ መርዛማ ይሆን ብዬ ራሴን እየጠየኩ አገኛለሁ። በዚህ የመከፋፈል እና በስሜታዊ አለመግባባቶች በሰፈኑበት ዘመን ትህትና እና ጨዋነት የጠፋ ይመስላል።

ብልግና፣ ስህተት መፈለግ እና ሌሎችን ክፉ መናገር ሁሉ በጣም የተለመዱ ናቸው። በጣም ብዙ ተመራማሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ አዝናኞች እና ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ያለማቋረጥ ስድቦችን ይወረውራሉ። ብዙ ሰዎች ከእነሱ ጋር የማይስማማውን ማንኛውንም ሰው ማውገዝ፣ ማጥላላት እና ስም ማጥፋት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዳለው የሚያምኑ ይመስላሉ ይህም በጣም ያሳስበኛል። ብዙዎች በሚያሳዝኑ እና በሚጎዱ ንግግሮች የሌላውን ስም ለመጉዳት የቋመጡ ይመስላሉ።

ቁጣ በፍጹም አያሳምንም። ጠላትነት ማንንም አይገነባም። ጸብ ወደ ተነሳሱ መፍትሄዎች በፍጹም አይመራም። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ አንዳንድ ጊዜ የተከራካሪነት ባህሪን በራሳችን ቤተክርስቲያን ውስጥም እንኳን እናያለን። የትዳር ጓደኞቻቸውን እና ልጆቻቸውን ስለሚያንቋሽሹ፣ ሌሎችን ለመቆጣጠር ቁጣን ስለሚጠቀሙ እንዲሁም የቤተሰብ አባላትን “በዝምታ” ስለሚቀጡ ሰዎች እንሰማለን። ተዛላፊ ስለሆኑ ወጣቶች እና ልጆች እንዲሁም የስራ ባልደረቦቻቸውን ስም ስለሚያጠፉ ሰራተኞች እንሰማለን።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ይህ መሆን የለበትም። የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን፣ ከሌሎች ጋር በምናደርገው መስተጋብር—በተለይ የሃሳብ ልዩነት ሲኖረን ምሳሌ መሆን አለብን። የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታይን ለመለየት ከሚቻልባቸው እጅግ ቀላል መንገዶች አንዱ ያ ሰው ለሌሎች ሰዎች ያለው ርህራሄ ነው።

አዳኙ በስብከቱ ላይ በሁለቱም ወገን ለሚገኙ ተከታዮች ይህንን ግልፅ አድርጓል። “የሚያስተራርቁ ብጹዓን ናቸው፣” አለ፡፡1 “ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት” ብሏል።2 ከዚያም በእርግጥ፣ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁንም ባርኩ፤ ለሚጠሏችሁም መልካምን አድርጉ፣ እናም በከንቱ የሚነቅፉአችሁን እናም የሚያሳድዱአችሁን ውደዱ” ሲል እያንዳንዳችንን የሚፈትን ምክር ሰጥቷል።3

ከመሞቱ በፊት፣ አዳኙ አስራ ሁለቱን ሐዋርያቱን እርሱ እንደወደዳቸው እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ አዘዛቸው።4 በመቀጠልም፣ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ሲል አክሏል።5

የአዳኙ መልእክት ግልጽ ነው፦ የእርሱ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ሁኔታው ምንም ያህል ከባድ ቢሆን አንዳቸው ሌላውን ይገነባሉ፣ ያነሳሉ፣ ያበረታታሉ፣ ያሳምናሉ እናም ያነሳሳሉ። የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት አስታራቂዎች ናቸው።6

ዛሬ የሆሳዕና ሰንበት ነው። በምድር ላይ ከተመዘገቡት በጣም አስፈላጊውን እና እጅግ የላቀውን ክስተት ማለትም የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢያት ክፍያ እና ትንሳኤ ለማክበር በዝግጅት ላይ ነን። አዳኙን ማክበር ከምንችልባቸው ከተመረጡ መንገዶች አንዱ አስታራቂ መሆን ነው።7

