ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 1— የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ መልእክት ወንጌሌን ስበኩ፡- የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የማካፈል መመርያ (2023 (እ.አ.አ))
“ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 1” ወንጌሌን ስበኩ
ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 1
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ መልእክት
ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እግዚአብሔር በነቢያት በኩል ወንጌልን ለልጆቹ ገልጧል። ይህን ያደረገው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው። በጥንት ጊዜ፣ እንደ አዳም፣ ኖኅ፣ አብርሃም እና ሙሴ ላሉ ነቢያት ኢየሱስ ወንጌልን ገልጧል። ነገር ግን ብዙ ሰዎች አልተቀበሉትም።
ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ወንጌሉን አስተማረ እንዲሁም ቤተክርስቲያኑን መሰረተ። ሰዎች ኢየሱስን እንኳን አልተቀበሉትም። ከሞቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ ከጌታ እውነት እና ቤተክርስትያን መራቅ በስፋት ነበር። የወንጌል ሙላት እና የክህነት ስልጣን ከምድር ላይ ተወሰዱ።
ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ፣ እግዚአብሔር ሌላ ነቢይ፣ ጆሴፍ ስሚዝን ጠራው። እግዚአብሔር የወንጌልን ሙላት በእርሱ በኩል መለሰና የኢየሱስ ክርስቶስን ቤተክርስቲያን እንደገና እንዲያደራጅ ስልጣን ሰጠው።
የኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌል ሙላት በምድር ላይ መገኘት በዘመናችን ካሉት ታላላቅ በረከቶች መሃል አንዱ ነው። ወንጌል የሕይወትን በጣም ፈታኝ ጥያቄዎች እንድንመልስ ይረዳናል። ሕያው ነቢያት በአስቸጋሪ ጊዜያት ይመሩናል። የእግዚአብሔር የክህነት ስልጣን ልጆቹን ለመባረክ ዳግመኛ በምድር ላይ ነው።
ለማስተማር የቀረቡ ሃሳቦች
ይህ ክፍል ለማስተማር ለመዘጋጀት የሚረዳችሁን ምሳሌ ዝርዝር ያቀርባል። እንዲሁም ልትጠቀሙባቸው የምትሏቸው የጥያቄዎች እና ግብዣዎች ምሳሌዎችን ያካትታል።
ለማስተማር ስትዘጋጁ፣ የእያንዳንዱን ግለሠብ ሁኔታ እና መንፈሳዊ ፍላጎቶች በጸሎት አስቡ። ለማስተማር በጣም ጠቃሚ ሊሆን የሚችለውን ወስኑ። ሰዎች ሊረዷቸው የማይችሉትን ቃላት ለማብራራት ተዘጋጁ። ትምህርቶቹን አጭር ለማድረግ በማስታወስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚኖራችሁ አቅዱ።
በምታስተምሩበት ጊዜ የምትጠቀሙባቸውን ጥቅሶች ምረጡ። የ“ትምህርታዊ መሰረት” ክፍል ብዙ አጋዥ ጥቅሶችን ይዟል።
በምታስተምሩበት ጊዜ የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ እንዳለባችሁ አስቡ። እያንዳንዱ ግለሠብ እርምጃ እንዲወስድ የሚያበረታቱ ግብዣዎችን አቅዱ።
እግዚአብሔር የገባቸውን በረከቶች አጽንኦት ስጡ፣ እንዲሁም ስለምታስተምሩት ምስክርነትን አካፍሉ።
ከ15-25 ባለው ደቂቃ ውስጥ ለሰዎች ማስተማር የምትችሉት ነገር
ለማስተማር ከሚከተሉት መርሆዎች ውስጥ አንዱን ወይም ተጨማሪ ምረጡ። የእያንዳንዱ መርህ ትምህርት መሠረት ከዚህ ዝርዝር በኋላ ቀርቧል።
እግዚአብሔር የሚያፈቅረን የሰማይ አባታችን ነው
-
እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን ነው፣ እኛም የእሱ ልጆች ነን። እርሱ በአምሳሉ ፈጥሮናል።
-
እግዚአብሔር በግል ያውቀናል እንዲሁም ይወደናል።
-
እግዚአብሔር የከበረ ፍጹም የሥጋና የአጥንት አካል አለው።
-
እግዚአብሔር በዘለአለማዊ ሰላም እና የደስታ ሙላት ሊባርከን ይፈልጋል።
-
እግዚአብሔር ስለወደደን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ከኃጢአትና ከሞት እንዲያድነን ልኮልናል።
እግዚአብሔር በየትኛውም ዘመን ወንጌልን በነቢያት ይገልጣል
-
እግዚአብሔር ነቢያትን በምድር ላይ ወኪሎቹ እንዲሆኑ ይጠራቸዋል።
-
በጥንት ጊዜ እግዚአብሔር እንደ አዳም፣ ኖኅ፣ አብርሃም እና ሙሴ ያሉትን ነቢያት ጠርቷቸዋል።
-
ሕያው ነቢይ ዛሬ እኛን ለማስተማር እና ለመምራት ከእግዚአብሔር ራዕይን ይቀበላል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎት እና የኃጢያት ክፍያ
-
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው።
-
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ወንጌሉን አስተምሯል፣ ቤተክርስቲያኑንም አቋቁሟል።
-
