አጠቃላይ ጉባኤ
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለማገልገል ያስተምረናል
የሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለማገልገል ያስተምረናል

በአዳኛችን እርዳታ ውድ በጎቹን መውደድ እንዲሁም እሱ እንዳደረገው ልናገለግላቸው እንችላለን።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አለ፦

“መልካሙ እረኛ እኔ ነኝ መልካም እረኛ ህይወቱን ስለበጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። …

“አብም እንደሚያውቀኝ፣ እኔም አብን እንደማውቀው፦ እናም ህይወቴንም ለበጎቼ አሳልፌ ሰጠሁ።”1

በግሪክ እትሙ ውስጥ ያለው መልካም የሚለው የዚህ ቅዱስ ጽሁፍ ቃል “ቆንጆ፣ ድንቅ” ለማለትም ያገለግላል። ስለዚህ ዛሬ ስለመልካሙ እረኛ፣ ስለቆንጆው እረኛ፣ ስለድንቁ እረኛ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ለመናገር እሻለሁ።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ “ታላቅ እረኛ፣”2 “የእረኞች አለቃ፣”3 እንዲሁም “የነፍሳ[ችን] እረኛ እና ጠባቂ”4 ተብሎ ተጠርቷል።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ኢሳይያስ “መንጋውን እንደእረኛ ያሰማራል” ብሎ ጽፏል።5

በመፅሐፈ ሞርሞን “መልካሙ እረኛ”6 እንዲሁም “ታላቁና እውነተኛው እረኛ”7 ተብሎ ተጠርቷል።

በትምህርት እና ቃልኪዳኖች ውስጥ፣ “ስለዚህ እኔ በመሀከላችሁ ነኝ፣ እና እኔም መልካሙ እረኛ የእስራኤል ድንጋይ ነኝ።”8

በዘመናችን ፕሬዘደንት ኔልሰን እንዲህ ተናግረዋል፦ “መልካሙ እረኛ በመንጋው ውስጥ ያሉትን ሁሉንም በጎቹን በፍቅር ይንከባከባል፣ እኛም የእርሱ እውነተኛ የበታች እረኞች ነን። ፍቅሩን ማፍራት እንዲሁም አዳኝ እንድናደርግ እንደሚፈልገው በመመገብ፣ በመጠበቅ እና በመንከባከብ ለጓደኞቻችን እና ለጎረቤቶቻችን ያለንን ፍቅር መጨመር የእኛ መብት ነው።”9

በቅርቡ ፕሬዘደንት ኔልሰን እንዲህ ብለዋል፦ “የጌታ እውነተኛ እና ህያው ቤተክርስቲያን ምልክት ሁልጊዜም ለእያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጆች እና ለቤተሰቦቻቸው በሚደረግ የተደራጀ፣ የተመራ የአገልግሎት ጥረት ነው። ይህች የእርሱ ቤተክርስቲያን ስለሆነች፣ እኛም እንደ አገልጋዮቹ፣ ልክ እርሱ እንዳደረገው፣ አንዱን እናገለግላለን። በስሙ፣ በሀይሉ እና በስልጣኑ፣ እናም በእርሱ አፍቃሪ ደግነት እናገለግላለን።”10

ፈሪሳውያን እና ጻፎች “ይህስ ሃጢያተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል”11 ብለው ሲያጉረመርሙ የጠፋው በግ ምሳሌ፣ የጠፋው ሳንቲም ምሳሌ እና የአባካኙ ልጅ ምሳሌ በማለት የምናውቃቸውን ሦስት ቆንጆ ታሪኮችን በማቅረብ መልስ ሰጥቷል።

ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ሦስቱን ታሪኮች ባስተዋወቀበት ጊዜ ምሳሌ የሚለውን ቃል የተጠቀመው በነጠላ ቁጥር እንጂ በብዙ ቁጥር አለመሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።12 ጌታ የተለያየ ቁጥር ባላቸው በሦስት ታሪኮች ይኸውም በ100 በጎች፣ በ10 ሳንቲሞች እና በ2 ወንድ ልጆች አንድ የተለየ ትምህርት እያስተማረ ይመስላል።

