በአሞኒሀ ምድር ለነበሩት ሰዎች በአልማ፣ ደግሞም በአሙሌቅ የታወጁት ቃላት። እናም በአልማ ዘገባ መሰረት፣ እነርሱ በወህኒ ቤት ተጣሉ፣ እናም በውስጣቸው ባለው ታምራታዊ የእግዚአብሔር ኃይልም ተለቀቁ።
ከምዕራፍ ፱ እስከ ፲፬ አጠቃሎ የያዘ።
ምዕራፍ ፱
አልማ የአሞኒሀ ሰዎች ንስሃ እንዲገቡ አዘዘ—ጌታ በመጨረሻው ቀን ለላማናውያን መሀሪ ይሆናል—ኔፋውያን ብርሃኑን ከተዉ፣ በላማናውያን ይጠፋሉ—የእግዚአብሔር ልጅ በቅርቡ ይመጣል—ንስሃ የገቡትን፣ የተጠመቁትንና፣ በስሙም ካመኑት ያድናቸዋል። በ፹፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም በድጋሚ፣ እኔ አልማ አሙሌቅን ለመውሰድና ለህዝቡም፣ ወይም በአሞኒሀ ከተማ ላሉት ሰዎች፣ በድጋሚ ለመስበክ በእግዚአብሔር በመታዘዜ፣ እንዲህ ሆነ ለእነርሱ መስበኬን ስጀምር እንዲህ በማለት ከእኔ ጋር መጣላት ጀመሩ፥
፪ አንተ ማነህ? ምድር ታልፋለች በማለት ለእኛ ቢሰብክም የአንድን ሰው ምስክርነት እናምናለን ብለህ ትገምታለህን?
፫ እንግዲህ የተናገሩትን ቃላት አልተረዱም፤ ምድር እንደምታልፍም አያውቁምና።
፬ እናም ደግሞ እንዲህ አሉ፥ ይህች ታላቂቱ ከተማ በአንድ ቀን ትጠፋለች በማለት ብትተነብይም ቃልህን አናምንም።
፭ አሁን እነርሱ ልበ ጠጣርና አንገተ ደንዳና ሰዎች ስለነበሩ እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነት ድንቅ ስራን መስራት ይችላል ብለው አላወቁም።
፮ እናም እንዲህ አሉ፥ እንደዚህ ዓይነቱን ታላቅና ድንቅ እውነታ እንዲናገር በህዝቡ መካከል ከአንድ ሰው በላይ ምንም ስልጣን ሰጥቶ የማይልክ፣ እግዚአብሔር ማን ነው?
፯ እናም እጃቸውን በእኔ ላይ ለመጫን ተነሱ፤ ነገር ግን እነሆ፣ አልነኩኝም። እናም ለእነርሱ ለማወጅ በድፍረት ቆምኩ፣ አዎን፣ በድፍረት እንዲህ በማለት መሰከርኩ፥
፰ እነሆ፣ እናንተ ክፉና ጠማማ ትውልድ፣ የአባቶቻችሁን ባህል እንዴት ረሳችሁ፤ አዎን የእግዚአብሔርንስ ትዕዛዛት እንዴት በፍጥነት ረሳችሁ።
፱ አባታችን ሌሂስ በእግዚአብሔር እጅ ከኢየሩሳሌም እንደወጣ አታስታውሱምን? ከምድረበዳውስ ሁሉም በእርሱ እንደተመሩ አታስታውሱምን?
፲ እናም አባቶቻችንን ከጠላቶቻቸው እጅ ምን ያህል ጊዜ እንዳስለቀቀና፣ በወንድሞቻቸውም እጅ እንኳን ቢሆን፣ ከመጥፋት እንደጠበቃቸው በፍጥነት ረሳችሁትን?
