መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እና ኢኒስቲትዩት
የምታስተምሯቸውን ውደዱ


“የምታስተምሯቸውን ውደዱ፣” በአዳኝ መንገድ ማስተማር፦ በቤት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚያስተምሩ ሁሉ [2022 (እ.አ.አ)]

“የምታስተምሯቸውን ውደዱ፣” በአዳኝ መንገድ ማስተማር

ምስል
ኢየሱስ ክርስቶስ በጉድጓድ አጠገብ ካለች ሴት ጋር ሲያወራ

አዳኙ እንደ ምሳሌያችን ፍቅር የትምህርታችን ማነሳሻ ይሆናል።

የምታስተምሯቸውን ውደዱ

በመላው ምድራዊ አገልግሎቱ፣ አዳኙ ያደረገው ማንኛውም ነገር በፍቅር የተነሳሳ ነበር። የክርስቶስ ትክክለኛ ተከታዮች ለመሆን ስንጥር፣ በዚህ ተመሳሳይ ፍቅር መሞላት እንችላለን ( ዮሐንስ 13፥34–35ሞሮኒ 7፥47–488፥26 ይመልከቱ)። የአዳኙ ፍቅር በልባችን ውስጥ ሲኖር ሌሎች ስለክርስቶስ እንዲማሩ እና ወደ እርሱ እንዲመጡ ለመርዳት እያንዳንዱን መንገድ እንሻለን። ፍቅር የትምህርታችን ማነሳሻ ይሆናል።

የምታስተምሯቸውን ለመውደድ

  • ተማሪዎችን እግዚአብሄር በሚያያቸው መልኩ እዩዋቸው።

  • እነሱን ለማወቅ እሹ—ያሉበትን ሁኔታ፣ ፍላጎታቸውን፣ እና ጥንካሬያቸውን ተረዱ።

  • ለእነሱ በስም ጸልዩላቸው።

  • የሚከበሩበት እና የሚያበረክቱት ነገር ዋጋ እንዳለው የሚያውቁበት ደህንነት ያለው ቦታ ፍጠሩ።

  • ፍቅራችሁን ለመግለጽ ተገቢ መንገዶችን ፈልጉ።

አዳኙ በእያንዳንዱ ባስተማራቸው ውስጥ መለኮታዊ ብቃትን ተመለከተ

ብዙ ሰዎች በኢያሪኮ ስለ ዘኬዎስ ማወቅ ያለባቸውን ነገሮች ያውቁ እንደነበር ገመቱ። ግብር ሰብሳቢ—የግብር ሰብሳቢ አለቃ ነበር፣ በእርግጥ—ሃብታም ነበር። በግልፅ፣ አጭበርባሪ እና ሙሰኛ እንደሆነ አሰቡ። ነገር ግን ኢየሱስ የዘኬዎስን ልብ ተመለከተ እናም የተከበረ “የአብርሐም ልጅን” አየ ( ሉቃስ 19፥1–10 ይመልከቱ)። አዳኙ ሰዎችን እንደሚመስሉት ሳይሆን የተመለከተው ነገር ግን በትክክለኛ ማንነታቸው—እና መሆን የሚችሉትን ነበር። እንደ ስሞዖን፣ እንድሪያስ፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ ባሉ ያልተገሩ አሳ አጥማጆች ውስጥ፣ የእርሱን ቤተክርስቲያን የወደፊት መሪዎች ተመለከተ። በሚፈራው አሰዳጅ ሳኦል ውስጥ፣ ለነገሥታት እና ለአገራት ወንጌሉን የሚሰብክ “የተመረጠ ፅዋ” ተመለከተ ( ሐዋርያት 9፥10–15 ይመልከቱ)። በእናንተ እና በምታስተምሩት በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ፣ አዳኙ ገደብ የለሽ አቅም ያላቸው የእግዚአብሔር ወንድ ወይም ሴት ልጅን ይመለከታል።