ሆኖም በእነዚህ በእያንዳንዱ ታሪኮች ውስጥ ያለው በጣም አስፈላጊው ቁጥር አንድቁጥር ነው። እንዲሁም ከዚያ ቁጥር የምንወስደው ትምህርት በሽማግሌዎች ቡድን ውስጥ ላሉ 100 ሽማግሌዎች እና ዕጩ ሽማግሌዎች የበታች እረኛ ልትሆኑ ወይም የ10 ወጣት ሴቶች አማካሪ ወይም የ2 የመጀመሪያ ክፍል ልጆች አስተማሪ ልትሆኑ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ፣ ሁል ጊዜ አንድ በአንድ፣ በግል ታገለግሏቸዋላችሁ፣ ትንከባከቧቸዋላችሁ እንዲሁም ትወዷቸዋላችሁ። “እንዴት ያለ ሞኝ በግ ነው” ወይም “ለነገሩ ሳንቲሙን አልፈልገውም” ወይም “እንዴት ያለ አመጸኛ ልጅ ነው” አትሉም። እኔና አናንተ “ንፁህ የክርስቶስ ፍቅር” ቢኖረን13 በጠፋው በግ ታሪክ ውስጥ እንዳለው ሰው “ዘጠና ዘጠኙን ትተን [እስክናገኘው፣ እስክናገኘው ድረስ] የጠፋውን እንከተለዋለን።14 ወይም በጠፋው ሳንቲም ታሪክ ውስጥ እንዳለችው ሴት “መብራት አብርተን ቤቱን ጠርገን እስክናገኘው እስክናገኘው እስክናገኘው ድረስ በትጋት [በትጋት] እንፈልገዋለን።15 “ንጹሕ የክርስቶስ ፍቅር” ቢኖረን በአባካኙ ልጅ ታሪክ ውስጥ ያለውን አባት ምሳሌ እንከተላለን፤ “እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱ አቀፈውና ሳመው።”16

አንድ በግ ብቻ በጠፋው ሰው ልብ ውስጥ ያለው የመጣደፍ ስሜት ሊሰማን ይችላል? ወይም አንዲት ሳንቲም ብቻ በጠፋባት ሴት ልብ ውስጥ ያለው መጣደፍ? ወይም በአባካኙ ልጅ አባት ልብ ውስጥ ያለው በቃላት ሊገለጽ የማይችል ፍቅር እና ርህራሄ?

እኔና ባለቤቴ ማሪያ ኢዛቤል ኑሯችንን በጓቲማላ ሲቲ በማድረግ በማዕከላዊ አሜሪካ አገልግለናል። እዚያ የቤተክርስቲያኗ ታማኝ አባል ከሆነችው ከጁሊያ ጋር ለመገናኘት እድሉን አግኝቼ ነበር። ስለቤተሰቧ እንድጠይቃት የሚገፋፋ ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። እናቷ በ2011 (እ.አ.አ) በካንሰር ሳቢያ ሞተች። አባቷ በካስማው ታማኝ መሪ የነበረ ሲሆን ኤጲስ ቆጶስ እንዲሁም የካስማ ፕሬዘዳንቱ አማካሪ በመሆን ለብዙ አመታት አገልግሏል። እርሱም እውነተኛ የጌታ የበታች እረኛ ነበር። ጁሊያ ለመጎብኘት፣ ሌሎችን ለማገልገል እና አገልግሎት ለመስጠት ስለነበረው ያላሰለሰ ጥረት ነገረችኝ። በርግጥ ውድ የሆኑትን የጌታ በጎች በመመገብና በመጠበቅ ይደሰት ነበር። ድጋሚ አግብቶ የቤተክርስቲያኗ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ጸንቶ ነበር።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ፍቺ ፈጽሞ የነበረ ሲሆን አሁን እንደገና ብቻውን በቤተክርስቲያን እየተሳተፈ ይገኛል። በዚያ ምቾት አይሰማውም ነበር እንዲሁም ፍቺ በመፈጸሙ ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ይነቅፉኛል የሚል ሥሜት ነበረው። ልቡ በአሉታዊ መንፈስ በመሞላቱ በቤተክርስቲያን መሳተፍ አቆመ።

