አጠቃላይ ጉባኤ
“አንተም ከእኔ ጋር ሁን፣ እና እኔም ከአንተ ጋር፤ ስለዚህ ከእኔ ጋር ተራመድ”
የሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


“አንተም ከእኔ ጋር ሁን፣ እና እኔም ከአንተ ጋር፤ ስለዚህ ከእኔ ጋር ተራመድ”

እንዲሁም አዳኙ ከእኛ ጋር እንደሚኖር የገባው ቃል እውነት እንደሆነ እና ቃል ኪዳንን ለሚጠብቁ ለእያንዳንዱ የቤተክርስቲያኗ አባል ይሆናል።

በብሉይ ኪዳን፣ በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች እንዲሁም በታላቅ ዋጋ ዕንቁ1 ውስጥ የተገለፀው የጥንት ነቢይ ሔኖክ የጽዮንን ከተማ በመመስረት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ ነበረው።

ስለሔኖክ የአገልግሎት ጥሪ የሚናገረው የቅዱሳት መጻህፍት ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ “ከሰማይ እንዲህ የሚልን ድምጽ ሰማ፦ ልጄ ሔኖክ፣ ለእነዚህ ህዝቦች ተንብይና እንዲህ በላቸው—ንስሀ ግቡ፣ … ልቦቻቸው ጠጥረዋል፣ ጆሮዎቻቸውም ደንቁረዋል፣ እናም አይኖቻቸው ወደሩቅ አያዩም።”2

“ሔኖክ እነዚህን ቃላት ሲሰማም፣ በጌታ ፊት ወደመሬት ወደቀ፣ እና በጌታ ፊትም እንዲህ በማለት ተናገረ፥ ለምንድን ነው በፊትህ ሞገስን ያገኘሁት፣ እኔም ገና ልጅ ነኝ፣ እና ህዝቦች ሁሉ አይወዱኝም፤ አፌ ኰልታፋ ነውና፤ ስለዚህ እኔ የአንተ አገልጋይ ነኝ?”3

እባካችሁ ሔኖክ እንዲያገለግል በተጠራበት ወቅት የግል ድክመቶቹንና የአቅም ውስንነቶቹን በሚገባ ያውቅ እንደነበር አስተውሉ። እንዲሁም ሁላችንም በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ በቤተክርስቲያን አገልግሎታችን ውስጥ እንደ ሔኖክ ተሰምቶን እንደነበር አምናለሁ። ሆኖም፣ ጌታ ለሔኖክ የተማጽኖ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ አስተማሪ እንደሆነ እንዲሁም ዛሬ ለእያንዳንዳችን የሚሰራ እንደሆነ አምናለሁ።

“ጌታም ለሔኖክ እንዲህ አለው፥ ሂድና እንዳዘዝኩህ አድርግ፣ እናም ማንም አይጎዳህም። አፍህን ክፈት፣ እናም ይሞላል፣ እኔም የምትናገረውን እሰጥሀለሁ።…

“እነሆ መንፈሴ በአንተ ላይ አርፏል፣ ስለዚህ ቃላትህን ሁሉ አጸድቃለሁ፤ ተራሮችም ከአንተ ፊት ይሸሻሉ፣ እናም ወንዞችም ከሚሔዱበትም ይዞራሉ፤ አንተም ከእኔ ጋር ሁን፣ እና እኔም ከአንተ ጋር፤ ስለዚህ ከእኔ ጋር ተራመድ።4

በመጨረሻም ሔኖክ ታላቅ ነቢይ እንዲሁም ታላቅ ሥራን ለማከናወን በእግዚአብሔር እጅ የሚገኝ መሣሪያ ሆነ፣ ሆኖም አገልግሎቱን የጀመረው በዚያ መንገድ አልነበረም! ከዚያ ይልቅ አቅሙ በጊዜ ሂደት እየጎላ የሄደው ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር ሲሆን እና ከእርሱ ጋር ሲራመድ ነበር።

ጌታ ለሔኖክ የሰጠውን ምክር እንዲሁም ዛሬ ለእኔ እና ለእናንተ ምን ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል በጋራ በምንመክርበት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እናገኝ ዘንድ አጥብቄ እጸልያለሁ።

አንተም ከእኔ ጋር ሁን

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር እንሆን ዘንድ ለእያንዳንዳችን ግብዣውን ያቀርብልናል።5 ነገር ግን፣ በርግጥ ከእርሱ ጋር መሆንን የምንማረው እና ከእርሱ ጋር የምንሆነው እንዴት ነው?