ኢየሱስ አስራ ሁለት ሐዋርያትን በመጥራት ቤተክርስቲያኑን እንዲመሩ ስልጣን ሰቷቸዋል።
-
በህይወቱ ፍጻሜ ላይ፣ ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ እና በስቅለቱ ጊዜ ባሳለፈው መከራ ለሃጢያታችን ዋጋ ከፍሏል። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ትንሳኤ አድርጓል።
-
በኢየሱስ የስርየት መስዋዕትነት ምክንያት፣ ንስሀ ስንገባ ይቅር ልንባል እና ከኃጢአታችን መንጻት እንችላለን። ይህ ሰላምን ይሰጠናል እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር መገኘት እንድንመለስ እና የደስታ ሙላትን እንድንቀበል ያስችለናል።
-
በኢየሱስ ትንሳኤ ምክንያት፣ ከሞትን በኋላ ሁላችንም ዳግም እንነሳለን። ይህ ማለት የእያንዳንዱ ግለሠብ መንፈስ እና አካል እንደገና ተገናኝተው ለዘላለም ይኖራሉ ማለት ነው።
ውድቀት
-
የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ፣ በስፋት የታየ ከወንጌሉ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የመራቅ ሁኔታ ነበር።
-
በዚህ ጊዜ ሰዎች ብዙ የወንጌል ትምህርቶችን ለወጡ። ሰዎች እንደ ጥምቀት ያሉ የክህነት ሥርዓቶችንም ቀየሩ። የክህነት ስልጣን እና ኢየሱስ ያቋቋመው ቤተክርስቲያን እንደቀድሞው በምድር ላይ አልነበሩም።
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በጆሴፍ ስሚዝ በኩል በዳግም መመለስ
-
ጆሴፍ ስሚዝ መቀላቀል ይችል ዘንድ የትኛው እውነተኛ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን እንደሆነ ማወቅ ፈለገ። የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ በ1820 (እ.አ.አ) ተገለጡለት። ይህ ክስተት የመጀመሪያው ራዕይ ተብሎ ይጠራል።
-
እግዚአብሔር ቀደም ባሉት ዘመናት ነቢያትን እንደጠራው ሁሉ ጆሴፍ ስሚዝን ነቢይ እንዲሆን ጠራው።
-
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በጆሴፍ ስሚዝ አማካኝነት ዳግም ተመልሷል።
-
ሌሎች የሰማይ መልእክተኞች ክህነትን መለሱ እንዲሁም ጆሴፍ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤተክርስቲያን እንዲያደራጅ ስልጣን ተሰጠው።
-
ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም በሕያው በሆኑ ነቢያት እና ሐዋርያት አማካኝነት ቤተክርስቲያኑን መምራቱን ቀጥሏል።
መፅሐፈ ሞርሞን፦ ሌላኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት
-
መፅሐፈ ሞርሞን በጥንት ጊዜ በአሜሪካ በነበሩ ነቢያት የተጻፈ የቅዱሳን መጻህፍት ጥራዝ ነው። ጆሴፍ ስሚዝ በእግዚአብሔር ስጦታ እና ኃይል ተረጎመው።
-
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር፣ መፅሐፈ ሞርሞን የኢየሱስን አገልግሎት፣ አስተምሮት እና የአዳኝነት ተልእኮውን ምስክርነት ይሰጣል።
-
መፅሐፈ ሞርሞንን በማንበብ እና ትእዛዛቱን በማክበር ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን።
-
መፅሐፈ ሞርሞን የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በማንበብ፣ በማሰላሰል እና በመጸለይ ማወቅ እንችላለን። ይህ ሂደት ጆሴፍ ስሚዝ ነቢይ መሆኑን እንድናውቅም ይረዳናል።
እውነትን በመንፈስ ቅዱስ በኩል ለማወቅ ጸልዩ።
-
ጸሎት በእግዚአብሔር እና በልጆቹ መካከል ያለ የሁለት መንገድ ግንኙነት ነው።
-
ከልብ በመነጨ ጸሎት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ መልእክት እውነት መሆኑን ማወቅ እንችላለን።
-
ስንጸልይ፣ መንፈስ ቅዱስ ያስተምረናል እንዲሁም እውነትን ያረጋግጥልናል።
ሰዎችን ልትጠይቋቸው የምትችሏቸው ጥያቄዎች
የሚከተሉት ሰዎችን ልትጠይቋቸው የምትችሏቸው ጥያቄዎች ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ትርጉም ያለው ውይይቶችን እንድታደርጉ እና የአንድን ግለሠብ ፍላጎቶች እና አመለካከቶች እንድትረዱ ያግዛሉ።
-
ስለ እግዚአብሔር ምን ታምናለህ/ሽ?
-
ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ስሜት እንዴት ሊረዳህ/ሽ ይችላል?
-
ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ታውቃለህ/ሽ? ህይወቱ እና ትምህርቱ በአንተ/ቺ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ?
-
በዛሬው ግራ በሚያጋባ ዓለም ውስጥ አስተማማኝ መልሶችን እንዴት ማግኘት ይቻላል?
-
ዛሬ በምድር ላይ ሕያው ነቢይ እንዳለ ማወቅ እንዴት ሊረዳ ይችላል?
-
ስለ መጽሐፈ ሞርሞን ሰምተሃል/ሻል? ለምን አስፈላጊ እንደሆነ እናካፍል?
