ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፩


ሦስተኛው ኔፊ

የኔፊ መፅሐፍ
የሔለማን ልጅ የነበረው የኔፊ ልጅ

እናም ሔለማን፤ የአልማ ልጅ የነበረው፣ የአልማ ልጅ በሴዴቅያስ የመጀመሪያ የንግስ ዘመን የይሁዳ ንጉስ የነበረው ከኢየሩሳሌም የወጣው፣ የኔፊ ዝርያ የነበረውና የሌሂ ልጅ የነበረው፤ የሔለማን ልጅ ነበር።

ምዕራፍ ፩

የሔለማን ልጅ፣ ኔፊ፣ ከምድሪቱ ሄደ፤ እናም የእርሱ ልጅ ኔፊ መዛግብቱን ጠበቃቸው—ምልክቶች እንደዚሁም ድንቅ ነገሮች ብዙ ቢሆንም ኃጢአተኞች ፃድቃንን ለመግደል አቀዱ—የክርስቶስ መወለጃ ምሽትም ደረሰ—ምልክቱ ተሰጠ፣ እናም አዲስ ኮከብ ታየች—ውሸትና ማጭበርበር ተስፋፋ፣ እናም የጋድያንቶን ዘራፊዎች ብዙዎችን ገደሉ። ፩–፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ዘጠና አንደኛው ዓመት አለፈና ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣ ስድስት መቶ ዓመት ሆኖ ነበር፤ እናም ይኸውም ላኮኔዎስ በምድሪቱ ላይ ዋና ዳኛ የሆነበት ዓመት ነበር።

እናም የሔለማን ልጅ ኔፊ፣ የነሀስ ሠሌዳዎቹን በተመለከተና የተፃፉትን መዛግብት በሙሉ፣ እናም ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በቅድስና የተቀመጡትን ነገሮች በሙሉ በተመለከተ ለታላቁ ልጁ ለኔፊ ኃላፊነትን ሰጥቶት ከዛራሔምላ ምድር ሄደ።

ከዚያም ከምድሪቱ ተለይቶ ሄደ፣ እናም የሔደበትን ስፍራ ማንም አያውቅም ነበር፤ እናም ልጁ ኔፊ መዛግብቶቹን፣ አዎን፣ የዚህን ህዝብ መዝገብ በእርሱ ምትክ ሆኖ አስቀመጠ።

እናም እንዲህ ሆነ በዘጠና ሁለተኛው ዓመት መጀመሪያ፣ እነሆ፣ የነቢያቱ ትንቢት ይበልጥ በሙላት መፈፀም ጀመረ፤ በህዝቡ መካከል ታላላቅ ምልክቶች እናም ታላላቅ ተዓምራቶች መሆን ጀምረዋልና።

ነገር ግን በላማናዊው ሳሙኤል የተነገሩት ቃላት የተፈፀሙበት ጊዜው አልፎአል ሲሉ ጥቂቶች መናገር ጀምረው ነበር።

እናም በወንድሞቻቸው ሁኔታም በመደሰት እንዲህ ማለት ጀመሩ፥ እነሆ ጊዜው አልፎአልና የሳሙኤልም ቃላት አልተፈጸሙም፤ ስለዚህ፣ እናም ይህን ነገር በተመለከተ ደስታችሁና እምነታችሁ ከንቱ ነው።

እናም እንዲህ ሆነ እነርሱም በምድሪቱ ላይ ታላቅ ረብሻ አደረጉ፤ እናም የተነገሩት ነገሮች እንደማይፈጸሙ በመፍራት ያመኑት ሰዎች እጅግ ማዘን ጀመሩ።

ነገር ግን እነሆ፣ እምነታቸው ከንቱ አለመሆኑን ያውቁ ዘንድ ያንን ቀንና ያንን ምሽት፣ እናም ምንም ምሽት የሌለበትን እንደ አንድ ቀን የሚመስለው ቀን የሚሆንበትን በጽናት ጠበቁ።

እንግዲህ እንዲህ ሆነ በነቢዩ ሳሙኤል የተሰጠው ምልክት ካልተፈፀመ በስተቀር ሁሉም በነዚያ ወጎች የሚያምኑት እንዲሞቱ የሚደረግበት በማያምኑት የተመረጠ አንድ ቀን ነበረ።

