ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፳፩


ምዕራፍ ፳፩

የሊምሂ ህዝብ በላማናውያን ተመቱ እናም ተሸነፉ—የሊምሂ ህዝብ አሞንን አገኙ፣ እናም ተለወጡ—ለአሞን ስለሃያ አራቱ የያሬዳውያን ሰሌዳዎች ነገሩት። ከ፻፳፪–፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ሊምሂና ህዝቡ ወደ ኔፊ ከተማ ተመለሱና፣ በምድሪቱ ላይ እንደገና በሰላም መኖር ጀመሩ።

እናም እንዲህ ሆነ ከብዙ ቀናት በኋላ ላማናውያን በኔፋውያን ላይ በድጋሚ በቁጣ ተነሳሱና፣ በዙሪያው ወዳለው ምድር ድንበር መምጣት ጀመሩ።

አሁን ንጉሱ ለሊምሂ በመማሉ ምክንያት ሊገድሏቸው አልደፈሩም፤ ነገር ግን በጉንጮቻቸው ላይ መቱአቸው፣ እናም ስልጣናቸውን ተጠቀሙባቸው፤ እናም በትከሻቸው ከባድ ሸክም አስቀመጡባቸውና እንደደንቆሮ አህያ ይነዱአቸው ጀመር—

አዎን፣ ይህ ሁሉ የሆነው የጌታ ቃል ይፈፀም ዘንድ ነበር።

እናም አሁን የኔፋውያን ስቃይ ታላቅ ነበር፣ እናም ላማናውያን በሁሉም አቅጣጫ ስለከበቡአቸው ከእጃቸው የሚያስለቅቁበት ምንም መንገድ አልነበረም።

እናም እንዲህ ሆነ በስቃያቸው ምክንያት ህዝቡ በንጉሱ ላይ አቤቱታ ማቅረብ ጀመሩ፤ ከእነርሱም ጋር እንደገናም ለመዋጋት ፈለጉ። እናም በአቤቱታቸው ንጉሱን በአስከፊ ሁኔታ አሰቃዩት፤ ስለዚህ እነርሱም እንደፍላጎታቸው እንዲያደርጉ ፈቀደላቸው።

እናም በድጋሚ ተሰባሰቡና፣ መሳሪያዎቻቸውን ታጠቁ፣ እናም ላማናውያኖችን ከምድራቸው ለማባረር ወደ እነርሱ ሄዱ።

እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን መትተው መለሱአቸውና፣ ብዙዎቻቸውን ገደሉአቸው።

እናም አሁን በሊምሂ ህዝብ መካከል ታላቅ ልቅሶና ዋይታ ነበር፤ ባሏ የሞተባት ለባሏ አለቀሰች፣ ሴትና ወንድ ልጆች ለአባታቸው አለቀሱ፣ እናም ወንድሞች ለወንድሞቹ አዘነ።

አሁን በምድሪቱ ብዙ ባልቴቶች ነበሩ፣ እናም ከቀን ወደ ቀንም በኃይል ያለቅሱ ነበር፣ ታላቅ የሆነ የላማናውያን ፍርሃት በእነርሱ ላይ መጥቶ ነበርና።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ የማያቋርጠው ጩኸታቸው ቀሪዎቹን የሊምሂን ህዝብ በላማናውያኖች ላይ እንዲቆጡ አወካቸው፣ እናም በድጋሚ ለውጊያ ሄዱ፣ ነገር ግን በድጋሚ ተከላክለው መለሱአቸው፣ ብዙ ህይወት ጠፋባቸው።

፲፪ አዎን፣ ለሶስተኛ ጊዜ በድጋሚ ሄዱ፣ እንደገናም እንደዚያው ሆነባቸው፤ እናም ያልተገደሉት በድጋሚ ወደ ኔፊ ከተማ ተመለሱ።

፲፫ እናም ትቢያ እስኪሆኑ ድረስ እራሳቸውን ዝቅ አደረጉ፣ እናም እንደጠላቶቻቸው ፍላጎት ወዲህና ወዲያ እንዲወስዱአቸውና እንዲያሸክሙአቸው እራሳቸውን ወደ ባርነት ቀንበር በማስገደድ እንዲቀጡ እራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ።

