አጠቃላይ ጉባኤ
የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች
የሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች

ሕይወታችንን እንድንመራ ቅዱሳት መጻሕፍት ተሰጥተውናል። የዛሬው መልእክቴ እርሱ የተናገራቸውን የተመረጡ የአዳኛችንን ቃላት ያካትታል።

በክርስቶስ እናምናለን። የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት እንደመሆናችን መጠን እሱን እናመልካለን። እንዲሁም በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ያሉትን ትምህርቶቹን እንከተላለን።

ከውድቀት በፊት፣ የሰማዩ አባታችን አዳምና ሔዋንን በቀጥታ አናግሯቸዋል። ከዚያም በኋላ፣ አብ አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችን እና ቤዛችን አስተዋወቀ እንዲሁም “እርሱን [እንድንሰማው]” ትእዛዝ ሰጠን።1 ከዚህ አቅጣጫ በመነሳት “እግዚአብሄር” ወይም “ጌታ” የተናገራቸው የቅዱሳን ጽሑፎች መዛግብት ሁልጊዜ የያህዌ፣ ከሞት የተነሣው ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ናቸው ማለትም ይቻላል።2

ሕይወታችንን እንድንመራ ቅዱሳት መጻሕፍት ተሰጥተውናል። ነቢዩ ኔፊ እንዳስተማረን ይህንን ማድረግ አለብን፣ “የክርስቶስን ቃል ተመገቡ እላችኋለሁ፤ እነሆም የክርስቶስ ቃል ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች በሙሉ ይነግራችኋል”3። የኢየሱስን ምድራዊ አገልግሎቶች የሚዘግቡ አብዛኛዎቹ ቅዱሳት መጻህፍት እሱ ያደረገውን የሚገልጹ ናቸው። የዛሬው መልእክቴ የተመረጡ የአዳኛችንን ቃላት—እሱ የተናገረውን ያካትታል። እነዚህ በአዲስ ኪዳን (በመንፈስ አነሳሽነት የቀረቡትን የጆሴፍ ስሚዝ ጭማሬዎችን ጨምሮ) እና በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የተመዘገቡ ቃላት ናቸው። አብዛኛዎቹ የተመረጡት አዳኛችን በተናገረበት ቅደም ተከተል ነው።

“እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።”4

“እናም ፅድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ሁሉ ብፁአን ናቸው፣ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላሉና።”5

“የሚያስተራርቁ ሁሉ ብፁአን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።”6

“እነሆ፣ አታመንዝር ተብሎ በጥንቶቹ ተጽፏል፤

“ነገር ግን እንዲህ እላችኋለሁ፣ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።”7

“ባልንጀራህን ውደድ ጠላቶችህንም ጥላ እንደተባለ ሰምታችኋል፤

“ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁንም ባርኩ፤ ለሚጠሏችሁም መልካምን አድርጉ፣ እናም በከንቱ የሚነቅፉአችሁን እናም የሚያሳድዱአችሁን ውደዱ እላችኋለሁ፤

“የሰማይ አባታችሁ በክፉውም በመልካሙም ላይ ጸሃይን ያወጣል እና በጻድቃንም በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባል”።8

“ለሰዎች በደላቸውን ይቅር የምትሉ ከሆነ፣ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ ይቅር ይላችኋል፤

“ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።”9

“ከአለምስ ብትሆኑ አለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር ነገር ግን እኔ ከአለም መረጥኋችሁ እንጂ ከአለም ስላይደላችሁ ስለዚህ አለም ይጠላችኋል።”10

“ስለዚህ፣ የዚህን አለም ነገሮች አትፈልጉ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመገንባት፣ እና ጽድቁንም ለመመስረት ፈልጉ፣ እና እነዚህ ነገሮች ሁሉ ይጨመርላችኋል።”11

“ስለሆነም፣ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፣ ህግም ነቢያትም ይህ ነውና።”12

“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ፣ ነገር ግን ውስጣቸው ነጣቂ ተኩላ ከሆኑ ከሀሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።

“ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን፣ ወይም ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?

“መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም መጥፎ ፍሬ ያፈራል።”13

“በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማይ የሚገባ አይደለም።14

“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ።

“ቀንበሬንም በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።

“ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።”15

“በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።

“አሁን ሰው መስቀሉን ለማንሳት ሁሉንም ኃጢአተኝነትንና እያንዳንዱን ዓለማዊን ምኞት መካድ፣ እና ትእዛዛቴን መጠበቅ ማለት ነው።”16

“ስለዚህ አለምን ተው፣ እና ነፍሳችሁን አድኑ፤ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? ወይስ ሰው በነፍሱ ምትክ ምን ይሰጣል?”17

