ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፳፱


ምዕራፍ ፳፱

ብዙ አህዛብ መፅሐፈ ሞርሞንን አይቀበሉም—ሌላ መፅሐፍ ቅዱስ አያስፈልገንም ይላሉ—ጌታ ለብዙ ሀገሮች ይናገራል—በመጽሐፍት ላይ በሚፃፉት ዓለምን ይፈርዳል። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

ነገር ግን እነሆ፣ ከሰው ልጆች ጋር የገባሁትን ቃልኪዳኔን አስብ ዘንድ፣ የእስራኤል ቤት የሆኑትን ህዝቤን ደግሜ ለመሰብሰብ ክንዴን ለሁለተኛ ጊዜ አነሳ ዘንድ፤

እናም ደግሞ ዘርህንም አንደማስታውስ፤ እናም የዘርህ ቃል ከአፌ ወደ ዘርህ እንደሚያልፍ፤ ቃሌም የእስራኤል ቤት ለሆኑት ህዝቦቼ አርማ ይሆን ዘንድ ወደ ምድር ዳርቻ እንደሚያፏጭ፤ ለአንተ ኔፊና ደግሞ ለአባትህ የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሰው ዘንድ፤ በዚያን ቀን በእነርሱ መካከል ድንቅ ስራን መስራት ስቀጥል፣ ብዙዎች ይኖራሉ—

እናም ቃሎቼ ወደፊት ስለሚያፏጩ—ብዙ አህዛብ እንዲህ ይላሉ፣ መፅሐፍ ቅዱስ! መፅሐፍ ቅዱስ! መፅሐፍ ቅዱስ አለን፣ እናም ሌላ መፅሐፍ ቅዱስ ሊኖር አይችልም።

ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ሞኞች ሆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይኖራቸዋል፤ እናም ከእኔ የጥንት የቃል ኪዳን ህዝቦቼ ከአይሁዶች ይወጣል። እናም ከአይሁዶች ስለተቀበሉት መፅሐፍ ቅዱስ እንዴት አድርገው ያመሰግናሉ? አዎን፣ አህዛብስ ምን ማለታቸው ነው? ችግርን፣ የጉልበት ስራንና፣ የአይሁዶችን ስቃይ፣ እንዲሁም ለአህዛብ ደህንነትን ለማምጣት ለእኔ ያላቸውን ትጋት ያስታውሳሉ?

እናንት አህዛብ ሆይ፣ የጥንት የቃል ኪዳን ህዝቦቼ አይሁዶችን ታስታውሳላችሁ? አታስታውሱም፤ ነገር ግን እናንተ ረግማችኋቸዋልና፣ ጠልታችኋቸዋል፣ እናም እነሱን ለመመለስም አልፈለጋችሁም። ነገር ግን እነሆ፣ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በራሳችሁ ላይ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ጌታ ህዝቤን አልረሳሁምና።

እናንት ሞኞች፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አለን፣ እናም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ አንፈልግም የምትሉ። በአይሁዶች ካልሆነ በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስን አግኝታችኋልን?

ከአንድ በላይ ሀገር እንዳለ አታውቁምን? እኔ ጌታ አምላካችሁ፣ ሰዎችን ሁሉ እንደፈጠርኩ፣ እናም እኔ በባህር ደሴቶች ያሉትን እንደማስታውስና በላይ በሰማይ እንዲሁም በታች በምድር እንደምገዛ፣ ለሰው ልጆች ቃሌን፣ አዎን፣ ለሁሉም የምድር ሀገሮችም እንኳን እንደማመጣ አታውቁምን?

ስለዚህ ቃሌን በይበልጥ ስለተቀበላችሁ ታጉረመርማላችሁ? እኔ እግዚአብሔር ስለመሆኔ፣ አንዱን ሀገር እንደሌላኛው እንደማስታውሰው፣ የሁለት ሀገሮች ምስክርነት ለእናንተ ምስክር መሆኑን አታውቁምን? ስለሆነም፣ ለአንዱ ሀገር እንደተናገርኩት ለሌላኛውም አንድ አይነት ቃል እናገራለሁ። እናም ሁለቱ ሀገሮች ሲገናኙ የሁለቱ ሀገሮች ምስክርነትም ደግሞ ይገናኛሉ።

እናም ይህን የማደርገውም ለብዙዎች እኔ ትናንትም፣ ዛሬና ለዘለዓለም አንድ መሆኔን፤ ቃሌንም በፈቃዴ መሰረት እንደምናገር አረጋግጥ ዘንድ ነው። እናም አንድ ቃል በመናገሬ ሌላ መናገር አይችልም ብላችሁ ትገምታላችሁ፤ ምክንያቱም ስራዬ ገና አላለቀም፤ ወይም ይህ እስከ ሰው ዘር መጨረሻ፣ ከዚያም እስከ ዘለዓለም ድረስ አያልቅም።

ስለሆነም፣ እናንተ መፅሐፍ ቅዱስ ስላላችሁ የእኔን ቃል ሁሉ ይዟል ብላችሁ አታስቡ፤ እኔን ሌላም እንዲፃፍ አላደርግም ብላችሁ አታስቡ።

፲፩ በምስራቅና በምዕራብና፣ በሰሜን፣ እናም በደቡብና፣ በባህሩ ደሴት ያሉትን ሰዎች ሁሉ እኔ የተናገርኳቸውን ቃላት ሁሉ ይፅፋ ዘንድ አዛቸዋለሁና፤ በመፅሐፉ ውስጥ በተፃፉትም፣ ማንኛውንም ሰው እንደስራው፣ በተፃፈው መሰረት ዓለምን እፈርዳለሁ

፲፪ እነሆም፣ ለአይሁዶች እናገራለሁ እናም ይፅፉታል፤ ለኔፋውያንም ደግሞ እናገራለሁ፣ እናም ይፅፉታል፤ እኔ መርቼ ያወጣኋቸው የእስራኤል ቤት ለሆኑት ለሌሎቹ ነገዶችም ደግሞ እናገራለሁ፣ እናም ይፅፉታል፤ እኔም ለሁሉም የምድር ሀገሮችም ደግሞ እናገራለሁ፣ እናም ይፅፉታል።

፲፫ እናም እንዲህ ይሆናል አይሁዶች የኔፋውያን ቃል ይኖራቸዋል፣ ኔፋውያንም የአይሁዶች ቃል ይኖራቸዋል፤ እናም ኔፋውያንና አይሁዶች የጠፉት የእስራኤል ነገዶች ቃል ይኖራቸዋል፤ እናም የጠፉት የእስራኤል ነገዶችም የኔፋውያንና የአይሁዶች ቃል ይኖሩዋቸዋል።

፲፬ እናም እንዲህ ይሆናል ከእስራኤል ቤት የሆኑት ህዝቤ በርስተ ምድራቸው ይሰበሰባሉ፤ እናም ቃሌም ደግሞ በአንድ ይሰበሰባል። ከቃሌና የእስራኤል ቤት ከሆኑት ህዝቤ ጋር የሚጣሉትን፣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔንና፣ ለአብርሃም ለዘለዓለም ዘሩን እንደማስታውስ ቃል መግባቴን አሳያቸዋለሁ።