ከእኔ ጋር የሚለው ቃል ባሉበት መቆየትን ወይም መርጋትን እንዲሁም ያለማንገራገር መጽናትን ያመለክታል። ሽማግሌ ጄፍሪ አር. ሆላንድ እንዳብራሩት “ከእኔ ጋር” የሚለው ቃል እንደ ድርጊት “‘መቆየት—እስከ መጨረሻው መቆየት’ ማለት ነው። ያ የወንጌል መልዕክት ጥሪ በአለም ላይ… ላሉ ሁሉ ነው። ኑ፣ ግን ለመቆየት ኑ። በማያወላውል እምነት እና ጽናት ኑ። ለራሳችሁ ስትሉ እንዲሁም ከእናንተ በኋላ ለሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ስትሉ በዘላቂነት ኑ።”6 ስለዚህ በበጎም ሆነ በክፉ ጊዜ፣ ለአዳኙ እና ለቅዱስ አላማዎቹ ባለን ታማኝነት ስንጸና እና የተሰጠን ስንሆን ከክርስቶስ ጋር እንሆናለን።7

ዳግም በተመለሰው ወንጌል ቃል ኪዳኖች እና ሥርዓቶች አማካኝነት የእርሱን ቀንበር8 በላያችን ለመሸከም ያለንን የመምረጥ ነጻነት በመጠቀም ከጌታ ጋር መኖር እንጀምራለን። ከሰማይ አባታችን እና ከሞት ከተነሳው አንዲሁም ከህያው ልጁ ጋር ያለን የቃል ኪዳን ግንኙነት እጅግ የላቀ የአመለካከት፣ የተስፋ፣ የሰላም እና የዘላቂ ደስታ ምንጭ ነው፤ እንዲሁም ህይወታችንን የምንገነባበት የጠንካራ ዓለት መሠረት9 ነው።

ከአብ እና ከልጁ ጋር ያለንን የግል የቃል ኪዳን ትስስር ለማጠናከር ያለማቋረጥ በመጣር ከእርሱ ጋር እንኖራለን። ለምሳሌ በተወዳጅ ልጁ ስም ወደ ዘለአለማዊ አባት ከልብ መጸለይ ከእነርሱ ጋር ያለንን የቃል ኪዳን ግንኙነት ያሳድጋል እንዲሁም ያጠናክራል።

የክርስቶስን ቃል በእውነት በመመገብ ከእርሱ ጋር እንሆናለን። የአዳኙ ትምህርት እንደ ቃል ኪዳኑ ልጆች ወደ እሱ እንድንቀርብ ያደርገናል10 እንዲሁም ልናደርጋቸው የሚገቡንን ነገሮች ሁሉ ይነግረናል።11

በቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ለመሳተፍ በትጋት በመዘጋጀት፣ የቃል ኪዳን ተስፋዎቻችንን በመገምገም እና በማሰላሰል እንዲሁም ከልብ ንስሃ በመግባት ከእርሱ ጋር እንሆናለን። ቅዱስ ቁርባንን በብቁነት መካፈል የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳችን ላይ ለመውሰድ ፈቃደኞች ስለመሆናችን እና በዚያ ቅዱስ ሥርዓት ለመሳተፍ ከሚያስፈልገው አጭር ጊዜ በኋላ “ሁልጊዜ እሱን ለማስታወስ”12 የምንጥር ስለመሆናችን ለእግዚአብሔር ምስክር ነው።

ልጆቹን በምናገለግልበት ጊዜና ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በማገልገል እግዚአብሔርን ስናገለግል ከእርሱ ጋር እንሆናለን።13

አዳኙ እንዳለውም፣ “እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፤ ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።”14

አዳኙ ከእኛ ጋር ሊሆን ከሚችልባቸው ብዙ መንገዶች ጥቂቶቹን በአጭሩ ገልጫለሁ። አሁን ደግሞ እንደ እርሱ ደቀ መዝሙርነታችን በምንሰራው ነገር ሁሉ ክርስቶስን የሕይወታችን ትኩረት ማድረግ ስለምንችልባቸው ሌሎች ትርጉም ያላቸው መንገዶች እንድንጠይቅ፣ እንድንፈልግ፣ እንድናንኳኳ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንድናውቅ እያንዳንዳችንን እጋብዛለሁ።

እኔም ከአንተ ጋር

አዳኙ ለተከታዮቹ የገባው ቃል ኪዳን ድርብ ነው፤ ከእርሱ ጋር ብንሆን እሱ ከእኛ ጋር ይሆናል። ነገር ግን በእርግጥ ክርስቶስ አንድ በአንድ እና በግለሰብ ደረጃ ከእናንተ እና ከእኔ ጋር ይሆን ዘንድ ይቻለዋልን? የዚህ ጥያቄ መልሱ በግልፅ አዎን ነው!

