ምዕራፍ ፴፫
ዜኖስ ሰዎች በሁሉም ስፍራ መፀለይ፣ እና ማምለክ እንዳለባቸው፣ እናም ፍርድም በወልድ አማካኝነት እንደሚለውጥ አስተማረ—ዜኖቅ በወልድ አማካኝነት ምህረት እንደሚሰጥ አስተማረ—ሙሴ በምድረበዳው የእግዚአብሔርን ልጅ ምሣሌ የሆነውን አንስቷል። በ፸፬ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አልማ እነዚህን ቃላት ከተናገረ በኋላ፣ እርሱ የተናገረውንም ፍሬ ያገኙ ዘንድ በአንድ አምላክ ማመን እንዳለባቸው፣ ወይንም ዘሩን ወይም በልባቸው መትከል ይገባቸዋል ብሎ እርሱ ስለተናገረው ቃል እንዴት እንደሚተክሉ፣ ወይም እንግዲህ በምን ዓይነት ሁኔታ እምነትን መለማመድ እንዳለባቸው ለማወቅ በመፈለግ ላኩበት።
፪ እናም አልማ እንዲህ አላቸው፥ እነሆ፣ ከምኩራባችሁ በመባረራችሁ አምላካችሁን ማምለክ እንደማትችሉ ተናግራችኋል። ነገር ግን እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፤ አምላክን ማምለክ አንችልም ብላችሁ ከገመታችሁ እጅግ ተሳስታችኋል፤ እናም ቅዱሳት መፃሕፍትን መመርመር አለባችሁ፤ ይህንን አስተምረውናል ብላችሁ ከገመታችሁ አልተረዳችኋቸውም።
፫ የጥንቱ ነቢይ ዜኖስ፣ ፀሎትን እና አምልኮትን በተመለከተ የተናገረውን ማንበባችሁን ታስታውሳላችሁን?
፬ እርሱም እንዲህ ብሏልና፥ እግዚአብሔር ሆይ፣ ፀሎቴን በምድረበዳው በነበርኩበት ጊዜም እንኳን ስለሰማኸኝ አንተ መሃሪ ነህ፤ አዎን፣ ጠላቶቼ ለሆኑትም ለእነዚያ በፀለይኩኝ ጊዜ መሃሪ ነበርክ፣ እናም እነርሱም ለእኔ ደግ እንዲሆኑልኝ አድርገሃል።
፭ አዎን፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ እናም በስፍራዬ ሆኜ ወደአንተ ስጮህ ምህረትን ሰጥተኸኛል፣ በፀሎቴ ወዳንተ ስጮህ እነሆ ሰምተኸኛል።
፮ እናም በድጋሚ አቤቱ እግዚአብሔር ወደቤቴም በተመለስኩኝ ጊዜ ፀሎቴን ሰምተሃል።
፯ እናም፣ ጌታ ሆይ፣ ወደ እልፍኜም በሄድኩኝ ጊዜና ወደ አንተ በፀለይኩ ጊዜ ሰምተኸኛል።
፰ አዎን ልጆችህ በሰዎች ሳይሆን በአንተ እንዲሰሙ ወደ አንተ ሲጮሁ መሃሪ ነህ፣ እናም አንተ ትሰማቸዋለህ።
፱ አዎን፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ለእኔ መሃሪ ሆነሀል፣ እናም በጉባዔህም መካከል ጩኸቴን ሰማህ።
፲ አዎን፣ እናም በተጣልኩና በጠላቶቼ በተጠላሁ ጊዜ ደግሞ ሰምተኸኛል፤ አዎን፣ ጩኸቴን ሰምተሃልና፣ በጠላቶቼም ተቆጥተሃል፣ እናም በፈጣኑ ጥፋትህም በቁጣህ ጎብኝተሃቸዋል።
፲፩ እናም በሥቃዬና በቅንነቴ ምክንያት ሰምተኸኛል፤ እናም በልጅህ አማካኝነት ለእኔ መሃሪ ሆነሃል፤ ስለዚህ በስቃዬ ሁሉ ወደአንተ እጮሀለሁ፣ ደስታዬ በአንተ ነውና፤ በልጅህ አማካኝነት ፍርድህን ከእኔ አርቀሃልና።
፲፪ እናም አሁን አልማ እንዲህ አላቸው፥ በጥንት ነቢያት የተፃፉትን እነዚያን ቅዱሳት መጻሕፍት ታምናላችሁን?
