አጠቃላይ ጉባኤ
በእርግጥ ይቅርታ ተደርጎልኛልን?
የሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በእርግጥ ይቅርታ ተደርጎልኛልን?

ሙሉ እና ፍጹም የሆነ የይቅርታ የተስፋ ቃል ለሁሉም ተሰጥቷል—ይህም በመጨረሻው በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ነው።

ከበርካታ አመታት በፊት፣ እህት ናትረስ እና እኔ ወደ አይዳሆ ተዛወርን፣ በእዚያም አዲስ ንግድ ጀመርን። በዚያ ቢሮ ውስጥ ረጅም ጊዜያትበስራ አሳልፈናል። ደግነቱ፣ ከስራ ቦታ በጥቂት ርቀት ላይ ነበር የምንኖረው። በየሳምንቱ፣ ሻውና እና ሦስቱ ሴት ልጆቻችን—ሁሉም ከስድስት ዓመት በታች ናቸው—አንድ ላይ ምሳ ለመብላት ወደ ቢሮ ይመጣሉ።

አንድ ቀን ከቤተሰብ ምሳ በኋላ፣ የአምስት ዓመቷ ሴት ልጃችን ሚሼል በተለጣፊ ወረቀት ላይ የግል መልእክት በመጻፍ በቢሮ ስልኬ ላይ እንደለጠፈች አስተዋልኩ።

በቀላሉ እንዲህ ይላል፣ “አባዬ፣ እኔን መውደድ አስታውስ። ያንተው፣ ሚሼል።” ይህ ለአንድ ወጣት አባት በጣም አስፈላጊ ስለሆኑት ነገሮች ኃይለኛ ማስታወሻ ነበር።

ወንድሞች እና እህቶች የሰማይ አባታችን ሁል ጊዜ እንደሚያስታውሰን እና እርሱ ፍጹም እንደሚወደን እመሰክራለሁ። የኔ ጥያቄ ይህ ነው፡- እርሱን እናስታውሰዋለን? እና እኛ እሱን እንወደዋለን?

ከአመታት በፊት፣ የአጥቢያ ቤተክርስትያን መሪ ሆኜ አገልግያለሁ። ከወጣቶቻችን አንዱ የሆነው ዳኒ በሁሉም መንገድ ጎበዝ ነበር። እሱ ታዛዥ፣ ደግ፣ ጥሩ፣ እንዲሁም አፍቃሪ እና ቸር ልብ ነበረው። ሆኖም፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ መልካም ካልሆኑ ቡድኖች ጋር መቀላቀል ጀመረ። አደገኛ ዕፆችን በተለይም ሜታምፌታሚን የመሰሉትን መውሰድ ጀመረ እና በሱስ እና በጥፋት አንሸራታች ጎዳና ቁልቁል ተጓዘ። ብዙም ሳይቆይ፣ መልኩ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። ማንነቱን ለመለየት አስቸጋሪ ነበር። በጣም ጉልህ የሆነ ለውጥ በዓይኖቹ ውስጥ ነበር —ደስተኛ እንዳልነበረ ከዓይኖቹ ይነበብ ነበር። ደጋግሜ እሱን ለማናገር ሞከርኩ፣ ነገር ግን ምንም ውጤት አልተገኘም። እሱ ፍላጎት አልነበረውም።

ይህ አስገራሚ ወጣት ሲሰቃይ እና በፊት ከነበረው የተለየ ህይወት ሲመራ ማየት ከባድ ነበር! እሱ የበለጠ ብዙ ችሎታ ነበረው።

ከዚያም አንድ ቀን የሱ ተአምር ጀመረ።

ወደ ሚሲዮን ከመሄዱ በፊት ታናሽ ወንድሙ ምስክርነቱን ባካፈለበት የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ ተገኘ። በስብሰባው ወቅት ዳኒ ለረጅም ጊዜ ያልተሰማው ነገር ተሰማው። የጌታ ፍቅር ተሰማው። በመጨረሻም ተስፋ ኖረው።

