ምዕራፍ ፲፫
ይሁዳና ኢየሩሳሌም ባለመታዘዛቸው ይቀጣሉ—ጌታም ለህዝቡ ይማፀናል፣ እናም ሕዝቡን ይፈርዳል—የፅዮን ሴት ልጆች በዓለማዊነታቸው የተነሳ የተረገሙና የተሰቃዩ ናቸው—ኢሳይያስ ፫ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እነሆም፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ፣ ምርኩዝን፣ እና ድጋፍን፣ የዳቦን ድጋፍ ሁሉ እናም የውሃንም ድጋፍ ሁሉ ይወስዳል—
፪ ሀያሉን ሰውና፣ ተዋጊውንም፣ ፈራጁንም፣ ነቢዩንም፣ ብልሁንና፣ ሽማግሌውን ሰው ይወስዳል፤
፫ የሀምሳ አለቃውንና፣ የተከበረውን ሰው፣ አማካሪውንም፣ እና ብልሁን ሠራተኛና፣ ጥሩ ተናጋሪውን ይወስዳል።
፬ እናም ልዑሎቻቸው ይሆኑ ዘንድ ሕፃናትን እሰጣቸዋለሁ፣ ሕፃናቶችም እነርሱን ይገዛሉ።
፭ እናም ሕዝቡ ይጨቆናል፣ አንዱ በሌለኛው፣ እንዲሁም አንዱ በጎረቤቱ፤ ሕፃናቱ በሽማግሌው ላይ እንዲሁም ፀያፍ አድራጊዎች በተከበረው ላይ ይኮራሉ።
፮ አንድ ሰው በአባቱ ቤት ውስጥ ወንድሙን በያዘ ጊዜ፣ እናም እንዲህ ሲለው፥ አንተ ልብስ አለህ፣ አለቃም ሁንልን፣ እናም ይህም ጥፋት ከእጅህ በታች እንዲሆን አትፍቀድ—
፯ በዚያ ቀን እንዲህ በማለት ይምላል—ባለመድሀኒት አልሆንም፤ ምክንያቱም በቤቴ ዳቦም ሆነ ልብስ የለምና፤ የሕዝቡም አለቃ አታድርጉኝ።
፰ የክብሩን ዐይን ለማስቆጣት፣ ምላሳቸውና ስራቸው ጌታን ስለሚፃረሩ ኢየሩሳሌም ፈረሰች፣ እናም ይሁዳ ወደቀች።
፱ በፊታቸው የሚታየው በእነርሱ ላይ ይመሰክራል፣ እናም ኃጢአታቸው እንደሰዶም አይነት እንደሆነ ያውጃል፣ እናም ሊደብቁት አይችሉም። በራሳቸው ላይ ኃጢያትን በማምጣታቸው ለነፍሳቸው ወዮላቸው!
፲ የስራቸውን ፍሬ ይበላሉና፤ ፃድቃንን መልካም ይሆንላችኋል በላቸው።
፲፩ ወዮላቸው ለክፉዎች፤ ይጠፋሉና፤ የስራቸውም ዋጋ በእነርሱ ላይ ይሆናል!
፲፪ እናም ሕዝቤ፣ ሕፃናት ጨቋኛቸው ናቸው፣ እንዲሁም ሴቶች ገዢዎቻቸው ናቸው። ሕዝቤ ሆይ፣ የመሩአችሁ ያስቱአችኋል፣ እንዲሁም የምትሄዱበትንም መንገዳችሁን ያጠፋሉ።
፲፫ ጌታ ለሙግት ተነስቷል፣ እናም በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ቆሟል።
፲፬ ጌታ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከልዑሎች ጋር ለፍርድ ይገባል፤ ምክንያቱም የወይኑን ቦታ እና በቤታችሁ የሚገኙት ድሆችን ብዝበዛ የጨረሳችሁ እናንተ ናችሁ።
፲፭ እናንት ምን ማለታችሁ ነው? ሕዝቤን ታደቁአቸዋላችሁ፣ እና የድሆችንም ፊት ትፈጫላችሁ፣ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
፲፮ ከሁሉም በላይ፣ ጌታ እንዲህ አለ፥ የፅዮን ሴት ልጆች ትዕቢተኛ ስለሆኑና አንገታቸውን በማስገግ ስለሚራመዱና በሚሄዱበት ጊዜ ዐይናቸውን በማጣቀስ፣ ፈጠን ብለው በመራመድ እናም በእግራቸው እያቃጨሉ በመሄዳቸው ምክንያት—
፲፯ ስለዚህ ጌታ የፅዮንን ሴት ልጆች ራስ በቡሃነት ይመታል፣ እናም ጌታ ሀፍረተ-ስጋቸውን ይገልጣል።
፲፰ በዚያ ቀን ጌታ የሚያንቃጭለውን ጌጣቸውን፣ መርበብን፣ እና ጨረቃ የሚመስለውን የአንገት ጌጣቸውን ውበት ያስወግዳል።
፲፱ ሰንሰለቱንና አምባሩን፣ እና መሸፈኛውን፤
፳ ቆብና የእግር አልቦውን፣ እና የራስ ማሰሪያውንና፣ የሽቶውን ዕቃ፣ እና የጆሮ ቀለበቶቹን፤
፳፩ ቀለበት እና የአፍንጫ ጌጥ፤
፳፪ ውድ ሱፍ ልብስንም፣ ካባውንንም፣ መጎናፀፊያውንም፣ እና ፀጉር መጠቅለያውን፤
፳፫ መስታወቱንም፣ ከጥሩ በፍታ የተሰራውንም ልብስ፥ ራስ ማሰሪያውንም፥ ዓይነ ርግቡንም ያስወግዳል።
፳፬ እናም እንዲህ ይሆናል፣ በጥሩ ሽታ ፈንታ ግማት፣ እና በመታጠቅያው ፈንታ ቀዳዳ፤ ጠጉርንም በመነቀስ ፈንታ መላጣነት፤ በተብለጨለጨው ልብስ ፈንታ ማቅ፤ በውበትም ፈንታ ጠባሳ ይሆናል።
፳፭ ወንዶችሽ በሰይፍ ጀግኖችሽም በውጊያ ይወድቃሉ።
፳፮ እናም በሮችዋ ያዝናሉ ያለቅሱማል፤ እናም ተስፋ በመቁረጥ በመሬት ላይ ብቻዋን ትቀመጣለች።