አጠቃላይ ጉባኤ
የፓትሪያርክ በረከታችሁን መቼ እንደምትቀበሉ
የሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:47

የፓትሪያርክ በረከታችሁን መቼ እንደምትቀበሉ

በረከታችሁን ስትቀበሉ፣ የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደሚወዷችሁ እና እናንተ ላይ በግለሰብ ደረጃ እንዴት እንደሚያተኩሩ ትገነዘባላችሁ እንዲሁም ይሰማችኋል።

ትላንትና ውድ ጓደኛዬ ሽማግሌ ራንዳል ኬ. ቤኔት ስለ የፓትሪያርክ በረከቶች ተናገሩ። ትቅ መልዕክት ነበረ እናም አነሳስቶናል። ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ስለ የፓትሪያርክ በረከቶች እኔም ልናገር? ፓትርያርኮች፣ የፓትርያርክ በረከት ለማግኘት የሚቀርቡ ጥያቄዎች እየበዙ ሲሄዱ ጥሪያችሁን ማጉላታችሁን ስትቀጥሉ ጌታ እንዲባርካችሁ እጸልያለሁ።

ወደ ካስማ ስብሰባዎች ስሄድ ከካስማው ፓትሪያርክ እና ከባለቤቱ ጋር ሁልጊዜ እገናኛለሁ። ፓትሪያርኮች በእግዚአብሔር የተጠሩ የዋህ፣ ታዛዥ እና አስደናቂ መሪዎች ናቸው። ብዙ ድንቅ መንፈሳዊ ተሞኩሮዎችን ይነግሩኛል። በረከት ስለሰጡት ከሁሉም ትንሽ ስለሆነው እና ከሁሉም ትልቅ ስለሆነው ሰው ዕድሜ እጠይቃቸዋለሁ። እስካሁን፣ ትንሹ 11 ዓመት እና ትልቁ ደግሞ 93 ዓመት ነበሩ።

የፓትሪያርክ በረከቴን የተቀበልኩት ከተጠመኩኝ ከሁለት ዓመት በኋላ የቤተክርስቲያኗ አዲስ አባል ሳለሁ በ19 ዓመቴ ነበር ። የእኔ ፓትሪያርክ በጣም በዕድሜ የገፉ ነበሩ። ቤተክርስቲያኗን በ1916 (እ.አ.አ) ነበር የተቀላቀሉት እናም በጃፓን የቤተክርስቲያኗ መስራች ነበሩ። ከዚያ አስደናቂ የጌታ ደቀመዝሙር የፓትሪያርክ በረከቴን መቀበሌ ትልቅ ክብር ነበር። የእርሳቸውን የጃፓንኛ ቋንቋ ለመረዳት በጣም ከባድ ነበር፣ ነገረ ግን ኃይለኛ ነበር።

ያገኘኋቸው ፓትርያርኮች ብዙ ግለሰቦች የፓትሪያርክ በረከቶቻቸውን ልክ በሚስዮን ሊያገለግሉ ሲሉ እንደሚቀበሉ ይነግሩኛል። ውድ ወጣት ወንዶች፣ ወጣት ሴቶች፣ ወላጆች እና ኤጲስ ቆጶሳት፣ የፓትሪያርክ በረከቶች ሚስዮንን ለማገልገል ለመዘጋጀት ብቻ አይደሉም የሚጠቅሙት። ብቁ የተጠመቁ አባሎች ለእነሱ ጊዜው ትክክለኛ ሲሆን የፓትሪያርክ በረከትን መቀበል ይችላሉ።1

ውድ ጎልማሳ አባሎች፣ የተወሰናችሁት የፓትሪያርክ በረከቶቻችሁን አልተቀበላችሁም። አስታውሱ፣ የጊዜ ገደብ የለውም።

የባለቤቴ እናት በ91 ዓመቷ ከመሞቷ በፊት በሴቶች መረዳጃ ማህበር ውስጥ እንደ አስተማሪ ታገለግል የነበረች በጣም ንቁ የቤተክርስቲያን አባል ነበረች። የፓትሪያርክ በረከትን እንዳልተቀበለች ሳውቅ በጣም ነበር ያዘንኩት። በህይወቷ ውስጥ ብዙ ችግሮችን ተጋፍጣ ነበር እናም የክህነት ተሸካሚ በቤቷ ውስጥ ስላልነበረ፣ ብዙ የክህነት በረከቶችን አልተቀበለችም ነበር። የፓትሪያርክ በረከት መፅናናት በሚያስፈልጋት ጊዜ መጽናናትን ሊሰጣት ይችል ነበር።

ጎልማሶች፣ የፓትሪያርክ በረከትን ካልተቀበላችሁ፣ እባካችሁን አትጨነቁ! የሁሉም የመንፈሳዊ የጊዜ ሰሌዳ ይለያያል። እድሜያችሁ 35 ወይም 85 ከሆነ እና ፍላጎቱ ካላችሁ፣ በረከታችሁን ስለመቀበል ከኤጲስ ቆጶሳችሁ ጋር ተነጋገሩ።

