ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፰


ምዕራፍ ፰

አልማ በሜሌቅ አስተማረ፣ እናም አጠመቀ—በአሞኒሀ ተቀባይነትን አላገኘም እናም ወጥቶ ሄደ—መልአኩ እንዲመለስና ለህዝቡም ስለ ንስሃ እንዲጮህ አዘዘው—በአሙሌቅ ተቀባይነትን አገኘ፣ እናም ሁለቱ በአሞኒሃ ሰበኩ። በ፹፪ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ አልማ ሊፃፉ ያልቻሉትን ብዙ ነገሮች ለጌዴዎን ህዝብ ካስተማረ፣ የቤተክርስቲያኗን ስርዓት በዛራሔምላ ምድር እንዳደረገው ካቋቋመ በኋላ፣ ከጌዴዎን ምድር ተመለሰ፤ አዎን፣ ካከናወናቸው ስራዎች ራሱን ለማሳረፍ በዛራሔምላ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ።

እናም በኔፊ ህዝብ ላይ ዘጠነኛ የመሳፍንቱ ንግስና በዚሁ ተፈጸመ።

እናም እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ የአስረኛ ዓመት የንግስ ዘመን መጀመሪያ ላይ አልማ ከዚያ ቦታ ሄደና፣ ጉዞውን በሲዶም ወንዝ በስተምዕራብ፣ በምድረበዳው ዳርቻ በምዕራብ በኩል ወደ ሜሌቅ አደረገ።

እናም እርሱ በተሾመበት በእግዚአብሔር ቅዱሱ ስርዓት መሰረት በሜሌቅ ምድር ህዝቡን ማስተማር ጀመረ፤ እናም በሜሌቅ ምድር ሁሉ ህዝቡን ማስተማር ጀመረ።

እናም እንዲህ ሆነ ህዝቡ ከምድረበዳው በምድሪቱ ዳርቻ በኩል ያሉት ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። እናም በምድሪቱ ያሉት ሁሉም ተጠምቀው ነበር፤

በሜሌቅ ስራውን በጨረሰ ጊዜ ለቆ ሄደ፣ እናም በሜሌቅ በስተሰሜን በሚገኘው ምድር ለሶስት ቀናት ጉዞ አደረገ፤ እናም አሞኒሀ ወደምትባል ከተማ መጣ።

አሁን ምድራቸውንና ከተማቸውን፣ እናም መንደራቸውን፣ አዎን፣ ትናንሽ ከተሞቻቸውንም እንኳን ቢሆን ቦታውን መጀመሪያ በያዘው ሰው ስም መጥራት የኔፊ ህዝብ ልምድ ነበር፤ እናም ይህ ልምድ በአሞኒሀ ምድርም የሆነ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ አልማ ወደ አሞኒሀ ከተማ በመጣ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ለእነርሱ መስበክ ጀመረ።

አሁን ሰይጣን በአሞኒሀ ከተማ ያሉትን ሰዎች ልብ በጥብቅ ይዞ ነበር፤ ስለሆነም የአልማን ቃል አያዳምጡም ነበር።

ይሁን እንጂ አልማ በከተማ ባሉት ሰዎች ላይ እግዚአብሔር መንፈሱን ያፈስ ዘንድ በኃያሉ ፀሎቱም ከእግዚአብሔር ጋር ታገለ፤ በንስሃም ያጠምቃቸው ዘንድ በመንፈስ ብዙ ሰራ።

፲፩ ይሁን እንጂ ልባቸውን አጠጥረው እንዲህ አሉት፥ እነሆ፣ አንተ አልማ መሆንህን እናውቃለን፤ እናም እንደባህልህ በብዙ ቦታዎች ባቋቋምካቸው ቤተክርስቲያኖች ላይ ሊቀ ካህን መሆንህን እናውቃለን፤ እኛ ከአንተ ቤተክርስቲያን አይደለንም፣ እናም በእነዚህ ዓይነት የሞኞች ባህል አናምንም።

፲፪ እናም አሁን እኛ ከአንተ ቤተክርስቲያን ባለመሆናችን በእኛ ላይ ኃይል እንደሌለህ እናውቃለን፤ እናም የፍርድ ወንበሩንም ለኔፊያሀ ሰጥተሀል፣ ስለዚህ በእኛ ላይ ዋና ዳኛ አይደለህም።

፲፫ እንግዲህ ህዝቡ ይህንን በተናገረ ጊዜና ቃሉን ሁሉ በተቃወሙና፣ እርሱንም በሰደቡትና፣ ላዩ ላይ በተፉበትና፣ ከከተማቸው እንዲወጣ ባደረጉት ጊዜ፣ ከቦታው ሄደ፣ እናም አሮን ተብላ ወደምትጠራ ከተማ ጉዞውን አደረገ።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ሀዘኑ ከብዶት ከቦታውም በተጓዘ ጊዜ፣ በአሞኒሀ ከተማ ባሉት ሰዎች ክፋትም ምክንያትም በመከራና በነፍስ ስቃይ ተጓዘ፤ አልማ እንደዚህ በሀዘን ጫና እየተጓዘ እያለ እንዲህ ሆነ፣ እነሆ የጌታ መልአክ ታየው፣ እንዲህም አለው፥

፲፭ አልማ አንተ የተባረክህ ነህ፤ ስለዚህ ራስህን አቅና እናም ሀሴትን አድርግ፣ የምትደሰትበት ታላቅ ምክንያት አለህና፤ መልዕክቱንም ከተቀበልክ ከመጀመሪያው ጀምሮ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመጠበቅ ታማኝ በመሆንህ የትልቁ ደስታህ መንስኤ ሆነሀልና። እነሆ ይህንን ለአንተ የሰጠሁህ እኔ ነኝ።