-
ስለ ጸሎት ያለህን/ሽን እምነት ታጋሪያለሽ/ራለህ? ስለ ጸሎት ያለንን እምነት እናካፍል?
ልታቀርቡ የምትችሏቸው ግብዣዎች
-
ያስተማርነው እውነት መሆኑን ለማወቅ እግዚአብሄርን በጸሎት ትጠይቃላችሁ? (በዚህ ትምህርት የመጨረሻ ክፍል ላይ ያለውን “ለማስተማር የሚሆን ሐሳብ፡ ጸሎት” ተመልከቱ።)
-
ስለ አስተማርነው የበለጠ ለማወቅ በአሁኑ እሁድ ቤተክርስቲያን ትገኛላችሁ?
-
መፅሐፈ ሞርሞንን አንብባችሁ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለማወቅ ትጸልያላችሁ? (የተወሰኑ ምዕራፎችን ወይም ቁጥሮችን ልትጠቁሙ ትችላላችሁ።)
-
የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ትጠመቃላችሁ? (ከዚህ ትምህርት በፊት ያለውን “የጥምቀት እና የማረጋገጫ ግብዣ” ተመልከቱ።)
-
ለሚቀጥለው ጉብኝት ቀጠሮ መያዝ እንችላለን?
የትምህርት መሰረት
ይህ ክፍል የወንጌልን እውቀት እና ምስክርነት እንድታጠናክሩ እና ለማስተማር እንዲረዳችሁ እንድታጠኑ ትምህርት እና ጥቅስ ይሰጣችኋል።
እግዚአብሔር የሚያፈቅረን የሰማይ አባታችን ነው
እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን ነው፣ እኛም የእሱ ልጆች ነን። እርሱ በአምሳሉ ፈጥሮናል። እርሱ የከበረ፣ ፍጹም የሆነ “እንደ ሰው ሊዳሰስ እና ሊጨበጥ የሚችል የስጋና የአጥንት አካል” አለው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 130:22)።
እግዚአብሔር በግል ያውቀናል፣ ከምንረዳውም በላይ ይወደናል። ፈተናዎቻችንን፣ ሀዘኖቻችንን እና ድክመቶቻችንን ያውቃል፣ በዚያ መሃልም ሊረዳንም ይፈልጋል። በእድገታችን ይደሰታል እንዲሁም ትክክለኛ ምርጫዎችን እንድናደርግ ይረዳናል። ከእኛ ጋር ሊነጋገር ይፈልጋል፣ እኛም እርሱን በጸሎት ማናገር እንችላለን።
እንድንማር፣ እንድናድግ እና እሱን እንድንመስል እግዚአብሔር በምድር ላይ ይህን ልምድ ሰጥቶናል። ፍጹም በሆነ ፍቅር ከሞትን በኋላ ወደ እርሱ እንድንመለስ ይፈልጋል። ነገር ግን ይህንን በራሳችን ማድረግ አንችልም። እግዚአብሔር ስለወደደን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲቤዠን ልኮልናል። “ዓለም [በእርሱ] እንዲድን … እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና”(ዮሐንስ 3፥16)።
እግዚአብሔር በዘለአለማዊ ሰላም እና የደስታ ሙላት ሊባርከን ይፈልጋል። እነዚህን በረከቶች እንድንቀበል እድል የሚሰጠንን እቅድ አዘጋጅቶልናል። ይህ እቅድ የመዳን እቅድ ተብሎ ይጠራል (ትምህርት 2 ይመልከቱ)።
እግዚአብሔር በየትኛውም ዘመን ወንጌልን በነቢያት ይገልጣል
ነቢያት በምድር ላይ የእግዚአብሔር ተወካዮች ናቸው።
እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያሳይበት አንዱ አስፈላጊ መንገድ ነቢያትን በመጥራት፣ የክህነት ስልጣንን በመስጠት ለእርሱ እንዲናገሩ በማነሳሳት ነው። ነቢያት በምድር ላይ የእግዚአብሔር ተወካዮች ናቸው። የብሉይ ኪዳን ነቢይ አሞጽ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ሚስጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” (አሞፅ 3፥7) በማለት ጽፏል። በህይወት ካሉ ነቢያት የምናገኛቸው አንዳንድ በረከቶች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች። ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት እና ቤዛነት የሚመሰክሩ የእርሱ ልዩ ምስክሮች ናቸው።
ትምህርቶች። እውነትን ከስህተት እንድንለይ ነቢያት ከእግዚአብሔር መመሪያ ይቀበላሉ። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት እንድንጠብቅ እና ስንወድቅ ንስሃ እንድንገባ ያስተምሩናል። ኃጢአትን ያወግዛሉ ስለ ውጤቱም ያስጠነቅቃሉ።
የነቢያት ትምህርቶች ወደ እግዚአብሔር ያነሱናል እንዲሁም እርሱ ለእኛ የሚፈልገውን በረከቶች እንድንቀበል ይረዱናል። ትልቁ ደህንነታችን በነቢያቱ በኩል የተሰጠውን የጌታን ቃል በመከተል ላይ ነው።
የክህነት ስልጣን። አሁን ላይ ያለው ነቢይ በምድር ላይ የክህነት ስልጣን ባለቤት ነው። ክህነት የእግዚአብሔር ስልጣን እና ሃይል ነው። ለእግዚአብሔር ልጆች መዳን ነቢዩ በእርሱ ስም የመናገር እና የማድረግ ስልጣን አለው።
የቤተክርስቲያን መመርያ። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በሐዋሪያት እና በነቢያት ላይ የተመሰረተ ነው (ኤፌሶን 2፥19–20፣ 4፥11–14 ተመልከቱ)።
