ምዕራፍ ፲፪
ኔፊ የቃልኪዳኑን ምድር፣ የነዋሪዎችዋን ጻድቅነት፣ ኃጢያት እና ጥፋትን፤ የእግዚአብሔርን በግ በእነርሱ መካከል መምጣትን፤ አስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት እና አስራ ሁለቱ ሐዋርያት እስራኤልን እንዴት እንደሚፈርዱ፣ እና በእምነት ማጣት የመነመኑትን አሰቃቂና መጥፎ ሁኔታ በራዕይ አየ። ከ፮፻–፭፻፺፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ መልአኩ እንዲህ አለኝ፥ ተመልከት፣ እነሆ ያንተን ዘሮች፣ ደግሞም የወንድሞችህን ዘሮች እይ። እኔም ተመለከትኩና የቃል ኪዳንን ምድር አየሁ፤ አዎን፣ ቁጥራቸው እንደባህር አሸዋ እንደሆነ ያህል ብዛት ያላቸውን ህዝቦች ተመለከትኩ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ ብዛት ያላቸው ህዝቦች እርስ በእርስ ለመዋጋት በአንድነት ተሰባስበው አየሁ፤ እናም በህዝቦቼ መካከል ጦርንና የጦር ወሬን፣ እና በጎራዴ ታላቅ የሆኑ ግድያዎችን አየሁ።
፫ እናም እንዲህ ሆነ በፀብና በጦርነት ሁኔታ ውስጥ በምድሪቱ ብዙ ትውልድ ሲያልፍ አየሁ፤ እናም፣ አዎን፣ ብዙ ያልቆጠርኳቸውን ከተማዎችን እንኳን ተመለከትኩ።
፬ እናም እንዲህ ሆነ በቃልኪዳኑ ምድር ላይ የጨለማ ጭጋግን ተመለከትኩ፤ መብረቅንም አየሁ፣ የነጎድጓድንም ድምፅ፣ የመሬት መንቀጥቀጥና የተለያዩ አሰቃቂ የሆኑ ድምፆችን ሁሉ ሰማሁ፤ ምድርና አለቶች ሲሰነጠቁም አየሁ፤ ተራሮች እየተሸረፉ ሲንከባለሉም አየሁ፣ ለጥ ያሉ የምድር ሜዳዎች ሲሰባበሩም አየሁ፤ የሰመጡ ብዙ ከተሞችም አየሁ፣ በእሳት የተቃጠሉ ብዙዎችንም አየሁ፤ በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የፈረሱ ብዙዎችንም አየሁ።
፭ እናም እንዲህ ሆነ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ካየሁ በኋላ፣ የጨለማ ጭጋግ ከምድር ገፅ ሲጠፋ አየሁ፣ እናም እነሆ በጌታ ታላቅና አስፈሪ ፍርድ ምክንያት ያልጠፉ ብዙዎችን ተመለከትኩ።
፮ እናም ሰማያት ሲከፈቱና የእግዚአብሔር በግ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፣ እርሱም ወረደና እራሱን አሳያቸው።
፯ እናም መንፈስ ቅዱስ በሌሎች አስራ ሁለት ላይ እንደወረደም ተመለከትኩም፣ እመሰክራለሁም፤ እነርሱም በእግዚአብሔር የተሾሙና የተመረጡ ነበሩ።
፰ እናም መልአኩ እንዲህ ሲል ተናገረኝ—እነሆ የአንተን ዘር እንዲያገለግሉ የተመረጡትን አስራ ሁለቱን የበጉን ደቀመዛሙርት ተመልከት።
፱ እናም እርሱ እንዲህ አለኝ—የበጉን አስራ ሁለት ሐዋሪያት ታስታውሳለህን? እነሆ የእስራኤል አስራ ሁለቱን ነገዶች የሚፈርዱት እነርሱ ናቸው፤ ስለዚህ እናንተ ከእስራኤል ቤት ናችሁና አስራ ሁለቱ የዘርህ አገልጋዮች በእነርሱ ይፈረዳሉ።
