ምዕራፍ ፲፪
አቢናዲ የህዝቡን ጥፋትና የንጉስ ኖህን ሞት በመተንበዩ ታሰረ—የሀሰት ካህናት ቅዱስ መፅሐፍትን ጠቀሱ እናም የሙሴንም ህግ ለመጠበቅ አስመሰሉ—አቢናዲ እነርሱን አስርቱን ትዕዛዛት ማስተማር ጀመረ። በ፻፵፰ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ ከሁለት ዓመታት በኋላ አቢናዲ እንዳያውቁት ሆኖ በመካከላቸው ተደብቆ መጣ፣ እናም እንዲህ በማለት በመካከላቸው መተንበይ ጀመረ፥ ጌታ እንዲህ ሲል አዞኛል—አቢናዲ ወደ ህዝቦቼ ሂድና ተንብይ፣ በእኔ ቃላት ላይ ልባቸውን አጠጥረዋልና፤ ለመጥፎ ስራቸው ንስሃ አልገቡም፤ ስለዚህ፣ በቁጣዬ እጎበኛቸዋለሁ፣ አዎን በኃይለኛው ቁጣዬ በክፋታቸውና በእርኩሰታቸው ምክንያት እጎበኛቸዋለሁ።
፪ አዎን፣ ለዚህ ትውልድ ወዮለት! እናም ጌታም አለኝ፥ እጅህን ዘርጋና እንዲህ ብለህ ተንብይ፥ ጌታ እንዲህ ይላል፣ እንዲህም ይሆናል፣ ይህ ትውልድ በጥፋቱ የተነሳ ወደ ባርነት ይወሰዳል፣ ጉንጩንም ይመታል፤ አዎን በሰዎች ይነዳልም ይገደላልም፣ እናም የሰማይ ጥንብ አንሳዎችና፣ ውሾች፣ አዎን፣ የዱር አራዊቶችም ሥጋቸውን ይቀረማመቱታል።
፫ እናም እንዲህ ይሆናል፣ የንጉስ ኖህ ህይወት እሳት ውስጥ እንደገባ ጨርቅ ይሆናል፤ እኔ ጌታ መሆኔን ያውቃልና።
፬ እናም እንዲህ ሆነ ይህን የኔፊን ህዝብ በታላቅ ስቃይ እመታዋለሁ፣ አዎን፣ በረሃብና በቸነፈር፤ እናም ቀኑን ሙሉ እንዲያለቅሱ አደርጋለሁ።
፭ አዎን፣ እናም በትከሻቸው ሸክም እንዲሸከሙ አደርጋለሁ፣ እናም አንደበት እንደሌለው አህያም ይነዳሉ።
፮ እናም እንዲህ ይሆናል በረዶን በመካከላቸው እልካለሁ፣ ይመታቸዋልም፤ እናም በምስራቅ ንፋስም ደግሞ ይመታሉ፤ ተምች ደግሞ ምድራቸውን ይወራሉ፣ እህላቸውንም ይጨርሳሉ።
፯ እናም በታላቅ ቸነፈር ይመታሉ—እናም ይህንን ሁሉ የማደርገው በክፋታቸውና በእርኩሰታቸው የተነሳ ነው።
፰ እናም እንዲህ ይሆናል፣ ንስሃ ካልገቡ በቀር ከምድር ገፅ አጠፋቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ ታሪካቸውን አስቀርተው ይሄዳሉ፣ እናም ምድሪቱን ለሚወርሱ ትውልድ አስቀምጥላቸዋለሁ፤ አዎን፣ ይህንንም የማደርገው የሌላው ሀገር የዚህን ህዝብ እርኩሰት እንዲያውቀው ነው። እናም አቢናዲ በዚህ ህዝብ ላይ ብዙ ነገሮችን ተንብዮአል።
፱ እናም እንዲህ ሆነ በእርሱ ተቆጥተው ነበር፤ እናም ወሰዱትና በንጉሱ ፊትም አስረው አቀረቡት፣ ለንጉሱም እንዲህ አሉት፥ እነሆ፣ ስለህዝብህ በክፉ የተነበየውን ሰው፣ እናም እግዚአብሔር እንደሚያጠፋቸው የሚናገረውን በፊትህ አምጥተናል።
፲ እናም ደግሞ ህይወትህን በሚመለከት ክፉን ነገር ተንብዮአል፤ እናም ህይወትህ በሚነደው እሳት ውስጥ እንደሚሆነው ጨርቅ እንደሚሆን ተናግሯል።