የአዳኙ የሃጢያት ክፍያ ጸብን ጨምሮ ሁሉንም ክፋት እንድናሸንፍ አስችሎናል። አትሳሳቱ፣ ጸብ ክፉ ነው ! ኢየሱስ ክርስቶስ “የፀብ መንፈስ ከእኔ አይደለም፣ የፀብ አባት ከሆነ እናም የሰዎችን ልብ እርስ በርስ እንዲጣሉ በቁጣ ከሚያነሳሳው ከዲያብሎስ እንጂ” በማለት አውጇል።8 ጸብን የሚያራምዱ ሰዎች አስበውትም ይሁን ሳያስቡት ከሰይጣን የጨዋታ መጽሐፍ ውስጥ አንድ ገጽ እየወሰዱ ነው። “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም።”9 በቃላት ጥቃታችን የሰይጣንን እቅዶች መደገፍ እና ከዚያም አምላክን ማገልገል እንደምንችል ማሰብ የለብንም።

ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ አንዳችን ሌላችንን የምንንከባከብበት መንገድ በጣም አስፈላጊ ነው! በቤት ውስጥ፣ በቤተክርስቲያን፣ በስራ ቦታ እና በበይነመረብ ላይ ሌሎችን የምናነጋግርበት እና ስለእነርሱ የምናወራበት መንገድ በጣም አስፈላጊ ነው። ዛሬ፣ ከፍ ባለ እና ቅዱስ በሆነ መንገድ ከሌሎች ጋር እንድንገናኝ እጠይቃለሁ። እባካችሁ በጥሞና አዳምጡ። ፊት ለፊትም ሆነ ከኋላ ስለሌላ ሰው ልንለው የምንችለው “ምግባረ መልካም፣ የሚያስደስት ወይም መልካም ሃተታ ወይም ምስጋና”10የእኛ የግንኙነት መስፈርት መሆን አለበት።

በአጥቢያችሁ ውስጥ ያሉ ጥንዶች ቢፋቱ፣ ወይም ወጣት ሚስዮናዊ ወደ ቤት ቢመለስ፣ ወይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ልጅ ምስክርነቱን ከተጠራጠረ፣ የእናንተ ፍርድ አያስፈልጋቸውም። በቃላችሁ እና በድርጊታችሁ ውስጥ የሚታየውን የኢየሱስ ክርስቶስ ንጹህ ፍቅር ሊሰማቸው ይገባል።

አንድ ጓደኛ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምታምኑትን ሁሉ የሚጥስ ጠንካራ የፖለቲካ ወይም የማህበራዊ አመለካከቶች ቢኖረው የእናንተ የብስጭት ምላሽ ጥቅም የለውም። የመግባቢያ ድልድዮችን መገንባት ከእናንተ ብዙ ተጨማሪ ነገሮችን ይጠይቃል፤ ሆኖም ጓደኛችሁ የሚያስፈልገው በትክክል ያ ነው።

ጸብ መንፈስን ያርቃል—ሁልጊዜ። ጸብ ግጭትን የመፍታት መንገድ ነው የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ያጠናክራል፤ ነገር ግን በጭራሽ አይደም። ጸብ የምርጫ ጉዳይ ነው። ማስታረቅ የምርጫ ጉዳይ ነው። ከጸብ እና ከእርቅ አንዱን የመምረጥ ነጻነት አላችሁ። አሁን እና ሁሌም አስታራቂዎች ለመሆን እንድትመርጡ አሳስባችኋለሁ።11

ወንድሞች እና እህቶች፣ ዓለምን ቃል በቃል መለወጥ እንችላለን—በአንድ ጊዜ አንድን ሰው እና አንድን ግንኘነት። እንዴት? ትክክለኛ የሀሳብ ልዩነቶችን እንዴት በጋራ መከባበር እና ክብር የተመላበት ውይይት መፍታት እንደሚቻል ሞዴል በማድረግ።

የአመለካከት ልዩነቶች የህይወት አካል ናቸው። አንድን ጉዳይ ሁልጊዜ በተመሳሳይ መንገድ ከማያዩ ታማኝ የጌታ አገልጋዮች ጋር በየቀኑ እሠራለሁ። ስለምንነጋገርባቸው ነገሮች ሁሉ ሀሳባቸውን እና እውነተኛ ስሜታቸውን፣በተለይም ጥንቃቄ በሚያሻቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስማት እንደምፈልግ ያውቃሉ።