የቤተክርስቲያኗ አዲስ አባላት፣ ሰለ የፓትሪያርክ በረከቶች ሰምታችኋልን? ቤተክርስቲያኗን ስቀላቀል የፓትሪያርክ በረከትን ስለመቀበል እድል አልሰማውኝም ነበር፣ ነገር ግን ውድ ኤጲስ ቆጶሴ ስለ የፓትሪያርክ በረከቶች ነገረኝ እና ከተጠመኩኝ ብኋላ እንድቀበል አበረታታኝ። ውድ አዲስ አባሎች፣ እናንተም የፓትሪያርክ በረከትን መቀበል ትችላላችሁ። ጌታ ለዚህ ቅዱስ እድል እንድትዘጋጁ ይረዳችኋል።

የፓትሪያርክ በረከትን ሁለት ዓላማዎች እናስብ፦

  1. የፓትሪያርክ በረከት ከጌታ ለአናንተ የመጣ የግል ምክርን ይይዛል።2

  2. የፓትሪያርክ በረከት በእስራኤል ቤት ውስጥ የመጣችሁበትን የዘር ሃረግ ይገልጻል።

የፓትሪያርክ በረከታችሁ ከሰማይ አባታችሁ የመጣ መልዕክት ነው እናም በመላ ህይወታችሁ ውስጥ የሚመሯችሁን ቃል ኪዳኖች እና የተነሳሱ ምክሮች ይይዛል። የፓትሪያርክ በረከት ህይወታችሁ እንዴት እንደሚሆን አያስቀምጥም ወይም ሁሉንም ጥያቄያችሁን አይመልስም። አስፈላጊ የህይወት ክስተትን ካልገለጸ ያንን እድል አናገኝም ብላችሁ አትውሰዱት። በተመሳሳይ መልኩ፣ በበረከታችሁ የተጠቀሱት ሁሉም ነገሮች በዚህ ህይወት ውስጥ እንደሚሳኩ ማረጋገጫ የለም። የፓትሪያርክ በረከት ዘላለማዊ ነው እናም ብቁ ሆናችሁ ከኖራችሁ በዚህ ህይወት ውስጥ ያልተፈጸሙ በረከቶች በሚቀጥለው ህይወት ውስጥ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።3

የዘር ሃረግ እወጃን ስትቀበሉ፣ የእስራኤል ቤት እና የአብርሐም ፍሬ እንደሆናችሁ ታውቃላችሁ። 4 የዚህን ጠቀሜታ ለመገንዘብ፣ ጌታ በአብርሐም አማካኝነት ለእስራኤል ቤት የገባው ቃል ኪዳኖች ላይ አተኩሩ።

እነዚያ ቃል ኪዳኖች የሚያካትቱት፦

  • “ዘሮቹ ይበዛሉ (ዘፍጥረት 17፥5–6አብርሐም 2፥93፥14 ተመልከቱ)።

  • “የእሱ ፍሬ ወይም ዘሮች፣ ወንጌልን ይቀበላሉ እናም ክህነትን ይሸከማሉ (አብርሐም 2፥9 ተመልከቱ)።

  • “በፍሬው አገልግሎት አማካኝነት፣ ‘ሁሉም የምድር ቤተሰቦች በደህንነት በረከቶች፣ እንዲሁም የዘለአለም ህይወት በሆኑት የወንጌል በረከቶች ይባረካሉ’ (አብርሐም 2፥11)።”5

እንደ የቤተክርስቲያኗ አባላት፣ እኛ የቃል ኪዳኑ ልጆች ነን።6 የወንጌልን ህጎች እና ስርዓቶች ስናከብር የአብርሐማዊ ቃል ኪዳን በረከቶችን እንቀበላለን።

ለፓትሪያርክ በረከታችሁ መዘጋጀት በሰማይ አባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላችሁ እምነት እንዲጨምር ይረዳል። እናም የፓትሪያርክ በረከታችሁን ስትቀበሉ እና ስታነቡት እና ስታሰላስሉት፣ የበለጠ በእነሱ ላይ ማተኮር ትችላላችሁ።

ፕሬዘደንት ቶማሳ ኤስ. ሞንሰን እንዲህ አስረድተዋል፣ “ለሌሂ ሊያሆናን የሰጠው ተመሳሳይ ጌታ ለህይወታችን ምሪትን ለመስጠት፣ ለደህንነታችን ችግሮችን ለማሳወቅ፣ እና ወደ ቃል ኪዳን ምድር ሳይሆን ወደ የሰማይ ቤታችን መንገዱን ለመጥረግ ዛሬ ለእኔ እና ለእናንተ ያልተለመደ እና ጠቃሚ ስጦታን ይሰጣል።”7