፲ እናም ያየሀቸው እነዚህ አስራ ሁለቱ አገልጋዮች በዘርህ ላይ ይፈርዳሉ። እናም እነሆ ለዘለዓለም ፃድቃን ናቸው፤ በእግዚአብሔር በግ ባላቸው እምነት ምክንያት ልብሳቸው በደሙ ነፅቶአልና።
፲፩ መልአኩም አለኝ—ተመልከት! እኔም ተመለከትኩ፣ እናም እነሆ ሶስት ትውልዶች በፅድቅ ሲያልፉ ተመለከትኩ፤ ልብሳቸውም እንደ እግዚአብሔር በግ ነጭ ነበር። መልአኩም አለኝ—እነዚህ በእርሱ ባላቸው እምነት ምክንያት በበጉ ደም ነፅተዋል።
፲፪ እናም እኔ ኔፊ ደግሞ በፅድቅ ያለፉትን የአራት ትውልዶች ብዙዎችን ተመለከትኩ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ የምድር ብዙዎች በአንድ ላይ ተሰብስበው አየሁ።
፲፬ መልአኩም እንዲህ አለኝ—ዘርህን፣ እንዲሁም ደግሞ የወንድሞችህን ዘሮች ተመልከት።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ እነሆ የእኔ ዘር የሆኑትን በብዛት በወንድሞቼ ዘር ላይ በአንድ ላይ ተሰብስበው ተመለከትኩ፣ እናም እነርሱ በአንድ ላይ ለመዋጋት ተሰብስበው ነበር።
፲፮ መልአኩምም እንዲህ ብሎ ተናገረኝ—እነሆ አባትህ ያየው መጥፎ ውሃ ምንጭ፣ አዎን፣ የተናገረው ወንዙ፤ የእዚህም ጥልቀት እንደ ሲኦል ጥልቅ ነው።
፲፯ ዐይኖችንም የሚያሳውሩና የሰው ልጆችን ልብ የሚያጠጥሩ፣ እና እንዲስቱና እንዲጠፉ ወደ ሰፊው ጎዳና እነርሱን የሚመሩ የጨለማው ጭጋጋት የዲያብሎስ ፈተናዎች ናቸው።
፲፰ እናም አባትህ ያየው ትልቁና ሰፊው ህንፃ የሰው ልጆች ከንቱ ሀሳብና ኩራት ነው። እናም ትልቅ አስፈሪ ገደል፣ አዎን፣ እንዲሁም የዘለዓለማዊው አምላክ ፍትህ ቃል፣ መንፈስ ቅዱስ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁንና፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለዘለአለም የሚመሰክርለት፣ የእግዚአብሔር በግ የሆነው መሲህ ይለያቸዋል።
፲፱ መልአኩም እነዚህን ቃላት ሲናገር፣ መልአኩ ይሆናሉ ብሎ እንደተናገረው የወንድሞቼ ዘር ከእኔ ዘር ጋር ሲቃረን አየሁ፤ በእኔ ዘር ኩራትና በዲያብሎስ ፈተናዎች ምክንያት የወንድሞቼ ዘር የእኔን ዘር ህዝቦች ሲያሸንፉ አየሁ።
፳ እናም እንዲህ ሆነ የእኔን ዘር ያሸነፉትን የወንድሞቼን ዘር ህዝቦች ተመለከትኩ፣ አየሁም፤ እነርሱም በምድር ላይ በብዛት ሆነው ሄዱ።
፳፩ እናም እነርሱ በብዛት በአንድ ላይ ተሰብስበው ተመለከትኩ፤ በእነርሱም መካከል ጦርነትና የጦርነት ወሬዎችን ተመለከትኩ፤ በጦርነትና በጦርነት ወሬዎችም ብዙ ትውልዶች ሲያልፉ ተመለከትኩ።
፳፪ እናም መልአኩ እንዲህ አለኝ—እነርሱ እምነት በማጣት ይመነምናሉ።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ እነሆ እነርሱ እምነት በማጣት ከመነመኑ በኋላ ስራፈትና በሁሉም አይነት ርኩሰቶች የተሞሉ፣ የጠቆሩና፣ አፀያፊና መጥፎ ሰዎች ሆኑ።