መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እና ኢኒስቲትዩት
በመንፈስ አስተምሩ


“በመንፈስ አስተምሩ፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር፦ በቤት እና በቤተክርስቲያን ለሚያስተምሩ ሁሉ [2022 (እ.አ.አ)]

“በመንፈስ አስተምሩ፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር

4:17

በመንፈስ አስተምሩ

አዳኙ፣ ጆሴፍ ስሚዝን እና ሲድኒ ሪግደንን ወንጌሉን እንዲሰብኩ ባዘዛቸው ጊዜ፣ እንዲህ ሲል ቃል ገባላቸው፣ “ለምትሉት ማንኛቸውም ነገሮች ሁሉ ምስክር ይሰጣችሁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ይላካል” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 100፥8፤ እንዲሁም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 42፥15–1750፥17–22ይመልከቱ)። ወንጌልን ለሚያስተምሩ ሁሉ እናንተንም ጨምሮ ተመሳሳይ ቃል ኪዳን ተግባራዊ ይሆናል። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ስታስተምሩ፣ መንፈስ ቅዱስ ሊመራችሁ እና እውነታውን ለምታስተምሯቸው ሰዎች አዕምሮ እና ልብ ሊመሰክር አብሯችሁ ሊሆን ይችላል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 8፥2 ይመልከቱ)። ስታስተምሩ ብቻችሁን አይደላችሁም ምክንያቱም “የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና” (ማርቆስ 13፥11)።

መንፈስ ቅዱስ እውነተኛ አስተማሪ ነው። ማንኛውም ስጋ ለባሽ አስተማሪ ምንም ያህል የተካነ ወይም ልምድ ያለው ቢሆን፣ እውነታን በመመስከር፣ ስለክርስቶስ በመመስከር እና ልብን በመቀየር የእርሱን ሚና መጫወት አይችልም። ነገር ግን ሁሉም አስተማሪዎች የእግዚአብሔርን ልጆች በመንፈስ እንዲማሩ በመርዳት መሳሪያዎች መሆን ይችላሉ።

በመንፈስ ለማስተማር

  • በመንፈስ እራሳችሁን አዘጋጁ።

  • ተማሪዎቹ ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች መንፈሳዊ ሀሳቦችን ስታገኙ ምላሽ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ ሁኑ።

  • በመንፈስ ቅዱስ የሚማሩበትን ቦታ እና ዕድል ፍጠሩ።

  • ተማሪዎች የግል ራዕይን እንዲሹ፣ እንዲያውቁ፣ እና ተግባራዊ እንዲያደርጉ አግዙ።

  • ብዙ ጊዜ ምስክርነታችሁን ስጡ፣ተማሪዎች ስሜታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ እና ምስክርነታቸውን እንዲያካፍሉ ጋብዙ።

አዳኙ ለማስተማር እራሱን በመንፈሣዊ ያዘጋጅ ነበር

ለአገልግሎቱ ለመዘጋጀት ኢየሱስ “ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን” 40 ቀናትን በምድረ በዳ ውስጥ አሳለፈ (የጆሴፍ ስሚዝ ትርጉም፣ ማቴዎስ 4፥1 [በ ማቴዎስ 4፥1፣ የግርጌ ማስታወሻ ])። ነገር ግን የእርሱ መንፈሳዊ ዝግጅት የጀመረው ከረዥም ጊዜ በፊት ነበር። ሰይጣን ሲፈትነው “ለዛች ሰዓት” ያስቀመጣቸውን “የሕይወት ቃላት” ሊጠቀም ቻለ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥85)። ለማስተማር እራሳችሁን በመንፈሣዊ ለማዘጋጀት ስለምታደርጓቸው ጥረቶች አስቡ። በመንፈሣዊ ዝግጅታችሁ ወቅት የአዳኙን ምሳሌ መከተል ስለምትችሉበት መንገድ ከማቴዎስ 4፥1–11 ምን ትማራላችሁ?

