እንደ ክርስቲያን በክርስቶስ የማምንበትን ምክንያት ታውቃላችሁ?
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ሁሉ ከሥጋዊ ሞት ለማዳን እና ከእግዚአብሔር ጋር የዘላለም ሕይወት ለመስጠት መከራ መቀበል፣ መሞት እና መነሳት ነበረበት።
ከአመታት በፊት በአንድ ምሽት ከስራ በኋላ፣ ከኒውዮርክ ከተማ ወደ ቤቴ ኒው ጀርዚ በሚሄደው የተለመደ አውቶቡስ ተሳፈርኩ። በአጋጣሚ አጠገቤ የተቀመጠችው ሴት በኮምፒውተሬ ላይ የምጽፈውን አስተውላ፣ “በክርስቶስ … ታምናለህ?” ብላ ጠየቀችኝ። “አዎ፣ አምናለሁ!” አልኩኝ። ስንነጋገር፣ ውብ ከሆነች እስያዊት ሀገሯ በኒውዮርክ ከፍተኛ ፉክክር ባለው በመረጃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለመስራት ወደ አካባቢው እንደመጣች ተረዳሁ።
እንደልማድ “እንደ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ የማምንበትን ምክንያት ታውቂያለሽ?” ብዬ ጠየቅኳት። እሷም እንደተለመደው ምላሽ ሰጥታኝ እንድነግራት ጋበዘችኝ። ነገር ግን ለመናገር ስሞክር ብዙ ሃሳቦች አእምሮን ከሚያጥለቀልቁበት ከእነዚያ ጊዜያት እንደ አንዱ ተሰማኝ። የክርስቲያንን “ለምን” ስለእንዲሁ ምንም ለማያውቅ እና በጣም ብልህ ለሆነ ሰው ስገልጽ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር። በቀላሉ “ኢየሱስ ክርስቶስን የምከተለው እርሱ በፈቃዱ መከራን ስለተቀበለ እና ለኃጢአቴ ስለሞተ ነው” ማለት አልቻልኩም። እርሷም፣ “ኢየሱስ መሞት ነበረበት? ብላ ልታስብ ትችላለች። እግዚአብሔር እንዲያው ከጠየቅነው ኃጢአታችንን ይቅር ሊለንና ከኃጢአታችን ሊያነጻን አይችልምን?”
በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እናንተ እንዴት ምላሽ ትሰጡ ነበር? ይህንን ለጓደኛችሁ እንዴት ታብራራላችሁ? ልጆች እና ወጣቶች፡ በኋላ ላይ እባካችሁ ወላጆቻችሁን ወይም መሪያችሁን “ኢየሱስ ለምን መሞት አስፈለገው?” ብላችሁ ጠይቋቸው። እናም ወንድሞች እና እህቶች፣ የምናዘዘው አለኝ፦ ምንም እንኳን ስለቤተክርስትያኗ ትምህርት፣ ታሪክ፣ ፖሊሲ እና ሌሎችንም አውቃለሁ ብዬ ባስብም በጊዜው የዚህ የእምነታችን ማዕከላዊ ጥያቄ መልስ በቀላሉ አልመጣልኝም። በዚያች ቀን፣ ለዘለአለማዊ ህይወት በጣም አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ የበለጠ ለማተኮር ወሰንኩ።
እንግዲህ ለአዲሷ ጓደኛዬ1 ከአካል በተጨማሪ መንፈስ እንዳለን እና እግዚአብሔር የመንፈሳችን አባት እንደሆነ2 አሳወኳት። ወደዚህ ምድር ከመወለዳችን በፊት ከሰማይ አባታችን ጋር እንደኖርን ነገርኳት።3 እርሱ እርሷን እና ልጆቹን ሁሉ ስለሚወዳቸው፣ እኛን በተከበረው አካሉ አምሳል አካልን እንድንቀበል4፣ የቤተሰብ አካል እንድንሆን5 እና እርሱ እንዳደረገው ከቤተሰቦቻችን ጋር በዘለአለም ህይወት እንድንደሰት6 እና ወደ እርሱ የፍቅር ህልውና እንድንመለስ እቅድ አዘጋጅቶልናል።7 ነገር ግን በዚህ ፈጽሞ በወደቀ ዓለም ውስጥ ሁለት ዋና ዋና መሰናክሎች ያጋጥሙናል በማለት ተናገርኩ፦ (1) አካላዊ ሞት—ሰውነታችን ከመንፈሳችን መለየት።8 በእርግጥ ሁላችንም እንደምንሞት ታውቃለች። እና (2) መንፈሳዊ ሞት—ኃጢአታችን፣ ስህተታችን፣ እና እንደ ሟች እንከኖቻችን ከቅዱስ ህልውናው ስለሚያርቁን ከእግዚአብሔር መለየት።9 እሷም ይህን ተረዳች።