ውድ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ወላጆች፣ የሽማግሌ ቡድን እና የሴቶች መረዳጃ ማህበር ፕሬዘደንቶች፣ የአጥቢያ ሚስዮን መሪዎች፣ የአገልጋይ ወንድሞች እና እህቶች፣ የጌታን ምሪት ለመሻት የፓትሪያርክ በረከትን ያልተቀበሉትን እነዚያን ወጣት ወንዶች እና ወጣት ሴቶች፣ ጎልማሳ አባሎች እና አዲስ አባሎች እባካችሁ አበረታቱ እናም እንዲዘጋጁ እርዱ።

የፓትሪያርክ በረከቴን በተደጋጋሚ እና በጸሎት አነባለው፣ ሁሌም ማበረታቻን ይሰጠኛል። ጌታ ከእኔ ምን እንደሚጠብቅ እገነዘባለው እናም ንስሃ እንድገባ እና ትሁት እንድሆን ይረዳኛል። ሳነበው እና ሳሰላስለው፣ የተገቡትን ቃል ኪዳኖች ለመቀብል በብቁነት ለመኖር እሻለሁ።

ልክ ብዙ ጊዜ ያነበብናቸው ቅዱሳት መጽሐፍቶች አዲስ ትርጉም እንደሚኖራቸው ሁሉ፣ የፓትሪያርክ በረከታችን በተለየ ሰዓት የተለየ ትርጉም ይኖረዋል። የእኔ በ30 ዓመቴ በነበረው ትርጉም ይልቅ አሁን በ50 ዓመቴ የተለየ ትርጉም አለው። ቃላቱ ይቀየራሉ ማለት ሳይሆን እኛ በተለየ መልኩ እናያቸዋለን ማለት ነው።

ፕሬዘደንት ዳለን ኤች. ኦክስ እንዳሉት፣ የፓትሪያርክ በረከት “የሚሰጠው በመንፈሳዊ መነሳሳት አማካኝነት ነው እናም በዚያ ተመሳሳይ መንፈስ ተፅዕኖ አማካኝነት መነበብ እና መተርጎም አለበት። የፓትሪያርክ በረከት ትርጉም እና አስፈላጊነት በጊዜ ሂደት ውስጥ በረከቱን ባነሳሳው ተመሳሳይ መንፈስ ኃይል አማካኝነት ደረጃ በደረጃ ይገለፃል።”8

ወንድሞች እና እህቶች፣ አፍቃሪው የሰማይ አባት እና ተወዳጅ ልጁ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ህያው እንደሆኑ እመሰክራለሁ። ይወዱናል። የፓትሪያርክ በረከቶች ከእነርሱ የሚመጡ ቅዱስ ስጦታዎች ናቸው። በረከታችሁን ስትቀበሉ፣ እነርሱ እንዴት እንደሚወዷችሁ እና እናንተ ላይ እንዴት እንደሚያተኩሩ ትገነዘባላችሁ እንዲሁም ይሰማችኋል።

መፅሐፈ ሞርሞን የኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ምስክርነት ነው። እናም በህያው ነቢይ በፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን በመመራቴ አመስጋኝ ነኝ።

ለአዳኛችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በጣም አመስጋኝ ነኝ። በዚህ የፋሲካ ሰንበት በእርሱ እና በትንሳኤው ላይ አተኩራለው፣ እናም አመለከዋለው እንዲሁም ስለ እርሱ መስዋዕትነት ምስጋና እሰጣለው። እርሱ በጥልቅ ስሜት ስለሚወደን እጅግ በጣም እንደተሰቃየ አውቃለው። እርሱ ለእኛ ባለው ፍቅር የተነሳ ከሞት እንደተነሳ አውቃለው። እውነተኛ ነው። ስለዚህ የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. General Handbook: Serving in The Church of Jesus Christ of Latter-day Saints [አጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ፦ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል]18.17፣ ChurchofJesusChrist.org ይመልከቱ።

  2. የፓትሪያርክ በረከቶች፣” True to the Faith ውስጥ (2004 ) (እ.አ.አ)፣ 112 ተመልከቱ።

  3. የፓትሪያርክ በረከቶች፣” በ True to the Faithውስጥ፣ 113 ተመልከቱ።

  4. አብርሐም 2፥10ተመልከቱ።

  5. አብርሐማዊ ቃል ኪዳን፣” በ True to the Faith፣ 5 ውስጥ።

  6. 3 ኔፊ 20፥25–26ተመልከቱ።

  7. ቶማሳ ኤስ. ሞንሰን፣ “የፓትሪያርክ በረከታችሁ፦ የሕይወት ሊያሆና፣” ኢንዛይን፣ ህዳር 1986 (እ.አ.አ)፣ 65።

  8. ዳለን ኤች. ኦክስ፣ “የፓትሪያርክ በረከቶች” Worldwide Leadership Training Meeting: The Patriarch፣ ጥር 8፣ 2005 (እ.አ.አ)፣ 10።