አጠቃላይ ጉባኤ
“እነሆ! እኔ የተአምራት አምላክ ነኝ”
የሚያዝያ 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


14:37

“እነሆ! እኔ የተአምራት አምላክ ነኝ”

ተአምራት፣ ምልክቶች እና ድንቆች ዛሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች መካከል፣ በእናንተ ሕይወት እና በእኔ ውስጥ አሉ፡፡

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ዛሬ በፊታችሁ መቆሜ እንዴት መታደል ነው። በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ቀድመው ንግግር ካደረጉት ጋር በመተባበር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው እንደሆነ እመሰክርላችኋለሁ። እሱ ቤተክርስቲያኑን ይመራል፣ እሱ ለነብዩ ፕሬዘዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን ይናገራል፣ እናም ሁሉንም የሰማይ አባት ልጆች ይወዳል።

በዚህ የትንሳኤ እሑድ የአዳኛችንን፣ የመድኃኒታችንን1 የሃያሉን አምላክ፣ የሰላሙን ልኡል የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ እንዘክራለን።2 በውሰት በተገኘው መቃብር ውስጥ ከሦስት ቀናት በኋላ በትንሳኤው የተገባደደው የኃጢያት ክፍያው፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደ ታላቁ ተአምር ሆኖ ይቆማል። “እነሆ፣” ሲል ተናገረ፣ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ ደግሞ የተአምራት አምላክ ነኝ።”3

“ክርስቶስ ወደ ሰማይ በማረጉ እናም አብን በሰዎች ልጆች ላይ ያለውን ምህረት ለመጠየቅ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ በኩል በመቀመጡ ተአምራት ቆመዋልን?፣”4 ሲል ነቢዩ ሞርሞን በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ጠየቀ። እሱም መለሰ፣ “እነሆ አልቆሙም እላችኋለሁ፤ መላዕክቶችም ቢሆኑ የሰው ልጆችን ማገልገላቸውን አላቆሙም።”5

ስቅለቱን ተከትሎ ከሌሎች ጥቂት ሴቶች ጋር የኢየሱስን አካል ለመቀባት ወደ መቃብሩ ለሄደችው ለማሪያም የጌታ መልአክ ተገለጠላት። መልአኩም እንዲህ አለ፦

“ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?”6

“ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።”7

የመፅሐፈ ሞርሞን ነቢይ አቢናዲ ስለዚያ ተአምር ገልጿል፦

“ክርስቶስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ፣ … ትንሣኤም ሊኖር አይችልም ነበር።

“ነገር ግን ትንሳኤ አለ፤ ስለዚህ ሞት ድል አይኖረውም፤ እናም የሞት መውጊያ በክርስቶስ ተውጧል።”8

የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራዊ ተግባራት የጥንት ደቀ መዛሙርት “ይህ ሰው እንዴት ያለ ነው! እርሱ ነፋሳትንና ውኃን እንኳ ያዝዛልና እነሱም ይታዘዙለታል።” በማለት እንዲገረሙ አድርጓቸዋል።9

የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስን ተከትለው ወንጌልን ሲያስተምር በመስማት ላይ ሳሉ ብዙ ተአምራትን ተመልክተዋል። “ዕውሮች ሲያዩ፣ አንካሶችም ሲሄዱ፣ ለምጻሞች ሲነጹ፣ ደንቆሮዎችም ሲሰሙ፣ ሙታን ሲነሱ፣ ድሆችም ወንጌል ሲሰበክላቸው” አይተዋል።10

ተአምራት፣ ምልክቶች እና ድንቆች ዛሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች መካከል፣ በእናንተ ሕይወት እና በእኔ ውስጥ አሉ፡፡ ተአምራት መለኮታዊ ተግባራት፣ መገለጫዎች፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ገደብ የለሽ ኃይል መግለጫዎች እና “ትናንትም፣ ዛሬም እስከ ዘላለምም ያው ”11፣ መሆኑን ማረጋገጫ ናቸው። ባሕሮችን የፈጠረው ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጥ ሊያሰኛቸው ይችላል፣ ለዓይነ ስውራን ማየትን የሰጠው እርሱ የእኛን እይታ ወደ ሰማይ ሊያነሳ ይችላል፣ ለምጻሞችን ያነፃ እርሱ ድክመቶቻችንን ሊያስተካክልልን ይችላል፤ አቅመ ደካማውን ሰው የፈወሰ እርሱ “ኑ፣ ተከተሉኝ”12፣ በማለት እንድንነሳ ሊጠራን ይችላል።

