ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፫


ምዕራፍ ፫

አምሊኪውያን እንደ ትንቢቱ ቃል እራሳቸው ላይ ምልክት አደረጉ—ላማናውያን በአመፃቸው ተረገሙ—ሰዎች እርግማናቸውን በላያቸው ላይ ያመጣሉ—ኔፋውያን ሌሎች የላማናውያንን ሠራዊት አሸነፉ። ከ፹፯–፹፮ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ በጦር መሳሪያ ያልተገደሉት ኔፋውያን የተገደሉትን ከቀበሩ በኋላ፣ የሞቱት ቁጥር ብዙ ስለነበሩ ለመቁጠር አይቻልም ነበር፣ የሞቱትን ከቀበሩ በኋላ በሙሉ ወደ ስፍራቸው እናም ወደ ቤታቸውና ወደ ሚስቶቻቸውና ወደ ልጆቻቸው ተመለሱ።

አሁን ብዙ ሴቶችና፣ ልጆች፣ ደግሞም ብዙ መንጋና፣ ከብቶቻቸው በጎራዴ ተገድለውባቸው ነበር፤ እናም ደግሞ በርካታ የእህል እርሻዎቻቸው ወድመዋል፣ በሰዎች ሰራዊት ተረጋግጠውባቸዋልና።

እናም አሁን በሲዶም ወንዝ ዳርቻ የተገደሉት ላማናውያንና አምሊኪውያን ሁሉ በሲዶም ወንዝ ውስጥ ተጥለው ነበር፤ እናም እነሆ በርካታ አጥንቶች በባህር ወለል ውስጥ ናቸው፣ እነርሱም ብዙ ናቸው።

እናም አምሊኪውያን እንደላማናውያን ግንባራቸው ላይ ቀይ ምልክት በማድረጋችው ከኔፋውያን ተለይተው ነበር፤ ይሁን እንጂ እንደላማናውያን ራሳቸው እንዲላጭ አላደረጉም።

እንግዲህ የላማናውያን ራስ ተላጭቶ ነበር፣ እናም ከታጠቁት ቆዳና ደግሞ ከታጠቁት የጦር መሳሪያና፣ ጦርና፣ ቀስትና፣ ድንጋይና፣ ወንጭፍና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮች በስተቀር እርቃናቸውን ነበሩ።

እናም አባቶቻቸው በኔፊ፣ በያዕቆብ፣ በዮሴፍ፣ እናም በሳም ፍፁምና ቅዱስ በሆኑት ወንድሞቻቸው ላይ በመተላለፋቸውና፣ በማመፃቸው ምክንያት በእርግማን በተደረገባቸው ምልክት መሰረት የላማናውያን ቆዳ ጥቁር ነበር።

እናም ወንድሞቻቸው ሊያጠፉአቸው ፈለጉ፤ ስለሆነም እነርሱ የተረገሙ ሆኑ፤ እናም ጌታ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ፣ አዎን፣ በላማንና በልሙኤል፣ ደግሞም በእስማኤል ልጆችና፣ በእስማኤላውያን ሴቶች ላይ ምልክትን አደረገባቸው።

እናም ይህ የተደረገው ዘሮቻቸው ከወንድሞቻቸው ዘሮች ጋር እንዲለዩ፣ ጥፋታቸውን ከሚያረጋግጠው ከተሳሳተው ባህል ጋር ራሳቸው እንዳይቀላቅሉና እንዳያምኑ ጌታ እግዚአብሔርም ይጠብቃቸው ዘንድ ነው።

እናም እንዲህ ሆነ ዘሩን ከላማናውያን ጋር የቀላቀለ ማንኛውም በዘሩ ላይ ተመሳሳይ እርግማንን ያመጣል።

ስለዚህ በላማናውያን መመራት የፈለገ ማንኛውም በስሙ ይጠራል፣ እናም በላዩ ላይም ምልክት ይደረግበታል።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ በላማናውያን ባህል የማያምን ነገር ግን፣ ከኢየሩሳሌም ምድር የመጡትን ታሪኮች፣ እናም የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ባመኑትና እነርሱን በሚጠበቁት፣ ደግሞ ትክክል በሆኑት፣ የአባቶቻቸውን ባህል የሚያምኑ ማንኛቸውም ከዚህ ጊዜ በኋላ ኔፋውያን ወይንም የኔፊ ህዝብ ተብለው ተጠርተዋል—