፲፬ እናም እስከ ጥልቅ ትህትና ድረስ ራሳቸውን ትሁት አደረጉ፤ እናም ወደ እግዚአብሔር በኃይል ጮሁ፤ አዎን፣ ከስቃያቸው ያስለቅቃቸው ዘንድ ቀኑን ሙሉ ወደአምላካቸው ጮኸዋል።

፲፭ እናም አሁን በክፋታቸው የተነሳ ጌታ ጩኸታቸውን ለማዳመጥ ዘግይቷል፤ ይሁን እንጂ፣ ጌታ ፀሎታቸውን ሰምቷል፣ ሸክማቸውንም ማቃለል እንዲጀምሩ የላማናውያንን ልብ ማራራት ጀመረ፤ ይሁን እንጂ ጌታ ከባርነት እነርሱን የማዳኑ አስፈላጊነት ውሳኔው ላይ አላደረሰም።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ቀስ በቀስ መበልፀግ ጀመሩ፣ እናም በርሃብ እንዳይሰቃዩ እህልና መንጋዎችን እና ተክሎችን በብዛት ማምረት ጀመሩ።

፲፯ አሁንም ከወንዶቹ የሚበልጡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ነበሩ፣ ስለዚህ ንጉስ ሊምሂ ባሎቻቸው ለሞቱባቸውና ለልጆቻቸው በረሃብ እንዳይጠፉ ማንኛውም ሰው እነርሱን ለመደገፍ ያለውን እንዲያካፍል አዘዘ፤ እናም ይህን ያደረገው የተገደሉት ቁጥራቸው ብዙ በመሆኑ ነበር።

፲፰ አሁን የሊምሂ ህዝቦች እስከሚቻላቸው ድረስ በአንድነት በቡድን ተጠጋግተው፣ እናም እህሎቻቸውና መንጋዎቻቸውን ይጠብቃሉ፤

፲፱ እናም ንጉሱ ራሱ፤ በዘዴ በላማናውያን እጅ እወድቃለሁ በማለት ይፈራ ስለነበር፣ ጠባቂዎቹን ካልወሰደ በቀር ከከተማው ግንብ ውጪ የራሱን ደህንነት አያምንም።

እናም የላማናውያን ሴት ልጆችን የሰረቁትንና ታላቅ ጥፋት በእነርሱ ላይ እንዲመጣ ያደረጉትን፣ ወደ ምድረበዳው የሸሹትን ካህናት በዘዴም ይወስዷቸው ዘንድ ህዝቡ በዙሪያው ያለውን ምድር እንዲጠብቅ አደረገ።

፳፩ ይቀጡአቸው ዘንድ ፍላጎት ነበራቸውና፤ በምሽትም ወደ ኔፊ ምድር መጥተዋልና እናም እህሎቻቸውንና ብዙ የከበሩ ነገሮቻቸውን ወስደዋልና፣ ስለዚህም እነርሱን አድፍጠው ጠበቁአቸው።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ፣ አሞንና ወንድሞቹ ወደ ምድሪቱ እስኪመጡ ድረስ፣ በላማናውያንና በሊምሂ ህዝብ መካከል ምንም ረብሻ አልነበረም።

፳፫ እናም ንጉሱ ከጠባቂው ጋር ከግንቡ ውጪ በሆነበት ጊዜ፣ አሞንንና ወንድሞቹን አገኘና፣ የኖህ ካህን ናቸው ብሎም ገመተ፣ ስለዚህ እንዲወሰዱና፣ በገመድ እንዲታሰሩ እናም ወደ ወህኒ ቤት እንዲጣሉ አደረገ። እናም የኖህ ካህናት ቢሆኑ ኖሮ እንዲሞቱ ያደርግ ነበር።

፳፬ ነገር ግን እንዳልሆኑ፣ ነገር ግን የእርሱ ወንድሞች መሆናቸውን እናም ከዛራሄምላ ምድር እንደመጡ ባወቀ ጊዜ፣ እጅግ ታላቅ በሆነ ደስታ ተሞልቶ ነበር።