ብዙዎቻችሁ ከምትገነዘቡት በላይ ተአምራትን ተመልክታችኋል። ከኢየሱስ ሙታንን ማስነሳት ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ሊመስል ይችላል። ግን መጠኑ ተአምርን አይለይም፣ ከእግዚአብሄር መምጣቱን ብቻ ነው እንጂ። አንዳንዶች ተዓምራት እንዲሁ አጋጣሚ ወይም እድል እንደሆኑ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ነብዩ ኔፊ “ጥቅም ለማግኘት፣ የእግዚአብሔርን ኃይልና ተአምራት ለሚንቁ፣ እናም የራሳቸውን ጥበብና ትምህርት ለራሳቸው [የሚሰብኩትን] ”13፣ አውግዟል።

ተአምራት የሚከናወኑት “ለማዳን ኃያል በሆነው”14፣ በመለኮታዊ ኃይል ነው። ተአምራት የእግዚአብሔር የዘላለም ዕቅድ ቅጥያዎች ናቸው፣ ተአምራት ከሰማይ ወደ ምድር የሚያገናኙ የሕይወት መስመር ናቸው።

ባለፈው የመኸር ወቅት እህት ራዝባንድ እና እኔ ከ600,000 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች በ16 የተለያዩ ቋንቋዎች በዓለም ዙሪያ በሚተላለፈው የፊት ለፊት ዝግጅት ላይ ለመገኘት ወደ ጎሸን ዩታ በማቅናት ላይ ነበርን።16 ፕሮግራሙ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣት ጎልማሶች በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ ክስተቶች ላይ ባቀረቧቸው ጥያቄዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነበር። እህት ራዝባንድ እና እኔ ጥያቄዎቹን በግል ገምግመን ነበር፤ ጆሴፍ ስሚዝ የእግዚአብሔር ነቢይ ስለመሆኑ፣ መገለጥ በሕይወታችን ውስጥ ስላለው ኃይል፣ በመመለስ ሂደት ላይ ስላለው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና እኛ ዋጋ ስለምንሰጣቸው እውነቶች እና ትእዛዛት እንድንመሰክር ዕድሉን ሰጠን። ብዙዎች ዛሬ በማድመጥ ላይ ያሉ የዚያ ተአምራዊ ክስተት አካል ነበሩ።

መጀመሪያ ላይ ስርጭቱ እንዲተላለፍ የታቀደው በሰሜናዊ ኒው ዮርክ ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ደን ውስጥ ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ ብሎ በመሰከረበት ቦታ ነበር፦ “ድምፃቸው እና ክብራቸው መግለጥ ከሚቻለው በላይ የሆነ ሁለት ግለሰቦች ከእኔ በላይ በአየር ላይ ቆመው አየሁ። አንዱም ስሜን በመጥራት እና ወደ ሌላው በማስመልከት አናገረኝ--ይህ ውድ ልጄ ነው። እርሱን ስማው!16 ወንድም እና እህቶች፣ ያ ተአምር ነበር።

