ምዕራፍ ፲
ሌሂ ከምናሴ የዘር ሐረግ ነው—አሙሌቅ ለአልማ የሆነውን መለኮታዊ ትዕዛዝ አወሳ—የፃድቃኖች ፀሎት ህዝቡ እንዲድኑ ያደርጋል—ፃድቅ ያልሆኑት ጠበቆች እና ዳኞች ለህዝቡ ጥፋት መሰረትን ይጥላሉ። በ፹፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እንግዲህ እነዚህ በአሞኒሀ ምድር ለነበሩት ሰዎች አሙሌቅ እንዲህ በማለት የሰበካቸው ቃላት ናቸው፥
፪ እኔ አሙሌቅ ነኝ፤ የአሚናዲ የዘር ሐረግ የሆነው የእስማኤል ልጅ የሆነው የጊዶናን ልጅ ነኝ፤ እናም ይኸው እራሱ አሚናዲ ነበር በእግዚአብሔር እጅ በቤተመቅደሱ ግድግዳ ላይ የተፃፈውን የተረጎመው።
፫ እናም አሚናዲ የኔፊ የዘር ሐረግ፣ ከኢየሩሳሌም ምድር የወጣው፣ የምናሴ የዘር ሐረግ የሆነው የሌሂ ልጅ ነበር፣ እርሱም በወንድሞቹ እጅ ወደግብፅ የተሸጠው የዮሴፍ ልጅ ነበር።
፬ እናም እነሆ፣ እኔን በሚያውቁኝ ሰዎች ሁሉ መካከል ትንሽ ዝና ያለኝ ሰው አይደለሁም፤ አዎን፣ እናም እነሆ ብዙ ነገድና፣ ወዳጆች አሉኝ፤ ታታሪ ሆኜ በመስራትም ደግሞ ብዙ ሀብትን አፍርቻለሁ።
፭ ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ሁሉ በኋላ፣ የጌታን መንገድ እናም ሚስጥሩንና ድንቅ ኃይሉን ብዙም አላውቅም ነበር። እነዚህን ነገሮች ብዙም አላውቅም እላለሁ፤ ነገር ግን እነሆ፣ ስህተተኛ ነኝ፣ የእርሱን ሚስጥሮችና አስደናቂ ሀይል አይቻለሁና፤ አዎን፣ እንዲሁም የዚህን ሕዝብ ሕይወት ሲጠብቅም።
፮ ይሁን እንጂ፣ ብዙ ጊዜ ተጠርቼ ባለመስማቴ ልቤን አጠጥሬ ነበር፤ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ አወቅሁ፤ ሆኖም ይህን ለማወቅም አልፈቀድኩም፤ ስለዚህ በልቤ ክፋት በመሳፍንቱ አስረኛ ዓመት የንግስ ዘመን እስከ ሰባተኛው ወር አራተኛ ቀንም ድረስ እንኳን በእግዚአብሔር ላይ ለማመፅ ሄድኩ።
፯ የቅርብ ዘመዴን ለማየት በተጓዝኩ ጊዜ፣ እነሆ የጌታ መልአክ ታየኝና እንዲህ አለኝ፥ አሙሌቅ የጌታን ነቢይ፣ አዎን፣ ቅዱሱን ሰው፣ በእግዚአብሔር የተመረጠውን ሰው፣ ምግብን ትመግበዋለህና ወደ ራስህ ቤት ተመለስ፤ በዚህ ህዝብ ኃጢያት የተነሳ ለብዙ ቀናት ጾሟል፣ ተርቧልም፣ እናም በቤትህ ተቀብለህ መግበው፣ እርሱም አንተንና ቤትህን ይባርካል፤ እናም የጌታ በረከት በአንተና በቤትህ ላይ ይሆናል።
፰ እናም እንዲህ ሆነ ለመልአኩም ድምፅ ታዘዝኩና፣ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። እናም በምሄድበት ጊዜ መልአኩ በቤትህ ትቀበለዋለህ ሲል የተናገረኝን ሰው አገኘሁት—እናም እነሆ ይህም የእግዚአብሔርን የሆኑትን በተመለከተ ሲያናገራችሁ የነበረው ሰው ራሱ ነበር።
፱ እናም መልአኩ እርሱ ቅዱስ ሰው ነው አለኝ፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር መልአክ የተነገረ ስለሆነ ቅዱስ መሆኑን አውቃለሁ።
