አጠቃላይ ጉባኤ
ከሁሉ አስፈላጊ የሆነውን አስታውሱ
የሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆነውን ነገር አስታውሱ

ከሁሉም በላይ አስፈላጊው የሆነው ነገር ከሰማይ አባት እና ከውድ ልጁ፣ ከቤተሰቦቻችን እና ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት እና መንፈሱ እንዲመራን መፍቀዳችን ነው።

በዚህ ቅዳሜና እሁድ አዳኙ ከሃጢያት ከፍያ መስዋዕቱ በፊት በድል አድራጊነት ወደ እየሩሳሌም መግባቱን ስናስታውስ፣ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል”1 የሚለውን የተስፋ እና የማጽናኛ ቃላቶቹን አስታውሳለሁ።

እርሱን እወደዋለሁ። እርሱን አምነዋለው። እርሱ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን እመሰክራለሁ።

ይህ ምስክርነት ባለቤቴ ባርባራ በሞተችበት ባለፉት አራት ዓመታት ተኩል ውስጥ አጽናንቶኛል፣ አበርትቶኛል። ትናፍቀኛለች።

ብዙ ጊዜ፣ ስለ ዘላለማዊ ትዳራችን እና በአንድነት ስለነበረን ህይወት አሰላስላለሁ።

ባርባራን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት እንዳገኝኋት እና ያ ተሞክሮ በምስዮን ላይ የተማርኩትን “የመከታተል” ችሎታ እንዴት እንድጠቀም እንዳስተማረኝ ከዚህ ቀደም አጋርቻለሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኘን በኋላ በፍጥነት መከታተል ነበረብኝ ምክንያቱም እሷ ቆንጆ፣ ተወዳጅ እና በጣም የተጨናነቀ ማህበራዊ ህይወት ስለነበራት ነው። እሷ የምትቀረብ እና ተግባቢ ስለነበረች ቀደም ብዬ ተማረኩ። ጥሩነቷን አደነኩ። እኔና እሷ አብረን መሆን እንዳለብን ተሰማኝ። በአእምሮዬ ያን ያህል ቀላል መሰለኝ።

እኔና ባርባራ ተቀጣጠርን መገናኘት ጀመርን፣ እናም ግንኙነታችን ማደግ ጀመረ፣ ነገር ግን ከእኔ ጋር ጋብቻ መመስረት ለእርሷ ትክክል ስለመሆኑ እርግጠኛ አልነበረችም።

የእኔ ማወቅ በቂ አልነበረም፣ ባርባራ ለራሷ ማወቅ ነበረባት። ስለ ጉዳዩ በጾም እና በጸሎት ጊዜ ብናሳልፍ ባርባራ ከሰማይ ማረጋገጫ እንደምትቀበል አወኩ።

ለራሳችን ለማወቅ በግል እንድንጾም እና እንድንጸልይ ቅዳሜና እሁድ ሳንገናኝ አሳለፍን። እንደ እድል ሆኖ፣ እኔ ያገኘሁትን አይነት ማረጋገጫ አገኘች። ቀሪው፣ እነሱ እንደሚሉት ታሪክ ነው።

ባርባራ ስትሞት፣ ልጆቻችን ባርባራ እንዲያስታውሷቸው የምትፈልጋቸውን በርካታ ትምህርቶች በመቃብሯ ላይ አኖሩ። ከእነዚህ ትምህርቶች ውስጥ አንዱ “ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆነው ነገር ለረጅም ጊዜ የሚቆየው ነው” የሚለው ነው።

ዛሬ፣ ከሁሉ በላይ አስፈላጊ ስለሆነው ነገር ጥቂት ስሜቶችን እና ሀሳቦችን ከልቤ አካፍላለሁ።

በመጀመሪያ፣ ከሰማይ አባታችን እና ከልጁ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ግንኙነት አሁን እና በዘለአለም ውስጥ ከሁሉ በላይ አስፈላጊ ነው።