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ አልማ በመከራቸው ትሁት እንዲሆኑ ላስገደዳቸው ድሆች ስለሰጠው ትምህርት እና ምስክርነት እንማራለን። በትምህርቱ ውስጥ ቃሉን፣ መተከል እና እንክብካቤ ሊደረግለት ከሚገባው ዘር ጋር አነጻጽሮታል፤ እንዲሁም “ቃሉ“ የኢየሱስ ክርስቶስ ህይወት፣ ተልዕኮ እና የሃጢያት ክፍያ መሥዋዕት መሆኑን ገልጿል።

አልማ እንዲህ ብሏል፣ “እንዲህ ከሆነ፣ ዋይታ በላያችሁ ይመጣባችኋል፤ ነገር ግን ይህም ካልሆነ፣ በዐይናችሁ ወደዚህና ወደዚያ ተመልከቱ፣ እናም የእግዚአብሔር ልጅ ህዝቡን ሊያድን እንደሚመጣና፣ ለህዝቡ ኃጢያት ክፍያ እንደሚሰቃይና እንደሚሞት፣ እናም ሰዎች እንደስራቸው በመጨረሻውና በፍርዱ ቀን እንዲፈረድባቸው በፊቱ ይቆሙ ዘንድ ትንሳኤን ያመጣ ዘንድ በድጋሚ ከሙታን እንደሚነሳ ማመን ጀምሩ።”15

ይህን በአልማ የተሰጠውን “የቃሉን“ መግለጫ በመያዝ፣ እባካችሁ ከዚያ በኋላ ለይቶ ያወጣውን የሚያነቃቃ ግንኙነት አስቡ።

እናም አሁን … ይህን ቃል በልባችሁ እንድትተክሉ፣ እፈልጋለሁና፣ ማደግ በጀመረ ጊዜ በእምነታችሁ ተንከባከቡት። እናም እነሆ፣ እርሱም ዛፍ ይሆናል፣ እስከዘለዓለማዊው ህይወትም በእናንተ ያብባል። በልጁም ደስታ አማካኝነት ሸክማችሁን እንዲቀልልላችሁ እግዚአብሔር ይፍቀድላችሁ። እናም ይህን ሁሉ እንኳን ከፈቀዳችሁ ማድረግን ትችላላችሁ።”16

በልባችን ለመትከል መጣር ያለብን ዘር የኢየሱስ ክርስቶስ ህይወት፣ ተልዕኮ እና ትምህርት የሆነውን ቃሉን ነው። እንዲሁም ዘሩ በእምነት ሲመገብ፣ ወደ ዘለዓለማዊው ህይወትም በእኛ ውስጥ የሚያብብ ዛፍ ሊሆን ይችላል።17

በሌሂ ራዕይ ውስጥ ያለው ዛፍ ምሳሌ ምን ነበር? ዛፉ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚወክል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።18

የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ቃሉ በውስጣችን አለ? የአዳኙ የወንጌል እውነቶች በልባችን የስጋ ሰሌዳ ላይ ተጽፈዋልን?19 ወደ እርሱ እየመጣን ነን? እንዲሁም የበለጠ እርሱን እየመሰልን ነን? የኢየሱስ ክርስቶስ ዛፍ በውስጣችን እያደገ ነውን? በእርሱ “አዲስ [ፍጥረታት]”20 ለመሆን እየጣርን ነን?21

ምናልባት ይህ ተዓምራዊ አቅም አልማ እንዲህ ብሎ እንዲጠይቅ አነሳስቶት ይሆናል፣ “በመንፈስ ከእግዚአብሔር የተወለዳችሁ ናችሁን? ። በፊታችሁስ ምስሉን ተቀብላችኋልን? በልባችሁስ ይህንን ታላቅ ለውጥ ተለማምዳችኋልን?22