፲፩ እናም እንደገና፣ በአውሬዎች እንደተጨፈለቀና በእግራቸውም እንደተረገጠ አገዳ፤ የደረቅ ሜዳ አገዳ ትሆናለህ ሲል ተናግሯል።
፲፪ እናም በድጋሚ፣ ሙሉ በሙሉ በሚያብብበት ጊዜ ንፋሱም ከነፈሰ በምድሪቱ ላይ እንደሚበተን እንደኮሸሽላ አበባ ትሆናለህ ብሏል። ጌታም እንደተናገረ አስመሰለ። እናም ንስሃ ካልገባህ፣ ይህ ሁሉ በአንተ ላይ ይሆናል፣ ይህ የሆነውም በኃጢያትህ የተነሳ ነው ሲል ተናግሯል።
፲፫ እናም አሁን፣ ንጉስ ሆይ፣ አንተ ምን ያህል ክፉን ነገርን ሰርተሃል፣ ወይም ህዝብህስ ምን ያህል ታላቅ ኃጢያትን ፈፅሞአል፣ በእግዚአብሔርስ ዘንድ የምንኮነነው በዚህ ሰው የሚፈረድብን?
፲፬ እናም አሁን፣ ንጉስ ሆይ፣ እነሆ፣ እኛ ጥፋተኞች አይደለንም፣ እናም አንተ ንጉስ ሆይ ኃጢያትን አላደረግህም፤ ስለዚህ፣ ይህ ሰው አንተን በሚመለከት ዋሽቷልና፣ በከንቱ ተንብዮአል።
፲፭ እናም እነሆ፣ እኛ ጠንካሮች ነን፣ ወደ ባርነትም አንመጣም፣ ወይም በጠላቶቻችንም በምርኮ አንወሰድም፤ አዎን፣ አንተ በምድሪቱ በልፅገሃል እናም ደግሞ ትበለፅጋለህ።
፲፮ እነሆ ሰውየውም ይህ ነው፣ እርሱን በእጅህ አሳልፈን እንሰጥሀለን፤ መልካም እንደመሰለህ በእርሱ ላይ አድርግ።
፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ኖህ አቢናዲ ወደ ወህኒ እንዲጣል አደረገ፤ እናም ከእርሱ ጋር ምን ማድረግ እንዳለበት ምክር ለማድረግ ካህናት ከእርሱ ጋር እራሳቸውን በአንድነት እንዲሰበስቡ አዘዘ።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ ለንጉሱ እንዲህ አሉት፥ እኛ እንድንጠይቀው ዘንድ ወደዚህ አምጣው፤ እናም ከፊታቸው እንዲመጣም ንጉሱ አዘዘ።
፲፱ እናም ይቃረኑት ዘንድ፣ በዚህም እርሱንም ለመክሰስ ምክንያት ያገኙ ዘንድ መጠየቅ ጀመሩ፤ ነገር ግን በጉብዝና መለሰላቸውና፣ ጥያቄአቸውን በሙሉ ተቋቋማቸው፣ አዎን፣ እስከሚደንቃቸውም፤ ጥያቄአቸውን ሁሉ ተቋቋመ እናም በሁሉም ቃላቸው ዝም አስኛቸው።
፳ እናም እንዲህ ሆነ ከእነርሱ መካከል አንዱ እንዲህ አለው፥ አባቶቻችን ያስተማሯቸው እናም እንዲህ የሚሉት እነዚህ የተፃፉት ቃላት የሚሉት ምንድን ነው፤
፳፩ ሰላምን ያበሰረ፤ መልካም የሆነውን መልካም የምስራች ወሬ ያበሰረ፣ ደህንነትን ያወጀ፣ ለፅዮንም አምላካችሁ ነግሶአል! ያለው፣ መልካም የምስራች ይዞ የመጣው በተራራው ላይ ያለው እግሮቹ እንዴት ያማሩ ናቸው፤
፳፪ ጠባቂዎቻችሁ ጮክ ይላሉ፤ በአንድነት ድምፅ ይዘምራሉ፤ ጌታ ፅዮንን በድጋሚ ሲያመጣ ዐይን ለዐይን ይተያያሉና፤
፳፫ በደስታ በድንገት ውጡ፤ የፈራረሳችሁ የኢየሩሳሌም ቦታዎች በአንድነት ዘምሩ፤ ጌታ ህዝቡን አፅናንቷል፣ ኢየሩሳሌምን አድኗልና።
፳፬ ጌታ ቅዱስ ክንዶቹን በሀገሩ ዐይን ላይ ገልጧል፣ እናም የአለም ዳርቻዎች ሁሉ የአምላካችንን ማዳን ያያሉ?