ኢየሩሳሌም በጎሸን ዩታ ውስጥ ሆነ።

በዓለም ዙሪያ የተከሰተው ወረርሽኝ ስርጭቱ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለፊልም ቀረጻ የጥንት ኢየሩሳሌምን የተወሰነ ክፍል አስመስለው ወደገነቡበት ወደ ጎሸን፣ ዩታ፣ እንዲዛወር አስገደደን። እሁድ ምሽት ላይ ከጎሸን ጥቂት ማይል ርቀት ላይ በነበርንበት ወቅት እህት ራዝባንድ እና እኔ ጥቅጥቅ ያለ ጭስ ከመድረሻችን አቅጣጫ ሲመጣ አየን። በአካባቢው ሰደድ እሳት ስለነበረ ስርጭቱ አደጋ ላይ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ነበረን። በእርግጥም፣ የእኛ የስርጭት ጊዜ በነበረው ለ12 ሰዓት 20 ደቂቃ ሲቀረው፣ በጠቅላላ አካባቢ ያለው የመብራት ኃይል ጠፋ። የመብራት ኃይል የለም! ስርጭት የለም። ሃይል ሊሰጠን የሚችል አንድ ጀነሬተር እንዳለ እንዳዶች አስበው ነበር፣ ነገር ግን በእጃችን ላሉት ዘመናዊ መሣሪያዎች እንደሚሆን ማረጋገጫ አልነበረም።

ጭስ ከእሳቶች

ተራኪዎችን፣ ሙዚቀኞችን እና ቴክኒሻኖችን፣ የራሳችን የቤተዘመድ አባላት የሆኑትን 20 ወጣት ጎልማሳዎችን ጨምሮ በፕሮግራሙ የምንሳተፍ ሁላችንም ሊከናወን በነበረው ነገር ላይ ሙሉ በሙሉ ተረባርበን ነበር። ከዕንባዎቻቸው እና ከግራ መጋባታቸው ርቄ በመሄድ ጌታ ተአምር እንዲያደርግ ተማፀንኩ። እንዲህ ስል ጸለይኩኝ “የሰማይ አባት፣ ብዙ ጊዜ ተአምር አልጠይቅም፣ ግን አሁን አንድ ተአምር እጠይቃለሁ። ይህ ስብሰባ በዓለም ዙሪያ ላሉት ወጣት ጎልማሳዎቻችን ሁሉ ሲባል መደረግ አለበት። ፈቃድህ ከሆነ ለመቀጠል የመብራት ኃይል እንፈልጋለን።”

12 ሰዓት ከሰባት ደቂቃ ሲሆን የመብራት ኃይሉ በጠፋበት ፍጥነት ወዲያውኑ ተመለሰ። ከሙዚቃ እና ማይክሮፎኖች እስከ ቪዲዮዎች እና ሁሉም የማስተላለፊያ መሳሪያዎች ድረስ ሁሉም ነገር መሥራት ጀመረ። እኛም ዝግጅቱን ቀጠልን። ተዓምር ተደርጎልን ነበር።

የሙዚቃ ዝግጅት በፊት ለፊት ክስተት ወቅት

እኔና እህት ራዝባንድ በዛ ምሽት ወደ ቤታችን ለመመለስ መኪና ውስጥ ሳለን ፕሬዘዳንት እና እህት ኔልሰን ይህንን የቴክስት መልእክት ላኩልን፤ “ሮን፣ የመብራት ኃይሉ እንደጠፋ እንደሰማን ተአምር እንዲከሰት እንደጸለይን እንድታውቁ እንፈልጋለን።”

በኋለኛው ቀን ቅዱሳን መጽሃፍት ውስጥ፣ “እኔ ጌታ የሰማይን ሀይላት ለመጠቀም እጆቼን እዘረጋለሁና፤ አሁን ልታዩት አትችሉም፣ ነገር ግን ከትንሽ ጊዜ በኋላ ታዩታላችሁ፣ እናም እኔ እንደሆንኩኝ፣ እናም በህዝቤ መካከል ለመንገስ እንደምመጣም ታውቃላችሁ።”17፣ ተብሎ ተጽፏል።

በትክክል የሆነው ነገር ይኸው ነበር። ጌታ እጁን ዘረጋ እናም የመብራት ኃይሉ መጣ።

በቀደመው ክፍለ ጊዜ ፕሬዚዳንት ኔልሰን በሃይል እንዳስተማሩት ተአምራት የሚሠሩት በእምነት ኃይል ነው። ነቢዩ ሞሮኒ ሕዝቡን አደፋፈረ፣ “በሰው ልጆች መካከል እምነት ከሌለ እግዚአብሔር በመካከላቸው ተአምር መስራት አይችልም፤ ስለሆነም እስከሚያምኑ ድረስ እራሱን አልገለፀላቸውም።”