በጥንት ዘመን የነበሩ ነቢያት
አዳም በምድር ላይ የመጀመሪያው ነቢይ ነበር። እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ለአዳም ገለጸ እናም ለእርሱም የክህነት ስልጣን ሰጠ። አዳም እና ሔዋን ልጆቻቸውን እነዚህን እውነቶች አስተማሯቸው እናም እምነት እንዲያሳድጉና በወንጌል እንዲኖሩ አበረታታቸው።
በመጨረሻ የአዳምና የሔዋን ዘር በአመጻ ምክንያት ከወንጌል ራቁ። ይህም ክህደት ወይም ውድቀት ወደሚባል ሁኔታ አመራ። ክህደት በሁሉም ቦታ ሲሥፋፋ፣ እግዚአብሔር የወንጌል ሥርዓቶቹን ለማስተዳደርና ለማስተማር አስፈላጊ የሆነውን የክህነት ስልጣኑን መልሶ ይወስዳል።
ብሉይ ኪዳን ብዙ የክህደት ክስተቶችን መዝግቧል። እነዚህን ጊዜያት ለማቆም፣ እግዚአብሔር ሌላ ነቢይ በመጥራት ልጆቹን ረዳቸው። ለእነዚህ ነቢያት የወንጌልን እውነት እንደገና ገለጠላቸው እንዲሁም የክህነትን ስልጣን ሰጣቸው። ከእነዚህ ነቢያት መካከል አንዳንዶቹ ኖኅ፣ አብርሃም እና ሙሴ ነበሩ። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በጊዜ ሂደት ሰዎች ነብያትን ተቃወሙ እንዲሁም ወደቁ።
የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎት እና የኃጢያት ክፍያ
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ኢየሱስ እና የኃጢያት ክፍያው እግዚአብሔር ለእኛ ባለው እቅድ ውስጥ ማዕከላዊ ናቸው። የኃጢያት ክፍያው በገተሰማኔ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እና በመስቀል ላይ መሰቃየቱንና መሞቱን እንዲሁም ትንሳኤውን ያጠቃልላል።
ከአዳምና ከሔዋን ጊዜ ጀምሮ፣ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛቸው እና ቤዛቸው ሆኖ መምጣት በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። የሰማይ አባት ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ከ2,000 ዓመታት በፊት ነው።
ኢየሱስ ፍጹም፣ ኃጢያት የሌለው ህይወት ኖረ። ወንጌሉን አስተምሯል እንዲሁም ቤተክርስቲያኑን መስርቷል። እንዲያስተምሩ እና እንደ ጥምቀት አይነት ቅዱስ ሥርዓቶችን እንዲፈፅሙ የክህነት ስልጣን ሰጣቸው። ቤተክርስቲያኑንም እንዲመሩም ስልጣን ሰጣቸው።
በህይወቱ ፍጻሜ፣ ኢየሱስ በጌቴሴማኒ በደረሰበት መከራ እና በስቅለቱ የኃጢአታችንን ዋጋ ከፈለ። በኢየሱስ የስርየት መስዋዕትነት ምክንያት፣ ንስሀ ስንገባ ከኃጢአታችን ልንነጻ እንችላለን። ይህ ወደ እግዚአብሔር መገኘት እንድንመለስ እና የደስታ ሙላትን እንድንቀበል ያስችለናል።
ኢየሱስ ከተሰቀለ በኋላ፣ በሰማይ አባት ኃይል ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል። በኢየሱስ ትንሳኤ ምክንያት ሁላችንም ከሞትን በኋላ እንነሳለን። ይህ ማለት የእያንዳንዱ ግለሠብ መንፈስ እና አካል እንደገና ይገናኛሉ እንዲሁም እያንዳንዳችን ፍፁም በሆነው በትንሣኤ አካል ለዘላለም እንኖራለን ማለት ነው። (“የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ”ን በትምህርት 2 ተመልከቱ።)
ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ “የሐይማኖታችን መሰረታዊ መርሆች ቢኖሩ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ፣ እንዲሁም እርሱ እንደሞተ፣ እንደተቀበረ፣ እና በሶስተኛውም ቀን እንደተነሳ፣ እንዲሁም ወደ ሰማይ እንዳረገ የሚመሰክሩት የሐዋርያቶችና የነብያቶች ምስክርነቶች ናቸው፤ እናም ሁሉም ሐይማኖታችን የሚመለከቱ ሌላ ነገሮች በሙሉ የዛ አካል ቅጥያዎች ብቻ ናቸው።” (የቤተክርስቲያን ፕሬዘዳንቶች ትምህርቶች፡ ጆሴፍ ስሚዝ [2007] 49)።
ውድቀት
ከኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በኋላ፣ ሐዋርያቱ የክርስቶስን ትምህርት በንጽሕና ለመጠበቅ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ሥርዓትን ለማቆየት ፈልገው ነበር። ሆኖም ግን፣ ብዙ የቤተክርስቲያን አባላት ከሐዋርያት እና ኢየሱስ አስተምሮት ከነበረው ትምህርት ራቁ።
ሐዋርያት ከተገደሉ በኋላ፣ ከወንጌል እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን መራቅ በስፋት ነበር። ይህ ውድቀት አንዳንዴ ታላቁ ክህደት ይባላል። በዚህ ምክንያት፣ እግዚአብሔር የክህነት ስልጣንን ከምድር ላይ ወሰደ። ይህ እጦት ቤተክርስቲያኗን ለመምራት የሚያስፈልገውን ሥልጣንን ያካትታል። በዚህም ምክንያት፣ ኢየሱስ ያቋቋመው ቤተክርስቲያን ከምድር ላይ ጠፋ።
