ምዕራፍ ፲፫
ኤተር በዮሴፍ ዘር በአሜሪካ ውስጥ ስለምትገነባ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ተናገረ—እርሱም ትንቢትን ተናገረ፤ አስወገዱት፤ የያሬዳውያንን ታሪክ ፃፈ፣ እናም ስለያሬዳውያን መጥፋት አስቀድሞ ተናገረ—በምድሪቱ ሁሉ ላይ ጦርነት አየለ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ሞሮኒ፣ የፃፍኩላቸውን ሰዎች ጥፋት በተመለከተ ታሪኬን ለመጨረስ እቀጥላለሁ።
፪ እነሆ፣ እነርሱም የኤተርን ቃላት በሙሉ አልተቀበሉም፤ እርሱ ሰው ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ ሁሉንም ነገሮች በእውነት ነግሮአቸዋል፤ እናም ውኃውም ከምድሪቱ ገፅ ከሸሸ በኋላ ከሁሉም መሬት በላይ የተመረጠች ምድር፣ በጌታ የተመረጠች ምድር እንደሆነች፤ ስለሆነም ጌታ በዚህች ምድሪቱ ላይ የሚኖሩት ሰዎች ሁሉ እንዲያገለግሉት ይፈልጋል፤
፫ እናም ይህም የጌታ ቅዱስ የማምለኪያ ቦታ፣ ከሰማይም የምትወርደው የአዲሲቷ ኢየሩሳሌም ስፍራ እንደነበረችም ነግሮአቸዋል።
፬ እነሆ፣ ኤተር የክርስቶስን ቀናት ተመልክቷል፣ እናም በዚህች ምድር ላይም ስለአዲሲቷ ኢየሩሳሌምም በተመለከተ ተናግሯል።
፭ እናም ደግሞ ስለእስራኤል ቤት፣ እናም ሌሂ ስለመጣበት ስለኢየሩሳሌም በተመለከተ ተናግሯል—ጠላቶቹም ከተደመሰሰ በኋላ ቅዱሲቷ ከተማ ለጌታ በድጋሚ እንደምትገነባ፤ ስለዚህ ኢየሩሳሌም በጥንት ጊዜ የነበረች በመሆኗ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ልትሆን እንደማትችል፤ ነገር ግን በድጋሚ መገንባት እንደሚገባት፣ እናም የጌታ ቅዱስ ከተማ እንደምትሆን፤ እናም ይህችም ለእስራኤል ቤትም እንደምትገነባ ተናግሯል—
፮ እናም ለዮሴፍ ዘር ቅሪቶችም አዲሲቷ ኢየሩሳሌም በዚች ምድር ትገነባለች፣ ለዚህም ነገር ምሳሌ ነበር፤
፯ ዮሴፍ አባቱን ወደ ግብፅ እንዳመጣው እርሱም በዚያው ሞቷል፤ ስለዚህ ለዮሴፍ አባት እንዳይጠፋ መሃሪ እንደሆነለት ሁሉ የዮሴፍ ዘርም እንዳይጠፋ መሃሪ ለመሆን፣ ጌታ የዮሴፍን ዘር ቅሪት ከኢየሩሳሌም አስወጥቷል።
፰ ስለዚህ፣ የዮሴፍ ቤት ቅሪት በዚህ ምድር ላይ ይገነባሉ፤ ይህችም ለእነርሱ የውርስ ምድር ትሆናለች፤ እናም እንደ ጥንቷ ኢየሩሳሌምም ቅዱስ ከተማ ለጌታ ይገነባሉ፤ እናም ምድር እስከምታልፍ መጨረሻዋ እስከሚሆን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አይቀላቀሉም።
፱ እናም አዲስ ሰማይ እና አዲስ ምድር ይኖራል፤ እናም የጥንቶቹ ከማለፋቸው በስተቀር እንደ ጥንቱ ይሆናሉ፣ እናም ሁሉም ነገሮች አዲስ ሆነዋል።