፲ እናም በድጋሚ፣ እርሱ የመሰከራቸው ነገሮች እውነት መሆናቸውን አውቃለሁ፤ እነሆም እንዲህ እላችኋለሁ፣ ጌታ ሕያው እንደሆነ እነዚህን ነገሮች ለእኔ ለመግለፅ መልአኩን ልኳል፤ እናም እርሱ ይህንን ያደረገው አልማ በእኔ ቤት በቆየበት ወቅት ነው።
፲፩ እነሆም፣ ቤቴን ባርኳል፣ እኔን፣ ሚስቴን፣ ልጆቼንና፣ አባቴን እናም ዘመዶቼን ባርኳል፤ አዎን፣ ዘሮቼን በሙሉ ባርኳል፣ እናም ጌታ በተናገረው ቃል መሰረት በረከቱ በእኛ ላይ ሆኗል።
፲፪ እናም አሁን፣ አሙሌቅ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ እነርሱ የተከሰሱባቸውን ነገሮች እናም ደግሞ በውስጣቸው ባለው የትንቢት መንፈስ ስለሚመጡት ነገሮቹ የሚመሰክሩ ከአንድ ምስክር በላይ እንዳለ በመመልከታቸው ህዝቡ መገረም ጀመረ።
፲፫ ይሁን እንጂ፣ በተንኮል ስራቸው በቃላቸው ይይዟቸው ዘንድ፣ በእነርሱም ላይ ምስክር ያገኙባቸው ዘንድ፣ በህግ መሰረት እንዲፈረድባቸው ወደ ዳኛዎቻቸው አሳልፈው ይሰጧቸው ዘንድ፣ እና በሚያስመስሉት ወይም በእነርሱ ላይ በሚመሰክሩባቸው ወንጀል መሰረት እንዲገደሉ ወይም ወደ እስር ቤት እንዲጣሉ ዘንድ እነርሱን ለመጠየቅ ያሰቡ በመካከላቸው አንዳንድ ነበሩ።
፲፬ አሁን እነዚህ ጠበቆች የነበሩት፣ በፍርድ ጊዜ በዳኞቹ ፊት በወንጀሉ ህጉን እንዲዳኙ በህዝቡ የተቀጠሩት፣ እንዲሁም የተሾሙት ሰዎች ሊያጠፏቸው ሲፈልጉ የነበሩ ናቸው።
፲፭ አሁን እነዚህ ጠበቆች የህዝቡን ጥበብና ሴራ ሁሉ የተማሩት ናቸው፣ እናም ይህ በሙያቸው ባለሙያ እንዲሆኑ እንዲያስችላቸው ነው።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ አሙሌቅን ቃሉን እንዲያጥፍ ያደርጉት ዘንድ ወይም ለሚናገረውን ተቃራኒ ይሆኑ ዘንድ ይጠይቁት ጀመር።
፲፯ እንግዲህ አሙሌቅ ዕቅዳቸውን ለማወቅ እንደሚችል አያውቁም። ነገር ግን እንዲህ ሆነ እርሱን መጠየቅ ሲጀምሩ፣ ሀሳባቸውን ገመተ እናም እንዲህ አላቸው፥ እናንተ ክፉና ጠማማ ትውልድ፣ ጠበቆች እና ግብዞች፣ የዲያብሎስን መሰረት እየመሰረታችሁ ናችሁና፤ የእግዚአብሔርን ቅዱሳን ለመያዝ መያዣና ወጥመድ ዘርግታችኋልና።
፲፰ የፃድቃኖችን መንገድ ለማጣመም፣ እናም የእግዚአብሔርን ቁጣ በራሳችሁ ላይ እንዲመጣ ለማድረግ፣ ለዚህ ህዝብ ፍፁም ጥፋት እንኳን ዕቅድ አዘጋጅታችኋል።
፲፱ አዎን፣ የመጨረሻው ንጉሳችን ሞዛያ የሚሾመው ማንም የለምና፣ ይህ ህዝብም በራሱ ድምፅ እንዲመራ በማድረግ መንግስቱን ለመስጠት በተቃረበበት ወቅት፣ በጥሩ ሁኔታ እንዲህ ብሏል—አዎን፣ እርሱ ጥሩ ተናግሯል፣ የዚህ ህዝብ ድምፅ ክፋትን የሚመርጥበት ጊዜው መምጣት ካለበት፣ ይህም ማለት ህዝቡ በመተላለፍ የሚወድቅበት ጊዜው የሚመጣ ከሆነ ለጥፋትም ይደርሳሉ።