በዚህ ጊዜ ሰዎች ብዙ የወንጌል ትምህርቶችን ለወጡ። አብዛኛው የሰማይ አባት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ እና የመንፈስ ቅዱስ እውነተኛ ተፈጥሮ እውቀት ተዛባ ወይም ጠፋ። ሰዎች እንደ ጥምቀት ያሉ የክህነት ሥርዓቶችንም ቀየሩ።
ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እውነት ፈላጊ ወንዶች እና ሴቶች የተቀየሩትን ትምህርቶች እና ልማዶች ለማሻሻል ሞክረዋል። የበለጠ መንፈሳዊ ብርሃን ለማግኘት ፈልገው ነበር። ብዙዎችም ስለእውነት ዳግም መመለስ አስፈላጊነት ተናግረዋል። ጥረታቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እንዲደራጁ አድርጓል።
ይህ ጊዜ ለሃይማኖታዊ ነፃነት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ ምክንያት ሆኗል። ይህም ከእግዚአብሔር እውነትን እና ሥልጣንን ወደነበረበት ለመመለስ መንገድ ከፍቷል።
ነቢያት እና ሐዋሪያት ስለታላቁ ክህደት አስቀድመው ተናግረው ነበር (2 ተሰሎንቄ 2፥1–3 ተመልከቱ)። እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና ቤተክርስቲያኑ ወደ ምድር እንደሚመለሱ ተንብየው ነበር (የሐዋርያት ሥራ 3፡20–21 ተመልከቱ)። መውደቅ ባይኖር ኖሮ ዳግም መመለስ ባላስፈለገ ነበር።
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በጆሴፍ ስሚዝ አማካኝነት ዳግም መመለስ
የመጀመሪያው ራዕይ እና የጆሴፍ ስሚዝ እንደ ነቢይ መጠራት
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሙላት በምድር ላይ ባልነበረባቸው ክፍለ ዘመናት፣ የሰማይ አባት ልጆቹን ማግኘት ቀጠለ። በጊዜ ሂደት፣ እንደገና በወንጌሉ ሙላት እንዲባረኩ መንገዱን አዘጋጀ። ሁኔታዎቹ ሲመቻቹ፣ ወንጌል እና የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንዲታደስ ጆሴፍ ስሚዝን እንደ ነቢይ ጠራው።
ጆሴፍ ስሚዝ ታላቅ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በነበረበት ምስራቃዊ ዩናይትድ ስቴትስ ይኖር ነበር። የቤተሰቡ አባላት ለእግዚአብሔር የተሰጡ እና እውነትን ይፈልጉ ነበር። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እውነት እንዳላቸው ይናገሩ ነበር። እናም ጆሴፍ የትኛው ትክክል እንደሆነ ለማወቅ ፈለገ (የጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፡18 ተመልከቱ)። መፅሐፍ ቅዱስ “አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት” እንዳለ ያስተምራል (ኤፌሶን 4፥5)። ጆሴፍ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የተሳተፈ ቢሆንም የትኛውን መቀላቀል እንደሚገባው ግራ ተጋባ። በኋላም እንዲህ አለ፥
“በተለያዩ የሀይማኖቶች ክፍሎች መካከል የነበረው ክርክር እና ጠብ ታላቅ ስለነበረ፣ እንደ እኔ ወጣት ለነበረ ግለሠብ… የትኛው ትክክለኛ እና የትኛው የተሳሳተ እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚወስንበት ምንም መንገድ አልነበረም።
“በዚህ የቃላት ጦርነት እና በአስተያየት ሁካታ መካከል፣ ለራሴ ሁልጊዜም፥ ምን ይደረግ? እላለሁ። ከእነዚህ ቡድኖች ሁሉ የትኛዎቹ ትክክል ናቸው፤ ወይስ ሁሉም የተሳሳቱ ናቸውን? ከእነርሱ አንዱ ትክክል ከሆነ፣ የትኛው ነው፣ እና እንዴት አውቀዋለሁ?” (የጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥8፣ 10)
እንደ ብዙ ሰዎች፣ ጆሴፍ ስሚዝ ስለ ነፍሱ መዳን ጥያቄዎች ነበሩት። ኃጢአቱ ይቅር እንዲባልለት እና በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ እንዲሆን ፈልጎ ነበር። በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መካከል እውነትን እየፈለገ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ያነብ ነበር “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል” የሚለውን ምክር ተከተለ (ያዕቆብ 1:5)።
