ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፳፬


ምዕራፍ ፳፬

እስራኤል ትሰበሰባለች፣ የሺህ ዓመት እረፍትን ትደሰትበታለች—ሉሲፈር በአመፅ ምክንያት ከሰማይ ተጥሏል—እስራኤል ባቢሎንን (ዓለምን) ድል ታደርጋታለች—ኢሳይያስ ፲፬ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

ጌታ በያዕቆብ ላይ ምህረቱን ያወርዳልና፣ በድጋሚም እስራኤልን ይመርጣል፣ በራሳቸውም ምድር ላይ ያኖራቸዋል፤ እንግዳዎቹም ከእነርሱ ጋር ይገናኛሉ፣ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጣበቃሉ።

እናም ህዝቡ ይዘው ወደ ራሳቸው ቦታ ያመጧቸዋል፤ አዎን፣ ከሩቅም እስከምድር ዳርቻም፤ እናም ወደ ቃል ኪዳን ምድራቸውም ይመለሳሉ። የእስራኤልም ቤት ባለቤት ያደርጓቸዋል፣ እናም የጌታ ምድር እንደ ወንድና ሴት ገረዶች ይሆናሉ፤ የማረኩአቸውንም ይማርካሉ፤ እናም ጨቋኞቻቸውን ይገዛሉ።

እናም በዚያን ቀን እንዲህ ይሆናል ጌታ ከሀዘናችሁ፣ ከፍርሃታችሁም፣ እናም ከአስከፊው እንድታገለግሉ ከተደረጋችሁባት ባርነት እረፍት ይሰጣችኋል።

እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፣ ይህንን ምሳሌ በባቢሎን ንጉስ ላይ አንስታችሁ እንዲህ ትላላችሁ—አስጨናቂው እንዴት ፀጥ አለ፣ ወርቃማዋስ ከተማ እንዴት አረፈች!

ጌታ የኃጥአንን በትር፣ የመሪዎችንም ዘንግ ሰብሯል።

ህዝቡን ያለማቋረጥ በጭካኔ የመታ፣ ሀገሮችን በቁጣ የመራ፣ ስደት ይሆንበታል፣ እናም ማንም አያስጥለውም።

መላው ምድር እረፍት ላይ ነው፣ ፀጥታም ሆኖአል፣ በዝማሬም ተነስተዋል።

አዎን፣ ጥድና የሊባኖስ ዝግባ አንተ ከተጋደምክ ጀምሮ ማንም ይቆርጠን ዘንድ አልመጣብንም ብለው በአንተ ደስ አላቸው።

ሲኦል ከበታች አንተ በመምጣትህ ልትገናኝህ ታወከች፤ የሞቱትንም የምድር ታላላቆች ለአንተ አንቀሳቀሰች፤ የሃገሮችን ነገስታቶች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ለአንተ አስነሳች።

ሁሉም ይናገራሉ ለአንተም እንዲህ ይላሉ—አንተም ደግሞ እንደ እኛ ደካማ ሆንክን? አንተ ልክ እንደ እኛ ሆንክን?

፲፩ ውበትህ ወደ መቃብር መጥቷል፤ የበገናህም ድምፅ አይሰማም፤ ብል ከበታችህ ተነጥፏል፣ ትልም ይሸፍንሃል።

፲፪ አቤቱ ሉሲፈር፣ አንተ የንጋት ልጅ ሆይ! እንዴት ከሰማይ ወደቅህ? አንተ ሀገሮችን ያዋረድክ፣ እንዴት ከምድር በታች ተቆረጥህ!

፲፫ አንተም በልብህ ወደ ሰማይ አርጋለሁ፣ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ አደርጋለሁ፤ በሰሜን ዳርቻም በመሰብሰቢያውም ተራራ ደግሞ እቀመጣለሁ፤

፲፬ ከደመናዎችም ከፍታ በላይ አርጋለሁ፤ እንደ ልዑልም እሆናለሁ ብለሃል።

፲፭ ነገር ግን ወደ ሲዖል፣ ወደጥልቁም ጉድጓድ ትወርዳለህ።

፲፮ የሚያዩህም ያተኩሩብሃል፣ ያስተውሉሀልም፣ እናም ይላሉ—ምድርን ያንቀጠቀጠ፣ መንግስታትን ያናወጠ ሰው ይህ ነውን?