ጌታ “ከእኔ ጋር ሁን፣ እኔም ከአንተ ጋር23 በማለት ለሔኖክ የሰጠውን ትምህርት ሁል ጊዜ ማስታወስ አለብን። እንዲሁም አዳኙ ከእኛ ጋር እንደሚኖር የገባው ቃል እውነት እንደሆነ እና ቃል ኪዳንን ለሚጠብቁ ለእያንዳንዱ የቤተክርስቲያኗ አባል እንደሚሆን እመሰክራለሁ።

ስለዚህ ከእኔ ጋር ተራመድ።

ሐዋርያው ጳውሎስ ጌታን የተቀበሉ አማኞችን “ስለዚህ በእርሱ ተመላለሱ” ሲል መክሯቸዋል።24

በአዳኙ መመላለስ እና ከእርሱ ጋር መራመድ ሁለት ወሳኝ የደቀመዝሙርነት አስፈላጊ ዘርፎችን ያጎላል፦ (1) የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ማክበር እና (2) ከአብ እና ከወልድ ጋር የሚያስተሳስሩንን ቅዱስ ቃል ኪዳኖች ማስታወስ እና ማክበር።

ዮሐንስ አወጅ፦

“ትዕዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።

“አውቄዋለሁ የሚል ትዕዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።

“ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሟል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን።

“በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።”25

ኢየሱስ ክርስቶስ “ኑ፣ ተከተሉኝ” 26 እና “ከእኔ ጋር ተራመዱ” 27 ብሎ ይጠይቃል።

በእምነት ወደፊት ስንገፋ እና በጌታ የየዋህነት መንፈስ ስንራመድ ፣28 በሃይል፣ በጥበቃ እና በሰላም እንደምንባረክ እመሰክራለሁ።

ምስክርነት እና የተስፋ ቃል

አልማ ለህያው ነፍሳት ሁሉ ከጌታ የመጣውን ፍቅራዊ ተማፅኖ ገልጿል።

“እነሆ፣ ለሰው ሁሉ ግብዣን ልኳል፣ የምህረት ክንድ ወደ እነርሱ ተዘርግቷልና፣ እናም እንዲህ ይላል፦ ንስሀ ግቡ፣ እናም እኔ እቀበላችኋለሁ።

“… ወደ እኔ ኑ፣ እናም ከህይወት ዛፍም ፍሬ ትካፈላላችሁ፤ አዎን የህይወትን ዳቦና ውኃ በነፃ ትመገባላችሁ እናም ትጠጣላችሁ።”29

የአዳኙ ተማፅኖ ፍፁም ሁሉንም የሚያካትት በመሆኑ ላይ አፅንዖት እሰጣለሁ። አሁን በህይወት ያለውን፣ ከዚህ በፊት የኖረውን እና ገና ወደፊት በምድር ላይ የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው በጸጋው እና በምህረቱ ለመባረክ ይጓጓል።

አንዳንድ የቤተክርስቲያኗ አባላት ከዚህ የጉባኤ ማእከል መድረክ እና በአለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች በተደጋጋሚ የሚነገሩት ትምህርቶች፣ መርሆች እና ምስክርነቶች እውነት እንደሆኑ ይቀበላሉ—ነገር ግን እነዚህ ዘላለማዊ እውነቶች ለህይወታቸው እና ላሉባቸው ሁኔታዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማመን ሊቸገሩ ይችላሉ። ከልባቸው ያምናሉ እንዲሁም በታዛዥነት መንፈስ ያገለግላሉ፤ ነገር ግን ከአብ እና ከአዳኙ ልጁ ጋር ያላቸው የቃል ኪዳን ግንኙነት ገና በህይወታቸው ውስጥ ህያው እና የሚቀይር እውነታ አልሆነም።

ለእናንተ አንድ በአንድ እና በግለሰብ ደረጃ ለመግለፅ የሞከርኳቸውን የወንጌል እውነቶች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ልታውቋቸው እና ሊሰሟችሁ እንደሚችሉ ቃል እገባለሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ አፍቃሪ እና ህያው አዳኝ እና ቤዛ እንደሆነ በደስታ እመሰክራለሁ። በእርሱ ከኖርን፣ እርሱም በእኛ ይኖራል።30 በእርሱ ስንመላለስ እና ከእርሱ ጋር ስንራመድ ብዙ ፍሬ በማፍራት እንባረካለን። እንዲህ የምመሰክረውም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ዘፍጥረት 5፥18–24ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 107፥48–57ሙሴ 6–7 ይመልከቱ።

