“ማርቲን ሀርስ ጆሴፍ ስሚዝን ረዳው፣” የትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ታሪኮች [2024 (እ.አ.አ)]
“ማርቲን ሀርስ ጆሴፍ ስሚዝን ረዳው፣” ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ታሪኮች
1828–1829 (እ.አ.አ)
ማርቲን ሀሪስ ጆሴፍን ረዳው
ጌታን ማመንን መማር
አንድ ቀን ጆሴፍና ኤማ በፔንሰልቬንያ ይኖሩ በነበረበት ወቅት ማርቲን ሃሪስ የተባለ ጓደኛ እነርሱን ሊጠይቃቸው መጣ። ማርቲን ኒው ዮርክ ውስጥ አንድ ትልቅ የእርሻ ቦታ ነበረው። ጆሴፍ በወርቅ ሰሌዳዎች ላይ የነበረውን ሥራ ያውቅ ነበር። ከዚህ በፊት ጆሴፍን ረድቶት ነበር እናም አሁን ደግሞ እሱን ለመርዳት ሊያደርገው የሚችል ተጨማሪ ነገር መኖሩን ማወቅ ፈልጎ ነበር።
ቅዱሳን፣ 1፥49
ጆሴፍና ኤማ አመስጋኞች ነበሩ። ብዙ ሰዎች ጆሴፍ እየዋሸ እንደነበር ያስቡ ነበር። የወርቅ ሰሌዳዎቹን እውነተኛነት የሚያምን እንደ ማርቲን ያለ ጓደኛ መኖር ጥሩ ነበር።
ቅዱሳን፣ 1፥49
ጆሴፍ ሰሌዳዎቹን ሲተረጉም ማርቲን የሚናገረውን ይፅፍ ነበር። ማርቲን ጌታን በዚህ ታላቅ ሥራ በመርዳቱ በጣም ተደስቶ ነበር።
ቅዱሳን፣ 1፥50
የማርቲን ሚስት ሉሲ ደስተኛ አልነበረችም። ጆሴፍ የወርቅ ሰሌዳዎች እንደነበሩት አላመነችም ነበር። ጆሴፍ ማርቲንን እያታለለው መስሏት ነበር። ማርቲን ወደ ኒው ዮርክ ተመልሶ ጆሴፍን መርዳት እንዲያቆም ፈለገች።
ቅዱሳን፣ 1፥149–50
ማርቲን ግን ከጆሴፍ ጋር መሥራቱን ቀጠለ። ሉሲ እየሠሩ ያሉትን ነገር ማንበብ ብትችል እሷም እንደምታምን አሰበ። ከዚያም የተተረጎሙትን ገጾች ወደ ኒው ዮርክ ወስዶ ለሚስቱ ማሣየት ይችል እንደሆነ ጆሴፍን ጠየቀ። ጆሴፍ በጸሎት እግዚአብሔርን እንደሚጠይቅ ነገረው።
ቅዱሳን፣ 1፥50–51
ማርቲን ገጾቹን እንዲወስድ እንዳይፈቅድለት እግዚአብሔር ለጆሴፍ ነገረው። ማርቲን፣ ጆሴፍን በድጋሚ እንዲጸልይ ጠየቀው። ጆሴፍ ጸለየ፣ እናም ተመሳሳይ መልስ አገኝ። ነገር ግን ማርቲን ገጾቹን ለሚስቱ ሊያሳያት በጣም ፈለገ እናም ጆሴፍ ጓደኛውን ለመርዳት ፈለገ። ጆሴፍ ለሦስተኛ ጊዜ ጸለየ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ጆሴፍ ምን ማድረግ እንዳለበት መወሰን እንደሚችል ነገረው።
ቅዱሳን፣ 1፥51
ጆሴፍ ማርቲን ገጾቹን ወደ ኒው ዮርክ መውሰድ እንደሚችል ነገረው ነገር ግን ሊያሳይ የሚችለው ለተወሰኑ የቤተሰቡ አባላት ብቻ እንደሆነ አስጠነቀቀው። ከዚያም ገጾቹን በሁለት ሳምንት ውስጥ መልሶ ማምጣት ነበረበት። ማርቲን በዚህ ሐሳብ ተስማማና ገጾቹን ይዞ ሄደ።
ቅዱሳን፣ 1፥51
ማርቲን ከሄደ በኋላ ጆሴፍና ኤማ አንድ ሕፃን ልጅ ወለዱ። ይሁን እንጂ ሕፃኑ ሞተ፤ ኤማም ታመመች። ኤማ እና ጆሴፍ በጣም አዘኑ።
ቅዱሳን፣ 1፥51–52
ጆሴፍ ስለ ኤማ ተጨነቀ። ጆሴፍ ስለ ማርቲንም ተጨነቀ። ሁለቱ ሳምንታት አለፉ፣ ማርቲን ግን አሁንም አልተመለሰም። ኤማም ተጨነቀች።
ቅዱሳን፣ 1፥52
ኤማ፣ ማርቲንን ለመፈለግ ወደ ኒው ዮርክ እንዲሄድ ለጆሴፍ ነገረችው። ጆሴፍ ማርቲንን በወላጆቹ ቤት አገኘው። ጆሴፍ ማርቲንን ስለ ገጾቹ ሲጠይቀው ማርቲን በጣም አዘነ። ገጾቹ ጠፍተዋል አለ። የትም ቦታ ቢፈልግ ሊያገኛቸው አልቻለም ነበር።
ቅዱሳን፣ 1፥52–53
ጆሴፍ በጣም አዘነ እንዲሁም ፈራ። ማርቲን ገጾቹን እንዲወስድ መፍቀዱ ስህተት እንደነበረ አወቀ። ወደ ቤት ተመልሶ በመሄድ ምን እንደተፈጠረ ለኤማ ነገራት። መልአኩ ሞሮኒ መጥቶ የወርቁን ሰሌዳዎች መልሶ ወሰደ። ጆሴፍ ትሁት ከሆነ እና ንስሐ ከገባ ሰሌዳዎቹን መልሶ ሊያገኛቸው እና እንደገና ሊተረጉማቸው እንደሚችል ነገረው።
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 3፥5–11፤ 10፥1–3፣ ቅዱሳን፣ 1፥53–54
ጆሴፍ ለበርካታ ሳምንታት፣ የሰራውን ስህተት እያሰላሰለ ቆየ። ጸልዮ ይቅርታን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ይቅር አለው። የእግዚአብሔርን ሥራ ለማስቆም ጥረት በሚያደርጉ ሰዎች ገጾቹ እንደተሰረቁ ለጆሴፍ ነገረው። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን ሥራ ሊያስቆም የሚችል ሰው የለም። እግዚአብሔር ሥራው እንዲቀጥል እቅድ ነበረው።
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 3፥1–10፣ ቅዱሳን፣ 1፥54–55
ሞሮኒ ሰሌዳዎቹን ለጆሴፍ መለሰለት። ትሑት ከሆኑ እና በእርሱ ካመኑ ሥራውን በብዙ መንገድ ሊረዱ እንደሚችሉ እግዚአብሔር ለጆሴፍና ለማርቲን ነገራቸው። መፅሐፈ ሞርሞንን ወደ አለም ለማምጣት ይረዳሉ። ይህ መጽሐፍ በሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎች ንስሀ እንዲገቡና በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ ይረዳቸዋል።
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 3፥16–20፣ 5፥21–35፣ ቅዱሳን፣ 1፥56–57