መንፈስ ትክክለኛ አስተማሪ እና የመለወጥ ትክክለኛ ምንጭ ነው። ኃይለኛ የወንጌል ትምህርት ዝም ብሎ ትምህርትን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ማስተማር ከመጀመራችሁ በፊት እራሳችሁን በመንፈሣዊ ማዘጋጀትን ይጠይቃል። በመንፈሣዊ ከተዘጋጃችሁ፣ ስታስተምሩ የመንፈስን ምሪት የበለጠ ለመስማት እና ለመከተል ትችላላችሁ። በትምህርታችሁ ውስጥ መንፈስ ቅዱስን የመጋበዝ መንገዱ እርሱን ወደ ሕይወታችሁ መጋበዝ ነው። ይህ የአዳኙን ምሳሌ በትጋት መከተልን እና ወንጌሉን በፍጹም ልባችሁ መኖርን ያካትታል። ማንኛችንም ይህን ፍፁም በሆነ ሁኔታ ማድረግ ስለማንችል፣ በተጨማሪ በየቀኑ ንስሃ መግባት ማለትም ነው።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ለማስተማር እራሳችሁን በመንፈሣዊ ማዘጋጀት ማለት ለእናንተ ምን ማለት ነው? እራሳችሁን በመንፈሣዊ የምታዘጋጁበትን መንገድ ለማሻሻል ምን ለማድረግ ትነሳሳላችሁ? መንፈሳዊ ዝግጅት በትምህርታችሁ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችለው እንዴት ይመስላችኋል?

ቅዱሳት መጻህፍት ፦ መጽሐፈ ዕዝራ 7፥10ሉቃስ 6፥12አልማ 17፥2–3፣ 9ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 11፥2142፥13–14

አዳኙ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ ነበር

የምኩራቡ አለቃ ኢያኢሮስ በኢየሱስ እግር ላይ በመውደቅ ለመሞት እያጣጣረች የነበረችውን ልጁን እንዲረዳት ተማፀነው። ኢየሱስ በድንገት በቆመ ጊዜ እርሱ እና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢያኢሮስ ቤት ወደሚያመራው የተጨናነቀ ጎዳና ላይ እየሄዱ ነበር። “ማነው የነካኝ?” ብሎ ጠየቀ። የማይጠበቅ ጥያቄ ይመስል ነበር—በሰዎች ግርግር ውስጥ ማን ነበር የማይነካው? ነገር ግን አዳኙ በዚያ ግርግር ውስጥ የሆነ ሰው በለተየ ፍላጎት እና እምነት የሚሰጠውን ፈውስ ለመቀበል እንደቀረበው ተገነዘበ። የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ለመጎብኘት አሁንም ሰዓት ይኖራል። ነገር ግን ልብሱን ለነካችው ሴት እንዲህ አላት፣ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል፣ በሰላም ሂጂ” ( ሉቃስ 8፥41–48ይመልከቱ)።

እንደ አስተማሪ አንዳንድ ጊዜ ለማስተማር የተዘጋጃችሁትን ለመጨረስ ስትቸኩሉ እራሳችሁን ልታገኙ ትችላላችሁ። ያ አስፈላጊ ሊሆን ቢችልም፣ በችኮላችሁ ሳታስቡት የምታስተምሩትን ግለሰብ አንገብጋቢ ፍላጎት አልፋችሁ አለመሄዳችሁን እርግጠኞች ሁኑ። ለማስተማር ስትዘጋጁ ከምትሹት መንፈሳዊ ምሪት በተጨማሪ፣ ስታስተምሩም የመንፈስ ምሪትን እሹ። የተማሪዎችን ፍላጎት፣ ጥያቄዎች እና ዝንባሌዎች ለማወቅ ሞክሩ። መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ ተማሪ ያስተማራችሁትን እንዴት እንደተቀበለ ወይም እንደተገነዘበ እንድታስተውሉ ሊረዳችሁ ይችላል። አንዳንዴ ዕቅዳችሁን እንድትቀይሩ ሊያነሳሳችሁ ይችላል። ለምሳሌ፣ አስባችሁት ከነበረው የበለጠ ብዙ ጊዜ በአንድ ርዕስ ላይ ማሳለፋችሁ ወይም አሁን ለተማሪዎች የበለጠ ጠቃሚ የሆነን ነገር ለማስቀደም የተወሰኑ ውይይቶችን ለወደፊት ማቆየታችሁ ሊገርማችሁ ይችላል።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ አንድ ወላጅ ወይም ሌላ አስተማሪ እንደተማሪ ያሏችሁን ፍላጎቶች እንደሚያውቅ መቼ ተሰምቷችሁ ያውቃል? የምታስተምሯቸው ሰዎች ትምህርቱን ከመጨረስ ይልቅ ፍላጎታችሁ እነሱ እንዲማሩ እንደሆነ ያውቃሉ? ፍላጎታችሁን በተሻለ ሁኔታ መግለፅ የምትችሉት እንዴት ነው?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ 1 ኛ ጴጥሮስ 3፥15አልማ 32፥1–940፥141፥142፥1