በእዚህ ምንባብ ምክንያት፣ ጆሴፍ ምን ማድረግ እንደሚገባው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወሰነ። በ1820 (እ.አ.አ) የጸደይ ወራት በቤቱ አቅራቢያ ወደሚገኝ የዛፍ ቁጥቋጦ ሄዶ ለጸሎት ተንበረከከ። በጆሴፍ ስሚዝ ወይም በእሱ መሪነት በጸሃፊዎች የተመዘገቡት ራዕዩ አራት ዘገባዎች አሉ (የወንጌል አርእስቶች ድርሰቶች፣ “የመጀመሪያ ራዕይ መለያዎች”ን ተመልከቱ)። ቅዱሳን መጻሕፍት ተብሎ በተገለጸው ዘገባ ላይ ልምዱን እንደሚከተለው ገልጿል፥
“የብርሀን አምድ በራሴ ትክክል ላይ አየሁ፣ ከፀኃይ ብርሀን የበለጠ፣ በላዬ ላይ እስኪያርፍ ድረስ በዝግታወረደ። … ብርሀኑም በእኔ ላይ ባበራም ጊዜ ብርሀናቸውና ክብራቸው ከሚገለፀው በላይ የሆነ ሁለት ሰዎች በአየር ከእኔ በላይ ቆመው አየሁ። አንዱም ስሜን በመጥራት አናገረኝ እንዲሁም ወደ ሌላው እየጠቆመ --ይህ ውድ ልጄ ነው። አድምጠው!” (ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥16-17)አለኝ።
በእዚህ ራዕይ እግዚአብሔር አብ እና ልጁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለጆሴፍ ስሚዝ ታዩ። አዳኙ ወደ ማናቸውም ቤተክርስቲያን እንዳይቀላቀል ነገረው።
በዚህ ራዕይ በሌላ ዘገባ፣ ጆሴፍ አዳኙ የተናገረውን አካፍሏል፡- “ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል። … እነሆ እኔ የክብር ጌታ ነኝ ፡፡ በስሜ የሚያምኑ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖራቸው ለዓለም ተሰቅዬአለሁ ፡፡
ከራእዩ በኋላ፣ ጆሴፍ እንዲህ በማለት በጥልቀት አስቧል “ነፍሴ በፍቅር ተሞላች፣ ለብዙ ቀናት በታላቅ ደስታ ሃሴት አደረኩ፣ ጌታም ከእኔ ጋር ነበር” (የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ፣ ሰመር 1832፣ 3 ፣josephsmithpapers.org፤ ዘመናዊ አጻጻፍ እና ሥርዓተ ነጥብ)።
በዚህ ራዕይ ምክንያት፣ ጆሴፍ ስሚዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ሆነ እንዲሁም ስለ አምላክነት አስፈላጊ እውነቶችን ተማረ። ለምሳሌ፣ የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን ተማረ። እነርሱ በስሙ ሲጠሩት በግል እንደሚያውቁት ተረዳ። ጆሴፍ ምህረት እንደተደረገለት ሲነገረው፣ እግዚአብሔር መሐሪ መሆኑን ተገነዘበ። ይህ አጋጣሚ በደስታ ሞላው።
እግዚአብሔር ከብዙ ቀደምት ነቢያት ጋር እንዳደረገው፣ በእርሱ በኩል የወንጌል ሙላትን ወደ ምድር የሚመለስበት ነቢይ እንዲሆን ጆሴፍ ስሚዝን ጠራው። ይህ ዳግም መመለስ የእግዚአብሔር ልጆች በዚህ ዓለም ደስታን በሚመጣው ዓለም ደግሞ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኙ ያግዛቸዋል—ሁሉም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት።
የክህነት እና የክህነት ቁልፎች መመለስ
አብ እና ወልድ ከታዩ በኋላ፣ ሌሎች የሰማይ መልእክተኞች ወደ ጆሴፍ ስሚዝ እና ወደ ጓደኛው ኦሊቨር ካውደሪ ተላኩ። መጥምቁ ዮሐንስ ትንሣኤ እንዳደረገ ፍጥረት ተገልጦ የአሮናዊ ክህነትን እና ቁልፎችን ሰጣቸው። የአሮናዊ ክህነት የማጥመቅ ስልጣንን ያካትታል።
ብዙም ሳይቆይ፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ—ሦስቱ የክርስቶስ የመጀመሪያ ሐዋርያት—ትንሳኤ እንዳደረጉ ሰዎች ታይተው የመልከ ጼዴቅ ክህነትን እና ቁልፎቹን ለጆሴፍ ስሚዝ እና ለኦሊቨር ካውድሪ ሰጡ። ይህ ክህነት ክርስቶስ በጥንት ጊዜ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ተመሳሳይ ሥልጣን ነው።
በከርትላንድ ቤተመቅደስ ውስጥ፣ ሙሴ፣ ኤልያስ እና ኤላይጃ ለጆሴፍ ስሚዝ እና ኦሊቨር ካውድሪ ተገልጠው በኋለኛው ቀን የእግዚአብሔርን ስራ ለማከናወን አስፈላጊ የሆኑትን ተጨማሪ ስልጣን እና የክህነት ቁልፎችን ሰጡ። ሙሴ እስራኤልን የመሰብሰቢያ ቁልፎች ሰጠ። ኤልያስ የአብርሃምን ወንጌል ዘመን አስረከበ። ኤላይጃ የማተም ኃይል ቁልፎችን ሰጠ። (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 110፡11–16 ይመልከቱ፤ አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፣ 3.1 ተመልከቱ።)
የቤተክርስቲያን አደረጃጀት
