አጠቃላይ ጉባኤ
አዕምሮዬ በዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ሀሳብ ላይ ተያዘ
የሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


13:26

አዕምሮዬ በዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ሀሳብ ላይ ተያዘ

የኢየሱስ ክርስቶስን ሃሳብ በትኩረት መያዛችሁን ስትቀጥሉ ሰማያዊ ምሪት ብቻ ሳይሆን ሰማያዊ ሀይልም እንደምታገኙ ቃል እገባላችኋለሁ።

በዚህ ውብ የፋሲካ በዓል ውስጥ “ምራን ኦ ሃያል ያህዌ” የሚለውን መዝሙር ጸሎት አስተጋባለው።1

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የሚገኝ አንድ አስደናቂ ታሪክ ቅዱሳት መጻህፍት ጣዖት አምላኪ የማያምን አድርገው ስለሚገልጹት ከታዋቂ ቤተሰብ ስለወጣ አልማ ስለሚባል አንድ ወጣት ይናገራሉ።2 አቀላጥፎ የሚናገርና የሚያሳምን ነበር፤ ሌሎች እሱን እንዲከተሉት ለማሳመንም ማሞጋገስን ይጠቀም ነበር። በሚያስደንቅ ሁኔታ አንድ መልዓክ ለአልማ እና ለጓደኞቹ ታያቸው። አልማ መሬት ላይ ወደቀ እንዲሁም በጣም ደክሞ ምንም ማድረግ የማይችል ስለነበር ወደ አባቱ ቤት ተወሰደ። ራሱን የሳተ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ለሦስት ቀናት ቆየ።3 በኋላም፣ በዙሪያው ላሉት ራሱን የማያውቅ የነበረ ቢመስልም የእግዚአብሄርን ትእዛዛት ስለማያከብረው ህይወቱ በማሰብ ነፍሱ ስታዝን አእምሮው በጣም ንቁ እንደነበር ገለጸ። አእምሮው “በኃጢአቶ[ቹ] ብዛት ትውስታ”4 እና “በስቃይ ለዘላለም ተጨንቆ”5 እንደነበር ገልጿል።

በጥልቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኖ “የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለተባለው፣ የዓለምን ኃጥያት ለመክፈል [እንደሚመጣ]” በልጅነቱ የተማረውን አስታወሰ።6 ቀጥሎም ይህን በጣም የሚያነቃቃ ንግግር አደረገ፦ “አዕምሮዬ በዚህ ሃሳብ ላይ በተያዘበት ጊዜ በልቤ እንዲህ በማለት አለቀስኩ፥ የእግዚአብሄር ልጅ የሆንከው ኢየሱስ ሆይ ምህረትህን በእኔ ላይ አድርግልኝ።”7 የአዳኙን መለኮታዊ ኃይል በለመነ ጊዜ አንድ ተዓምራዊ ነገር ተፈጠረ፦“ይህንን ባሰብኩ ጊዜ ህመሜን ደግሞ ለማስታወስ አልቻልኩም” ሲል ተናግሯል።8 በድንገት ሰላምና ብርሃን ተሰማው። “እንደ እኔ ደስታ ሃያል እና ጣፋጭ ሊሆን የሚችል ምንም [አልነበረም]”9 ሲል ተናግሯል።

አልማ በኢየሱስ ክርስቶስ ሃሳብ “ተያዘ”። “ያዘ” የሚለውን ቃል ለአካላዊ ሁኔታ በምንጠቀምበት ጊዜ እንዲህ ልንል እንችላለን፣ “ሊወድቅ ሲል የመጠበቂያ አግዳሚውን ያዘ”፣ ማለትም አስተማማኝ መሠረት ያለውን በጠንካራ ሁኔታ የተተከለን ነገር በፍጥነት እንዲሁም አጥብቆ ያዘ ማለት ነው።

በአልማ ሁኔታ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን የሃጢያት መስዋዕት ሀያል እውነት የጨበጠው እና አጥብቆ የያዘው አእምሮው ነበር። በዚያ አውነት ላይ በእምነት በመተግበር እንዲሁም በእግዚአብሄር ሃይል እና ጸጋ ከተስፋ መቁረጥ ድኖ እና በተስፋ ተሞልቶ ነበር።