አዳኙ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ እንዲማሩ እድሎችን ሰጠ

በኢየሱስ ጊዜ እርሱ በእውነት ማን እንደነበረ መረዳት ለብዙ ሰዎች ከባድ ነበረ፣ ነገር ግን ብዙ አስተሳሰቦች ነበሩ። ደቀመዛሙርቱ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ሌሎችም ኤሊያስ፣ ሌሎችም ኤርሚያስ ወይም ከነቢያት አንዱ” ብለው መለሱ። ነገር ግን ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ የሌሎችን አስተያየት ወደ ጎን በመተው ወደገዛ ልባቸው እንዲመለከቱ የሚጋብዝን ጥያቄ እንዲህ ጠየቀ፦ “እናንተስ እኔን ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ?” መልሳቸውን “ከስጋ እና ደም” ሳይሆን፣ በቀጥታ “ከሰማያት [ካ]ለው አባ[ት]” እንዲያገኙት ፈለገ። እንደዚህ ዓይነት ምስክርነት ነበር—ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጣ የግል ራዕይ— ጴጥሮስን “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ እንዲናገር ያደረገው ( ማቴዎስ 16፥13–17ይመልከቱ)።

በኋለኞቹ ቀናት በመንፈስ ለመዳን፣ የምታስተምሯቸው ሰዎች የእውነትን መንፈሳዊ ምስክርነት ይፈልጋሉ። እርሱን ለእነሱ መስጠት አትችሉም፣ ነገር ግን እንዲሹት መጋበዝ፣ ማበረታታት፣ ማነሳሳት እና ማስተማር ተችላላችሁ። በቃላችሁ እና በተግባራችሁ አማካኝነት መንፈስ ቅዱስ ለወንጌል ትምህርት እንዴት አስፈላጊ እንደሆነ ግልፅ ማድረግ ትችላላችሁ። ለምሳሌ፣ ስለምትፈጥሩት እና ስለምታበረታቱት የትምህርት ሁኔታ አስቡ። በክፍል ውስጥ የወንበሮችን አቀማመጥ ወይም ለተማሪዎች ሰላምታ የምትሰጡበት እና መስተጋብር የምትፈጥሩበት መንገድ የመሳሰሉ ቀላል ነገሮች ተማሪዎች ለሚኖራቸው ልምድ መንፈሳዊ መድረክ ይፈጥራል። እናንተ ለማስተማር በመንፈስ እንደምትዘጋጁት ሁሉ ተማሪዎች እራሳቸውን ለመማር በመንፈስ እንዲያዘጋጁ መጋበዝም ትችላላችሁ። ለሚያመጡት መንፈስ ሃላፊነትን እንዲወስዱ ጠይቁ። መንፈስም ስለኢየሱስ ክርስቶስ እና ስለወንጌሉ ሲመሰክር እንዲሰማቸው ለእነሱ እድል መስጠት ትችላላችሁ። ያ ምስክርነት ለእነሱ እንደ “አለት” ይሆናቸዋል “የገሃነም ደጆችም አይች[ላቸውም]” (ማቴዎስ 16፥18)።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ለወንጌል ትምህርት መንፈሳዊ ሁኔታ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ምን ነገር ተገንዝባችኋል? የእሱን መገኘት የሚቀንሰውስ ምንድን ነው? የምታስተምሯቸው ሰዎች ከመንፈስ እንዲማሩ ምን ሊረዳቸው ይችላል? ብዙ ጊዜ የምታስተምሩበትን ቦታና ሁኔታ አስቡ። እዚያ ስትሆኑ ምን ይሰማችኋል? መንፈስ እዚያ እንዲገኝ እንዴት በውጤታማነት መጋበዝ ትችላላችሁ?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ ሉቃስ 24፥31–32ዮሐንስ 14፥2616፥13–15ሞሮኒ 10፥4–5ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 42፥16–1750:13–24