ይህ የፍትህ ህግ ውጤት መሆኑን አሳወቅኳት። ይህ ዘለአለማዊ ህግ ለእያንዳንዱ ኃጢያታችን ወይም የእግዚአብሔርን ህግጋት ወይም እውነት መጣስ ዘለአለማዊ ቅጣት እንዲከፈለን ይጠይቃል፣ አለበለዚያ በቅዱስ መገኘቱ ውስጥ ለመኖር ልንመለስ ፈጽሞ አንችልም።10 ይህ ፍትሃዊ አይደለም፤ አምላክም “ፍትህን መካድ አይችልም”።11 ይህንን ተረድታለች ነገር ግን እግዚአብሔር መሐሪ፣ አፍቃሪ እና የዘለአለም ህይወታችንን ለማምጣት የሚጓጓ መሆኑን በቀላሉ ተረዳች።12 ተንኮለኛ፣ ኃይለኛ፣ የክፋት እና የውሸት ምንጭ ጠላት እንደሚቃወመን ለጓደኛዬ አሳወቅኳት።13 ስለዚህ፣ እነዚህን ሁሉ ተቃውሞዎችና መሰናክሎች ለማሸነፍ ማለቂያ የሌለው አምላካዊ ኃይል ያለው ሰው ሊያድነን ይገባል።14
ከዚያም መልካሙን ዜና አካፈልኳት—“ለህዝቡ ሁሉ የሚሆን …የምስራች”15—“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለአለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”16 ለጓደኛዬ እንደመሰከርኩት ለእናንተም ኢየሱስ ክርስቶስ ያ አዳኝ፣ እንደተሰቃየ፣ እንደሞተ፣ እና ከሞት እንደተነሳ፣ እንዲሁም በወሰን የለሽ የኃጢያት ክፍያው የሰው ልጆችን ሁሉ ከሥጋዊ ሞት ለመዋጀት17 ከእግዚአብሔር እና ከቤተሰቦቻችን18 ጋር እርሱን ለሚከተሉ ሁሉ የዘለአለም ህይወትን እንደሚሰጥ እመሰክራለሁ። ። መፅሐፈ ሞርሞን እንዲህ ይላል፣ “በሞት ላይ ድልን በማግኘት፣ ለሰው ልጆች እንዲማልድ ለወልድ ኃይልን በመስጠት፤ እንደዚህም እግዚአብሔር … ለሰዎች ልጆች [በፍትህ እና] በበርህራሄ ይሞላል፣ የሞትን እስር በመበጣጠስ፣ በራሱም ላይ ክፋታቸውንና መተላለፋቸውን በማድረግ፣ … የፍትህን ፍላጎት አሟልቷል።”19
እግዚአብሔር የገለጠው ኢየሱስን ለመከተል እና የዘለአለምን ህይወት ለመቀበል ልንወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች የክርስቶስ ትምህርት ይባላሉ። እነሱም “በኢየሱስ ክርስቶስ እና በኃጢያት ክፍያው ማመን፣ ንስሃ መግባት፣ መጠመቅ [ወደ ኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን]፣ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መቀበል እና እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናትን ያካትታሉ።20 እነዚህን እርምጃዎች ለጓደኛዬ አካፍያለሁ፣ ነገር ግን ነቢያት እና ሐዋርያት የክርስቶስ ትምህርት የእግዚአብሔርን ልጆች እንዴት እንደሚባርክ በቅርቡ ያስተማሩባቸው አንዳንድ መንገዶች እዚህ አሉ።
ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፦ “ንጹህ የክርስቶስ ትምህርት ሃያል ነው። የሚረዳውን እና በእርሱ ወይም በእርሷ ህይወት ላይ ለመተግበር የሚሻን ሰው ሁሉ ህይወት ይቀይራል።”21
ሽማግሌ ዲተር ኤፍ. ኡክዶርፍ፣ “የለወጣቶች ጥንካሬ [መመሪያ] የክርስቶስን ትምህርት በማወጅ [እና] እናንተ [ወጣቶች] [በእሱ] ላይ የተመሰረቱ ምርጫዎች እንድታደርጉ ይጋብዛል” በማለት አስተምረዋል።22
ሽማግሌ ዴል ጂ. ሬንለንድ፣ “ሚስዮናውያን የሚያስተምሯቸውን ሰዎች እንዲተገብሩ የሚጠይቋቸውን ነገሮች ራሳቸውም እንዲተገብሩ እንጋብዛቸዋለን፦ ይኸውም የክርስቶስን ትምህርት በህይወታቸው ውስጥ እንዲተገብሩ እና በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ እንዲቆዩ ነው” 23 በማለት ተናግረዋል።