ምንም እንኳን ለመለወጥ ፍላጎት ቢኖረውም፣ ለዳኒ ያ አስቸጋሪ ነበር። የእሱ ሱሶች እና አብሮ የሚመጣውም የጥፋተኝነት ስሜት ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ነበር።

አንድ ቀን ከሰአት በኋላ፣ የደጃፍ ሳር በመቁረጥ እያለሁ፣ ዳኒ ሳያሳውቅ በመኪናው መጣ። በጣም እየታገለ ነበር። ሳር መቁረጫውን አቁሜ በበረንዳ ደረጃ ላይ ጥላ ስር አብረን ተቀመጥን። በዛን ጊዜ ነበር የልቡን ስሜት ያጋራኝ። ተመልሶ መምጣት በእውነት ፈልጎ ነበር። ሆኖም ግን ከሱሱና ከአኗኗሩ ለመመለስ እጅግ በጣም ከባድ ነበር። በዚህ ላይ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶት ነበር፣ ይህን ያህል በመራቁ በጣም አፈረ። እሱም “በእርግጥ ይቅርታ ማግኘት እችላለሁን? ብሎ ጠየቀ። በእርግጥ የመመለሻ መንገድ አለ?”

በእነዚህ ስጋቶች ያለውን የልቡን ሃሳብና ስሜት ከገለጽ በኋላ፣ አልማ ምዕራፍ 36ን አንድ ላይ አነበብን፡

“አዎ፣ ሁሉንም ኃጢአቶቼንና በደሎቼን አስታወስኩ።…

“አዎን፣ … ወደ አምላኬ በፊቱ ለመቅረብ ያለኝ ሀሳብ በሚያስቸግር ስቃይ ነፍሴን እንድትሰቃይ አደረጋት።” (ቁጥር 13–14).

ከእነዚህ ጥቅሶች በኋላ ዳኒ “የተሰማኝ ልክ እንደዚህ ነው!” አለ።

እናም ቀጠልን፥

“በኃጢአቶቼ ብዛትም በትውስታ በተሰቃየሁ ጊዜ፣ እነሆ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለተባለው፣ የዓለምን ኃጢያት ለመክፈል ስለሚመጣው፣ የአባቴን ትንቢት መስማቴን አስታወስኩኝ። …

“እናም አቤቱ፣ እንዴት ያለ ደስታ ተሰማኝ፤ እናም ምን ዓይነት አስደናቂ ብርሃንን አይቻለሁ” (ቁጥር 17፣ 20)።

እነዚህን ክፍሎች ስናነብ እንባዎች መፍሰስ ጀመሩ። የአልማ ደስታ ሲፈልግ የነበረው ደስታ ነበር!

አልማ በጣም ሃጢያተኛ እንደነበረ ተወያየን። ነገር ግን፣ አንዴ ንስሃ ከገባ በኋላ ወደ መጥፎ አመሉ። እሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ደቀ መዝሙር ሆነ። እናም ነቢይ ሆነ። የዳኒ አይኖች በአድናቆት ተከፈቱ። “ነብይ?” አለ።

እንዲህም መለስኩለት፣ “አዎ ነቢይ። በአንተ ላይ ምንም ጫና የለም!” አልኩት።

ኃጢያቶቹ እንደ አልማ የከፋ ባይሆኑም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ምክንያት የፍፁም ይቅርታ ቃል ለሁሉም ሰው እንደተሰጠ ተወያየን።

ዳኒ አሁን ተረዳ። ምን ማድረግ እንዳለበት አወቀ፡ በጌታ በመታመን እና እራሱን ይቅር በማለት ጉዞውን መጀመር ነበረበት!

የዳኒ ታላቅ የልብ ለውጥ ከተአምር የተናነሰ አልነበረም። ከጊዜ በኋላ ፊቱ ተለወጠ፣ እና የዓይኑ ብሩህነት ተመለሰ። ቤተመቅደስ ለመግባት ብቁ ሆነ! በመጨረሻም ተመለሰ!