ጆሴፍ ስሚዝ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤተክርስቲያን በምድር ላይ እንደገና እንዲያደራጅ መመሪያ ተሰጠው። በእርሱም በኩል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አስራ ሁለት ሐዋሪያትን ጠራ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ነቢያት የምንኖርበትን ጊዜ እንደ መጨረሻው ቀን ወይም የመጨረሻው ዘመን ይጠቅሳሉ። ከኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት በፊት ያለ ጊዜ ነው። ቤተክርስቲያኗ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የተባለችው ለዚያ ነው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 115፡3–4 ተመልከቱ፤ እንዲሁም 3 ኔፊ 27፡3–8 ተመልከቱ)።
የጊዜያችን ህያው ነቢያት እና ሐዋርያት
ኢየሱስ በስጋዊ አገልግሎቱ ወቅት ቤተክርስቲያኑን እንዲመሩ ሐዋርያትን እንደጠራው ሁሉ ዛሬም እንዲመሩ ሐዋርያትን ይጠራል። የቀዳሚ አመራር እና የአስራ ሁለቱ ሐዋርያትን ሸንጎ ቡድን እንደ ነብያት፣ ባለ ራእዮች እና ገላጮች ናቸው።
መላውን ቤተክርስቲያን የሚመራ እና ልዩ በሆነ መልኩ ለጌታ የመናገር ስልጣን ስላለው ነቢዩ ተብሎ የሚጠራው አንጋፋው ሐዋርያ ብቻ ነው። እሱ ስልጣን ያለው የጆሴፍ ስሚዝ ተተኪ ነው። እሱ እና አሁን ላይ ያሉት ሐዋርያት ጆሴፍ ስሚዝ በሰማያዊ መልእክተኞች እጅ በተሾመ ጊዜ በጀመረው ባልተሰበረ የሹመት ሰንሰለት ሥልጣናቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ይዋረዳል።
መፅሐፈ ሞርሞን፦ ሌላኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት
መፅሐፈ ሞርሞን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አይነት ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ጥራዝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ምስክር ነው፣ መጽሐፈ ሞርሞን ደግሞ የአገልግሎቱ፣ የትምህርቱ እና የእሱ አዳኝነት ተልዕኮ ሁለተኛ ምስክር ነው።
ጆሴፍ ስሚዝ ሞሮኒ በሚባል የሰማይ መልእክተኛ ለምዕተ አመታት ተደብቆ የነበረ ጥንታዊ መዝገብ ወዳለበት ኮረብታ ተመራ። በወርቅ ሰሌዳዎች (ቀጭን ብረቶች) ላይ የተቀረጸው ይህ መዝገብ አምላክ ከአንዳንድ ጥንታዊ የአሜሪካ ነዋሪዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የነቢያት ጽሑፎችን ይዟል። ጆሴፍ ስሚዝ ይህን መዝገብ በእግዚአብሔር ሀይል እና ስጦታ ተረጎመ።
በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የነበሩት ነቢያት ስለአዳኙ ተልዕኮ ያውቁና ወንጌሉን ያስተምሩ ነበር። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለእነዚህ ሰዎች ተገልጦ በግል አገለገለላቸው። ወንጌሉን አስተማራቸውና ቤተክርስቲያኑን መሰረተ።
መፅሐፈ ሞርሞንን ስንማር፣ ስንረዳ እና ትምህርቶቹን በተግባር ላይ ስናውል ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ይረዳናል። ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ “አንድ ወንድ [ወይም ሴት] ከማንኛውም መጽሐፍ ይልቅ [የመጽሐፉን] መመሪያዎችን በማክበር ወደ እግዚአብሔር ይቀርባሉ” (ትምህርቶች ጆሴፍ ስሚዝ፣ 64)ብሏል።
መፅሐፈ ሞርሞን የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለማወቅ ልናነበው፣ ልናሰላስልበት እና ልንጸልይበት ያስፈልጋል። የመፅሐፈ ሞርሞን ነቢይ ከልብ፣ በእውነተኛ ሃሳብ እና በክርስቶስ እምነት ስንጸልይ እግዚአብሔር የመጽሐፉን እውነት እንደሚገልጥልን ቃል ገብቷል (ሞሮኒ 10፡3–5 ተመልከቱ)። መጽሐፈ ሞርሞንን ማጥናት ዘላቂ ለሆነ መለወጥ አስፈላጊ ነው።
መፅሐፈ ሞርሞንን ስናነብ እና ስንጸልይበት፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ህይወታችንን የሚባርክ እውነቶችን እንማራለን። በተጨማሪም ጆሴፍ ስሚዝ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደነበረ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና ቤተክርስቲያን በእርሱ በኩል እንደተመለሱ እናውቃለን።
“መፅሐፈ ሞርሞንን በጸሎት መንፈስ በየቀኑስታጠኑበየቀኑየተሻሉ ውሳኔዎችን እንደምትወስኑ ቃል እገባለሁ። በምታጠኑት ነገር ላይ ስታሰላስሉ፣ የሰማይ መስኮቶች እንደሚከፈቱ፣ እንዲሁም ለራሳችሁ ጥያቄዎች መልስ እና ለግል ህይወታችሁ መመሪያ እንደምትቀበሉ ቃል እገባለሁ። በየቀኑ ራስችሁን በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ስታጠልቁ፣ ከእለቱ ክፋት መከላከያ እንደሚኖራችሁ ቃል እገባለሁ።”(ራስል ኤም ኔልሰን “The Book of Mormon: What Would Your Life Be Like without It? [መፅሐፈ ሞርሞን፡ ያለ እሱ ህይወትህ ምን ትመስላለች?]”) ኢንዛይን ወይም ህዳር 2017 (እ.አ.አ)፣ 62-63 ይመልከቱ።