፲፪ እናም እውነት የሆነውን የህዝባቸውን፣ እናም ደግሞ የላማናውያንን ሰዎች ታሪክ ያስቀመጡት እነርሱ ናቸው።

፲፫ አሁን ወደ አምሊኪውያን እንደገና እንመለሳለን፣ በእነርሱም ላይ ደግሞ ምልክት ተደርጎባቸዋልና፤ አዎን፣ በራሳቸውም ላይ ምልክት፣ አዎን፣ በግንባራቸው ላይ ቀይ ምልክት አድርገዋል።

፲፬ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ተፈፅሟል፤ ለኔፊ የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸውና፥ እነሆ፣ ላማናውያንን ረግሜአለሁ፣ እናም ለኃጢአታቸው ንስሃ ካልገቡና፣ ምህረትን እንዳደርግላቸው ዘንድ ወደ እኔ ካልተመለሱ በስተቀር፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም እነርሱም ሆኑ ዘሮቻቸው ከአንተ ከዘሮችህ ይለዩ ዘንድ ምልክት አደርግባቸዋልሁ።

፲፭ እናም በድጋሚ፥ ዘሩን ከወንድሞችህ ጋር የደባለቀውን በላዩ ላይ ምልክትን አደርጋለሁ፣ እነርሱም ደግሞ የተረገሙ ይሆኑ ዘንድ።

፲፮ እናም በድጋሚ ከአንተና ከዘሮችህ ጋር የተጣላውን ምልክት አደርግበታለሁ።

፲፯ እናም በድጋሚ፣ ከአንተ የተለየም ከእንግዲህ የአንተ ዘር ተብሎ አይጠራም፣ አንተንና የአንተ ዘር ተብሎ የሚጠራውን ሁሉ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም እባርካለሁ፤ እናም እነዚህም ለኔፊና ለዘሮቹ የጌታ ቃል ኪዳን ነበሩ።

፲፰ አሁን አምሊኪውያን በግንባራቸው ላይ ምልክት ማድረግ ሲጀምሩ የእግዚአብሔር ቃል እንደተፈፀመ አያውቁም ነበር፤ ይሁን እንጂ በግልፅ ከእግዚአብሔር ጋር ለአመፃ መጡ፤ ስለዚህ እርግማኑ በእነርሱ ላይ መሆኑ አስፈላጊ ነበር።

፲፱ እንግዲህ እርግማኑን በራሳቸው ላይ እንዳመጡት እንድትረዱ እፈልጋለሁ፤ እናም የተረገመ ሰውም እርግማኑን በራሱ ላይ ያመጣል።

አሁንም እንዲህ ሆነ በላማናውያንና በአምሊኪውያን በዛራሄምላ ምድር ከተደረገው ውጊያ በኋላ ብዙ ቀንም ሳይቆይ፣ የመጀመሪያው ሠራዊት አምሊኪውያንን ባገኘበት ቦታ በኔፊ ህዝብ ላይ ሌሎች የላማናውያን ሠራዊት መጡ።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ እነርሱን ከምድራቸው ለማስለቀቅ ወታደሮች ተላኩ።

፳፪ እንግዲህ አልማ በቁስሉ በመሰቃየቱ በዚህ ጊዜ ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት አልሄደም ነበር፤

፳፫ ነገር ግን ብዙ ወታደሮችን ላከባቸው፤ እናም ሄደው በርካታ ላማናውያኖችን ገደሉ፣ እናም የቀሩትን ከድንበራቸው ነድተው አስወጡኣቸው።

፳፬ እናም ከዚያ በኋላ ለጊዜው በጠላቶቻቸው ስለማይቸገሩ በድጋሚ ወደ ምድራቸው ተመልሰው ሰላምን መመስረት ጀመሩ።

፳፭ አሁን እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሆኑት፣ አዎን፣ እነዚህ ሁሉ ጦርነቶችና ፀቦች የተጀመሩትና የተፈፀሙት በመሣፍንቱ በአምስተኛው ዓመት የንግስ ዘመን ነበር።

፳፮ እናም ዘለዓለማዊ ደስታን፣ ወይም ዘለአለማዊ ስቃይን እንዲቀበሉ፣ እንደታዘዙለት መንፈስ እንደስራቸው፣ መልካምም ይሁን መጥፎ ዋጋቸውን ያገኙ ዘንድ በአንድ ዓመት ውስጥ ሺህ እናም አስር ሺህ ነፍስ ወደ ዘለአለማዊ ዓለም ተላኩ።

፳፯ ማንኛውም ሰው በመታዘዝ በሰማው ደመወዙን ይቀበላል፣ እናም ይህ እንደ ትንቢቱ መንፈስ ቃል መሰረት ነው፤ ስለዚህ እንደ እውነቱ ይሁን። እናም የመሳፍንቱ የአምስተኛ ዓመት አገዛዝ እንደዚህ ተፈፀመ።