በምታስተምሯቸው ሰዎች መካከል ታማኞች እና የተለወጡ የሚመስሉ ሌሎች ደግሞ ፍላጎት የሌላቸው ወይም እብሪተኞች የሚመስሉ ሊኖሩ ይችላሉ። በምታዩት ነገር ላይ ብቻ በመመስረት ግምት ላለመውሰድ ተጠንቀቁ። አዳኙ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ከተመለከተው የተወሰነውን መንፈስ ቅዱስ እንድትመለከቱ ሊረዳችሁ ይችላል—እንዲሁም እርሱ እንደወደዳቸው እናንተም መውደድ እንድትጀምሩ ይረዳችኋል።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ስለምታስተምሩት ስለእያንዳንዱ ሰው አስቡ እና የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እያንዳንዱ እንዴት እንደሚሰማቸው አሰላስሉ። በእሱ ወይም በእሷ ውስጥ ምን ማየት ይችላሉ? እነዚህ ሃሳቦች ያንን ግለሰብ በምታስተምሩበት መንገድ ላይ እንዴት ተፅዕኖ ያደርጋል?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ 1 ኛ ሳሙኤል 16፥7መዝሙረ ዳዊት 8፥4–5ሮሜ 8፥16–17ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 18፥10–14

አዳኙ ያውቀናል እንዲሁም ሁኔታዎቻችንን፣ ፍላጎቶቻችንን እና ጥንካሬዎቻችንን ይረዳል

የሳምራዊቷ ሴት ወደ ጉድጓዱ የመጣችው የወንጌል መልዕክት ለመስማት አልነበረም ። ውኃ ለማግኘት ነበር የመጣችው። ነገር ግን አዳኙ የእሷ ጥማት ከአካላዊ የዘለለ እንደሆነ ሊገነዘብ ቻለ። አስቸጋሪ ያልተረጋጋ የግንኙነቶች ታሪክ እንደነበራት አወቀ። ስለዚህ ኢየሱስ ፈጣን ትኩረቷን የሳበ አካላዊ ፍላጎቷ የሆነውን—ሕይወትን የሚያለመልመውን ውኃ—ወስዶ “ከሕይወት ውኃ” እና “ከዘላለማዊ ሕይወት” ጥልቅ መንፈሳዊ ፍላጎቷ ጋር አገናኘው። በንግግራቸው መጨረሻ ላይ፣ በከፊል እንዴት በደንብ እንዳወቃት በመነሳሳት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነበረ ሴቲቷ ግላዊ ምስክርነት አገኘች። “ያደረኩትን ሁሉ [እርሱ] ነገረኝ” አለች። “እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” ( ዮሐንስ 4፥6–29 ይመልከቱ)።

ክርስቶስ መሰል አስተማሪ መሆን የምታስተምሩትን ሰዎች ማወቅ እና በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ለመረዳት መጣርን ያካትታል። ስለሕይወታቸው ፍላጎት ማሳየት እና ርህራሄን ማሳየት ትችላላችሁ። ታሪኮቻቸውን፣ ችሎታዎቻቸውን፣ ዝንባሌዎቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን ለመረዳት መንገዶችን መፈለግ ትችላላችሁ። እንዴት የበለጠ መማር እንደሚችሉ ማወቅ ትችላላችሁ። ጥያቄዎችን መጠየቅ፣ በጥንቃቄ ማዳመጥ እና መመልከት ትችላላችሁ። ከሁሉም በላይ መንፈስ ብቻ መስጠት የሚችለውን ግንዛቤ ለማግኘት መጸለይ ትችላላችሁ። አንድ ሰውን የበለጠ ስታውቁ እሱ ወይም እሷ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ውስጥ የበለጠ ግላዊ ትርጉም እና ኃይል እንዲያገኙ ለመርዳት ትችላላችሁ። የአንድ ሰውን ጥማት ስትረዱ በአዳኙ የሕይወት ውኃ እንዴት እንደምታረኩት መንፈስ ሊያስተምራችሁ ይችላል።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ስለምታስተምሯቸው ሰዎች ምን አስቀድማችሁ ታውቃላችሁ? ለእነሱ ጠቃሚ የሆነው ምንድን ነው ? ጥንካሬያቸው ምንድን ነው? ችግራቸውምንድን ነው? እነሱን የበለጠ ለመረዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ መዝሙረ ዳዊት 139፥1–5ማቴዎስ 6፥25–32ማርቆስ 10፥17–21ዮሐንስ 10፥143 ኛ ኔፊ 17፥1–9