ጁሊያ ስለዚህ ታታሪ፣ አፍቃሪ እና ሩህሩህ ስለነበረ ድንቅ የበታች እረኛ ተናግራለች። እሱን እየገለጸች በነበረበት ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት የመጣደፍ ስሜት ወደ እኔ እንደመጣ በግልፅ አስታውሳለሁ። በእነዚያ ሁሉ ዓመታት፣ ለብዙዎች ብዙ ነገር ላደረገው ለዚያ ሰው አንድ ነገር ላደርግለት ፈለግኩኝ።

እሷም የሞባይል ቁጥሩን ሰጠችኝ እናም እሱን በግምባር የማግኘት እድል አገኛለሁ ብዬ ተስፋ በማድረግ መደወል ጀመርኩኝ። ከበርካታ ሳምንታት እና ከብዙ፣ ብዙ ያልተሳኩ የስልክ ጥሪዎች በኋላ አንድ ቀን በመጨረሻ ስልኩን አነሳ።

ሴት ልጁን ጁሊያን እንዳገኘኋት ነገርኩት፤ እናም ለብዙ አመታት የጌታን ውድ በጎች ባገለገለበት፣ በጠበቀበት እና በወደደበት መንገድ ተደነቅኩኝ። እንደዚያ አይነት አስተያየት አልጠበቀም ነበር። ከእርሱ ጋር በእውነት አይን ለአይን በግንባር ለመገናኘት እንደምፈልግ ነገርኩት። እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ለማድረግ የፈለግኩበትን ዓላማ ጠየቀኝ። “እንደዚህ ካለች ድንቅ ሴት አባት ጋር መገናኘት እፈልጋለሁ” ስል መለስኩለት። ከዚያም ለጥቂት ሰኮንዶች በስልኩ ውስጥ ጸጥታ ሰፈነ—ጥቂት ሰከንዶቹ የዘላለም ያህል መስለውኝ ነበር። በቀላሉ እንዲህ አለ፣ “መቼ እና የት?”

ያገኘሁት ቀን የጌታን ውድ በጎች የመጎብኘት፣ የማገልገል እና አገልግሎት የመስጠት አንዳንድ ልምዶቹን ለእኔ እንዲነግረኝ ጋበዝኩት። አንዳንድ ልብ የሚነኩ ታሪኮችን እየተናገረ በነበረበት ጊዜ፣ የድምፁ ቃና እንደተለወጠ እና ለብዙ ጊዜ የበታች እረኛው ተመልሶ ሲመጣ ይሰማው የነበረው ያው መንፈስ እንዳለ አስተዋልኩ። አሁን ዓይኖቹ በእምባ ተሞልተው ነበር። ይህ ለእኔ ትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ ባውቅም ምን እንደምል ግን አላወኩም ነበር። “አባት ሆይ እርዳኝ” ብዬ በልቤ ጸለይኩኝ።

በድንገት፣ ራሴን እንዲህ ስል ሰማሁት፣ “ወንድም ፍሎሪያን እንደጌታ አገልጋይ ከአጠገብህ ልንሆን ስላልቻልን ይቅርታ እጠይቅሃለሁ። እባክህ ይቅር በለን። በርግጥ እንደምንወድህ ልናሳይህ የምንችልበትን ሌላ እድል ስጠን። እንዲሁም እንደምንፈልግህ እንድናሳይህ። ለእኛ አስፈላጊ እንደሆንክ እንድናሳይህ።

በቀጣዩ እሁድ ተመልሶ መጣ። ከኤጲስ ቆጶሱ ጋር ረጅም ውይይት አደረገ ከዚያም ንቁ ተሳታፊ በመሆን ቀጠለ። ከጥቂት ወራት በኋላ ከዚህ አለም በሞት ተለየ—ቢሆንም ተመልሶ መጥቷል። ተመልሶ መጥቷል። በአዳኛችን እርዳታ ውድ በጎቹን መውደድ እንዲሁም እሱ እንዳደረገው ልናገለግላቸው እንደምንችል እመሰክራለሁ። እናም፣ በዚያ በጓቲማላ ከተማ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ተጨማሪ ውድ በግን ወደ መንጋው አመጣ። እናም ስለማገልገል የማልረሳውን ትምህርት አስተማረኝ። በመልካሙ እረኛ፣ በቆንጆው እረኛ ፣ በድንቁ እረኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።

አትም