እንዲህም ቀጠሉ፥

“እነሆ፣ የአልማ እና የአሙሌቅ እምነትም ነው ወህኒ ቤቱ ወደምድር እንዲወድቅ ያደረገው።

“እነሆ፣ የኔፊና የሌሂ እምነት ነበር ላማናውያንን እንዲለወጡ ያደረገው፣ ስለሆነም እነርሱም በእሳት እና በመንፈስ ቅዱስ ተጠመቁ።

እነሆ፣ የአሞን እና የወንድሙ እምነት ነበር ታላቅ የሆነ ተአምር በላማናውያን መካከል የሠራው። …

“እናም በማንኛውም ጊዜም እንኳን እምነት እስከሚኖራቸው ድረስ ተአምራትን ማንም አልሰራም፤ ስለዚህ እነርሱ አስቀድመው በእግዚአብሔር ልጅ አምነዋል።”18

በዚያ የቅዱሳት መጻሕፍት ቅደም ተከተል ላይ ማከል እችላለሁ፣ “የመብራት ኃይሉ በርቀት በሚገኘው የፊልም መቅረጫ በጎሸን ዩታ እንዲመለስ የተደረገው እምነት ባላቸው እጅግ ታላቅ ተአምር በፈለጉ ቀናተኛ ወጣት ተዋናይ፣ የስርጭት ባለሙያዎች፣ የቤተክርስቲያን መሪዎች እና አባላት፣ ሐዋርያ እና የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር።”

ተአምራት ለጸሎት መልስ ሆነው መምጣት ይችላሉ። እነሱም ሁል ጊዜ የምንለምናቸው ወይም የምንጠብቃቸው አይደሉም፣ ነገር ግን በጌታ ስንታመን እርሱ በዚያ ይገኛል፣ እናም እሱም ትክክል ይሆናል። ተአምራቱን ከምንፈልግበት ቅፅበት ጋር ያስማማል።

ጌታ ኃይሉን፣ ለእኛ ያለውን ፍቅር፣ ከሰማይ እስከ ሟች ተሞክሯችን እንደሚደርስ እና የላቀ ዋጋ ያለውን ለማስተማር ያለውን ፍላጎቱን ለማስታወስ ተአምራትን ያደርጋል። እርሱ በ1831(እ.አ.አ) ለቅዱሳን የተናገረው ተስፋው ዛሬም ቀጥሏል፣ “ለመፈወስ በእኔ እምነት ያለው፣ እና ለሞትም ያልተሰጠ፣ እርሱ ይፈወሳል።”19 በሰማያት ውስጥ የተደነገጉ ህጎች አሉ፣ እኛ ሁሌም ለእነሱ ተገዢዎች ነን።

የምንወደውን ሰው ለመፈወስ፣ ኢፍትሃዊ ድርጊትን ለመቀልበስ ወይም የመረረ ወይም ግራ የተጋባን ልብ ለማለስለስ በተአምር ተስፋ የምናደርግባቸው ጊዜያት አሉ። ነገሮችን በሟች ዓይኖች እየተመለከትን፣ ጌታ ጣልቃ እንዲገባ፣ የተሰበረውን እንዲያስተካክል እንፈልጋለን። በእምነት አማካኝነት ተአምሩ ይመጣል፣ ምንም እንኳን በፈለግነው ጊዜ ወይም የጠበቅነው መሻት ባይሆንም። እኛ ታማኝነታችን ያነሰ ወይም የእሱ ጣልቃ ገብነት የማይገባን ነን ማለት ነው? አይደለም። በጌታ የተወደድን ነን። እርሱ ለእኛ ሲል ሕይወቱን ሰጥቷል፣ እናም ንስሐ ስንገባ እና ወደ እሱ ስንቀርብ የኃጢያት ክፍያው ከሸክም እና ከኃጢአት እኛን መለየቱን ቀጥሏል።