፲ እናም አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ትመሰረታለች፤ እናም በእርሷም የሚኖሩባት የተባረኩ ይሆናሉ፤ ምክንያቱም በበጉ ደም ልብሳቸው የነፃው እነርሱ ናቸውና፤ እናም እነርሱም ከእስራኤል ቤት ከነበሩት ከዮሴፍ ዘር ቅሪት ጋር ተቆጥረዋልና።
፲፩ እናም ደግሞ የጥንቷ ኢየሩሳሌም ትመሰረታለች፤ እናም በውስጧ የሚኖሩትም የተባረኩ ናቸው፣ በበጉ ደም ታጥበዋልና፤ እናም እነርሱም ነበሩ ተበትነው የነበሩት፣ እናም በምድሪቷ በአራቱም ማዕዘናት፣ እናም ከሃገሪቱ ከበስተሰሜን በኩል የተሰባሰቡት፣ እናም እግዚአብሔር ከአባታቸው ከአብርሃም ጋር የገባውን የቃል ኪዳን በረከት ተካፋዮች የሆኑት።
፲፪ እናም እነዚህ ነገሮች በሚመጡበት ጊዜ እንዲህ የሚሉት ቅዱሳን መፃህፍት ይፈጸማሉ፥ መጨረሻ የሚሆኑት በመጀመሪያ የነበሩት ነበሩ፤ እናም በመጨረሻ የነበሩት መጀመሪያ የሚሆኑም ነበሩ።
፲፫ እናም ከዚህ የበለጠን ልጽፍ ነበር፣ ነገር ግን ተከልክያለሁ፤ ነገር ግን የኤተር ትንቢቶች ታላቅና አስደናቂዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ምንም የማይረባ አድርገው ቆጠሩት እናም አውጥተው ጣሉት፤ እናም በቀንም እራሱን በድንጋይ ዋሻ ደበቀ፣ እናም በምሽት በመሄድ ለህዝቡ መሆን ስለሚገባቸው ነገሮች ይመለከታል።
፲፬ እናም በድንጋይ ዋሻ ውስጥ በተቀመጠ ጊዜ በምሽት በህዝቡ ላይ የሚመጣውን ጥፋት በመመልከት የሚቀሩትን የዚህን ታሪክ ቃል ፃፈ።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ እርሱንም ከህዝቡ መካከል ባስወጡበት ዓመት በህዝቡ መካከል ታላቅ ጦርነት ተጀመረ፣ ምክንያቱም የተነሳሱ ኃያላን የሆኑ እናም ይነገሩ በነበሩት ሚስጢራዊ የክፋት እቅዳቸውም ቆሪያንተመርን ለማጥፋት የፈለጉ ብዙ ሰዎች ነበሩና።
፲፮ እናም እንግዲህ የጦርነትን ጥበብ እናም የዓለምን ማጭበርበር ሁሉ ቆሪያንተመር ከአጠና በኋላ፣ ስለዚህ ሊገድሉት ከፈለጉት ጋር ተዋጋ።
፲፯ ነገር ግን መልከ መልካም የሆኑት የቆሆር ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆቹ እንዲሁም እርሱም ንሰሃ አልገቡም፤ የቆሪሆርም መልከ መልካም ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ንሰሃ አልገቡም፤ እናም በአጠቃላይ መልከ መልካም ከሆኑት በምድሪቱ ሁሉ ላይ ካሉት ወንዶች እና ሴቶች ልጆች ማንም ንሰሃ የገባ አልነበረም።
፲፰ ስለሆነም፣ እንዲህ ሆነ ኤተር በድንጋይ ዋሻ በኖረበት በመጀመሪያው አመት፣ መንግስቱን ያገኙ ዘንድ ከቆሪያንተመር ላይ በሚዋጉት በሚስጢራዊው ሴራዎች በጎራዴ የተገደሉ ብዙ ሰዎች ነበሩ።
፲፱ እናም እንዲህ ሆነ የቆሪያንተመር ልጆችም ብዙ ተዋጉ፣ ብዙም ደም ፈሰሳቸው።