፳ እናም አሁን እንዲህ እላችኋለሁ፣ ጌታ ክፋታችሁን በጥሩ ሁኔታ ይፈርዳል፤ በተገቢው ሁኔታም ለህዝቡ በመልአኩ ድምፅ፤ ንስሃ ግቡ፣ ንስሃ ግቡ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና በማለት ይጮሀል።
፳፩ አዎን፣ በመልአኩ ድምፅ በተገቢው ሁኔታ እንዲህ በማለት ይጮሀል፥ በህዝቤ መካከል ፍትህንና ፍርድን በእጄ ይዤ እመጣለሁ።
፳፪ አዎን፣ እናም በምድሪቱ አሁን ባሉት ፃድቃኖች ፀሎት ባይሆን ኖሮ፣ ፍፁም በሆነው ጥፋቱ አሁን ይጎበኛችሁ ነበር እላለሁ፤ ይሁን እንጂ በኖህ ጊዜ እንደነበሩት ሰዎች በጥፋት ውሀ አይሆንም፣ ነገር ግን በረሃብና፣ በቸነፈር እንዲሁም በጎራዴ ይሆናል።
፳፫ ነገር ግን በፃድቃኖች ፀሎት ድናችኋል፤ አሁንም ስለዚህ ፃድቃኖችን ከመካከላችሁ ከጣላችሁ ጌታ እጁን አያሳርፍም፤ ነገር ግን በኃያሉ ቁጣው በእናንተ ላይ ይመጣል፤ በረሃብና በቸነፈር እንዲሁም በጎራዴ ትመታላችሁ፤ እናም ንስሃ ካልገባችሁ በቀር ጊዜው ቀርቧል።
፳፬ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ህዝቡ ይበልጥ በአሙሌቅ ተቆጣ፣ እናም እንዲህ በማለትም ጮኹ፥ ጻድቅ በሆነው ህጋችን ላይ፣ እናም በመረጥናቸው በብልሁ ጠበቃዎቻችን ላይ ይህ ሰው ክፉን ይናገራል።
፳፭ ነገር ግን አሙሌቅ እጁን ዘረጋ፣ እናም በኃይል እንዲህ በማለት ጮኸ፥ አቤቱ እናንት ክፉና ጠማማ ትውልድ፣ ሰይጣን ለምን በልባችሁ ትልቅ ቦታን ይይዛል? ለምንስ በእናንተ ላይ እንደእውነቱ የተነገሩትን ቃላት እንዳትረዱ ዐይናችሁን ለማሳወር ስልጣን እንዲኖረው ራሳችሁን ትሰጡታላችሁ?
፳፮ እነሆም በህጋችሁ ተቃራኒን መስክሬአለሁን? እናንተም አትረዱም፤ ከህጋችሁ ተቃራኒን ተናግረሃል ትላላችሁ፤ ነገር ግን እኔ አልተናገርኩም፣ ነገር ግን ህጋችሁን በመደገፍ ኩነኔአችሁን ተናግሬአለሁ።
፳፯ እናም አሁን እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ የዚህ ህዝብ ጥፋት መሰረቱ ፃድቃን ባልሆኑት ጠበቆቻችሁና ዳኞቻችሁ መጣል ጀምሯል።
፳፰ እናም አሁን እንዲህ ሆነ አሙሌቅ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ ህዝቡ እንዲህ በማለት በእርሱ ላይ ጮኸ፥ አሁን ይህ ሰው የዲያብሎስ ልጅ እንደሆነ እናውቃለን እኛን ዋሽቶናልና፤ ከህግጋቶቻችንም ተቃራኒ የሆነውን ተናግሯልና። እናም አሁን ይህን አለመቃረኑን ይናገራል።
፳፱ እናም በድጋሚ፣ ጠበቆቻችንና ዳኞቻችንን አጥብቆ ነቅፏል።
፴ እናም እንዲህ ሆነ እነዚህን ነገሮች በእርሱ ላይ እንዲያስታውሱ ጠበቆቹ በልባቸው አስቀመጡት።
፴፩ እናም ከእነርሱ መካከል ዚኤዝሮም የሚባል አንድ ሰው ነበር። ከእነርሱ መካከል ዋና ባለሙያ በመሆን በህዝቡም መካከል በርካታ እንቅስቃሴዎችን ስለነበረው አሙሌቅንና አልማን ለመክሰስ ግንባር ቀደም ነበር።
፴፪ አሁን የጠበቆቹ ዓላማ ገንዘብ ለማግኘት ነበር፤ እናም በተቀጠሩበት መሰረትም ገንዘብን ያገኛሉ።