ከብዙ ወራት በኋላ ዳኒ የሙሉ ጊዜ ሚስዮን ለማገልገል ማመልከቻ ማስገባት ይፈልግ እንደሆነ ጠየቅኩት። የእርሱ መልስ የሚገርም ነበር።

እሱ እንዲህ አለ፣ “ሚሲዮን ባገለግል ደስ ይለኛል፣ ነገር ግን የት እንደነበርኩ እና ያደረኳቸውን ነገሮች ታውቃለህ! ብቁ እንዳልሆንኩ አስቤ ነበር።”

እኔም እንዲህ ብዬ መለስኩኝ፣ “ትክክል ልትሆን ትችላለህ። ይሁን እንጂ ጥያቄ ከማቅረብ የሚከለክለን ነገር የለም። ከተከለከልክ፣ ቢያንስ ጌታን ለማገልገል ልባዊ ፍላጎት እንዳሳየህ ታውቃለህ።” አይኖቹ በደስታ አበሩ። በዚህም ሀሳብ በጣም ተደመመ። ለሱ ይህ ትንሽ የመሳካት እድል ያለው ቢመስልም፣ እሱ እድሉን ለመሞከር ፈቃደኛ ነበር።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ እሱን በሚያስገርም ሁኔታ፣ ሌላ ተአምር ተፈጠረ። ዳኒ የሙሉ ጊዜ ሚስዮን ለማገልገል ጥሪ ደረሰው።

ዳኒ በሚስዮን መስክ ከደረሰ ከጥቂት ወራት በኋላ፣ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ። የሱም ፕሬዚዳንት በቀላሉ፣ “ይህ ወጣት ምንድን ነው? እስካሁን ካየኋቸው ሚስዮናውያን ሁሉ የሚያስደንቅ ሚስዮናዊ ነው!” እንደምታዩት ይህም ፕሬዘዳንት የጊዜያችን የሆነውን ታናሹን አልማ አግኝቷል።

ከሁለት አመት በኋላ፣ ዳኒ በሙሉ ልቡ፣ ኃይሉ፣ ሃሳቡ እና ጥንካሬው ጌታን በማገልገል በክብር ወደ ቤት ተመለሰ።

በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ የእሱን የሚስዮናዊ ንግግር ተከትሎ፣ ወደ ቤት ተመለስኩ፣ ወዲያውኑ በር ሲንኳኳ ሰማሁ። በዚያም አይኖቹ በእንባ ተሞልተው ዳኒ ቆሞ ነበር። እሱም “ለአንድ ደቂቃ ማውራት እንችላለን?” አለ። ወደዚያው በረንዳ ደረጃ ወደ ውጭ ወጣን።

እሱም፣ “ፕሬዝዳንት፣ በእውነት ይቅርታ የተደረገልኝ ይመስልሃል?” አለ።

አሁን እንባዬ አብሮት መውረድ ጀመረ። ስለ አዳኙ ለማስተማር እና ለመመስከር ሁሉንም የሰጠ የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ደቀ መዝሙር በፊቴ ቆሞ ነበር። እሱ የአዳኙ የሀጢያት ክፍያ የመፈወስ እና የማጠናከሪያ ሀይል አምሳያ ነበር።

እኔም እንዲህ አልኩኝ “ዳኒ! በመስታወት ውስጥ አይተሃል? ዓይንህን አይተሃል? በብርሃን ተሞልተዋል አንተም በጌታ መንፈስ ታበራለህ። በእርግጥ ይቅርታ ተደርጎልሃል! አንተ ድንቅ፡ ነህ! አሁን ማድረግ ያለብህ በህይወትህ ወደፊት መግፋት ነው። ወደ ኋላ አትመልከት! የሚቀጥለውን ሥርዓት በእምነት ተጠባበቅ።”