ገጠመኞቻችን የአልማን ያህል አስገራሚ ላይሆኑ ቢችሉም ዘላለማዊ ጠቀሜታ አላቸው። አዕምሯችን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በይቅርታ መሥዋዕቱ “ሃሳብ ላይ ተይዘዋል” እንዲሁም ነፍሶቻችን እርሱን ተከትሎ የሚመጣው ደስታ እና ብርሃን ተሰምቷቸዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ሃሳብ መጠበቅ

በዚህ የትንሳኤ ወቅት የማቀርበው ጸሎት ያለማቋረጥ እና በጉጉት ወደ አእምሯችን እንዲፈስ በመፍቀድ፣ በምናስበው እና በምናደርገው ነገር ውስጥ እንዲመራን ይህንን የኢየሱስ ክርስቶስ ሃሳብ በነፍሳችን ክፍል ውስጥ10 እንድንቀርጸው፣ እንድናጠነክረው እና እንድንይዘው እንዲሁም ያለማቋረጥ የአዳኙን ፍቅር ጣፋጭ ደስታ እንዲያመጣ ነው።11

በኢየሱስ ክርስቶስ ሃይል አእምሯችንን መሙላት ማለት የምናስበው ስለእርሱ ብቻ ነው ማለት አይደለም። ነገር ግን ሀሳባችን ሁሉ በፍቅሩ፣ በህይወቱ እና በትምህርቱ እንዲሁም በሃጢያት ክፍያ መስዋዕቱ እና በታላቁ ትንሳኤው የተከበበ ነው ማለት ነው። ኢየሱስ በፍጹም በተረሳ ጥግ ላይ አይሆንም ምክንያቱም ሁልጊዜ ስለእርሱ የምናስባቸው ሃሳቦች አሉን እና “በውስጣችን ያለው ሁሉ ነገር እርሱን ያወድሳል።”12 እንጸልያለን እንዲሁም ወደእርሱ እንድንቀርብ ያደረጉንን ተሞክሮዎች በአእምሯችን መላልሰን እናስባቸዋለን። ጥድፊያ በተሞላበት ህይወታችን ውስጥ የሚመላለሱትን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የዕለት ተዕለት ሀሳቦች ችላ በማለት ለማስታገስ መለኮታዊ ምስሎችን፣ ቅዱሳት መጻህፍትን እና በመንፈስ የተነሳሱ መዝሙሮችን ወደ አእምሯችን እንጋብዛለን። ለእርሱ ያለን ፍቅር በዚህ በምድራዊ ህይወት ውስጥ ከመከፋት እና ከሀዘን አይከልለንም ነገር ግን ፈተናዎችን ከራሳችን በላይ በሆነ ጥንካሬ እንድናልፍ ያስችለናል።

ኢየሱስ፣ ስለአንተ ማሰብ

ደረቴን በደስታ ይሞላታል፤

ግን ፊትህን ማየቱ ይበልጥ ያስደስታል

በመገኘትህም ማረፍ፡፡13

እናንተ የእግዚአብሔር የመንፈሥ ልጆች መሆናችሁን አስታውሱ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳብራራው እኛ “የእግዚአብሔር ዘመዶች ነን።”14። ወደ ምድር ከመምጣታችሁ ከረዥም ጊዜ በፊት ከራሳችሁ ማንነት ጋር ኖራችኋል። የሰማይ አባታችን ወደምድር እንድንመጣ፣ እንድንማር እና ወደእርሱ እንድንመለስ ፍጹም ዕቅድ አዘጋጅቶልናል። ወሰን በሌለው የሃጢያት ክፍያ መስዋዕቱ እና በትንሳኤው ከመቃብር ባሻገር እንድንኖር እንዲሁም በእርሱ ላይ እምነትን ስንለማመድ እና ለሃጢያታችን ንስሃ ስንገባ ይቅር እንድንባል15 እና የዘላለምን ህይወት14እንድናገኝ ተወዳጅ ልጁን ልኳል።

ለአዕምሯችን እና ለነፍሳችን የተለየ ትኩረት መስጠት

በዚህ ምድራዊ ህይወት አእምሯችን እና መንፈሳችን ልዩ ትኩረት ይፈልጋሉ።17 አእምሯችን መልካሙን እና ክፉውን እንድንመርጥ፣ እንድናውቅ ይፈቅድልናል።18 እግዚአብሔር አባታችን እንደሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እና ትምህርታቸው እዚህ የደስተኝነት መመሪያችን እንዲሁም ከመቃብር ባሻገር ደግሞ የዘለአለም ህይወት መሆኑን የሚያረጋግጥ ምስክርነትን መንፈሳችን ይቀበላል።