እናም እንዲህ ሆነ የኔፊ ልጅ፣ ኔፊ፣ ይህንን የህዝቡን ክፋት በተመለከተ ጊዜ፣ ልቡ እጅግ አዝኖ ነበር።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ እርሱም ሄደና በምድሪቱ ላይም ወደቀ፣ እናም ወደ አምላኩ ለህዝቡ፣ አዎን፣ በአባቶቻቸው ወግ ላይ ባላቸው እምነት የተነሳ ሊጠፉ ለተቃረቡት ድገፋ በኃይል ጮኸ።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ቀኑን በሙሉ ወደ ጌታ በኃይል ጮኸ፤ እናም እነሆ የጌታ ድምፅ እንዲህ ሲል ወደ እርሱ መጣ፥

፲፫ ራስህን አቅና፤ እናም ተደሰት፤ እነሆም፣ ጊዜው ቀርቧልና፣ በዚህች ምሽትም ምልክት ይሰጣል፣ እናም በሚቀጥለውም ቀን በቅዱሳን ነቢያቶቼ አንደበት እንዲነገሩ ያደረግሁአቸውን በሙሉ እንደሚፈጸሙ ለዓለም ለማሳየት ወደ ዓለም እመጣለሁ።

፲፬ እነሆ፣ ከዓለም መፈጠር ጀምሮ ለሰው ልጆች እንዲያውቋቸው ያደረኳቸውን ነገሮች በሙሉ ለመፈጸም፣ እናም የአብንና፣ የወልድን ፈቃድ፣ የአብን ፈቃድ በእኔም አማካኝነት፣ እናም የወልድን በስጋዬም አማካኝነ ለመፈጸም እመጣለሁ። እናም እነሆ፣ ጊዜው ተቃርቧል፤ በዚህች ምሽትም ምልክቱ ይሰጣል።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ለኔፊ የተነገሩት ቃላት እንደተነገሩት ተፈጸሙ፤ እነሆም፣ ፀሀይ በምትጠልቅበት ጊዜ ጨለማ አልነበረም፤ እናም ምሽት በሆነም ጊዜ ጨለማ ባለመኖሩ ሰዎች መገረም ጀምሩ።

፲፮ እናም የነቢያቱን ቃላት የማያምኑ፤ በመሬት ላይ የወደቁ እናም የሞቱ የሚመስሉ ብዙዎች ነበሩ፤ ምክንያቱም ታላቁ የጥፋት ዕቅድ በነቢያቱ ቃላት ለሚያምኑት የተወጠነው እንዳልተሳካ ያውቃሉና፤ ተሰጥቶ የነበረው ምልክት ቀድሞውኑ ቀርቦአልና።

፲፯ እናም የእግዚአብሔር ልጅ በአጭር ጊዜ እንደሚታይ ማወቅ ጀመሩ፤ አዎን በአጠቃላይ በምድር ገጽ ላይ ያሉት፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ፤ በምድሪቱ በስተሰሜን እስከደቡብ ያሉት ሰዎች በሙሉ ወደ መሬት እስከሚወድቁም ድረስ እጅግ ተደንቀው ነበር።

፲፰ ነቢያቶቹ ስለ እነዚህ ነገሮች ለብዙ ዓመታት መመስከራቸውን፣ እናም የተሰጣቸውም ምልክት መድረሱን አውቀዋልና፤ እናም በክፋታቸውና ባለማመናቸው ምክንያት መፍራት ጀመሩ።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ በዚያን ምሽት በሙሉ ምንም ጨለማ አልነበረም፣ ነገር ግን እንደ እኩለ ቀን ብርሃን ነበር። እናም እንዲህ ሆነ በትክክለኛው ስርዓት መሰረት፣ በጠዋቱ በድጋሚ ፀሀይ ወጣችና፣ በተሰጠው ምልክትም የተነሳ ቀኑም ጌታ የሚወለድበት መሆኑን አውቀው ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ፣ አዎን፣ ሁሉም ነገሮች፣ እያንዳንዱም በነቢያቱ ቃላት መሰረት ነበሩ።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ ደግሞም እንደቃሉ አዲስ ኮከብ ታየ።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ ከዚህ ጊዜ በኋላ ልባቸውን እንዲያጠጥር፤ በታዩትም ምልክቶች እንዲሁም አስገራሚ ነገሮች እንዳያምኑ በሰይጣን አማካኝነት በሰዎች መካከል ውሸት መሰራጨት ጀመረ፤ ነገር ግን እነዚህ ውሸቶችና ማጭበበር ቢኖሩም አብዛኞቹ ማመን ጀመሩ፣ እናም ወደ ጌታ ተለወጡ።

፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ኔፊና፣ ብዙ ሌሎች፣ በሰዎቹ መካከል ለኃጢያት ታላቅ ስርየት ወደሚገኝበት ንስሃ ለማጥመቅ ሔደ። እናም ሰዎቹ በድጋሚ በምድሪቱ ሠላምን ማግኘት ጀመሩ።

፳፬ እናም ጥቂቶች የሙሴን ህግጋት ማክበር አስፈላጊ አለመሆኑን በቅዱሳን መጻህፍት ለማረጋገጥ በመስበክ ጥረት ከሚያደርጉት በስተቀር ፀብ አልነበረም። እንግዲህ በዚህ ነገርም ቅዱሳን መጽሐፍትን ባለመረዳታቸው ስህተትን ፈጽመው ነበር።

፳፭ ነገር ግን እንዲህ ሆነ በአፋጣኝ ተለወጡ፣ እናም የነበሩትንም ስህተቶች እንዲያውቁ ተደርገው ነበር፤ ምክንያቱም ህጉ ገና አለመፈጸሙ፤ እናም በማንኛውም ሁኔታም ሁሉም መፈፀም እንደሚገባቸው እንዲያውቁት ተደርገዋል፤ አዎን፣ ይህም መፈፀም እንዳለበት ቃል ወደ እነርሱ መጣ፤ አዎን፣ ሁሉም እስከሚፈፀም አንዲት ነጥብ ወይም ምልክት አታልፍም፤ ስለዚህ በዚሁ ዓመት ስህተታቸውን እንዲያውቁ ተደርገው ነበር፣ እናም ጥፋታቸውን ተናዘዙ

፳፮ እናም የሁሉም ቅዱሳን ነቢያት የትንቢት ቃላት መሰረት የተሰጡት ምልክቶች በመፈፀም የተነሳ ዘጠና ሁለተኛው ዓመት ምስራች ለህዝቡ አምጥቶ አለፈ።

፳፯ እናም እንዲህ ሆነ በተራራ ከሚኖሩት፣ ምድርን ከወረሩት፣ ይዞታቸውና የሚስጥር ቦታቸው በጣም ጠንካራ ሆኑ ሰዎች ሊያሸንፏቸው ከማይችሉት የጋድያንቶን ዘራፊዎች በስተቀር ዘጠና ሶስተኛው ዓመት በሰላም ዓለፈ፣ ስለዚህ በርካታ ግድያዎች እናም በህዝቡ ውስጥ ብዙ ግድያዎችን ፈጸሙ፤

፳፰ እናም እንዲህ ሆነ ወደ እነርሱ የሸሹ ብዙ ኔፋውያን ተቃዋሚዎች በመኖራቸው፤ እነርሱም በምድሪቱ በቀሩት ኔፋውያን ላይ ታላቅ ሀዘን እንዲሆን ባደረጉት ምክንያት በዘጠና አራተኛው ዓመት በታላቅ መጠን መጨመር ጀመሩ።

፳፱ እናም ደግሞ በላማናውያን መካከል የታላቁ ሀዘን መንስኤ ነበር፤ እነሆም፣ የደረሱ እናም ዕድሜአቸው የጨመረ ብዙ ልጆች ነበሩአቸውና እናም ራሳቸውን ቻሉና፣ ከጋድያንቶን ዘራፊዎች ጋር እንዲቀላቀሉ ዞራማዊ በነበሩ በጥቂቶች በውሸታቸው እንዲሁም በሸንጋዩ ቃላቶቻቸው ተመርተው ነበርና።

እናም ደግሞ ላማናውያን እንደዚህ ተሰቃዩ፣ እናም በሚያድገው ትውልድ ኃጢያት የተነሳም እምነታቸውና ፅድቃቸው መመናመን ጀመረ።