የክርስቶስ ትምህርት በችግር ላይ ላሉት ወይም በቤተክርስቲያን ውስጥ ቦታ እንደሌላቸው ለሚሰማቸው ኃይል ይሰጣቸዋል ምክንያቱም ሽማግሌ ዲ ቶድ. ክርስቶፈርሰን እንደተናገሩት “ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ሞቷል [እናም] ይወደኛል” በማለት እንዲያረጋግጡ ስለሚረዳቸው ነው።24
ወላጆች፣ ልጃችሁ ከወንጌል መርህ ወይም ትንቢታዊ ትምህርት ጋር ችግር ካላቸው፣ እባካችሁ ማንኛውንም አይነት ክፉ ነገር መናገርን ወይም ስለቤተክርስቲያኗ ወይም ስለመሪዎቿ የሚደረግ ማነሳሳትን አቁሙ።25 እነዚህ አናሳ፣ ዓለማዊ አካሄዶች ከደረጃችሁ በታች ናቸው እናም በልጃችሁ የረጅም ጊዜ ታማኝነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣሉ።26 ውድ ልጃችሁን መጠበቃችሁ ወይም ለእነሱ መሟገታችሁ ወይም ከእሱ ወይም ከእርሷ ጋር የአብሮነት ምልክቶችን ማሳየታችሁ ስለእናንተ በጣም ጥሩ ነገር ይናገራ። ነገር ግን ባለቤቴ ጄን እና እኔ ከግል ተሞክሮ የምናውቀው ለምትወዱት ልጃችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ለምን ሁላችንም አጥብቀን እንደምንፈልግ እና አስደሳች ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን ማስተማር እሱን ወይም እሷን እንደሚያበረታ እና እንደሚፈውስ ነው። በአብ ዘንድ እውነተኛ ጠበቃቸው ወደሆነው ወደ ኢየሱስ እንመልሳቸው። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዳስተማረው፣ “… በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።” ከዚያም “ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ” እንድንጠነቀቅ ይነግረናል።27
በቅርቡ እኔና ጄን፣ ሙሴ የናሱን እባብ በተቅበዘበዙት የእስራኤል ልጆች ፊት የዘረጋበትን ምድረ በዳ ጎበኘን። ጌታ በመርዛማ እባቦች የተነደፉት ሁሉ በቀላሉ ቢመለከቱት እንደሚፈውሳቸው ቃል ገብቶ ነበር።28 የጌታ ነቢይ የክርስቶስን ትምህርት በፊታችን በመያዝ “ህዝብ[ን] ለመፈወስ ይችል ዘንድ” እያደረገ ነው።29 በዚህ አለም ምድረ በዳ ውስጥ ምንም አይነት ንክሻ ወይም መርዝ ወይም ተጋድሎ ቢያጋጥመን፣ ጥንት እና በአሁኑ ጊዜ እንደሚፈውሳቸው ባለማመናቸው ስላልተመለከቱ በሚያሳዝን ሁኔታ ሊፈወሱ እንዳልቻሉ ሰዎች አንሁን።30 መፅሐፈ ሞርሞን “እነሆ…መንገዱ ይህ ነው፤ ሰው በእግዚአብሔር መንግስት መዳን የሚችልበት ከሰማይ በታች የተሰጠ ሌላ ምንም መንገድም ሆነ ስም የለምና። አሁንም እነሆ፣ ይህ የክርስቶስ ትምህርት ነው” በማለት ያረጋግጣል።31
በዚያ ምሽት በኒው ጀርዚ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን እንደሚያስፈልገን እና ትምህርቱን ለማካፈል ለእኔ አዲስ እህት ለእሷ ደግሞ አዲስ ወንድም ሰጣት። ሰላማዊ፣ የመንፈስ ቅዱስ የማረጋገጫ ምስክርነት ተሰማን። የምትገኝበትን መረጃዋን እንድታካፍል እና ከሚስዮናውያን ጋር ውይይቱን እንድትቀጥል ጋበዝኳት። ይህን ለማድረግ ደስተኛ ነበረች።
እስራኤልን በሁሉም ማህበረሰባችን እና ቤተሰባችን ውስጥ ስንሰበስብ ለመውደድ፣ ለመካፈል እና ለመጋበዝ32 “በቅዱስ መሲህ መልካም ስራ እና ምህረትና ጸጋ [እና አስተምሮት] በስተቀር፣ በእግዚአብሄር ፊት ማንም ስጋ ሊኖር እንደማይችል ያውቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች ለምድር ነዋሪዎች እንዲያውቁት ማድረግ እንዴት ታላቅ ነገር ነው”33 በማለት መፅሐፈ ሞርሞን ያውጃል። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።