፲፩ አዎን፣ ለእኛ ባለው ወደር በሌለው ስልጣኑና ምህረቱ፣ እንዲሁም በረዥም ፅናቱ ባይሆን ኖሮ ከዚህ ጊዜ በፊት ከምድረ ገፅ ሊወገድ በማይቻልበት መጥፋት ይገባን ነበር፣ እናም ምናልባት መጨረሻ ለሌለው ጉስቁልና ወዮታ እንሰጥ ነበር።
፲፪ እነሆ፣ እላችኋለሁ፣ አሁን እርሱ ንስሃ እንድትገቡ ያዛችኋል፤ እናም እናንተ ንስሃ ካልገባችሁ በምንም መንገድ የእግዚአብሔርን መንግስት ልትወርሱ አትችሉም። ነገር ግን እነሆ፣ ይህ ብቻ አይደለም—እርሱ ንስሃ እንድትገቡ አዟችኋል፣ አለበለዚያም እናንተን ከምድረ ገፅ ፈፅሞ ያጠፋችኋል፤ አዎን፣ በቁጣውም ይጎበኛችኋል፣ እናም ጽኑ ቁጣው ከእናንተ አይመልስም።
፲፫ እነሆ፣ ትዕዛዛቴን እስከጠበቃችሁ ድረስ፣ በምድሪቱ ላይ ትበለፅጋላችሁ ብሎ ለሌሂ የተናገራቸውን ቃላት አታስታውሱምን? እናም በድጋሚም እንዲህ ተብሏል፤ ትዕዛዛቴን እስካልጠበቃችሁ ድረስ ከጌታ ፊት ትለያላችሁ።
፲፬ እንግዲህ ላማናውያን የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እስካልጠበቁ ድረስ፣ ከጌታ ፊት እንደተለዩ እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ። አሁን በዚህ ነገር የጌታ ቃል ማረጋገጫ እንደሆነ እናያለን፣ እናም ላማናውያን በምድሪቱ መተላለፍ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ከእርሱ ፊት ተለይተዋል።
፲፭ ይሁን እንጂ እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፣ በኃጢአታችሁ ከቀጠላችሁ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለእነርሱ ይቀልላቸዋል፤ አዎን እናም ንስሃ ካልገባችሁ በዚህ ህይወትም ቢሆን እንኳን ለእነርሱ የበለጠ ቀላል ይሆናል።
፲፮ ለላማናውያን ብዙ የተስፋ ቃል ተሰጥቶአቸዋልና፤ በአባቶቻቸው ወግ ምክንያት ነው በድንቁርና እንዲቀሩ ስላደረጋቸውና፤ ስለዚህ ጌታ ለእነርሱ መሀሪ ይሆናል፣ እናም በምድሪቱ ላይ ህይወታቸውን ያረዝማል።
፲፯ እናም በአንድ ወቅት በቃሉ ወደማመንና፣ የተሳሳተውን የአባቶቻቸውንም ወግ ወደ መረዳት ይደርሳሉ፤ እናም ብዙዎች ይድናሉ፣ ጌታ ስሙን ለሚጠሩ ሁሉ መሀሪ ይሆናልና።
፲፰ ነገር ግን እነሆ፣ በኃጢአታችሁ የምትቀጥሉ ከሆነ ላማናውያን በእናንተ ላይ የሚላኩ በመሆናቸው በምድሪቱ ላይ የመቆያችሁ ቀን አይረዝምም፤ ንስሃ የማትገቡም ከሆነ እናንተ በማታውቁበት ወቅት ይመጣሉ፣ እናም ፍፁም በሆነ ጥፋትም ትጎበኛላችሁ፤ ይህም በፅኑ የጌታ ቁጣ መሰረት ነው።
፲፱ ህዝቡን ለማጥፋት እናንተ በክፋት እንድትኖሩ አይፈቅድላችሁም። እኔ ግን አይሆንም እላችኋለሁ፤ ለጌታ አምላካቸው ታላቅ ብርሃንን ታላቅ እውቀትን ካገኙ በኋላ በኃጢያትና በመተላለፍ ለመውደቅ የሚቻላቸው ከሆነ የኔፊ ህዝብ የተባሉትን ሁሉ ላማናውያን እንዲያጠፏቸው ቢፈቅድ ይሻለዋል።
፳ አዎን፣ በጌታ የተወደዱ ሰዎች ከሆኑ በኋላ፣ አዎን፣ ከሁሉም ሀገር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ህዝብ በላይ የተወደዱ ከሆኑ በኋላ፣ ሁሉንም ነገሮች በፍላጎታቸው፣ በእምነታቸው፣ በፀሎታቸው መሰረት፣ ስለነበረው፣ እና ስለሆነው፣ እናም ስለሚመጣው እንዲያውቁ ከተደረጉ በኋላ፤
፳፩ በእግዚአብሔር መንፈስ ከተጎበኙ በኋላ፣ ከመልአኩ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ፣ የጌታ ድምፅም ከተናገራቸው በኋላና፣ የትንቢት መንፈስና የራዕይ መንፈስ፣ ደግሞም ብዙ ስጦታዎች በልሳን የመናገር ስጦታ፣ እናም የመስበክ ስጦታና፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታና የመተርጎም ስጦታ ከተሰጣቸው በኋላ፤
፳፪ አዎን፣ ከኢየሩሳሌም ምድር በጌታ እጅ በእግዚአብሔር እንዲለቀቁ ከተደረጉ በኋላ፣ ከረሃብ፣ ከበሽታና ከሁሉም ዓይነት ተውሳክ ከዳኑ በኋላ፤ ከዚያም በኋላ እንዳይጠፉ ለጦርነት በመበርታት ጠነከሩ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከባርነት በመውጣትና፣ እስካሁን እንዲቀመጡና እንዲጠበቁ ሆነዋል፤ እናም በሁሉም ነገሮች ሀብታም እስኪሆኑ ድረስ በልፅገዋል—
፳፫ እናም አሁን እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ይህ ህዝብ ብዙ በረከቶችን ከጌታ አግኝቶ ካለው ብርሃንና እውቀት በተቃራኒ የሚተላለፍ ከሆነ፣ ይህ ሁኔታ ከሆነ፣ እነርሱም ወደ መተላለፍ የሚወድቁ ከሆነ፣ ከእነርሱ የበለጠ ለላማናውያን የሚቀልላቸው ይሆናል እላችኋለሁ።
፳፬ እነሆም፣ የጌታ ቃል ኪዳን ለላማናውያን ተዘርግቷል፤ ነገር ግን እናንተ የምትተላለፉ ከሆነ ለእናንተ አይሆኑም፤ ምክንያቱም ጌታ እናንተ በእርሱ ላይ የምታምፁ ከሆነ ከምድረ ገፅ ፈፅሞ ትጠፋላችሁ በማለት በግልፅ ቃል አልገባምን እንዲሁም በጥብቅ አላወጀምን?