“ማንም ሰው የሱን ፍቃድ ቢያደርግ፥ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሄር ዘንድ ይሁን ፣ወይም ከእኔ ዘንድ እንደመነጨ ታውቃላችሁ።”18

“እኔ እላችኋለሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።

“የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ እናም የሚፈልግም ያገኛል፤ እናም ለሚያንኳኩ ይከፈትላቸዋል።”19

“ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፣ ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ፣ እረኛውም አንድ ይሆናል።”20

“ኢየሱስም እንዲህ አላት ትንሣኤና ህይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ህያው ይሆናል።

“ህያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለአለም አይሞትም።”21

“ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።

“ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

“ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።

“በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።”22

“ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”23

“ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፥ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እነደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።”24

“እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት25

“እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፣ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ።” 26

“እንግዲህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣

“ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው፤ እነሆም እኔ እስከ አለም ፍፃሜ ድረስ ሁልጌዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”27

በቅድስት ሀገር ካገለገለ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ በአሜሪካ አህጉር ለነበሩ ጻድቃን ተገለጠ። እዚያ ከተናገራቸው ቃላቶች መካከል ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው፦

“እነሆ፣ እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ። ሰማያትንና ምድርን፣ እናም በውስጧ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ፈጥሬአለሁ። ከመጀመሪያው ጀምሮ ከአብ ጋር ነበርኩኝ። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ አለ፤ በእኔም የአብ ስሙን አስከብሯል።”28

“እኔ የአለም ብርሃንና ህይወት ነኝ። እኔ አልፋና ኦሜጋ፣ የመጀመሪያው እና የመጨረሻው፣ ነኝ።

“እናም ከእንግዲህ ደምን በማፍሰስ አታበረክቱልኝም፤ አዎን፣ መስዋእቶቻችሁና የሚቃጠሉት መስዋእቶች ማንኛውንም ስለማልቀበል መስዋእቶቻችሁ እናም የሚቃጠሉት መስዋእቶቻችሁ ይቆማሉ።

“እናም ለእኔም መስዋእት የተሰበረ ልብና የተዋረደ መንፈስ ታቀርባላችሁ። ወደ እኔም በተሰበረ ልብና በተዋረደ መንፈስ የሚመጣ በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ አጠምቀዋለሁ።…

“እነሆ ዓለምን ከኃጢያት ለማዳን ለዓለም ቤዛነትን ለማምጣት ወደ ዓለም መጥቻለሁ።29

“እናም በድጋሚ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ንሰሃ ግቡና በስሜም ተጠመቁ፣ እናም እንደህፃናት ሁኑ፣ አለበለዚያ በምንም መንገድ የእግዚአብሔርን መንግስት ልትወርሱ አትችሉም።30

“ስለዚህ እንደ እኔ ወይንም በሰማይ እንዳለው ፍፁም እንደሆነው አባታችሁ ፍፁም እንድትሆኑ እፈልጋችኋለሁ።31

“እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ዘወትር ንቁ መሆን እና መፀለይ አለባችሁ፤ አለበለዚያ በዲያብሎስ ትፈተናላችሁ እናም የእርሱ ምርኮኛም ትሆናላችሁ።32

“ስለዚህ ዘወትር በስሜ ወደ አብ መፀለይ ይኖርባችኋል፤33

“ስለዚህ፣ ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ በስሜ አድርጉት፤ ስለዚህ ቤተክርስቲያኗን በስሜ ጥሯት፤34

“እነሆ ወንጌልን ሰጥቻችኋለሁ እናም ለእናንተ የሰጠኋችሁ ወንጌሌም ይህ ነው ወደ አለም የመጣሁት የአባቴን ፈቃድ ለመፈፀም ነው ምክንያቱም አባቴ ልኮኛልና።

“አባቴም በመስቀል እሰቀል ዘንድ ልኮኛል፤ እናም በመስቀል ላይ ከተሰቀልኩ በኋላ፣ ሰዎችን ሁሉ ወደ ራሴ አመጣ ዘንድ፣ …መልካምም ይሁኑ መጥፎ በስራቸው እንዲፈረድባቸው በእኔ ፊት ለመቆም ይችሉ ዘንድ፣ ተሰቅያለሁ።” 35

“እንግዲህ ትዕዛዜ ይህች ናት፥ በምድር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ ንሰሃ ግቡ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን በመቀበል ትቀደሱ ዘንድ፤ በመጨረሻው ቀን በፊቴ ያለእንከን ትቆሙ ዘንድ ወደ እኔ ኑ፣ እናም በስሜ ተጠመቁ።”36

በክርስቶስ እናምናለን። ትምህርቶቹን እንዴት ማወቅ እና መከተል እንዳለብን በተናገረው እቋጫለሁ።

“አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አፅናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የንገረኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።”37

የእነዚህን ትምህርቶች እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አረጋግጣለሁ፣ አሜን።

አትም