ጌታ “መንገዳችሁ የእኔ መንገዶች አይደሉም ”20፣ ብሎ አስታውሶናል። “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።”21፣ በማለት ግብዣ ያቀርባል—ረፍት ከጭንቀት፣ ከብስጭት፣ ከፍርሃት፣ ካለመታዘዝ፣ ስለምንወዳቸው ሰዎች ከመጨነቅ፣ ከጠፋ ወይም ካልተሳካ ህልም ። በግራ መጋባት ወይም በሀዘን ውስጥ ሰላም ማግኘት ተዓምር ነው። የጌታን ቃል አስታውሱ፤ “ስለዚህ ጉዳይ በአዕምሮህ ሰላም አልተናገርኩልህምን? ከዚህስ የበለጠ ከእግዚአብሔር ምንስ አይነት ምስክርነትን ታገኛለህ?”22 ተዓምሩ የልዑል ልጅ ታላቁ ያህዌ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰላም ምላሽ እየሰጠ መሆኑ ነው።

ልክ በአትክልቱ ስፍራ ማሪያምን በስም እየጠራ እንደተገለጠላት፣ እምነታችንን እንድንጠቀም እኛንም ይጠራናል። ማርያም እርሱን ለማገልገል እና ለመንከባከብ ፈልጋ ነበር። የጠበቀችው የእርሱን ትንሳኤ አልነበረም፣ ነገር ግን በታላቁ የደስታ እቅድ መሰረት ነበር።

“ከመስቀሉ ላይ ውረድ፣ ”23 በማለት የማያምኑ ሰዎች በቀራንዮ በእርሱ ላይ አፌዙበት። እሱ እንደዚህ ያለ ተአምር ማድረግ ይችል ነበር። ነገር ግን መጨረሻውን ከመጀመሪያው ያውቅ ነበር፣ እናም ለአባቱ እቅድ ታማኝ ለመሆን ወስኖ ነበር። ያ ምሳሌ በእኛ ላይ ጠንካራ ተፀእኖ ማሳደር ይኖርበታል።

በፈተና ላይ በምንሆንባችው ጊዜያት ለእኛ እንዲህ ሲል ተናግሯል፣ “ ጎኔ ላይ የተወጋሁት ቁስል፣ እናም በእጄ እና በእግሬ ላይ ያሉትን የምስማር ምልክቶች አስቧቸው፤ እናም እምነት ይኑራችሁ፣ ትእዛዛቴን ጠብቁ፣ እናም መንግስተ ሰማያትን ትወርሳላችሁ። ”24 ያ ወንድሞች እና እህቶች ለሁላችን ቃል የተገባልን ተአምር ነው።

የጌታችንን የትንሳኤ ተአምር በዚህ የትንሳኤ እሁድ ስናከብር፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ እንደመሆኔ መጠን፣ ለሰማይ አባታችን ያቀረባችሁት አቤቱታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎቱ ሁሉ ባሳየው ፍቅር እና ቁርጠኝነት ምላሽ እንዲያገኝ፣ በሕይወታችሁ ውስጥ የአዳኝ ኃይል እንዲሰማችሁ በትህትና እፀልያለሁ። በሚመጣው ሁሉ ጽኑ እና ታማኝ እንድትሆኑ እባርካችኋለሁ። የጌታ ፈቃድ ከሆነ—ለእኛ በጎሸን እንደተደረገልን ተአምር ለእናንተም እንዲደረጉላችሁ እባርካችኋለሁ። “ነቢያት እና ሐዋሪያት የፃፉለትን ይህንን ኢየሱስን [ስት]ፈልጉት፤ በዚህም የእግዚአብሔር አብ ፀጋ፣ እናም ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስና፣ ስለእነርሱ የሚመሰክረው መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ውስጥና፣ ከእናንተ ጋር ለዘለዓለም ይኑር።”28የሚሉትን እነዚህን ከሰማይ የተላኩ በረከቶች በሕይወታችሁ ውስጥ ፈልጉ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።