አጠቃላይ ጉባኤ
ኮቪድ-19 እና ቤተመቅደሶች
የሚያዝያ 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


6:40

ኮቪድ-19 እና ቤተመቅደሶች

የቤተ መቅደስ ቃል ኪዳኖቻችሁን እና በረከቶቻችሁን በአእምሮአችሁ እና በልባችሁ ውስጥ ከሁሉም በላይ ጠብቁ። ለገባችሁት ቃል ኪዳኖች ታማኝ ሁኑ።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ በእውነት ከመንፈሳዊ ድግስ ተቋድሰናል። በጠቅላላው ጉባኤ ለተደረጉት ጸሎቶች፣ መልእክቶች እና መዝሙሮች ምን ያህል አመስጋኝ ነኝ። የትም ብትሆኑ ከእኛ ጋር ስለተሳተፋችሁ እያንዳንዳችሁን አመሰግናለሁ።

ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እና ጥሩ ዓለም አቀፋዊ ዜጎች ለመሆን ካለን ፍላጎት የተነሳ ሁሉንም ቤተመቅደሶች ለጊዜው ለመዝጋት ከባድ ውሳኔ አድርገናል። በተከተሉት ወራቶች፣ በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ቤተመቅደሶችን ቀስ በቀስ እንደገና ለመክፈት ተነሳሳን። የአካባቢ መንግስት ደንቦችን እና የደህንነት ፕሮቶኮሎችን በጥብቅ በመከተል በአሁኑ ጊዜ ቤተመቅደሶች በአራት ደረጃዎች በመከፈት ላይ ይገኛሉ።

በደረጃ 1 ውስጥ በሚገኙ ቤተመቅደሶች ቀደም ሲል የራሳቸውን ቡራኬ የተቀበሉ ጥንዶች እንደባል እና ሚስት መታተም ይችላሉ።

በደረጃ 2 ውስጥ በሚገኙ ቤተመቅደሶች፣ የራስን ቡራኬ መቀበልን፣ የባል እና የሚስት መታተምን እና የልጆች ከወላጆች ጋር መታተምን ጨምሮ ሁሉም ለህያዋን የሚሰጡ ሥርዓቶች ይከናወናሉ። በቅርቡ የ2ኛ ደረጃ መስፈርቶችን አሻሽለናል እናም ለወጣቶቻችን፣ ለአዲስ አባሎቻችን እና ለሌሎችም ውስን የጊዜያዊ የቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃድ ላላቸው ለቅድመ አያቶቻቸው በወኪል ጥምቀቶች ላይ እንዲሳተፉ ፈቅደናል።

በደረጃ 3 ላይ በሚገኙ ቤተመቅደሶች ቀጠሮ ያላቸው በሕይወት ላሉት ሥርዓቶች ብቻ ሳይሆን ለሟች ቅድመ አያቶች በሁሉም የውክልና ሥርዓቶች ላይም ሊሳተፉ ይችላሉ።

ደረጃ 4 ወደ ሙሉ፣ መደበኛ የቤተመቅደስ እንቅስቃሴ መመለስ ነው።

በዚህ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ ወቅት ውስጥ ላሳያችሁት ትዕግስት እና ለታማኝ አገልግሎታችሁ አመስጋኞች ነን። በቤተመቅደስ ውስጥ የማምለክ እና የማገልገል መሻታችሁ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በደማቅ ሁኔታ እንዲበራ እጸልያለሁ።

ወደ ቤተመቅደስ መቼ እንደምትመለሱ እያሰባችሁ ይሆናል። መልሱም፦ የአካባቢ መንግስት ህጎች ሲፈቅዱ ቤተመቅደሳችሁ ይከፈታል። በአካባቢያችሁ ያለው የኮቪድ-19 ሁኔታ ከአደጋ ነፃ የሆነ ገደብ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ፣ ቤተመቅደሳችሁ እንደገና ይከፈታል። የቤተመቅደስ እድላችሁን ለማስፋት የኮቪድ ቁጥሮች በአከባቢያችሁ እንዲቀንሱ የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።

እስከዛ፣ የቤተመቅደሳችሁን ቃል ኪዳኖች እና በረከቶች በአእምሮአችሁ እና በልባችሁ ውስጥ ከሁሉም በላይ ጠብቁ። ለገባችሁት ቃል ኪዳኖች ታማኝ ሁኑ።

የወደፊቱን እኛ አሁን እየገነባን ነው! አርባ አንድ ቤተመቅደሶች በአሁኑ ጊዜ በግንባታ ወይም በመታደስ ላይ ናቸው። ባለፈው ዓመት ምንም እንኳን ወረርሽኙ ቢከሰትም ለ21 አዳዲስ ቤተመቅደሶች የመሬት ቁፋሮ ስራ ተጀምሯል።

ሁኔታዎቻቸው በሚፈቅዱት መጠን በተደጋጋሚ በቤተመቅደስ የመገኘት ቅዱስ እድል እንዲኖራቸው የጌታን ቤት ወደ አባሎቻችን ይበልጥ የቀረበ ለማድረግ እንፈልጋለን።

20 አዲስ ቤተመቅደሶችን የመገንባት ዕቅዳችንን ሳስተዋውቅ፣ ዛሬ ይህን ታሪክ ለማድረግ ለመርዳት ሕይወታቸውን የቀደሱትን—ከዚ ቀደም ስላሉ እና አሁንም ስላሉ—መስራቾች አሰላስላለው እንዲሁም ከፍ አደርጋለሁ። በሚከተሉት ቦታዎች አዲስ ቤተመቅደስ ይገነባል፦ኦስሎ፣ ኖርዌይ፤ ብራስልስ፣ ቤልጂየም፤ ቪየና ኦስትሪያ፤ ኩማሲ፣ ጋና፤ ቤይራ፣ ሞዛምቢክ፤ ኬፕ ታውን፣ ደቡብ አፍሪካ፤ ሲንጋፖር፣ የሲንጋፖር ሪፐብሊክ፤ ቤሎ ሆሪዞንቴ፣ ብራዚል፤ ካሊ፣ ኮሎምቢያ፤ ኬሬታሮ፣ ሜክሲኮ፤ ቶሬን፣ ሜክሲኮ፤ ሄሌና፣ ሞንታና፤ ካስፐር፣ ዮሚንግ፤ ግራንድ ጀንክሽን፣ ኮሎራዶ፤ ፋርሚንግተን፣ ኒው ሜክሲኮ፤ በርሊ አይዳሆ፤ ኢዩጂን፣ ኦሬገን፤ ኤልኮው፣ ኔቫዳ፤ ዮርባ ሊንዳ፣ ካሊፎርኒያ እና ስሚዝፊልድ ዩታ።

ቤተመቅደሶች የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በሙሉነት መመለስ ላይ ጠቃሚ ክፍል ናቸው። የቤተመቅደስ ሥርዓቶች ህይወታችንን በሌላ መንገድ በማይገኝ ሃይል እና ጥንካሬ ይሞላሉ። ለእነዛ በረከቶች እግዚአብሔርን እናመሰግናለን።

ይህንን ኮንፈረንስ ስንዘጋ ለእናንተ ያለንን ፍቅር እንደገና እንገልፃለን። እግዚአብሔር በእያንዳንዳችሁ ላይ በረከቶቹን እና የጥበቃ እንክብካቤን እንዲያፈስባችሁ እንፀልያለን። በጋራ በቅዱስ አገልግሎቱ ላይ ተሰማርተናል። በድፍረት፣ ሁላችንም በክቡሩ የጌታ ሥራ እንግፋ! ለዚህም በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም እጸልያለሁ፣ አሜን።