፳ እናም በሁለተኛው ዓመት ወደ ቆሪያንተመር እንዲሔድ እና እርሱ እና ቤተሰዎቹም በሙሉ ንሰሃ ከገቡ ጌታ ለእርሱ መንግስቱን እንደሚሰጠው ህዝቡንም እንደሚያድን በመናገር እንዲተነብይ የጌታ ቃል ለኤተር መጣ—
፳፩ አለበለዚያ ግን ይጠፋሉ፣ እናም ከእርሱ በስተቀር ቤተሰዎቹ በሙሉ ይጠፋሉ። እናም እርሱም ሌሎች ህዝቦች ምድሪቱን ለውርስ እንደሚቀበሉ የተነገረውን ትንቢት በተመለከተ ሲፈፀም እንዲያይ ብቻ በህይወት ይቆያል፤ እናም ቆሪያንተመርም በእነርሱ ይቀበራል፤ እናም ከቆሪያንተመር በስተቀር እያንዳንዱ ነፍስም ይጠፋል።
፳፪ እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመርም፣ ቤተሰዎቹም፣ እንዲሁ ህዝቡ ንሰሃ አልገቡም፤ እናም ጦርነቱም አልቆመም፤ እነርሱም ኤተርን ለመግደል ፈለጉ፣ ነገር ግን እርሱ ሸሸ፣ እናም በድንጋይ ዋሻ ውስጥ በድጋሚ ራሱን ደበቀ።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ሻረድ ተነሳ፣ እርሱም ደግሞ ከቆሪያንተመር ጋር ተዋጋ፤ እናም አሸነፈው፣ በሦስተኛውም ዓመት ወደ ግዞት አስገባው።
፳፬ እናም የቆሪያንተመር ወንድ ልጆች በአራተኛው ዓመት ሻረድን አሸነፉት፣ እናም በድጋሚ ለአባታቸው መንግስትን አስገኙ።
፳፭ እንግዲህ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ጦርነት ተጀመረ፤ እያንዳንዱ ሰው ከቡድኑ ጋር በመሆን ለሚፈልገው ነገር ተዋጋ።
፳፮ እናም ዘራፊዎች ነበሩ፤ እናም በአጠቃላይ በምድሪቱ ላይ ሁሉም ዓይነት ክፋቶች ነበሩ።
፳፯ እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመር በሻረድ እጅግ ተቆጥቶ ነበር፤ እናም በድጋሚም ከእርሱ ጋር ለመዋጋት ከጦሩ ጋር ሄደ፤ እናም እነርሱም በታላቅ ቁጣ ተገናኙ፤ እናም በጊልጋል ሸለቆም ተገናኙ፤ እናም ጦርነቱም እጅግ የከፋ ነበር።
፳፰ እናም እንዲህ ሆነ ሻረድ ከእርሱ ጋር ለሦስት ቀናት ተዋጋ። እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመር አሸነፈው፣ እናም በሔሽሎን ሜዳ እስከሚመጣም ድረስ አሳደደው።
፳፱ እናም እንዲህ ሆነ በሜዳማው ቦታም ሻረድ ተዋጋው፤ እናም ቆሪያንተመርን አሸነፈው፣ እናም መልሶ ወደ ጊልጋል ሸለቆ አሳደደው።
፴ እናም ቆሪያንተመር በጊልጋል ሸለቆ በድጋሚ ከሻረድ ጋር ተዋጋ፣ እናም በዚያም ሻረድን አሸነፈው እናም ገደለው።
፴፩ እናም ሻረድም ቆሪያንተመርን ጭኑ ላይ አቆሰለው፤ እርሱም ለሁለት ዓመታት በድጋሚ ወደ ጦርነቱ አልተመለሰም ነበር፤ በዚህም ጊዜ በምድሪቱ ላይ የነበሩት ሰዎች ሁሉ የደም መፋሰስ ያደርጉ ነበር፣ እናም እነርሱንም የሚያቆማቸው ማንም አልነበረም።