ሚስዮናውያን ቤተሰብን ሲያስተምሩ

ስናስተምር ተማሪዎች የራሳቸውን የእውነት መንፈሳዊ ምስክርነት እንዲሹ መጋበዝ እንችላለን።

አዳኙ ሌሎች ሰዎች ግላዊ መገለጥን እንዲሹ፣ እንዲገነዘቡ እና ተግባራዊ እንዲያደርጉ አግዟቸዋል

ጌታ ከእኛ ጋር መነጋገርን ይፈልጋል እንዲሁም ከእኛ ጋር እየተነጋገረ እንዳለ እንድናውቅ ይፈልጋል። በ1829 (እ.አ.አ)፣ ኦሊቨር ካውደሪ የተባለ የ22 ዓመት የትምህርት ቤት አስተማሪ ማንም ሰው ግላዊ ራዕይን መቀበል እንደሚችል የሚገልፀውን አስደሳች ትምህርት እየተማረ ነበር። ነገር ግን ብዙዎቻችን ከጠየቅናቸው ተመሳሳይ የሆኑ ጥያቄዎች ነበሩት “በእርግጥ ጌታ ለእኔ ለመናገር እየሞከረ ነውን? ምን እየተናገረ እንዳለ እንዴት ማወቅ እችላለሁ?” እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ኢየሱስ ክርስቶስ ኦሊቨርን ስለጥልቅ መንፈሳዊ የምርምር ጊዜ ወደኋላ ተመልሶ እንዲያስብ ጋበዘው። “ለአዕምሮህ ሰላምን አልተናገርኩኝምን?” ብሎ ጠየቀ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 6፥21–24ይመልከቱ)። ከዚያም መንፈስ ሊናገር ስለሚችልባቸው ሌሎች መንገዶች ኦሊቨርን አስተማረው ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 8፥2–39፥7–9፤ እንዲሁም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 11፥12–14ይመልከቱ)።

አብዛኛውን ጊዜ መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ በሚል ዓለም ውስጥ በመኖራችን፣ ሁላችንም የመንፈስን ድምፅ የመገንዘብ እርዳታን እንሻለን። ሳንገነዘበው መንፈስ ተሰምቶን ሊሆን ይችላል። ሁላችንም እንዴት መንፈስን መሻት፣ ተፅዕኖዎቹን መገንዘብ እና በሚሰጠን መነሳሳት ላይ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ እንደምንችል መማር እንችላለን። ስታስተምሩ መንፈስ የሚናገርበትን መንገዶች እና እንዴት ከእነሱ ጋር እንደተነጋገረ እንዲያውቁ ተማሪዎችን አግዙ። እንደአስተማሪ ከምትሰጧቸው ታላቅ ስጦታዎች ውስጥ አንዱ የምታስተምሯቸውን ሰዎች በዚህ የእድሜ ልክ ግላዊ ራዕይ ፍለጋ ሂደት መርዳት ነው።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ግላዊ ራዕይን ስለመቀበል መማር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ራዕይን እንዴት እንደምትሹ እና እንደምትገነዘቡ የሆነ ሰው ረድቷችሁ ያውቃልን? የምታስተምሯቸው ሰዎች ከመንፈስ ቅዱስ የሚያመጣን ራዕይ እንዲሹ፣ እንዲገነዘቡ እና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማበረታታት የምትችሉት እንዴት ነው?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ ገላትያ 5፥22–23አልማ 5፥45–47ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 42፥61121፥33ጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ 1፥8–20