የአልማ አዕምሮ በኢየሱስ ክርስቶስ ሃሳብ ላይ ተይዟል። ህይወቱን ቀይሮታል። አጠቃላይ ጉባኤ ጌታ እንደናደርግ እና እንድንሆን የሚፈልገውን የምንረዳበት ጊዜ ነው። እንዲሁም እድገታችንን የማንፀባረቂያ ጊዜ ነው። የሥራ ምድቦቼ በመላው አለም እንድዞር ስላደረጉኝ የጽድቅ ታታሪ የቤተክርስቲያን አባላት ቀጣይነት ያለው መንፈሳዊ ጥንካሬን አይቻለሁ።

ከአምስት ዓመታት በፊት የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እውነተኛ ስም በመጠቀም በምናደርገው ነገር ሁሉ አዳኙን የበለጠ ጠቃሚ በሆነ ቦታ እንድናስቀምጠው ተጠይቀን ነበር።19 የእርሱን ስም በበለጠ ከልብ በሆነ ስሜት እየተናገርን ነው።

ከአራት አመታት በፊት፣ የቅዱስ ቁርባን ስብሰባችንን በመቀነስ፣ ትኩረታችንን በጌታ ቅዱስ ቁርባን ላይ ጨምረናል። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ እያሰብን ነው እንዲሁም ሁሌም እርሱን ለማስታወስ በገባነው ቃልኪዳን በጣም ቆራጦች ነን።20

ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ባስከተለው መራራቅ እንዲሁም በ ኑ፣ ተከተሉኝእርዳታ፣ በሳምንቱ ውስጥ የአዳኙን አምልኮአችንን በማገዝ የአዳኙ ትምህርቶች በቤታችን ውስጥ ጎልተው ታይተዋል።

የፕሬዝዳንት ረስልኤም. ኔልሰንን “እርሱን ስሙት” ምክር በመከተል21 የመንፈስ ቅዱስ ሹክሹክታን የመገንዘብን እና በህይወታችን ውስጥ የጌታን እጅ በህይውታችን ውስጥ የማየት ችሎታችንን እያዳበርን ነው።

የቤተመቅደሶች መሰራት ማስታወቂያ እና መጠናቀቅ ከመነገሩ ጋር በተደጋጋሚ ወደ ጌታ ቤት እየገባን እና እርሱ የገባቸውን በረከቶች እየተቀበልን ነው። የአዳኛችን እና የቤዛችን አቻ የሌለው ውበት የበለጠ ኃይልን እየተሰማን ነው።

ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ ብለዋል፦ “በቀላሉ ወይም በቀጥታ ጠንካራ [ደቀ መዝሙር] የመሆን መንገድ የለም፡፡ ትኩረታችን መሆን ያለበት በአዳኛችን እና በወንጌሉ ላይ ነው። በሁሉም አስተሳሰባችን ወደ እርሱ ለመመልከት መጣር በአእምሮ ጠንካራ መሆንን ይጠይቃል።”22

ትኩረታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማድረግ በዙሪያችን ያሉ ሌሎች ነገሮች ሁሉ—አሁንም እያሉ—ለእርሱ ባለን ፍቅር ይታያሉ። አስፈላጊነታቸው አነስተኛ የሆኑ ትኩረትን የሚቀንሱ ነገሮች እየጠፉ ይሄዳሉ እንዲሁም ከብርሃኑ እና ከባህሪው ጋር የማይጣጣሙትን እናስወግዳለን። ይህን የኢየሱስ ክርስቶስ ሀሳብ በትኩረት መያዛችሁን ስትቀጥሉ፣ በእርሱ ስትታመኑ እና ትዕዛዛቱን ስትጠብቁ፣ ሰማያዊ ምሪት ብቻ ሳይሆን ለቃል ኪዳኖቻችሁ ጥንካሬን፤ ለችግሮቻችሁ ሰላምን እንዲሁም ለበረከቶቻችሁ ደስታን በሚያመጣ በሰማያዊ ሃይልም ትባረካላችሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ አስታውሱ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት እኔና ካቲ የማትን እና የሳራ ጆንሰንን ቤት ጎበኘን። በግድግዳው ላይ የውድ ቤተሰባቸው ፎቶ፣ የአዳኙ የሚያምር ምስል እና የቤተመቅደስ ሥዕል አለ።

