ምዕራፍ ፲፬
ፅዮንና ሴቶች ልጆችዋ ይድናሉ፣ እናም በሺኛው ዘመን ይነፃሉ—ኢሳይያስ ፬ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም በዚያ ቀን፣ ሰባት ሴቶች አንድን ወንድ ይይዛሉ፣ የራሳችንን ዳቦ እንበላለን፣ እንዲሁም የራሳችንን ልብስ እንለብሳለን፣ ሀፍረታችንን ለማስወገድ በስምህ ብቻ እንጠራ ይላሉ።
፪ በዚያ ቀን የጌታ ቅርንጫፍ ያማረና የከበረ ይሆናል፤ ከእስራኤል ለመጡት የምድሪቱ ፍሬ ታላቅና ውብ ይሆናል።
፫ እናም እንዲህ ይሆናል፣ በፅዮን የቀሩና በኢየሩሳሌም የቀሩ፣ በኢየሩሳሌም በሕያዋን መካከል የተመዘገቡ ሁሉ ቅዱስ ተብለው ይጠራሉ—
፬ ጌታ የፅዮንን ሴት ልጆች እድፍ ባጠበ ጊዜ፣ እና የኢየሩሳሌምንም ደም በፍርድ መንፈስና በሚያቃጥል መንፈስ ከመካከልዋ ባነፃ ጊዜ ቅዱስ ተብለው ይጠራሉ።
፭ እናም ጌታ በፅዮን ተራራ ባለ ማደሪያ ላይና፣ በመሰብሰቢያዎቿ ላይ፣ በቀን ደመናንና፣ ጢስን በሌሊትም የሚበራውን የእሳት ብርሃን ይፈጥራል፤ በፅዮን ክብር ሁሉ ላይ መጋረጃ ይሆናልና።
፮ እናም በቀን ከሙቀት ለመጠለያ ቦታ፣ ለመሸሸጊያም ቦታ፣ እናም ከውሽንፍርና ከዝናብ መሸፈኛ ድንኳን ይሆናል።