እውነትን በመንፈስ ቅዱስ በኩል ለማወቅ ጸልዩ።
እግዚአብሔር አባታችን ስለሆነ እውነትን እንድናውቅ ይረዳናል። መፅሐፈ ሞርሞንን ስናነብ እና ወደ እግዚአብሔር ስንጸልይ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ መልእክት እውነት መሆኑን ማወቅ እንችላለን። በእምነት እና በእውነተኛ ፍላጎት ስንጸልይ እርሱ ጥያቄዎቻችንን ይመልሳል እንዲሁም ህይወታችንን ይመራል።
እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ስንጸልይ፣ መንፈስ ቅዱስ ያስተምረናል እንዲሁም እውነትን ያረጋግጥልናል። ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጡ መልዕክቶች ኃይለኛ ናቸው። በስሜታችን፣ በሀሳቦቻችን እና በአመለካከታችን አማካኝነት ጸጥ ያሉ ማረጋገጫዎች ሆነው ይመጣሉ። (1 ነገሥት 19:11–12; ሔለማን 5:30፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 8:2ን ተመልከቱ)።
ቅዱሳን መጻህፍትን (በተለይም መፅሐፈ ሞርሞንን) በቋሚነት ማንበብ፣ በየሳምንቱ የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ መገኘት፣ እና ከልብ የሆነ ጸሎት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲሰማን እና እውነትን እንድናውቅ ይረዳናል።
ከአጭር እስከ መካከለኛ የትምህርት መዘርዝር
የሚከተለው ንድፍ አጭር ጊዜ ካላችሁ ለአንድ ሰው ልታስተምሩ የምትችሉት ነገር ምሳሌ ነው። ይህንን ንድፍ ስትጠቀሙ ለማስተማር አንድ ወይም ተጨማሪ መርሆችን ምረጡ። ለእያንዳንዱ መርህ የአስተምሮት መሰረት ቀደም ብሎ በትምህርቱ ውስጥ ቀርቧል።
ስታስተምሩ ጥያቄዎችን ጠይቁ እንዲሁም አዳምጡ። ሰዎች ወደ እግዚአብሄር እንዴት መቅረብ እንደሚችሉ እንዲማሩ የሚያግዙ ግብዣዎችን ጋብዙ። አንድ አስፈላጊ ግብዣ ግለሰቡ እንደገና ከእናንተ ጋር እንዲገናኝ መጋበዝ ነው። የትምህርቱ ቆይታ የሚወሰነው በምትጠይቋቸው ጥያቄዎች እና በአደማመጣችሁ ላይ ነው።
ከ3-10 በሚሆኑ ደቂቃዎች ውስጥ ሰዎችን ልታስተምሯቸው የምትችሏቸው ነገሮች
-
እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን ነው፣ እናም እኛን በመልኩ ነው የፈጠረን። እርሱ በግል ያውቀናል እንዲሁም ይወደናል። ዘላለማዊ በሆነ ሰላም እና የደስታ ሙላት ሊባርከን ይፈልጋል።
-
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። የእርሱ ተልእኮ ከኃጢአታችን እንድንነጻ፣ ሞትን እንድናሸንፍ እና የዘላለም ህይወት እንድንቀበል ማስቻል ነበር።
-
እግዚአብሔር ነቢያትን በምድር ላይ ወኪሎቹ እንዲሆኑ ይጠራቸዋል። በጥንት ጊዜ እንደ አዳም፣ ኖኅ፣ አብርሃም እና ሙሴ ያሉ ነቢያትን ጠርቷል። ሕያው ነቢይ ዛሬ እኛን ለማስተማር እና ለመምራት ከእግዚአብሔር ራዕይን ይቀበላል።
-
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎት ወቅት ቤተክርስቲያኑን አቋቋመ። የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ፣ ከወንጌሉ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሰፊ ውድቀት ነበር። ሰዎች እንደ ጥምቀት ያሉ ብዙ የወንጌል ትምህርቶችን እና የክህነት ሥርዓቶችን ለወጡ።
-
እግዚአብሔር ቀደም ባሉት ዘመናት ነቢያትን እንደጠራው ሁሉ ጆሴፍ ስሚዝን ነቢይ እንዲሆን ጠራ። የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጡለት። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በእርሱ አማካኝነይ ተመልሷል።
-
መፅሐፈ ሞርሞን የቅዱሳን መጻሕፍት ጥራዝ ነው። ልክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ነው እንዲሁም ስናነበው እና ትእዛዛቱን በተግባር ስናውል ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ይረዳናል። ጆሴፍ ስሚዝ በእግዚአብሔር ስጦታ እና ኃይል ተረጎመው።
-
በቅን ልብ በመጸለይ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር እንችላለን። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ መልእክት እውነት መሆኑን ማወቅ እንችላለን።