ቅዱሳት መጻህፍት
ያዕቆብ ፩


መፅሐፈ ያዕቆብ
የኔፊ ወንድም

ለወንድሞቹ የሰበካቸው ቃላት። እርሱ የክርስቶስን ትምህርት ለማጥፋት የተመኘውን ሰው አሳፈረው። የኔፊን ህዝብ ታሪክ በተመለከተ ጥቂት ቃላት።

ምዕራፍ ፩

ያዕቆብና ዮሴፍ ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑና ትዕዛዛቱን እንዲጠብቁ ለማሳመን ሞከሩ—ኔፊ ሞተ—ክፋት በኔፋውያን መካከል ተስፋፋ። ፭፻፵፬–፬፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።

እነሆም እንዲህ ሆነ፣ ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣ ሃምሳ አምስት ዓመታት አለፉ፤ ስለዚህ፣ ኔፊ፤ ለእኔ ለያዕቆብ እነዚህ ነገሮች የተፃፉበትን ትንሹን ሰሌዳ በተመለከተ ትዕዛዝን ሰጠኝ።

እናም እኔ ያዕቆብ፣ በጣም የከበሩ ናቸው ብዬ የማስባቸውን ጥቂት ነገሮች በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ እንድፅፍ፤ የኔፊ ህዝብ ተብለው ስለሚጠሩት ታሪክም ባጭሩ ካልሆነ በስተቀር መፃፍ እንደሌለብኝም ትዕዛዝን ሰጠኝ።

እርሱም የህዝቡን ታሪክ በሌላኛው የእርሱ ሰሌዳ ላይ መፃፍ እንዳለበት፣ እና እኔ እነዚህን ሰሌዳዎች ማቆየትና ለዘሮቼም፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ እንዳለብኝ ተናግሯል።

እናም ቅዱስ የሆነ ሰበካ፣ ወይም ታላቅ የሆነ ራዕይ፣ ወይም ትንቢት፣ ካለ በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ ዋና ዋናዎቹን መቅረፅ፣ እስከተቻለም ድረስ ለክርስቶስ እና ለህዝባችን ስል መጻፍ አለብኝ።

በእምነትና በታላቅ ጭንቀት የተነሳ ህዝባችንን በተመለከተ፣ ምን ነገሮች በእነርሱ ላይ መሆን እንዳለባቸው በእውነት ለእኛ ተገልፆልናል።

እናም ደግሞ እኛ ብዙ ራዕይና ብዙ የትንቢት መንፈስ ነበረን፣ ስለዚህ ስለክርስቶስ እና ስለሚመጣው መንግስቱም እናውቅ ነበር።

ስለሆነም የእስራኤል ልጆች በምድረበዳው በነበሩበት ወቅት በፈተናው ጊዜ በአመጽ እንደነበሩ ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ በማንኛውም መንገድ ቢሆን በቁጣው እንዳይምል፣ ህዝቦቻችን ወደ እረፍቱም ይገቡ ዘንድ ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ እናም የእግዚአብሔርን በጎነት እንዲካፈሉ እናሳምናቸው ዘንድ በትጋት ሠራን።

ስለዚህ፣ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ለቁጣ የሚቀሰቅሰውን አመፅ እንዳያምፁ፣ ነገር ግን ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ እንዲያምኑና፣ ሞቱን ይገነዘቡ ዘንድ፣ እናም የመስቀሉን ስቃይና የዓለምን መሳለቅ ይቀበሉ ዘንድ ለማሳመን እንድንችል የእግዚአብሔርን እርዳታ እንፈልጋለን፤ ስለሆነም፣ እኔ ያዕቆብ፣ የወንድሜ ኔፊን ትዕዛዛት ለመፈፀም ኃላፊነቱን ወሰድኩ።