አራቱ ሴት ልጆቻቸው ማዲ፣ ሩቢ፣ ክሌር እና ጁን እናታቸውን ምን ያህል እንደሚወዷት በደስታ ይናገሩ ነበር።

ልጆቹ ከዚህ ቀደም ለኖሩ የቤተሰብ አባላት ይጠመቁ ዘንድ ከአንድ አመት ለሚበልጥ ጊዜ ሣራ ቤተሰቡ አብሮ ወደ ቤተመቅደስ እንዲሄድ አዘወትራ የቅዳሜ ቀጠሮዎችን ትይዝ ነበር።

ሣራ ባለፈው ዓመት ህዳር ውስጥ ከቅዳሜ ይልቅ በታህሳስ የመጨረሻ ሳምንት ሐሙስ ዕለት የቤተሰብ የቤተ መቅደስ ቀጠሮ ያዘች። ማትን “በዚህ የምትስማማ ይመስለኛል” አለችው።

ሳራ ካንሰር ተገኝቶባት ነበር፣ ሆኖም ዶክተሮቹ ሁለት ወይም ሶስት ተጨማሪ ዓመታት ልትኖር እንደምትችል ገምተው ነበር። በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ፣ የሚመጣው ውጤት ምንም ቢሆን አዳኙን በሙሉ ልቧ እንደወደደች እና በእርሱ አማካኝነት “ድሉ አስቀድሞ እንደተገኘ” ሳራ ጠንካራ ምስክርነቷን አካፍላለች። ታህሣሥ እየተገባደደ ሲሄድ የሳራ ጤንነት ሳይታሰብ በፍጥነት እያሽቆለቆለ። ሄደ ከዚያም ሆስፒታል ገባች። ሐሙስ ታህሳስ 29 ማለዳ ላይ በጸጥታ ምድራዊ ህይወቷን አጠናቀቀች። ማት ሌሊቱን ሙሉ ከሣራ አጠገብ ነበር።

ልቡ ተሰብሮ እንዲሁም በአካል እና በስሜት ሙሉ በሙሉ ተዳክሞ ከሴት ልጆቹ ጋር እያዘነ ቤቱ ደረሰ። ማት ስልኩን ሲያይ ሣራ በዚያ ቀን ለመሳተፍ የያዘችውን ያልተለመደ የሀሙስ የቤተ መቅደስ ቀጠሮ አስታዋሽ ተመለከተ። ማት እንዲህ አለ “መጀመሪያ ሳየው፣ ይህ የሚሰራ አይመስለኝም ብዬ አሰብኩኝ።”

ሆኖም ከዚያ በኋላ የማት አዕምሮ በዚህ ሃሰብ ተያዘ፦ “አዳኙ ህያው ነው። ከቅዱስ ቤቱ ይልቅ እንደ ቤተሰብ የምንሄድበት ሌላ ቦታ የለም።”

የጆንሰን ቤተሰብ

ማት፣ ማዲ፣ ሩቢ፣ ክሌር እና ጁን ሣራ በያዘችላቸው ቀጠሮ መሠረት ወደ ቤተ መቅደሱ ደረሱ። እንባው በጉንጮቹ ላይ እየወረደ ማት ጥምቀቱን ከሴት ልጆቹ ጋር አከናወነ። ለሳራ ያላቸው ፍቅር እና ከእርስዋ ጋር ያላቸው ዘላለማዊ ጥምረት በጥልቀት ተሰማቸው እንዲሁም የአዳኙ አስደናቂ ፍቅር እና የሚያጽናና ሰላም ተሰምቷቸዋል። ማት እንዲህ ሲል በትህትና ተናግሯል፣ “ጥልቅ ሀዘን እና ሰቆቃ ቢሰማኝም የአባቴን አስደናቂ የደህንነት እቅድ በማወቅ በደስታ እጮኻለሁ።”

በዚህ የትንሳኤ ወቅት አዳኙ ስላቀረበው ወደር የለሽ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት እና ታላቅ ትንሳኤው ሙሉ እና ፍፁም እውነትነት እመሰክራለሁ። አዕምሮአችሁ በጥንካሬ እና ለዘላለም በኢየሱስ ክርስቶስ ሃሳብ ላይ ሲቆይ እንዲሁም የህይወታችሁ ትኩረት በአዳኙ ላይ ሲያዝ፣ ተስፋው፣ ሰላሙ እና ፍቅሩ እንደሚሰማችሁ ቃል እገባላችኋለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. “ምራን ኦ ሃያል ያህዌ” መዝሙር፣ ቁጥር 83።

