ምዕራፍ ፴፪
መላዕክት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይናገራሉ—ሰዎች መፀለይ እናም እውቀትን ከመንፈስ ቅዱስ ማግኘት አለባቸው። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን፣ እነሆ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እናንተ በጎዳናው ከገባችሁ በኋላ ምን ማድረግ እንደሚገባችሁ በመጠኑ በልባችሁ እንደምታሰላስሉ እገምታለሁ። ነገር ግን፣ እነሆ፣ ስለምን እነዚህን ነገሮች በልባችሁ ታሰላስላላችሁ?
፪ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበላችሁ በኋላ በመላዕክት ልሳን መናገር እንደምትችሉ የተናገርኳችሁን አታስታውሱም? እናም አሁን፣ በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በመላዕክት ልሳን መናገር እንዴት ትችላላችሁ?
፫ መላዕክት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይናገራሉ፤ ስለዚህ፣ የክርስቶስን ቃል ይናገራሉ። ስለሆነም፣ የክርስቶስን ቃል ተመገቡ እላችኋለሁ፤ እነሆ የክርስቶስ ቃል ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች በሙሉ ይነግራችኋልና።
፬ ስለሆነም፣ አሁን እነዚህን ቃላት ከተናገርኩ በኋላ፣ መረዳት ካልቻላችሁ፣ ይህም ስላልጠየቃችሁ፣ ወይም ስላላንኳኳችሁ ነው፤ ስለሆነም፣ ወደ ብርሃኑ አልመጣችሁም፣ ነገር ግን በጨለማው ትጠፋላችሁ።
፭ እነሆም፣ በድጋሚ እላችኋለሁ በመንገዱ የምትገቡ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን የምትቀበሉ ከሆነ፣ ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች ሁሉ ያሳያችኋል።
፮ እነሆ፣ ይህ የክርስቶስ ትምህርት ነው፣ እናም ለእናንተ በስጋ እራሱን እስከሚገልፅ ድረስ ሌላ ትምህርት አይሰጥም። እናም እርሱ ራሱን በስጋ ለእናንተ በሚገልፅበት ጊዜ፣ የተናገራችሁን ነገሮች በትጋት ታደርጋላችሁ።
፯ እናም አሁን እኔ ኔፊ፣ ብዙ ማለት አልችልም፤ መንፈስ እንዳልናገር አደረገኝ፣ እናም በሰዎች ባለማመን፣ ክፋትና፣ ባለማወቅ፣ እንዲሁም አንገተ ደንዳናነት የተነሳ አዝናለሁ፤ ምክንያቱም እውቀትን አልፈለጉም፣ ወይም ታላቁን እውቀት በግልፅ፣ እንዲሁም ቃል መግለጽ እስከሚቻልበት ያህል፣ በተሰጣቸውም ጊዜ አልተረዱምና።
፰ እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ አሁንም በልባችሁ እንደምታሰላስሉ አስተውላለሁ፤ እናም ይህን ነገር በሚመለከት መናገር ስላለብኝ ያሳዝነኛል። ሰዎችን እንዲፀልዩ የሚያስተምረውን መንፈስ ካዳመጣችሁት መፀለይ እንዳለባችሁ ታውቃላችሁ፤ እርኩስ መንፈስ ሰዎችን ፀሎት አያስተምርምና፣ ነገር ግን መፀለይ እንደሌለባቸው ያስተምራቸዋል።
፱ ነገር ግን እነሆ፣ ሳትታክቱ ዘወትር መጸለይ እንዳለባችሁ፤ በመጀመሪያ ወደ አብ በክርስቶስ ስም ካልፀለያችሁ ምንም ነገር ለጌታ ማከናወን እንደማይገባችሁ፣ እርሱም ስራችሁን ቅዱስ እንደሚያደርግላችሁ፣ ስራችሁም ለነፍሳችሁ ደህንነት እንደሚሆን እነግራችኋለሁ።