እንግዲህ ኔፊ መሸምገል ጀመረ፣ እናም በቅርቡ እንደሚሞት ተገነዘበ፤ ስለዚህ፣ አንድ ሰው አሁን በህዝቡ ላይ ንጉሥና መሪ እንዲሆን፣ በመሣፍንቱ አገዛዝ መሰረት ቀባው

ህዝቡ ኔፊን እጅግ በመውደዱ፣ እርሱም ለእነርሱ ታላቅ ጠባቂ በመሆኑ፣ የላባንንም ጎራዴ ለእነርሱ ለመከላከያ በመጠቀሙ፣ እናም ለደህንነታቸው በጊዜው ሁሉ በመስራቱ—

፲፩ ስለሆነም፣ ህዝቡ ስሙን በማስታወስ ለመቆየት ፈለጉ። እናም በነገስታት አገዛዝ መሠረት በእርሱ ምትክ የሚነግሱት ሁሉ ሁለተኛው ኔፊ፣ ሶስተኛው ኔፊና፣ ወዘተ ተብለው በህዝቡ ተሰየሙ፤ እናም ስማቸው ምንም ቢሆን፣ በህዝቡ እንዲህም ተሰየሙ።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ፣ ኔፊ ሞተ።

፲፫ አሁን ላማናውያን ያልነበሩት ህዝቦች ኔፋውያን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ፣ ኔፋውያን፣ ያዕቆባውያን፣ ዮሴፋውያን፣ ዞራማውያን፣ ላማናውያን፣ ልሙኤላውያን እና እስማኤላውያን ተብለው ይጠሩ ነበር።

፲፬ ነገር ግን፣ እኔ ያዕቆብ፣ ከእንግዲህ በኋላ እነርሱን በዚህ ስም አልለያቸውም፣ ነገር ግን የኔፊን ህዝቦች ለማጥፋት የሞከሩትን፣ ላማናውያን፣ ብዬ እጠራቸዋለሁ፣ እናም በነገስት አገዛዝ መሰረት፣ ለኔፊ ወዳጅ የሆኑትን፣ ኔፋውያን፣ ወይም የኔፊ ህዝብ፣ ብዬ እጠራቸዋለሁ።

፲፭ እናም አሁን እንዲህ ሆነ የኔፊ ህዝብ፣ በሁለተኛው ንጉስ የንግሥ ዘመን ልባቸውን ማደንደን ጀመሩ፣ እናም በጥቂቱ እራሳቸውን እንደ ጥንቱ ዳዊት እንዲሁም እንደ ልጁ ሰለሞን ብዙ ሚስቶችና ዕቁባቶችን በማድረግ በክፉ ልማድ የእራሳቸውን ፍላጎት ማሟላት ጀመሩ።

፲፮ አዎን፣ እናም ደግሞ እነርሱ ብዙ ወርቅና ብር መፈለግ ጀመሩ፣ እናም በኩራት እራሳቸውን ከፍ ማድረግ ጀመሩ።

፲፯ ስለዚህ፣ እኔ ያዕቆብ፣ መጀመሪያ መልእክቴን ከጌታ ካገኘሁ በኋላ በቤተመቅደስ ውስጥ ሳስተምራቸው እነዚህን ቃላት ሰጠኋቸው።

፲፰ እኔ ያዕቆብ፣ እናም ወንድሜ ዮሴፍ፣ ለዚህ ህዝብ ካህናትና መምህራን እንድንሆን በኔፊ እጅ ተቀብተን ነበር።

፲፱ እናም ኃላፊነቱንም በመውሰድ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በሙሉ ትጋት ካላስተማርናቸው የህዝቡን ኃጢኣት በራሳችን ላይ በመቀበል ኃላፊነታችንን ለጌታ አጎላን፤ ስለሆነም፣ ደማቸው ልብሳችንን እንዳይበክል ባለን ኃይል ሰራን፤ አለበለዚያ ደማቸው ልብሳችንን ይበክላልና፣ እናም በመጨረሻው ቀን እንከን የለሽ ሆነን አንገኝም።