ሁለተኛ፣ የቤተሰብ ግንኙነቶች በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል ናቸው።

በአገልግሎቴ በሙሉ፣ በአሰቃቂ የተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱ ብዙ ግለሰቦችን እና ቤተሰቦችን ጎብኝቻለሁ። በርካቶች ተፈናቅለዋል፣ተርበዋል፣ እናም ፈርተዋል። የሕክምና እርዳታ፣ ምግብ እና መጠለያ አስፈልጓቸዋል።

ቤተሰቦቻቸውም ያስፈልጓቸው ነበር።

አንዳንዶች የቅርብ ቤተሰብ በረከቶች ላይኖራቸው እንደሚችል አውቃለሁ፣ ስለዚህ እኔ ዘመዶችን፣ ጓደኞችን እና የቅርንጫፍ ቤተሰቦችን እንደ “ቤተሰብ” አካትታለሁ። እነዚህ ግንኙነቶች ለስሜታዊ እና አካላዊ ጤንነት አስፈላጊ ናቸው።

እነዚህ ግንኙነቶች ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሃሴትን እና የአንድነት ስሜትን ሊሰጡ ይችላሉ።

እነዚህን አስፈላጊ ግንኙነቶች ማሳደግ ምርጫ ነው። የቤተሰብ አባል የመሆን ምርጫ ቁርጠኝነትን፣ ፍቅርን፣ ትዕግስትን፣ መግባባትን እና ይቅርታን ይጠይቃል።2 ከሌላ ሰው ጋር የማንስማማበት ጊዜ ሊኖር ይችላል ነገር ግን ስሜታዊ መሆን የለብንም። በመጠናናት እና በትዳር ውስጥ፣ በቼዝቦርድ ላይ የምንንቀሳቀስ ዕቃዎች የሆንን ይመስል ድንገት አንዋደድም ወይም አንጠላላም። እርስ በርሳችን ለመዋደድ እና አንዳችን ሌላችንን ለመደገፍ እንመርጣለን። በሌሎች የቤተሰብ ግንኙነቶች ውስጥ እና ለእኛ እንደ ቤተሰብ ለሆኑ ጓደኞች እንዲሁ እናደርጋለን።

የቤተሰብ አዋጅ “መለኮታዊው የደስታ እቅድ የቤተሰብ ግንኙነት ከመቃብር ባሻገር እንዲቀጥልም ያስችላል። በቅዱስ ቤተ መቅደሶች የሚገኙትም ቅዱስ ስርዓቶች እና ቃል ኪዳኖችም ግለሰቦች ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመመለስ እና ቤተሰቦችም ለዘላለም እንዲጣመሩ ያስችላቸዋል” ይላል።3

ሌላው በጣም አስፈላጊ ነገር እጅግ ጠቃሚ በሆነው ግንኙነታችን እና ጎረቤቶቻችንን እንደ ራሳችን ለመውደድ በምናደርገው ጥረት በግል እና በህዝብ አገልግሎታችን ውስጥም ጭምር የመንፈስን መነሳሳት መከተል ነው። ይህንን ትምህርት የተማርኩት በሕይወቴ መጀመሪያ ላይ እንደ ኤጲስ ቆጶስ ሳገለግል ነበር።

በአንድ ቀዝቃዛ፣ በረዷማ የክረምት ምሽት፣ ከኤጲስ ቆጶሴ ቢሮ እየወጣሁ ሳለ በቅርንጫፍ ውስጥ አንዲት አረጋዊ መበለት ለመጎብኘት ከፍተኛ ስሜት ተሰማኝ። ሰዓቴን ተመለከትኩ - ከምሽቱ 4፡00 ነበር። እንደዚህ አይነት ጉብኝት ለማድረግ በጣም ዘግይቷል ብዬ አሰብኩ። በተጨማሪ በረዶ እየጣለ ነበር። እንደዚህ ባለ ሰዓት ላይ ከማስቸገር ይልቅ ይህችን ውድ እህት በጠዋት ለመጠየቅ ወሰንኩኝ። በመኪና ወደ ቤት ተመለስኩና ወደ መኝታዬ ሄድኩ ነገር ግን መንፈስ እያነሳሳኝ ስለነበረ ሌሊቱን ሙሉ ተጨነኩ።