፲፫ እነሆ፣ የምታምኑ ከሆነ፣ ዜኖስ የተናገረውን ማመን አለባችሁ፤ እነሆ እርሱ እንዲህ ብሏልና፥ በልጅህ አማካኝነት ቅጣትህን አርቀሀል።
፲፬ እናም እነሆ፣ ወንድሞቼ፣ ቅዱሳን መጽሐፍትን አንብባችሁ እንደሆን እጠይቃችኋለሁ? ካነበባችሁ የእግዚአብሔርን ልጅ እንዴት ላታምኑ ትችላላችሁ?
፲፭ ስለእነዚህ ነገሮች የተናገረው ዜኖስ ብቻ ነው ተብሎ አልተጻፈም፣ ነገር ግን ዜኖቅ ደግሞ ስለእነዚህ ነገሮች ተናግሯል—
፲፮ እነሆም እርሱ እንዲህ ብሏል፥ ጌታ ሆይ፣ ይህ ህዝብ በልጅህ አማካኝነት የሰጠኸውን ምህረት ስለማይረዳ አንተ ተቆጥተሀል።
፲፯ እናም አሁን፣ ወንድሞቼ፣ ከጥንት ነቢያት ሁለተኛው ስለእግዚአብሔር ልጅ መስክሯል፣ እናም ህዝቡ ቃሉን ስላላመኑ በድንጋይ ወግረው ገደሉት።
፲፰ ነገር ግን እነሆ፣ ይህ ብቻም አይደለም፤ ስለእግዚአብሔር ልጅ የተናገሩት እነዚህ ብቻ አይደሉም።
፲፱ እነሆ ሙሴም ስለእርሱ ተናግሮ ነበር፤ አዎን፣ እናም እነሆ፣ ይህን ቀና ብሎ የተመለከተ እንዲኖር ዘንድ እንደ ምሳሌ የሆነው በምድረበዳው ተሰቅሎ ነበር። እናም ብዙዎች ተመለከቱና፣ በህይወት ኖሩ።
፳ ነገር ግን የነገሮቹን ትርጉም ጥቂቶች ብቻ ተረዱ፣ እናም ይህም የሆነው በልባቸው ጠጣርነት የተነሳ ነው። ነገር ግን ብዙ ልበ ጠጣሮች ስለነበሩ አልተመለከቱም፣ ስለዚህም ጠፉ። ያንንም ያልተመለከቱበት ምክንያት እነርሱን እንደሚፈውስ ባለማመናቸው ነበር።
፳፩ ወንድሞቼ ሆይ፣ ትፈወሱ ዘንድ በቀላሉ በዓይናችሁ በመመልከት ለመፈወስ የምትችሉ ከሆነ፣ በፍጥነት አትመለከቱምን፣ ወይንስ ትጠፉ ዘንድ ዐይኖቻችሁን በዚያ ላይ ባለማመንስ ልባችሁን ማጠጠር፣ እናም ሰነፍ መሆን ይሻላችኋልን?
፳፪ እንዲህ ከሆነ፣ ዋይታ በላያችሁ ይመጣባችኋል፤ ነገር ግን ይህም ካልሆነ፣ በዐይናችሁ ወደዚህና ወደዚያ ተመልከቱ፣ እናም የእግዚአብሔር ልጅ ህዝቡን ሊያድን እንደሚመጣና፣ ለህዝቡ ኃጢያት ክፍያ እንደሚሰቃይና እንደሚሞት፣ እናም ሰዎች እንደስራቸው በመጨረሻውና በፍርዱ ቀን እንዲፈረድባቸው በፊቱ ይቆሙ ዘንድ ትንሳኤን ያመጣ ዘንድ በድጋሚ ከሙታን እንደሚነሳ ማመን ጀምሩ።
፳፫ እናም አሁን፣ ወንድሞቼ፣ ይህን ቃል በልባችሁ እንድትተክሉ እፈልጋለሁና፣ ማደግ በጀመረ ጊዜ በእምነታችሁ ተንከባከቡት። እናም እነሆ፣ እርሱም ዛፍ ይሆናል፣ እስከዘለዓለማዊው ህይወትም በእናንተ ያብባል። በልጁም ደስታ አማካኝነት ሸክማችሁን እንዲቀልልላችሁ እግዚአብሔር ይፍቀድላችሁ። እናም ይህን ሁሉ እንኳን ከፈቀዳችሁ ማድረግን ትችላላችሁ። አሜን።