  2. ሞዛያ 27፥8 ይመልከቱ።

  3. አልማ 36፥10 ይመልከቱ።

  4. አልማ 36፥17

  5. አልማ 36፥12

  6. አልማ 36፥17

  7. አልማ 36፥18። በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ “መያዝ” የሚለው ቃል ጥቅም ላይ የዋለበት ሌላው ጊዜ “የብረት ዘንጉን ጫፍ ስለያዙ ሰዎች” በተናገረበት ጊዜ ነው (1 ኔፊ 8፥24፣ 30)።

  8. አልማ 36፥19

  9. አልማ 36፥21

  10. “የህይወት ትልቁ ጦርነት የሚካሄደው በራሳችሁ ጸጥ ባለ ልባችሁ ውስጥ ነው” [ዴቪድ ኦ. መኬይ፣ በጉባኤ ሪፖርት ላይ፣ ሚያዚያ 1967 (እ.አ.አ)፣ 84]።

  11. “[ሐሳቦች] ሁሉም ድርጊቶች እንዲከናወኑ ያደርጋሉ። ሀሳባችን ተግባራችንን የሚቆጣጠር የመቀያየሪያ ሰሌዳ፣ የቁጥጥር ፓነል ነው” (Boyd K. Packer, That All May be Edified [1982], 33).

    ፕሬዚዳንት ዳለንኤች. ኦክስ እንዲህ ብለዋል “ክፉ ምኞቶችን ማጥፋት እና በጽድቅ ምኞቶች መተካት እንችላለን። ይህ ትምህርትን እና ልምምድን ያካትታል። ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ኤፍ. ስሚዝ እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል “ስለምኞታችን መማር በጣም ትልቅ ጠቀሜታ አለው’” (Pure in Heart [1988 እ.አ.አ] 149)።

  12. “ለሐያሉ ጌታ ምስጋና ይሁን” መዝሙር፣ ቁጥር 72።

  13. “Jesus, the Very Thought of Thee፣” መዝሙር፣ ቁጥር 141።

  14. የሐዋሪያት ስራ 17፥29

  15. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 58፥42–43፣ ይመልከቱ።

  16. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 14፥7ይመልከቱ።

  17. “አዎን፣ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም ሀሳብህንና የልብህን ፈቃድ እንደማያውቅ እንድታውቅ ዘንድ እነግርሀለሁ።” (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 6፥16)።

  18. “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል”(ሉቃስ 6፥45)።

  19. የራስል ኤም.ኔልሰንን “የቤተክርስቲያኒቷ ትክክለኛ መጠሪያ፣” ሊያሆና ህዳር 2018 ፣87–89 ይመልከቱ

  20. በየሳምንቱ በሚደረገው የቅዱስ ቁርባን ጸሎት ላይ የምንገባው ቃል ኪዳን “ሁልጊዜ እርሱን ለማስታወስ” ነው።(ሞሮኒ 4፥3ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥77)። መፅሐፈ ሞርሞን “አስታውሱ፣ አስታውሱ” የሚለውን ቃል ሁለቴ በተካታታይ በመጠቀም ያበረታታናል (ሞዛያ 2፥41አልማ 37፥13ሄለማን 5፥9)። የመንፈሳዊ ማስታወስ የሚመጣው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት ነው፦“መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐነሰ 14፥26)።

  21. ረሴል ኤም. ኔልሰን፣ “Hear Him፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2020 (እ.አ.አ.)፣ 90።

  22. ራስል ኤም. ኔልሰን፣““የኢየሱስ ክርስቶስን ሀይል ወደህይወታችን መሳብ”፣” ሊያሆና፣ግንቦት 2017 (እ.አ.አ)፣ 41። በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ ብለዋል፣ “[የኋለኛው ቀን ቅዱሳን] የሚሰማን ደስታ ካለንበት የህይወት ሁኔታዎች ጋር ያለው ተዛምዶ አነስተኛ ነው፤ ከህይወታችን ትኩረት ጋር የተያየዘ ነው።(“Joy and Spiritual Survival,” ሊያሆና፣ ህዳር 2016 [እ.አ.አ]፣82)።