አዳኙ ላስተማራቸው ሰዎች ጸለየ

ስምዖን ጴጥሮስ አዳኙ “ስምዖን፣ ስምዖን እነሆ ሰይጣን … [ተመኘህ]፣ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ” ብሎ ሲናገር ሲሰማ ምን እንደተሰማው አስቡ (ሉቃስ 22፥31–32)። ኢየሱስ ክርስቶስ ለእናንተ ወደ አብ እንደጸለየ ማወቃችሁ ተፅዕኖ የሚያደርግባችሁ እንዴት ነው? የጥንት አሜሪካ ህዝቦች እንደዚህ ዓይነት ልምድ ነበራቸው እናም እንዲህ ገለፁት፣ “እናም [ኢየሱስ] ወደ አብ ለእኛ ሲፀልይ በሰማነው ጊዜ ነፍሳችን የተሞላችበትን ዐይነት ደስታ ማንም ሊገምተው አይቻለውም” (3 ኛ ኔፊ 17፥17).

እናንተ ለሌላ ሰው—ሳታቋርጡ በስም ስትጸልዩ በውስጣችሁ ምን እንደሚከሰት ልታስቡም ትችላላችሁ። ጸሎታችሁ ስለዚያ ግለሰብ የሚሰማችሁን የቀየረው እንዴት ነው? ተግባራችሁን የቀየረው እንዴት ነው? በእርግጥ የሰማይ አባታችን ተማሪን የመርዳት ፍላጎት ያለውን የአስተማሪ ልባዊ ጸሎቶች ይሰማል እንዲሁም ይመልሳል። እና ብዙውን ጊዜ እነዚያን ጸሎቶች የሚመልስበት አንዱ መንገድ የአስተማሪውን ልብ በመንካት እና ተማሪው የእርሱ ፍቅር እንዲሰማው ለመርዳት እሱ ወይም እሷ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ወይም እንዲሉ በማነሳሳት ነው።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ስለምታስተምሯቸው ሰዎች ስታስቡ፣ ጸሎታችሁን የሚፈልግ የተለየ ፍላጎት ያለው ሰው ይኖር ይሆን? ስለእሱ ወይም ስለእሷ ምን ለመጸለይ ትገፋፋላችሁ? ተማሪዎች አንዳቸው ላንዳቸቸው እንዲጸልዩ ስትጋብዟቸው ምን ዓይነት በረከቶች ሊመጡ ይችላሉ?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ ዮሐንስ 17አልማ 31፥24–363 ኛ ኔፊ 18፥15–2419፥19–23፣ 27–34

አዳኙ ሁሉም የተከበሩ እና ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ እንደሚሰማቸው አረጋገጠ

በኢየሱስ ጊዜ የሐይማኖት መሪዎች የነበራቸው አጠቃላይ ዝንባሌ ሃጢያተኞችን ማግለል ነበር። በዚህ ምክንያት እነዚህ መሪዎች ኢየሱስ ከሃጢያተኞች ጋር መስተጋብር ሲፈጥር ሲመለከቱ ደነገጡ። ከእነዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር ግንኙነት የፈጠረ ሰው እንዴት መንፈሳዊ አስተማሪ ሊሆን ይችላል?