በማግስቱ ጠዋት፣ በቀጥታ ወደ መበለቲቱ ቤት በመኪና ሄድኩ። ልጇ በሩን ከፈተች እና በእንባ “ኦ ኤጲስ ቆጶስ፣ ስለመጣህ አመሰግናለሁ። እናቴ ከሁለት ሰአት በፊት ከዚህ አለም በሞት ተለየች“—በጣም አዝኜ ነበር። የልቤን ስሜት መቼም አልረሳውም። አለቀስኩ። ከዚህች ውድ መበለት በላይ ኤጲስ ቆጶሷ እጇን እንዲይዝ፣ እንዲያጽናናት እና ምናልባትም የመጨረሻውን በረከት እንዲሰጣት የተገባው ማን ነው? ሰበብ በማቅረቤ ምክንያት ከመንፈስ የመጣውን ይህንን ጠንካራ መነሳሳት ያንን እድል አጣሁ። 4

ወንድሞች እና እህቶች፣ ወጣት ወንዶች እና ወጣት ሴቶች እና የመጀመሪያ ክፍል ልጆች፣ የመንፈስን መነሳሳት መከተል በሁሉም ግንኙነታችን ውስጥ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ አንዱ እንደሆነ እመሰክራለሁ።

በመጨረሻም፣ በዚህ የሆሳዕና በአል፣ ወደ ጌታ መለወጥ፣ ስለ እርሱ መመስከር እና እሱን ማገልገል በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል መሆናቸውን እመሰክራለሁ።

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን የምሥክርነታችን መሠረት ነው። ምስክርነት በመንፈስ ቅዱስ በኩል በግለሰብ ልብ እና ነፍስ ላይ የተጻፈ የዘላለም እውነት ምስክር ወይም ማረጋገጫ ነው። በመንፈስ የተወለደ እና የበረታ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ህይወትን- አስተሳሰባችንን እና አኗኗራችንን ይለውጣል። ምስክርነት ወደ ሰማይ አባታችን እና ወደ መለኮታዊ ልጁ ያዞረናል።

አልማ እንዳስተማረው፣

“እነዚህን ነገሮች እኔ ራሴ እንደማውቃቸው አትገምቱምን? እነሆ፣ እነዚህ የምናገራቸው ነገሮች እውነት መሆናቸውን እንደማውቅ እመሰክርላችኋለሁ። እናም እርግጠኝነታቸውን እንዴት እንዳወቅሁ ትገምታላችሁ?

“እነሆ እነዚህ እንዲታወቁኝ የሆኑት በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ነው። እነሆ፣ እነዚህን ነገሮች ለራሴ ለማወቅ ለብዙ ቀናት ፆሜአለሁ እንዲሁም ፀልያለሁ። እናም አሁን እውነት መሆናቸውን ለራሴ አውቄአለሁ ጌታ እግዚአብሄር በቅዱስ መንፈሱ እንዲገለጽልኝ አድርጓል”። 5

ምስክርነት ብቻውን በቂ አይደለም። ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መለወጣችን እያደገ ሲሄድ፣ ስለ መልካምነቱ፣ ፍቅሩ እና ደግነቱ ለመመስከር እንዲሁ እንፈልጋለን።

ብዙ ጊዜ በጾም እሑድ የምሥክርነት ስብሰባዎቻችን ላይ “አመሰግናለሁ” እና “እወዳለሁ” የሚሉትን ሐረጎች “አውቃለሁ” እና “አምናለሁ” የሚሉትን ሐረጎች ከምንሰማው በላይ እንሰማለን።