ፕሬዘደንት ዳለን ኤች. ኦክስ እና ፕሬዘደንት ሔንሪ ቢ. አይሪንግ

የእኔ ሁለት ክቡር አማካሪዎች፣ ፕሬዘደንት ዳለን ኤች. ኦክስ እና ፕሬዘደንት ሔንሪ ቢ. አይሪንግ፣ ስሜታቸውን በሚገልጹበት መንገድ—በተለይ ሊለያዩ በሚችሉበት ጊዜ—አርአያ ናቸው። ይህን የሚያደርጉት አንዳቸው ለሌላው ባላቸው ንፁህ ፍቅር ነው። አንዱ ከሌላው የተሻለ እንደሚያውቅ አይናገርም ስለሆነም አቋሙን በጥብቅ መከላከል እንዳለበት አይጠቁምም። ሁለቱም ፉክክር አያሳዩም። እያንዳንዳቸው “ንጹሕ በሆነው የክርስቶስ ፍቅር”12 በፍቅር ስለተሞሉ ውይይታችን በጌታ መንፈስ መመራት ይችላል። እነዚህን ሁለት ታላላቅ ሰዎች ምንኛ እወዳቸዋለሁ እንዲሁም ምንኛ አከብራቸዋለሁ!

ፍቅር የጸብ መከላከያ ነው። ፍቅር ራስ ወዳድ እና ተከላካይ የሆነውን ፍጥረታዊውን ሰው እንድንጥል የሚፈቅድልን መንፈሳዊ ስጦታ ነው። ፍቅር የእውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ዋና ባህሪ ነው።13 ፍቅር አስታራቂን ይገልፃል።

ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት ስናዋርድ እና በሙሉ ልባች ስንጸልይ፣ እግዚአብሔር ፍቅርን ይለግሰናል።14

በዚህ የላቀ ስጦታ የተባረኩ ሁሉ ታጋሾች እና ደግ ናቸው። በሌሎች ላይ አይቀኑም እንዲሁም ራሳቸውን አስፈላጊ በማድረግ ውስጥ አይሳተፉም። በቀላሉ አይበሳጩም እንዲሁም በሌሎች ላይ ክፉ አያስቡም።15

ወንድሞች እና እህቶች፣ የክርስቶስ ንጹህ ፍቅር ዛሬ ለሚያስቸግረን ጸብ መልስ ነው። ፍቅር እርስ በእርሳችን ሸክምን ከመጫን ይልቅ “አንዳች[ን] የአንዳች[ንን] ሸክም [እንድናቀልል]”16 ይገፋፋናል። የክርስቶስ ንጹሕ ፍቅር “በሁሉም ጊዜና በሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ምስክር [እንድንሆን]”17 ያስችለናል፣ በተለይ በአስጨናቂ ሁኔታዎች ውስጥ። ፍቅር የክርስቶስ ወንዶች እና ሴቶች እንዴት እንደሚናገሩ እና እንደሚሰሩ ለማሳየት ያስችለናል—በተለይም ትችት ሲገጥማቸው።

አሁን፣ “ማንኛውም ዋጋ ተከፍሎበት ስለሚመጣ ሰላም” እያወራሁ አይደለም።18 እኔ እየተናገርኩኝ ያለሁት በቅዱስ ቁርባን ስትሳተፉ የምትገቧቸውን ቃል ኪዳን ከመጠበቅ ጋር በሚጣጣም መልኩ ሌሎችን ስለመያዝ ነው። አዳኙን ሁልጊዜም ለማስታወስ ቃል ኪዳን ገብታችኋል። ቁጣ በጣም በተሞላባቸው እና ጸብ ባለባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድታስታውሱ እጋብዛችኋለሁ። እርሱ የሚፈልገውን ለመናገር ወይም ለማድረግ ድፍረት እና ጥበብ እንዲኖራችሁ ጸልዩ። የሰላምን አለቃ ስንከተል የእርሱ አስታራቂዎች እንሆናለን።

