“ተማሪዎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጡ እርዱ፣” በአዳኝ መንገድ ማስተማር፦ በቤት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚያስተምሩ ሁሉ [2022 (እ.አ.አ)]
“ተማሪዎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጡ እርዱ፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር
ተማሪዎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጡ እርዱ
እንደ አስተማሪ የምታደርጉት ምንም ነገር የሰማይ አባትን እና ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውቁ እና ፍቅራቸው እንዲሰማቸው ከመርዳት በበለጠ ተማሪዎችን አይባርክም ( ዮሐንስ 17፥3 ይመልከቱ)። የሰማይ አባትን እና ኢየሱስ ክርስቶስን እንድታውቁ እና እንድትወዱ የረዷችሁን ልምዶችን አስቡ። ስለባህሪያቸው፣ ኃይላቸው እና ፍቅራቸው ለመማር ምን አድርጋችኋል? ለሰማይ አባት እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁ ፍቅር ደስታ ያመጣላችሁ እንዴት ነው? ከዚያም ፍቅራቸው እና ኃይላቸው ለእያንዳንዱ ለምታስተምሩት ሰው ምን ማድረግ እንደሚችል አስቡ። ( አልማ 26፥16 ሙሴ 5፥11 ይመልከቱ።)
በዚህ ሕይወት ውስጥ የመጨረሻ ግባችን የበለጠ እንደሰማይ አባታችን መሆን እና ወደ እርሱ መመለስ ነው። ያንን ግብ የምናሳካው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በመምጣት ነው ( ዮሐንስ 14፥6 ይመልከቱ)። ለዚህ ነው ነብዩ ኔፊ እንዳስተማረው “ስለ ክርስቶስ የምናስተምረው፣ በክርስቶስ የምንደሰተው” (2 ኛ ኔፊ 25፥26)።
እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ከአዳኙ የሚመጣ ብርሃን እና እውነት ያስፈልገዋል እንዲሁም ምላሽ ለመስጠት መምረጥ ይችላል። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አስተማሪ መሆን ማለት ሌሎች ትምህርቶቹን፣ የቤዛነት ኃይሉን እና ፍፁም ፍቅሩን እንዲረዱና እንዲተማመኑበት ማገዝ ማለት ነው። የሚከተሉት ሃሳቦች ሌሎች ኢየሱስ ክርስቶስን እዲያውቁ እና እንዲከተሉት እንዴት እንደምታነሳሱ እንደሚረዳችሁ አስቡ።
ተማሪዎች የጌታን ፍቅር፣ ኃይል እና ምህረት በሕይወታቸው ውስጥ እንዲገነዘቡ እርዱ
ስለ አዳኙ ፍቅር፣ ኃይል እና ምህረት ማወቅ መልካም ነው ነገር ግን ልንለማመደውም ይገባናል። በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ እርሱ ሰዎችን እንዴት እንደባረከ እና እንደፈወሰ መመልከት እርሱ ሊባርከን እና ሊፈውሰን እንደሚችል ታላቅ እምነት እንድናዳብር ይረዳናል። ለምሳሌ፣ ስለዳንኤል ልምዶች መማር የራሳችን የአንበሶች ጉድጓድ ሲያጋጥመን ጌታን ለማመን ካላነሳሳን ጎዶሎ ነው።
ተማሪዎች የጌታን “ውድ ምህረት” እንዲገነዘቡ ስታግዙ (1 ኛ ኔፊ1፥20)፣ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ እና በገዛ ልምዶቻቸው ውስጥ፣ ጌታ ከእነሱ ጋር እንዳለ እና በፍቃደኝነት ከጎናቸው እንደሚቆም ይሰማቸዋል እንዲሁም ያውቃሉ ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 68፥6 ይመልከቱ)። በግል ፍላጎታቸው እና ሁኔታቸው ውስጥ ስለጌታ ፍቅር እና ምህረት እውነታ ይመለከታሉ እንዲሁም ይሰማቸዋል።
ተማሪዎች ግንኙነታቸውን ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲያጠነክሩ እርዱ
ስለኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር እና የመማር አላማ እያንዳንዱ ሰው ወደ እርሱ እና ወደ ሰማይ አባታችን እንዲቀርቡ መርዳት ነው። የምታስተምሯቸውን ሰዎች ያንን አላማ በፍጹም እንዳይስቱ እርዱ። ቅዱሳት መጻህፍትን በማጥናት፣ ያለማቋረጥ ንስሃ በመግባት፣ ከሰማይ አባት ጋር በጸሎት በመነጋገር እና ስለአብ እና ወልድ በመመስከር ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠነክሩ አበረታቷቸው። ቃል-ኪዳኖችን ማድረግ እና መጠበቅ ከእነርሱ ጋር እንደሚያስተሳስረን ተማሪዎችን በቃል እና በምሳሌ አስተምሩ። ለእነርሱ ምንኛ ውድ እና ተወዳጅ እንደሆንን እንዲያውቁ እርዷቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ በፍፁም የሃጢያት ክፍያው አማካኝነት ወደ አባታችን የመመለሻ ብቸኛው መንገድ ስለመሆኑ ያላቸውን እምነት አጠንክሩ። ተማሪዎች “ስለአብ እና ወልድ [ከ]ሚመሰክረው” ከመንፈስ ቅዱስ ምስክርነትን እንዲቀበሉ እድሎችን ስጡ ( ሙሴ 5፥9 ይመልከቱ)።
ተማሪዎች በፍቃደኝነት የበለጠ እንደኢየሱስ ክርስቶስ ለመሆን እንዲጥሩ እርዱ
በመጨረሻም፣ ስለኢየሱስ ክርስቶስ መማር የበለጠ እንደእርሱ እንድንሆን ያነሳሳናል። ነገር ግን እንደእርሱ መሆን የሚከሰተው በክፍል ውስጥም ይሁን ከክፍል ውጪ በእምነት ስንተገብር፣ የእርሱን ምሳሌ ለመከተል ሆን ብለን ምርጫዎችን ስናደርግ እና ፀጋውን ስንቀበል ብቻ ነው። ተማሪዎች የበለጠ እንደአዳኙ መሆን የሚችሉባቸውን መንገዶች ያውቁ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንዲሹ ጋብዟቸው። ተማሪዎች እንደእርሱ መሆንን የሕይወት ተሞክሮ ለማድረግ ሲጥሩ ምሪትን እና እርዳታን ስጡ።
ያዕቆብ እንዲህ አስተምሯል “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ ከእግዚአብሔር የተሰጡት ሁሉም ነገሮች” ስለኢየሱስ ክርስቶስ ሊያተምሩን ይችላሉ (2 ኛ ኔፊ 11፥4)። ትምህርታችሁ ከነዚያ ነገሮች አንዱ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስን የእያንዳንዱ የማስተማር እና የመማር ልምድ ትኩረት አድርጉ። እናንተ እና ተማሪዎች “ስለክርስቶስ ስታወሩ፣ … በክርስቶስ ስትደሰቱ፣ … ስለ ክርስቶስ ስትሰብኩ” (2 ኛ ኔፊ 25፥26) መንፈስ ቅዱስ የአዳኙን ምስክርነት በእያንዳንዱ ሰው አዕምሮ እና ልብ ውስጥ መትከል ይችላል። ተማሪዎቻችሁ የሰማይ አባትን እና ኢየሱስ ክርስቶስን በራሳቸው እንዲያውቁ ስትረዱ፣ በመላ ሕይወታቸው ውስጥ ለእርዳታ፣ ለተስፋ እና ለፈውስ ወደ እነርሱ ይመለከታሉ።