በእርግጥ ኢየሱስ የተለየ አቀራረብ ነበረው። በመንፈስ የታመሙትን ለመፈወስ ፈለገ ( ማርቆስ 2፥15–17ሉቃስ 4፥17–18 ይመልከቱ)። በዙሪያቸው ካሉት ሰዎች የተለዩትን ወይም አስቸጋሪ ታሪክ ያላቸውን ሰዎች ያለማቋረጥ አገለገለ፤ ሃጢያት ከሰሩት ጋርም መስተጋብርን ፈጠረ። የሮማ ወታደርን እምነት አደነቀ ( ማቴዎስ 8፥5–13 ይመልከቱ)። ታማኝ ያልሆነውን ግብር ሰብሳቢ ከታማኝ ደቀመዛሙርቱ መካከል አንዱ እንዲሆን ጠራው ( ማርቆስ 2፥14 ይመልከቱ)። አንዲት ሴት በማመንዘር ስትከሰስ፣ ደህንነት እንዲሰማት አደረገ እንዲሁም ንስሃ እንድትገባ እና የተሻለ ሕይወት እንድትኖር አነሳሳት ( ዮሐንስ 8፥1–11 ይመልከቱ)።

ነገር ግን ኢየሱስ ከዛ በላይ አደረገ። በተከታዮቹ መካከል ይህንኑ የመቀበል እና የፍቅር ተመሳሳይ ባህሪ አስፋፋ። ወንጌልን ለሁሉም ሰዎች ለማድረስ ጊዜው ሲደርስ የእርሱ ምሳሌ በእርግጥ በሐዋርያቱ ልቦች ውስጥ ነበር። በጴጥሮስ ቃላት ውስጥ እንደዚህ ተገለልጿል፦ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት [እንደማያዳላ] በእውነት አስተዋልሁ” (የሐዋርያት ስራ 10፥34)።

እያንዳንዱ ለማስተማር የተጠራችሁለት ሰው በተወሰነ መልኩ ያለመከበር እና ዋጋ ያለመሰጠት ስሜት የመሰማት እድሉ ሰፊ ነው። በምትወዷቸው እና በምታከብሯቸው መንገድ ተቀባይነት እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን እንደሚፈለጉ ማሳየት ትችላላችሁ። ነገሮች ዝግተኛ ቢመስሉም ታጋሽ በመሆን የማይመጡትን፣ ችግር ያለባቸውን ወይም ፍላጎት የሌላቸው የሚመስሉትን መገናኘት ትችላላችሁ። ችግራቸውን ከአማኞች ጋር በመካፈል እያንዳንዱ ደህንነት እና ምቾት እንዲሰማው መርዳት ትችላላችሁ ። ከዛ በላይም ማድረግ ትችላላችሁ። ትምህርቱ በመከባበር፣ በአባልነት እና በፍቅር መንፈስ የሚሰጥበበትን ሁኔታዎች ለመፍጠር እንዲረዷችሁ ሁሉንም ተማሪዎች ማነሳሳት ትችላላችሁ።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ አንድ ሰው የተከበረ እና ዋጋ ያለው የመሆን ስሜት እንዲሰማው ምን ያግዛል? እንድ ሰው ሌሎችን ለማክበር እና ዋጋ ለመስጠት ምን ያነሳሳዋል? ስለምታስተምሯቸው ሰዎች በጸሎት ስታስቡ፣ ሁሉም የተቀባይት እና የተፈላጊነት ስሜት እንዲሰማቸው ምን ለማድረግ ትነሳሳላችሁ?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ ዮሐንስ 42 ኛ ኔፊ 26፥27–28፣ 33አልማ 1፥263 ኛ ኔፊ 18፥22–25