፲፮ እናም እነሆ፣ አንተ ወደ አሞኒሀ ከተማ እንድትመለስና ለከተማው ህዝብ በድጋሚ እንድትሰብክ ለማዘዝ ተልኬአለሁ፤ አዎን፣ ለእነርሱም ስበክ። አዎን፣ ንስሃ ካልገቡ በቀር ጌታ እግዚአብሔር እንደሚያጠፋቸው ንገራቸው።

፲፯ እነሆም፤ በዚህ ጊዜ የህዝባቸውን ነፃነት ለማጥፋት ያጠናሉ፣ (ጌታም እንዲህ ብሏልና) ይህም እርሱ ለህዝቡ ከተሰጠው ስርዓት፣ ፍርድና ትዕዛዛት ተቃራኒ ነው።

፲፰ አሁን እንዲህ ሆነ አልማ ከጌታ መላዕክት መልዕክቱን ከተቀበለ በኋላ ወደ አሞኒሀ ከተማ በፍጥነት ተመለሰ። እናም ወደ ከተማዋ በሌላ መንገድ፣ አዎን በአሞኒሀ ከተማ በስተደቡብ በኩል ገባ።

፲፱ እናም አልማ ወደ ከተማው በገባ ጊዜ ተርቦ ነበር፣ እናም ለአንድ ሰው እንዲህ አለው፥ ለትሁት የእግዚአብሔር አገልጋይ የሚበላውን ትሰጠዋለህን?

እናም ሰውየው እንዲህ አለው፣ እኔ ኔፋውያን ነኝ፣ እናም አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነቢይ እንደሆንክ አውቃለሁ፣ መልአኩ በራዕይ ትቀበለዋለህ ያለኝ ሰው አንተን ነህና። ስለዚህ፣ ወደ ቤቴ ከእኔ ጋር ሂድና፣ ምግቤን ከአንተ ጋር እካፈላለሁ፤ እናም ለእኔና ለቤቴ በረከት እንደምትሆን አውቃለሁ።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ ሰውየው በቤቱ ተቀበለው፤ ሰውየውም አሙሌቅ ይባል ነበር፤ እናም ዳቦና ስጋን በአልማ ፊት አቀረበለት።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ አልማ ዳቦ በላና ጠገበ፤ እናም አሙሌቅንና ቤቱን ባረከና ለእግዚአብሔር ምስጋናን አቀረበ።

፳፫ እናም ከበላና ከጠገበ በኋላ ለአሙሌቅ እንዲህ አለው፥ እኔ አልማ ነኝ፣ እናም በምድሪቱ ላይ ባሉት የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያናት ሊቀ ካህን ነኝ።

፳፬ እናም እነሆ፣ በራዕይና በትንቢት መንፈስ መሰረት በእዚህ ህዝብ ሁሉ መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ ተጠርቻለሁ፤ በዚህም ምድር ነበርኩ እናም እነርሱ አልተቀበሉኝም፣ ነገር ግን አስወጡኝ፣ እናም ለዘለአለም ወደዚህች ምድር ጀርባዬን ለመስጠት እያለሁ ነበር።

፳፭ ነገር ግን እነሆ፣ ለዚህ ህዝብ በድጋሚ ተመልሼ እንድተነብይ፣ አዎን እናም ክፋታቸውንም በተመለከተ በእነርሱ ላይ እንድመሰክር ታዝዤአለሁ።

፳፮ እናም አሁን፣ አሙሌቅ ስለመገብከኝና ስለተቀበልከኝ የተባረክህ ነህ፤ ለብዙ ቀንም በመፆሜ ተርቤ ነበርና።

፳፯ እናም አልማ ለህዝቡ መስበክ ከመጀመሩ በፊት ለብዙ ቀናት ከአሙሌቅ ጋር ቆየ።

፳፰ እናም እንዲህ ሆነ ሰዎቹ በኃጢአታቸው አስቀያሚነት እያደጉ ሄዱ።

፳፱ እናም ቃሉም ወደ አልማ እንዲህ ሲል መጣ፤ ሂድ፤ እናም ደግሞ ለአገልጋዬ ለአሙሌቅ፣ ለዚህ ህዝብ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናገር በለው—ንስሃ ግቡ፣ ጌታ ንስሃ ካልገባችሁ ይህንን ህዝብ በቁጣ እጎበኘዋለሁ ብሏልና፤ አዎን፣ እናም ኃያሉ ቁጣዬንም አልመልሰውም።

እናም አልማና አሙሌቅ ከህዝቡ መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ለማወጅ ሄዱ፤ እናም እነርሱ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ነበር።

፴፩ እናም በግዞት መያዝ እስከማይችሉ ድረስ ኃይል ተሰጥቶአቸው ነበር፤ ማንም ሰው ሊገድላቸው አይቻለውም ነበር፤ ይሁን እንጂ በሰንሰለት እስከሚታሰሩና ወደ እስር ቤትም እስከሚጣሉ ድረስ ስልጣናቸውን አልተጠቀሙበትም ነበር። አሁን ይህ የተደረገው ጌታ ስልጣኑን በእነርሱ እንዲያሳይ ነበር።

፴፪ እናም እንዲህ ሆነ ጌታ በሰጣቸው መንፈስና ኃይል መሰረት ወደ ፊት ሄዱ እናም ለህዝቡ ማስተማርና መተንበይ ጀመሩ።