፳፭ እናም አሁን አቢናዲ እንዲህ አላቸው፥ እናንተ ካህናት ናችሁን፣ እናም ይህን ህዝብ ለማስተማርና የትንቢትን መንፈስ የምትረዱ እያስመሰላችሁ፣ እናም ግን እነዚህን ነገሮች ምን ማለት እንደሆኑ ከእኔ ለማወቅ ትፈልጋላችሁን?
፳፮ እናም እንዲህ እላችኋለሁ የጌታን መንገድ ለምታጣምሙት ለእናንተ ወዮላችሁ! እነዚህን ነገሮች የምትረዱ ከሆናችሁ አታስተምሯቸውምና፤ ስለዚህ የጌታን መንገድ አጣምማችኋል።
፳፯ እናንተ ለመረዳት ልባችሁን አላዘጋጃችሁም፣ ስለዚህ፣ ብልህ አልነበራችሁም። ስለዚህ፣ ለዚህ ህዝብ ምን ታስተምራላችሁ?
፳፰ እናም እነርሱ፣ የሙሴን ህግ እናስተምራለን አሉ።
፳፱ እናም በድጋሚ እንዲህ አላቸው፥ የሙሴን ህግ ካስተማራችሁ ለምን እናንተስ አልጠበቃችሁትም? ለምንስ ልባችሁን በሀብት ላይ አደረጋችሁ? ለምንስ ዝሙትን ፈፀማችሁ፣ እንዲሁም ከጋለሞታዎች ጋር ጉልበታችሁን አባከናችሁ፣ ስለዚህም ጌታ በዚህ ህዝብ ላይ፣ አዎን እንዲያውም ታላቅ ክፋት በዚህ ህዝብ ላይ እንድተነብይ እስኪልከኝ፣ አዎን፣ እናም ይህን ህዝብ ኃጢያት እንዲፈፅም አደረጋችሁ?
፴ እውነትን እንደምናገር አታውቁምን? አዎን፣ እኔ እውነትን እንደምናገር ታውቃላችሁ፤ እናም በጌታ ፊት መንቀጥቀጥ አለባችሁ።
፴፩ እናም እንዲህ ይሆናል በኃጢአታችሁ የተነሳ ትመታላችሁ፣ ምክንያቱም የሙሴን ህግ እናስተምራለን ብላችኋልና። እናም ስለሙሴ ህግስ ምን ታውቃላችሁ? ደህንነት በሙሴ ህግ አማካኝነት ይመጣልን? እናንተ ምን ትላላችሁ?
፴፪ እናም ደህንነት በሙሴ ህግ አማካኝነት ይመጣል ብለው መለሱ።
፴፫ ነገር ግን አሁን አቢናዲ እንዲህ አላቸው፥ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ብትጠብቁ እንደምትድኑ አውቃለሁ፤ አዎን፣ በሲና ተራራ ጌታ እንዲህ ሲል ለሙሴ የሰጠውን ህግ ብትጠብቁ፥
፴፬ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ፣ ከባርነት ቤት ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።
፴፭ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አይኑራችሁ።
፴፮ በላይ በሰማይ ካለው፣ በታች በምድር ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረፀውን ምስል ለእናንተ አታድርጉ።
፴፯ አሁን አቢናዲ እንዲህ አላቸው፥ ይህንን ሁሉ አድርጋችኋልን? አላደረጋችሁም እላችኋለሁ። እናም ይህ ህዝብ ይህንን ሁሉ ነገር እንዲያደርግ አስተምራችኋልን? እኔ አላደረጋችሁም እላችኋለሁ።