ምስል
አባት ልጆችን ሲያስተምር

አስተማሪዎች የሚያስተምሯቸው ሰዎች የተወደዱ እንደሆኑ እንዲሰማቸው መርዳት ይችላሉ።

አዳኙ ፍቅሩን ላስተማራቸው ሰዎች ገለፀ

በኔፋውያን መካከል በድንቅ የሚያነቃቃ የትምህርት እና የአገልግሎት ቀን መጨረሻ ላይ ኢየሱስ የመሄጃ ሰዓቱ እንደደረሰ አየ። የሚጎበኛቸው ሌሎች ህዝቦች ነበሩት። “ወደ ቤታችሁ ሂዱና” አለ “እናም ለሚቀጥለው ቀን አዕምሮአችሁን አዘጋጁ።” ነገር ግን ሰዎቹ “እ[ያነቡ]” እዛው ቁጭ አሉ፣ “እርሱ ከእነሱ ጋር ትንሽ እንዲቆይ የሚፈልጉ በመምሰል በእርሱ ላይ [በማተኮር]” እየተመለከቱ። ያልተነገረ ፍላጎታቸውን በመገንዘብ እና “በርህራሄ በመሞላት” ኢየሱስ ትንሽ ቆየ (3 ኛ ኔፊ 17፥3፣ 5–6)። የታመሙትን እና የተጎሳቆሉትን ባረከ። ከእነሱ ጋር ተንበርክኮ ጸለየ። ከእነሱ ጋር አለቀሰ እናም ከእነሱ ጋር ተደሰተ።

3 ኛ ኔፊ 17 ውስጥ የሚገኙትን የአዳኙን ቃላት እና ተግባሮች በጸሎት ለማጥናት አስቡ። ላስተማራቸው ሰዎች ያሳየውን ፍቅር አሰላስሉ። የእርሱን የፍቅር መገለጫዎች በቅዱሳት መጻህፍት ሌሎች ቦታዎች ውስጥ ፈልጉ። ከዚያም ስለምታስተምሯቸው ሰዎች አስቡ። እንዴት ነው ለእነሱ ያላችሁን ፍቅር በተገቢ ሁኔታ መግለፅ የምትችሉት። መንፈስ ቅዱስ ይምራችሁ። ለምታስተምሯቸው ሰዎች ፍቅር መሰማት ወይም ያላችሁን ፍቅር መግለፅ ከባድ መስሎ ካገኛችሁት፣ ስለእግዚአብሔር ፍቅር በመመስከር ጀምሩ። ከዚያም “በልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ሁሉ ላይ በሚፈሰው [በክርስቶስ ንፁህ ፍቅር] ትሞሉ ዘንድ በሙሉ ልባችሁ ኃይል ወደ አብ ጸልዩ” (ሞሮኒ 7፥48)። እናም ትምህርትን ስለማስተማር ማሰባችሁ ፍቅርን በቃላችሁ እና በተግባራችሁ ከመግለፅ መቼም ሊገድባችሁ እንደማይገባ አስታውሱ። ብዙ ጊዜ ሰዎችን የምትንከባከቡበት መንገድ እንደምታስተምሯቸው ነገር ጠቃሚ ነው።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ አዳኙ ለእናንተ ያለውን ፍቅር እንድታውቁ የረዳችሁ እንዴት ነው? አንድ ወላጅ ወይም ሌላ አስተማሪ ፍቅሩ እንዲሰማችሁ የረዳችሁ እንዴት ነው? የምታስተምሯቸው ሰዎች እንደምትወዷቸው ያውቃሉ? አዳኙ እንደሚወዳቸው ያውቃሉ?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ ማርቆስ 6፥31–42ዮሐንስ 13፥3–16፣ 34–3515፥12–131 ኛ ቆሮንጦስ 13፥1–71 ኛ ዮሐንስ 4፥7–11

የምትማሩትን ነገር ተግባራዊ የምታደርጉባቸው አንዳንድ መንገዶች

  • ክፍል የምታስተምሩ ከሆነ፣ የተማሪዎችን ስሞች እወቁ እናም ስታስተምሩ ተጠቀሟቸው።

  • ተማሪዎች ሲሳተፉ ምስጋናችሁን ግለፁ።

  • ከማስተማራችሁ በፊት እና በኋላ ከተማሪዎች ጋር መስተጋብር ፍጠሩ።

  • ተማሪዎች እርስ በእርሳቸው የፍቅር እና የመከባበር መንፈስ እንዲያዳብሩ እርዷቸው።

  • ስታስተምሩ እና በሌሎች ጊዜዎች በደንብ አዳምጡ።

  • ለምታስተምሯቸው ሰዎች የአገልግሎት ድርጊቶችን አድርጉ።

  • ለምታስተምሯቸው ሰዎች ትርጉም የሚሰጡ መርሆዎች ላይ የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ የትምህርታችሁን ዕቅዶች ለመለወጥ ፍቃደኞች ሁኑ።

አትም