የዳኒ ተአምር ዛሬም ቀጥሏል። በቤተመቅደስ ውስጥ ጋብቻውን ፈጽሞ ወደ ትምህርት ቤት ተመለሰ፣ ከዚያም የማስተርስ ዲግሪ አግኝቷል። በጥሪውም ጌታን በክብርና በሃቀኝነት ማገልገሉን ቀጥሏል። ከሁሉም በላይ፣ እሱ አስደናቂ ባል እና ታማኝ አባት ሆኗል። እሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ደቀ መዝሙር ነው።

ፕሬዘደንት ረስል ኤም ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “ያለ [አዳኝ] ማለቂያ የሌለው የኃጢያት ክፍያ፣ ሁሉም የሰው ልጅ በማይታለፍ መልኩ ይጠፋል።”1 ዳኒ አልጠፋም ነበር፣ እኛም ለጌታ አልጠፋንም። ሊያነሳን፣ ሊያበረታንና ይቅር ሊለን በበሩ ላይ ቆሟል። እኛን እንደሚወደን ሁልጊዜ ያስታውሳል!

አስደናቂ የሆነው አዳኙ ለእግዚአብሔር ልጆች ያለው ፍቅር በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ተመዝግቧል፡ “እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እንዲህ በተናገረ ጊዜ፣ ዐይኑን በድጋሚ በህዝቡ ላይ በዙሪያው ያደርግ ነበር፤ እናም እንባ እያነቡ መሆናቸውንና፣ እርሱ ከእነርሱ ጋር ትንሽ እንዲቆይ የሚፈልጉ በመምሰል በእርሱ ላይ ያተኮሩ ይመስሉ እንደነበር ተመለከተ”(3 ኔፊ 17:5)።

አዳኙ ህዝቡን ሲያገለግል ሙሉ ቀን አሳልፏል። ሆኖም፣ ብዙ የሚሠራው ነገር ነበረው- ሌሎች በጎቹን መጎብኘት ነበረበት። ወደ አባቱ መሄድ ነበረበት።

እነዚህ ግዴታዎች ቢኖሩበትም፣ ህዝቡ ትንሽ ከእነርሱ ጋር እንዲቆይ እንደፈለጉ ተረዳ። ከዚያም፣ በርህራሄ በተሞላ በአዳኝ ልብ፣ በአለም ታሪክ ውስጥ ካሉት ታላላቅ ተአምራት አንዱ የሆነው ተከሰተ፤

ወደ ኋላ ቆየ።

ባረካቸው።

ልጆቻቸውን አንድ በአንድ አገለገለ።

ጸለየላቸው፣ አብሯቸው አለቀሰ።

እናም ፈወሳቸው። ( 3 ኔፊ 17ን፣ ተመልከቱ።)

ተስፋው ዘላለማዊ ነው፡ እርሱ ይፈውሰናል።

ከቃል ኪዳኑ መንገድ ለወጣችሁ፣ እባካችሁ ሁል ጊዜ ተስፋ እንዳለ፣ ሁል ጊዜ ፈውስ እና ሁል ጊዜም የመመለሻ መንገድ እንዳለ እወቁ።

የእሱ ዘላለማዊ የተስፋ መልእክት በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ ለሚኖሩ ሁሉ የፈውስ ቅባት ነው። ኢየሱስም እንዲህ ብሏል፣ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ”(ዮሀንስ 14፥6)።

ወንድሞች እና እህቶች፣ እርሱን መፈለግን፣ መውደድን እና እሱን ሁልጊዜ ማስታወስን እናስታውስ።

እግዚአብሔር ህያው እንደሆነ እናም እንደሚያፈቅረን እመሰክራለሁ። በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም አዳኝ ቤዛ እንደሆነ እመሰክራለሁ። እርሱ ሃያል ፈዋሽ ነው። አዳኜ ህያው እንደሆነ አውቃለሁ! በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻ

  1. ረስል ኤም ኔልሰን፣ “ለቤተመቅደስ በረከቶች መዘጋጀት፣” ኢንዛይን፣ መጋቢት 2002 (እ.አ.አ)፣ 21።

አትም