  2. ሙሴ 6፥27

  3. ሙሴ 6፥31

  4. ሙሴ 6፥32፣ 34፤ ትኩረት ተጨምሮበታል።

  5. ዮሐንስ 15፥4–9 ይመልከቱ።

  6. ጀፍሪ አር. ሆላንድ፣ “Abide in Meሊያሆና፣ግንቦት 2004 (እ.አ.አ)፣ 32።

  7. ዮሐንስ 15፥10 ይመልከቱ።

  8. ማቴዎስ 11፥29-30 ይመልከቱ።

  9. ሔላማን 5፥12 ይመልከቱ።

  10. 3 ኔፊ 27፥14–15 ይመልከቱ።

  11. 2 ኔፊ 32፥3 ይመልከቱ።

  12. ሞሮኒ 4፥35፥2

  13. ሞዛያ 2፥17 ይመልከቱ።

  14. ዮሐንስ 15፥10

  15. አልማ 33፥22

  16. አልማ 33፥23፤ ትኩረት ተጨምሮበታል።

  17. አልማ 26፥13 ይመልከቱ።

  18. ይህንን መርህ በ2017(እ.አ.አ) መንፈሳዊ ስብሰባ ላይ አብራርቼዋለሁ።

    “አልማ ‘ሄ[ደ]ና፣ በሰዎቹ ምኩራብና፣ በቤታቸው በመግባት የእግዚአብሔርን ቃል መስበክ ጀመ[ረ]፤ አዎን እናም ቃሉን በእነርሱ መንገድም እንኳን ሰበ[ከ]’” [አልማ 32፥1፤ ትኩረት ተጨምሮበታል]። በተጨማሪም የእግዚአብሔርን ቃል ከዘር ጋር አነፃፅሯል።

    “እንግዲህ፣ ዘሩ በልባችሁ ውስጥ እንዲተከል ሥፍራን ከሰጣችሁት፣ እነሆ፣ እውነተኛ ዘር ከሆነ ወይም መልካም ዘር ከሆነ፣ ባለማመናችሁ የጌታን መንፈስ በመቃወም የማትጥሉት ከሆነ፣ እነሆ፣ እርሱም በደረታችሁ ውስጥ ማደግ ይጀምራል፤ እናም ይህ ዕድገት በልባችሁ ውስጥ ሲሰማችሁ፣ በውስጣችሁ እንዲህ ማለት ትጀምራላችሁ—ይህ መልካም ዘር መሆን አለበት፣ ወይንም ቃሉ መልካም ነው፣ ምክንያቱም በነፍሴ ውስጥ ማደግ ጀመሯልና፤ አዎን ግንዛቤዬን ያበራልኝ ጀምሯል፤ አዎን፣ ለእኔም አስደሳች መሆን ጀምሯል’ [አልማ 32፥28፤ ትኩረት ተጨምሮበታል]።

    “የሚገርመው ነገር፣ ጥሩ ዘር በልብ ውስጥ ሲዘራ ማበጥ፣ መብቀል እና ማደግ ሲጀምር ዛፍ ይሆናል።

    “‘እናም እነሆ፣ ዛፍ ማደግ ሲጀምር፣ እንዲህ ትላላችሁ፥ ስርን እንዲያገኝ፣ እርሱም እንዲያድግ፣ እናም ፍሬን እንዲያስገኝልን፣ በታላቅ ጥንቃቄ እንንከባከበው። እናም አሁን እነሆ፣ በተገቢው ጥንቃቄ ከተንከባከባችሁት ስር ያገኛልም፣ ያድጋልም፣ እናም ፍሬን ያስገኛል።

    “ነገር ግን ዛፉን ከተዋችሁትና፣ ለእንክብካቤው ማሰብ ካቆማችሁ፤ እነሆ ስር አያገኝም፤ እናም የፀሐይ ሙቀት መጥቶ ባቃጠለው ጊዜ፣ ስር ስለሌለው ይደርቃል፤ እናም ትቆርጡትና ትጥሉታላችሁ።

    “እንግዲህ፣ ይህም የሆነው ዘሩ መልካም ስላልነበረ አይደለም፤ ወይም ፍሬውም ቢሆን ተፈላጊ ባለመሆኑ አልነበረም፣ ነገር ግን መሬታችሁ መካን በመሆኑ፣ እናም ዛፉን አትንከባከቡትም፤ ስለዚህ የዚህን ፍሬ አታገኙም።