፳፭ እናም አሁን በዚህ የተነሳ፣ እንዳትጠፉ ዘንድ፣ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ በማለት ወደዚህ ህዝብ መሄድ እና መጮህ እንዳለባቸው ለማወጅ ጌታ መልአኩን ብዙ ህዝቦቹን እንዲጎበኝ ልኳል።
፳፮ እናም የእግዚአብሔር ልጅ በክብር በሚመጣበት ቀን ከዚህ በኋላ ሩቅ አይደለም፤ እናም ክብሩ የአብ አንድያ ልጅ ክብር የሆነ፣ በፀጋ፣ በፍትህና በእውነት፣ በፅናት መሃሪና በታጋሽነት የተሞላ፣ የህዝቡን ጩኸት ለመስማትና መልስ ለመስጠት ፈጣን የሆነው ይሆናል።
፳፯ እናም እነሆ፣ በስሙ በማመን ለንስሃ የሚጠመቁትን ለማዳን ይመጣል።
፳፰ ስለዚህ፣ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፣ በነበሩበት መሰረት ሰዎች በሙሉ የስራቸውን ውጤት የሚሰበስቡበት ጊዜ ቀርቧልና—ፃድቃን ከሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ሀይልና መድሀኒት መሰረት የነፍሳቸውን ደህንነት ያጭዳሉ፤ እናም ክፉ ከሆኑ በዲያብሎስ ስልጣንና ግዞት መሰረት ለነፍሳቸው እርግማንን ያጭዳሉ።
፳፱ አሁን እነሆ፣ ይህ ወደ ህዝቡ የሚጮኸው የመልአክ ድምፅ ነው።
፴ እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እናንተ ወንድሞቼ ናችሁና፣ እናም የተወደዳችሁ መሆን ይገባችኋል፣ ለንስሃ የሚሆን ስራን መስራትም አለባችሁ፣ ምክንያቱም ልባችሁ በጌታ ቃል ላይ እጅግ ጠጥሯልና እናም የተሳሳታችሁና የወደቃችሁ ህዝቦች ናችሁ።
፴፩ አሁን እንዲህ ሆነ እኔ አልማ እነዚህን ቃላት ስናገር፣ እነሆ፣ ህዝቡ በእኔ ተቆጥቷል ምክንያቱም እነርሱ ልበ ጠጣር እና አንገተ ደንዳና ሰዎች እንደሆኑ ነግሬአቸዋለሁና።
፴፪ እናም ደግሞ የጠፉና የወደቁ ሰዎች መሆናቸውን በመናገሬ፣ በእኔ ተቆጡ፣ እናም ወደ ወህኒ ቤት ይጥሉኝ ዘንድ እጃቸውን ሊጭኑብኝ ፈለጉ።
፴፫ ነገር ግን እንዲህ ሆነ ጌታ በዚያን ጊዜ እኔን ወስደው ወህኒ ቤት እንዲጥሉኝ አልፈቀደላቸውም ነበር።
፴፬ እናም እንዲህ ሆነ አሙሌቅ ሄደና ወደፊት ቆሞ፣ ደግሞም መስበክ ጀመረ። እናም አሁን የአሙሌቅ ቃላት በሙሉ አልተፃፉም፣ ይሁን እንጂ ከቃሉ የተወሰነው ክፍል በዚህ መፅሐፍ ተፅፏል።