አዳኙ ላስተማራቸው ሰዎች ምስክርነትን ሰጠ

በደግነት በማስተማር እና በማገልገል የተለየ ወቅት ኢየሱስ ወንድሟ የሞተባትን ማርታን ለማፅናናት ፈለገ። “ወንድምሽ ይነሳል” በማለት ስለዘላለማዊ እውነት ቀላል ምስክርነትን አካፈላት (ዮሐንስ 11፥23)። የእርሱ ምስክርነት የራሷን ምስክርነት እንድታካፍል ማርታን አነሳሳት፦ “በመጨረሻው ቀን በትንሳኤ እንዲነሳ አውቃለሁ” (ዮሐንስ 11፥24)። ይህ ክስተት በ ዮሐንስ 11፥25–27 ውስጥ እንዴት እንደተደገመ አስተውሉ። ስለ አዳኙ ምሳሌ ምን ያስደንቃችኋል? የወንጌል እውነቶችን ምስክርነት ማካፈል የማስተማር አስፈላጊ አካል የሆነው ለምንድን ነው?

ምስክርነታችሁ በምታስተምሯቸው ሰዎች ላይ ኃይለኛ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ምስክርነታችሁ ልብ የሚነካ ወይም ረዥም መሆን የለበትም። እንዲሁም “ምስክርነቴን ማካፈል እፈልጋለሁ” በማለት መጀመር የለበትም። በቀላሉ የምታውቁትን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አካፍሉ። የእውነት ምስክርነት ቀጥታ እና ከልብ ሲሆን በጣም ኃይል አለው። ስለአዳኙ፣ ስለወንጌሉ እና በሕይወታችሁ ውስጥ ስላለው የእርሱ ኃይል በተደጋጋሚ መስክሩ እንዲሁም የምታስተምሯቸው ሰዎች ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ አበረታቷቸው። አንዳንድ ጊዜ በጣም ኃይለኛ ምስክርነት የሚሰጠው በአስተማሪው ሳይሆን በተማሪው እንደሆነ አስታውሱ።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ አንድ ሰው ምስክርነት በማካፈል የሚያሳድረውን ኃይለኛ ተፅዕኖ የሚገልፁ ምሳሌዎችን በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ፈልጉ። ከነዚያ ምሳሌዎች ምን ትማራላችሁ? በሌላ ሰው ምስክርነት የተባረካችሁት መቼ ነበር? ምስክርነታችሁን ማካፈላችሁ በምታስተምሯቸው ሰዎች ላይ ተፅዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው? እናንተስ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ የሐዋርያት ስራ 2፥32–38ሞዛያ 5፥1–3አልማ 5፥45–4818፥24–4222፥12–18ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 46፥13–1462፥3

የምትማሩትን ነገር ተግባራዊ የምታደርጉባቸው አንዳንድ መንገዶች

  • ተማሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሲያጠኑ መንፈስ ቅዱስ ምን እንዳስተማራቸው እንዲያካፍሉ ጠይቋቸው።

  • ስታስተምሩ መንፈሳዊ መነሳሳትን ለመቀበል ቀደም ብላችሁ ተዘጋጁ።

  • ስትዘጋጁ የሚመጡትን መንፈሳዊ ግፊቶች ፃፉ።

  • መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምራቸውን ነገር በፀጥታ እንዲያሰላስሉ ለክፍል አባሎች አልፎ አልፎ እድል ስጡ።

  • የመንፈስ ተፅዕኖዎችን ለመጋበዝ ቅዱስ መዝሙርን እና ፎቶዎችን ተጠቀሙ።

  • ዕቅድ ስታወጡ እና ስታስተምሩ የመንፈስ መነሣሣትን አዳምጡ እንዲሁም ዕቅዶቻችሁን ለማስተካከል ፍቃደኞች ሁኑ።

  • ስለሚማሩት ነገር ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ለሁሉም ተማሪዎች ዕድል ስጡ።

  • መንፈስ ሲገኝ መገንዘብ እንዲችሉ ሌሎችን እርዱ።

  • ስለእነርሡ መመስከር እንድትችሉ የምታስተምሯቸውን እውነቶች ኑሯቸው።

  • በድንገተኛና መደበኛ ባልሆኑ ወቅቶች ለማስተማር መነሳሳቶችን ተከተሉ።