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነትን አብዝታችሁ እንድትሰጡ እጋብዛለሁ። ስለምታመሰግኑበት ብቻ ሳይሆን ስለምታውቁት እና ስለምታምኑበት እና ስለሚሰማችሁም ነገር መስክሩ። አዳኙን ስላወቃችሁበት እና ስለወደዳችሁበት፣ ትምህርቱን ስለመኖር እና በህይወታችሁ ውስጥ ስላለው የማዳን እና የሚያስችል ሃይል ያሏችሁን ልምዶች መስክሩ። ስለምታውቁትስለምታምኑት እና ስለሚሰማችሁ ነገር ስትመሰክሩ፣ መንፈስ ቅዱስ ምስክርነታችሁን በትጋት ለሚሰሙት እውነትን ያረጋግጣል። ይህን የሚያደርጉት እናንተ ሰላማዊ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ መሆናችሁን ስላዩ ነው። የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ማለት እንደሆነ ያያሉ። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ተሰምቷቸው የማያውቁት ነገር ይሰማቸዋል። ንፁህ ምስክርነት ከተቀየረ ልብ ይመጣል እናም በመንፈስ ቅዱስ ሀይል እሱን ለመቀበል ዝግጁ በሆኑት ወደ ሌሎች ሰዎች ልብ ውስጥ ሊወሰድ ይችላል።

በምሥክርነታችሁ ምክንያት የሆነ ነገር የተሰማቸው ሰዎች የምሥክርነታችሁን እውነትነት እንዲያረጋግጥላቸው ጌታን በጸሎት ሊጠይቁት ይችላሉ። ከዚያም ለራሳቸው ማወቅ ይችላሉ።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የአለም አዳኝ እና ቤዛ እንደሆነ እንደማውቅ እመሰክርላችኋለሁ። እርሱ ህያው ነው። እርሱ ከሞት የተነሳው የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣ እና በነቢይ እና በሐዋርያት የምትመራ ይህቺ ቤተክርስቲያኑ ናት። አንድ ቀን ወደ ቀጣዩ ዓለም ስሸጋገር፣ ምስክርነቴ በደመቀ ሁኔታ ይነድ ዘንድ እጸልያለሁ።

በአገልግሎቴ ውስጥ፣ ከሁሉ አስፈላጊው ነገር ከሰማይ አባት እና ከሚወደው ልጁ፣ ከቤተሰቦቻችን እና ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት እና የጌታ መንፈስ በእነዚያ ግንኙነቶች እንዲመራን መፍቀድ፣ አስፈላጊ ስለሆኑት ነገሮች መመስከር ከሁሉ አስፈላጊ የሆነና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ መሆኑን ተረድቻለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ዮሐንስ 11፥25

  2. በወንጌል ቤተመጻህፍት ውስጥ (በChurchofJesusChrist.org ወይም በሞባይል መተግበሪያ ላይ)በወንጌል ርዕስ ውስጥ “ቤተሰብ፣” “አንድነት፣” እና “ፍቅር” የሚባሉትን አንቀጾች ስለእነዚህ እዕሶች ከቅዱሳት መጻህፍት እና ከነቢያት፣ ከሐዋሪያት፣ እና ከሌሎች የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ንግግሮች ለማንበብ ይመልከቱ፡፡

  3. ቤተሰብ፦ ለአለም የተላለፈ አዋጅ፣” ChurchofJesusChrist.org።

  4. የዚህ ተሞክሮ ዘገባ Susan Easton Black and Joseph Walkerበሱዛን ኢስተን ብላክ እና ጆሴፍ ዋከር፣ Anxiously Engaged: A Biography of M. Russell Ballard [2021 (እ.አ.አ))፣ 90–91 ውስጥ አለ።

  5. አልማ 5፥45–46

አትም