በዚህ ጊዜ ይህ መልእክት የምታውቁትን ሰው በእውነት እንደሚረዳ እያሰባችሁ ይሆናል። ምናልባት እሱ ወይም እሷ ለእናንተ ይበልጥ መልካም እንዲሆኑ ይረዳቸዋል ብላችሁ ተስፋ እያደረጋችሁ ይሆናል። እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ! ነገር ግን እናንተ ሰላም ፈጣሪዎች እንዳትሆኑ የሚከለክሉ የኩራት ወይም የቅናት ፍርፋሪዎች እንዳሉ ለማየት ወደ እናንተ ልብ በጥልቀት እንደምትመለከቱ ተስፋ አደርጋለሁ።19

እስራኤላውያንን ለመሰብሰብ እና ለዘለአለም የሚዘልቅ ግንኙነቶችን ስለመገንባት በቁም ነገር ካሰባችሁ ምሬትን ወደ ጎን የምትጥሉበትት ጊዜ አሁን ነው። በእኛ መንገድ ብቻ ካልሆነ የምትሉበት ማቆሚያ ጊዜው አሁን ነው። ሌሎች እናንተን ላለማበሳጨት በመፍራት እንዲሳቀቁ የምታደርጉትን ድርጊቶች ለማቆም ጊዜው አሁን ነው። የጦር መሳሪያችሁን የምትቀብሩበት ጊዜ አሁን ነው።20 የቃላት ትጥቃችሁ በስድብ እና ውንጀላ የተሞላ ከሆነ እነሱን ለማስወገድ ጊዜው አሁን ነው።21 በመንፈሳዊ ጠንካራ እንደሆነ የክርስቶስ ወንድ ወይም ሴት ትሆናላችሁ።

ቤተ መቅደሱ በእኛ መሻት ውስጥ ሊረዳን ይችላል። እዚያ የክርክር ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን ሰይጣንን ለማሸነፍ የሚያስችል የእግዚአብሔር ኃይል ይሰጠናል።22 እርሱን ከግንኙነታችሁ ውስጥ አውጡት! አለመግባባትን በነቀፍን ቁጥር ወይም ቂም መያዝን በተቃወምን ቁጥር ተቃዋሚውን እንደምንገስጸው አስተውሉ። በተቃራኒው የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙር ባሕርይ የሆነውን ርኅራኄን ማሳየት እንችላለን። አስታራቂዎች ጠላትን ይከላከሉታል።

እንደ ህዝብ እውነተኛ በኮረብታ ላይ ያለ “ሊሰወር የማይችል ብርሃን” እንሁን።23 ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የሰላም፣ የአክብሮት እንዲሁም አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ብሩህ መንገድ እንዳለ እናሳይ። እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች የሚያሳዩትን ፍቅር ስታሳዩ፣ ጌታ ጥረቶቻችሁን ከፍ ካለው ግምታችሁ ባሻገር በእጅጉ ያጎላዋል።

የወንጌል የመረጃ መረብ በዓለም ላይ ትልቁ የመረጃ መረብ ነው። እግዚአብሔር ሁሉም “ጥቁርም ነጭም፣ ባሪያውንና ነፃውን፤ ወንድን እና ሴትን” ወደ እርሱ እንዲመጡ ጋብዟል።24 ለሁሉም ሰው የሚሆን ቦታ አለ። ሆኖም፣ ለማንኛውም ዓይነት ጭፍን ጥላቻ፣ ውግዘት ወይም ክርክር ቦታ የለም

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ህይወታቸውን ሌሎችን በመገንባት ለሚያሳልፉ መልካሙ ይመጣል። ዛሬ ደቀመዝሙርነታችሁን ሌሎችን በምትንከባከቡበት መንገድ እንድትመረምሩት እጋብዛችኋለሁ። ባህሪያችሁ የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ ተከታይ የሚያስከብር፣ የሚያከብር እና የሚወክል እንዲሆን የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ማስተካከያ እንድታደርጉ እባርካችኋለሁ።

ጠብን በምልጃ፣ ጠላትነትን በማስተዋል እና ክርክርን በርኅራኄ እንድትተኩ እባርካችኋለሁ።

እግዚአብሔር ህያው ነው። ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው። የቤተክርስቲያኗ እራስ ሆኖ ቆሟል። እኛ አገልጋዮቹ ነን። የእርሱ አስታራቂዎች እንድንሆን ይረዳናል። ይህንን የምመሰክረው ቅዱስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።