ቅዱሳት መጻህፍት
ሙሴ ፪


ምዕራፍ ፪

[ሰኔ–ጥቅምት ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.)]

እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ—የተለያዩ አይነት ፍጥረታት ተፈጠሩ—እግዚአብሔር ሰውን ፈጠረ እና በሁሉም ነገሮች ላይ ግዛትን ሰጠው።

እንዲህም ሆነ ጌታም ለሙሴ እንዲህ ሲል ተናገረ፥ እነሆ፣ ስለዚህ ሰማይ እና ስለዚህ ምድር በሚመለከት እገልጥልሀለሁ፤ የምናገራቸውን ቃላት ጻፍ። ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፣ በአንድያ ልጄም እነዚህን ፈጠርኩ፤ አዎን፣ በመጀመሪያ ሰማይን ፈጠርኩ፣ እናም ከዚያም የምትቆምበትን ምድር ፈጠርኩ።

እና ምድርም ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች፣ እና አንዳችም አልነበረባትም፤ ጥልቁ በጨለማ እንዲዋጥ አደረግሁኝ፤ እና መንፈሴም በውሆች ላይ ሰፈፈ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።

እናም እኔ እግዚአብሔርም ብርሀን ይሁን አልኩ፤ እና ብርሀንም ሆነ።

እናም እኔ እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየሁ። እናም እኔ እግዚአብሔርም ብርሃንን ከጨለማ ለየኹት።

እናም እኔ እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብዬ ጠራሁት፣ ጨለማውንም ሌሊት ብዬ ጠራሁት፤ እናም ይህን ያደረኩትም በሀይሌ ቃል ነበር፣ እና የተናገርኩት ተከናወነ፤ እናም ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ፣ አንድ ቀን

ደግሞም፣ እኔ እግዚአብሔር እንዲህ አልኩ፥ በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፣ እና እንዳልኩትም ሆነ፤ እና እንዲህም አልኩ፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል፤ እና ይህም ተፈጸመ፤

እና እኔ እግዚአብሔር ጠፈርን አደረግሁ፣ እና ውኆች፣ አዎን፣ ከጠፈሩ በታችና ከጠፈሩ በላይ ያለውን ውኆች ለየኹኝ፣ እና ይህም እንደተናገርኩትም ሆነ።

እና እኔ እግዚአብሔርም ጠፈርን ሰማይ ብዬ ጠራሁት፤ እናም ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ፣ ሁለተኛ ቀን።

እና እኔ እግዚአብሔር እንዲህ አልኩ፥ ከሰማይ በታች ያለው ውሀ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፣ እናም እንዲህም ሆነ፤ እና እኔ እግዚአብሔር እንዲህ አልኩ፥ የብሱም ይገለጥ አልኩ፤ እናም እንዲህም ሆነ።

እና እኔ እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብዬ ጠራሁት፤ እና የውኃ መከማቻውንም ባሕር ብዬ ጠራሁ፤ እናም እኔ እግዚአብሔርም የሰራኋቸው ነገሮች ሁሉ መልካም እንደሆኑ አየሁ።

፲፩ እና እኔ እግዚአብሔርም እንዲህ አልኩ፥ ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል፣ እና ይህም እንዳልኩት ሆነ።

፲፪ እና ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች፤ እና እኔ እግዚአብሔርም የፈጠርኳቸው ነገሮች ሁሉ መልካም እንደሆኑ አየሁ።

፲፫ ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ፣ ሦስተኛ ቀን።

፲፬ እና እኔ እግዚአብሔርም እንዲህ አልኩ፥ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመናት ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ አልኩ፤

፲፭ በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እና እንዲህም ሆነ።

፲፮ እናም እኔ እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን አደረግሁኝ፣ እናም ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሰለጥን፣ እና ትንሹ ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን አደረግሁኝ፣ እና ትልቁ ብርሃን ጸሀይ ነበር፣ እናም ትንሹ ብርሀን ጨረቃ ነበር፤ ከዋክብትንም በቃላቶቼ መሰረት ደግሜ አደረግሁኝ።

፲፯ እና እኔ እግዚአብሔርም፣ ለምድር ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖርኳቸው፣

፲፰ እናም ጸሀይ በቀን እንዲሠለጥን፣ እና ጨረቃም በሌሊት እንዲሠለጥን፣ እና ብርሃንን ከጨለማ እንዲለዩ አደረግሁኝ፤ እና እኔ እግዚአብሔርም የሰራኋቸው መልካም እንደሁኑ አየሁ፤

፲፱ ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ፣ አራተኛ ቀን።

እና እኔ እግዚአብሔርም እንዲህ አልኩ፥ ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፣ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ።

፳፩ እናም እኔ እግዚአብሔርም ታላላቆች አሳነባሪዎችን፣ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፣ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠርኩኝ፤ እና እኔ እግዚአብሔርም የፈጠርኳቸው ነገሮች ሁሉ መልካም እንደሆኑ አየሁ።

፳፪ እና እኔ እግዚአብሔርም እንዲህ ብዬ ባረኳቸው፥ ብዙ ተባዙም የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።

፳፫ እና ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ፣ አምስተኛ ቀን።

፳፬ እናም እኔ እግዚአብሔርም እንዲህ አልኩ፥ ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፣ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ ታውጣ፤ እና ይህም ሆነ፤

፳፭ እና እኔ እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገናቸው አደረግሁ፣ እንስሳውንም እንደ ወገናቸው፣ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገናቸው አደረግሁኝ፤ እና እኔ እግዚአብሔርም እነዚህ ነገሮች ሁሉ መልካም እንደሆኑም አየሁ።

፳፮ እና እኔ እግዚአብሔርም ከመጀመሪያው ጀምሮ ከእኔ ጋር ለነበረው ለአንድያ ልጄ እንዲህ አልኩ ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንፍጠር፣ እናም ይህም ሆነ። እና እኔ እግዚአብሔርም እንዲህ አልኩ፥ የባህር አሶችንና፣ የሰማይ ወፎችን፣ ከብቶችንና፣ ምድርን ሁሉ፣ እናም በምድር በሚንቀሳቀሱ ፍጡራንን ሁሉ ይግዙ

፳፯ እና እኔ እግዚአብሔር ሰውን በመልኬም፣ በአንድያ ልጄ መልክ፣ ፈጠርሁት፤ ወንድና ሴት አድርጌም ፈጠርኳቸው።

፳፰ እና እኔ እግዚአብሔርም ባረኩአቸው፣ እንዲህም አልኳቸው፥ ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፣ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያው ፍጡራንን ሁሉ ግዙአቸው።

፳፱ እና እኔ እግዚአብሔርም ሰውን እንዲህ አልኩት፥እነሆ፣ መብል ይሆንህ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፣ እና የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጥቼሀለሁ።

እና ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ ሕያው ነፍስ ለሰጠኋቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ፣ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እና ይህም አንዳልኩት ሆነ።

፴፩ እና እኔ እግዚአብሔርም ያደረኳቸውን ሁሉ አየሁ፣ እና እነሆ፣ የሰራኋቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ መልካም ነበሩ፤ እና ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ፣ ስድስተኛ ቀን።