    “‘እናም ለእዚያ ፍሬ በእምነት ዓይን በመጠበቅ እንደዚህ ቃሉን የማትንከባከቡት፣ ከሆነ፣ ከህይወት ዛፍ ፍሬ በጭራሽ መቅጠፍ አትችሉም።

    “‘ነገር ግን ቃሉን የምትንከባከቡከሆነ፣ አዎን በእምነታችሁ በታላቅ ትጋት፣ ትዕግስት፣ እና ለዚያ ፍሬ በጉጉት በመጠበቅ የምትንከባከቡት ከሆነ፣ ይህም ስር ያወጣል፤ እናም እነሆ ይህም ወደ ዘለዓለማዊው ህይወት የሚያድግ ዛፍ ይሆናል’ [አልማ 32፥37–41፤ ትኩረት ተጨምሮበታል]። …

    “በሌሂ ህልም ውስጥ ያለው ዋናው ገጽታ የህይወት ዛፍ ነው—ይህም ‘የእግዚአብሔርን ፍቅር‘ የሚወክል ነው [1 ኔፊ 11፥21-22]።

    “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና’ [ዮሐንስ 3፥16]።

    “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ፣ ህይወት እና የኃጢያት ክፍያ እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለው ፍቅር ትልቅ መገለጫዎቹ ናቸው። ኔፊ እንደመሰከረው ይህ ፍቅር ‘ከሁሉም ነገሮች በላይ አስፈላጊ የሆነውን‘ እና ‘ለነፍስ በጣም ደስ የሚያሰኘውን‘ የሚወክል ነው [1 ኔፊ 11፥22–23፤ በተጫሪም 1 ኔፊ 8፥12፣ 15 ይመልከቱ]። የ1 ኔፊ ምዕራፍ 11 የህይወትን ዛፍ የአዳኝ ህይወት፣ አገልግሎት እና መስዋዕትነት ተምሳሌት—‘የእግዚአብሔርን ትህትና’ እንደሆነ ዝርዝር መግለጫ ያቀርባል [1 ኔፊ 11፥16]። ዛፉ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚወክል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

    “ዛፉ ላይ ስላለው ፍሬ የማሰብ አንዱ መንገድ የአዳኙን የኃጢያት ክፍያ በረከቶች መወከሉ ነው። ፍሬው ‘ከሁሉም ነገሮች በላይ አስፈላጊ የሆነ’ እና ‘ለነፍስ በጣም ደስ የሚያሰኝ’ [1 ኔፊ 8፥10] እንደሆነ ተገልጿል።

    “ጉልህ በሆነ መንገድ፣ የመፅሐፈ ሞርሞን [ሞሮኒ 10፥32] ዋና ጭብጥ፣ በሌሂ ራዕይ ውስጥ ያለው ሁሉም ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ የቀረበው ግብዣ ነው [ኔፊ 8፥19 ይመልከቱ]። (“በውስጣችን ያለ የቃሉ ኃይል [The Power of His Word Which Is in Us” [ለዲስ ሚስዮኖች በሴሚናር ላይ የተሰጠ መልዕክት፣ ሰኔ 27፣ 2017 እ.አ.አ]፣ 4–5)።

  19. 2 ቆሮንቶስ 3፥3 ይመልከቱ።

  20. 2 ቆሮንቶስ 5፥17

  21. የአልማ ንጽጽር እንደሚያስተምረን የማመን ፍላጎት በልባችን ውስጥ ዘርን ይዘራል፣ ዘሩን በእምነታችን መንከባከብ የሕይወትን ዛፍ ያበቅላል፣ እንዲሁም ዛፉን መንከባከብ ዛፉ “ከጣፋጭ ነገሮች ሁሉ በላይ ጣፋጭ [የሆነውን]” (አልማ 32፥42) እና “ከእግዚአብሔር ስጦታዎች ሁሉ [የላቀውን]”(1 ኔፊ 15፥36)ፍሬ እንዲሰጥ ያደርጋል።

  22. አልማ 5፥14

  23. ሞዛያ 6፥34፤ ትኩረት ተጨምሮበታል።

  24. ቆላስይስ 2፥6

  25. 1 ዮሐንስ 2፥3–6፤ ትኩረት ተጨምሮበታል።

  26. ሉቃስ 18፥22

  27. ሙሴ 6፥34

  28. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፥23ን ይመልከቱ።

  29. አልማ 5፥33–34፤ ትኩረት ተጨምሮበታል።

  30. ዮሐንስ 15፥5 ይመልከቱ።

አትም