፳፭ አሁን ንጉስ ሊምሂ አሞን ከመምጣቱ በፊት የዛራሄምላን ምድር እንዲፈልጉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ልኮ ነበር፣ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም ነበር፣ እናም በምድረበዳ ውስጥ ጠፍተው ነበር።

፳፮ ይሁን እንጂ፣ በህዝብ የነበረበት ምድር፣ አዎን፣ በደረቅ አጥንት የተሸፈነ ምድር፣ አዎን፣ በህዝብ የተሞላና የጠፋ ምድር አገኙ፤ እናም የዛራሄምላ ምድር ነው ብለው በመገመት ወደ ኔፊ ምድር ተመለሱ፣ ወደ ምድሪቱም ዳርቻ አሞን ከመምጣቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ደረሱ።

፳፯ እናም ከእነርሱም ጋር መዝገቡን፣ እንዲሁም አጥንታቸውን ያገኙትን ህዝብ መዝገብን አመጡ፤ እናም ሰሌዳውም የተቀረፀው በብረት አፈር ነበር።

፳፰ እናም አሁን ሊምሂ የተቀረፁትን ለመተርጎም ንጉስ ሞዛያ ከእግዚአብሔር ስጦታ እንዳለው ከአሞን አንደበት በማወቁ በድጋሚ ተደሰተ፤ አዎን፣ እናም አሞን ደግሞ ተደሰተ።

፳፱ ይሁን እንጂ ብዙዎች ወንድሞቻቸው ስለተገደሉባቸው አሞንና ወንድሞቹ በሃዘን ተሞልተው ነበር።

እናም ደግሞ ንጉስ ኖህና ካህናቱ ህዝቡ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢያትና ክፋት እንዲፈፅም አድርገው ነበር፤ ደግሞም በአቢናዲ ሞት አዘኑ፤ እናም ደግሞ በአልማና በእግዚአብሔር ኃይልና ጥንካሬ እናም አቢናዲ በተናገረው ቃል ባላቸው እምነት የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን በመሰረቱት ሰዎች መሄድ አለቀሱ።

፴፩ አዎን፣ ወዴት እንደሸሹ አላወቁምና ለሽሽታቸው አለቀሱ። አሁን እራሳቸውም ከእግዚአብሔር ጋር እርሱን ለማገልገልና ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ ቃል ኪዳን ስለገቡ፣ ከእነርሱ ጋር በደስታ ይቀላቀሉ ነበር።

፴፪ እናም አሁን አሞን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ንጉስ ሊምሂ፣ እናም ደግሞ ብዙዎች ህዝቦቹ እርሱን ለማገልገልና ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገብተዋል።

፴፫ እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ሊምሂና ብዙዎች ህዝቦቹ ለመጠመቅ ፈለጉ፤ ነገር ግን በምድሪቱ ከእግዚአብሔር ስልጣን የተሰጠው አንድም አልነበረም። እናም አሞን ይህን ነገር እራሱን ብቁ አገልጋይ አይደለሁም በማለት ለመፈፀም አልፈቀደም።

፴፬ ስለዚህ የጌታን መንፈስ በመጠበቅ፣ በዚያን ጊዜ ለራሳቸው ቤተክርስቲያን አላቋቋሙም ነበር። አሁን ወደ ምድረበዳው እንደሸሹት እንደ አልማና እንደ ወንድሙ መሆን ፈልገው ነበር።

፴፭ በፍፁም ልባቸው እግዚአብሔርን ለማገልገል ፈቃደኛ እንደሆኑ እንደምስክር እና አማኝ ለመጠመቅ ፈለጉ፣ ይሁን እንጂ ጊዜአቸውን አራዘሙ፣ የጥምቀታቸው ታሪክ ከዚህ ቀጥሎ ይቀርባል

፴፮ እናም አሁን የአሞንና የህዝቡ እናም የንጉስ ሊምሂና የህዝቡ ዕቅድ እራሳቸውን ከላማናውያን እጅና ከባርነት ማስለቀቅ ነበር።