፲፯ እናም ዓለምን ምድረበዳ ያደረገ፣ ከተሞቿንም ያጠፋ፣ የእስረኞቹንም በር ያልከፈተው ይህ እርሱ አይደለምን?

፲፰ የሁሉም ሀገሮች ንጉሶች፣ አዎን፣ ሁላቸውም፣ እያንዳንዳቸውም በየቤታቸው በክብር አንቀላፍተዋል።

፲፱ ነገር ግን አንተ እንደረከሰ ቅርንጫፍ፣ በሰይፉም ተወግተው እንደተገደሉት፣ ወደ ጉድጓዱ ድንጋዮች አዘቅት እንደወረዱት ቅሪቶች በእግሮች ስር እንደተረገጠም ሬሳ ከመቃብርህ ተጥለሃል።

ምድርህን አጥፍተሀልና ህዝብህንም ገድለሀልና፤ ከእነርሱ ጋር በመቃብር አንድ አትሆንም፣ የክፉ አድራጊዎች ዘር በፍፁም አይከበርም።

፳፩ እንዳያንሰራሩም ምድሪቷንም እንዳይዙ፣ የምድርንም ገፅ በከተሞቻቸው እንዳይሞሉ፣ በአባቶቻቸው ኃጢያት ምክንያት ልጆቹን ለግድያ አዘጋጁ።

፳፪ እኔም በእነርሱ ላይ እነሳለሁ ይላል የሰራዊት ጌታ፣ እናም ከባቢሎን ስምና ቅሪት ዘርንና ወንድ ልጅንና የወንድምን ወይም የእህትን ልጅ እቆርጣለሁ ይላል ጌታ።

፳፫ የጃርት መኖሪያ የውሃም መቆሚያ አደርጋለሁ፤ በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ ይላል የሰራዊት ጌታ።

፳፬ የሰራዊት ጌታ እንዲህ ሲል ምሏል—በእርግጥም እኔ እንዳቀድኩት ይሆናል፤ እኔ እንደወሰንኩትም ይቆማል—

፳፭ አሶርን በምድሬ አመጣታለሁ፣ በተራራዬም ላይ በእግሬ ስር እረግጠዋለሁ፤ ከዚያም ቀንበሩ ከእነርሱ ላይ ይወርዳል፣ ሸክሙም ከትከሻቸው ይወርዳል።

፳፮ በምድር ላይ ሁሉ የታቀደው ዕቅድ ይህ ነው፤ እናም በሃገር ሁሉ ላይ የተዘረጋው እጅ ይህ ነው።

፳፯ የሰራዊት ጌታ ይህንን አቅዶአል፣ የሚያከሽፈውስ ማነው? እጁም ተዘርግታለች የሚያስመልሳትስ ማነው?

፳፰ ንጉስ አካዝ በሞተበት ዘመን ይህ ሸክም ነበር።

፳፱ እናንተ ፍልስጤም ደስ አይበላችሁ፣ ምክንያቱም እናንተን የመታው በትሩ ተሰብሯል፤ ከእባቡ ስር እፉኝት ይመጣል፣ ፍሬውም የሚበር ቁጡ እባብ ይሆናል።

እናም የድሆች በኩር ይመገባል፣ ችግረኞችም በሰላም ይኖራሉ፤ እኔም ስራችሁን በረሃብ እገድላለሁ፣ እርሱ ደግሞ ቅሪቶቻችሁን ይገድላል።

፴፩ አንተ መግቢያ ሆይ ወዮ በል፤ አንቺ ከተማ ሆይ አልቅሺ፤ ፍልስጤም ሁላችሁም ቀልጣችኋል፤ ጢስ ከሰሜን ይመጣልና፣ እናም በእርሱ ቀነ ቀጠሮ ጊዜያት ማንም ብቸኛ አይሆንም።

፴፪ እንግዲህ ለሀገር መልዕክተኞች ምን ይመለሳልን? ጌታ ፅዮንን እንደመሰረተና፣ የሀገሮቹም ድሆች በውስጧ እንደሚጠጉ ነው።