“ለመሪዎች—አስተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳት፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር፦ በቤት እና በቤተክርስቲያን ለሚያስተምሩ ሁሉ [2022 (እ.አ.አ)]
“ለመሪዎች—አስተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳት፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር
ለመሪዎች—አስተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳት
የአንድ ለአንድ መስተጋብሮች
ብዙ ጊዜ የአስተማሪዎችን የተለዩ ፍላጎቶች ለማሟላት የተሻለው መንገድ የአንድ ለአንድ መስተጋብሮች ናቸው። ለምሳሌ፣ እንደመሪ፣ ከክፍል በፊት ወይም በኋላ ስለ በአዳኙ መንገድ ማስተማር መርሆዎች ለመወያየት ከአንድ አስተማሪ ጋር አጭር ውይይት ልታደርጉ ትችላላችሁ። አስተማሪው ሲያስተምር በመመልከት ለዚህ ውይይት ልትዘጋጁ ትችላላችሁ። የአስተማሪውን ጥንካሬዎች በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እና እርዳታ መስጠት የምትችሉባቸውን መንገዶች ለማግኘት ፈልጉ።
በአስተማሪው ጥንካሬ ላይ መገንባት የመሻሻል እድሎችን እንደመለየት አስፈላጊ ነው። ምን በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንዳለ እና የት ላይ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት በራሳቸው እንዲያስቡ በመጠየቅ ውይይቶችን ከአስተማሪዎች ጋር መጀመር ይረዳል።
ከአስተማሪዎች ጋር ስትገናኙ ለሚያበረክቱት አገልግሎት በደግነት እና በምስጋና ለማጠናከር እና ለማበረታታት መንገዶችን አስቡ።
የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎች
እያንዳንዱ አጥቢያ አስተማሪዎች ስለክርስቶስ መሰል ትምህርት መርሆዎች በጋራ የሚመካከሩበት የሩብ ዓመት የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎችን ማካሄድ አለበት። የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎችን ለወላጆችም ማካሄድ ይቻላል ( አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፦በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል፣ 13.5፣ ChurchofJesusChrist.org)ይመልከቱ።
እነዚህ ስብሰባዎች መካሄድ የሚኖርባቸው መቼ ነው?
የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎች የሚካሄዱት እሁድ በ50 ደቂቃዎቹ የትምህርት ጊዜ ወቅት ነው።
-
የክህነት፣ የሴቶች መረዳጃ ማህበር እና የወጣት ሴቶች አስተማሪዎች በአካባቢ መሪዎች እንደተወሰነው በመጀመሪያው ወይም በሶስተኛው እሁድ ላይ መሳተፍ ይችላሉ።
-
የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪዎች በአካባቢ መሪዎች እንደተወሰነው በሁለተኛው ወይም በአራተኛው እሁድ ላይ መሳተፍ ይችላሉ።
-
የመጀመሪያ ክፍል አስተማሪዎች በአጥቢያ የመጀመሪያ ክፍል እና በሰንበት ትምህርት አመራሮች እንደተወሰነው በማንኛውም እሁድ መሳተፍ ይችላሉ። ከተፈለገ የመጀመሪያ ክፍል አስተማሪዎች ከሌሎች አስተማሪዎች ተለይተው ልጆችን ስለማስተማር የተለዩ ሁኔታዎች ለመማከር ለብቻቸው ሊሰበሰቡ ይችላሉ። ይህ በ20 ደቂቃ የመዝሙር ሰዓት፣ መደበኛው የእሁድ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ወይም በኋላ ወይም በሳምንቱ ሌላ ቀን ውስጥ ሊካሄድ ይችላል። የመጀመሪያ ክፍል አስተማሪዎች በተመሳሳይ ሳምንት ውስጥ ሁሉንም የመጀመሪያ ክፍል ክፍለ ጊዜዎችን ሳይሳተፉ እንዳይቀሩ ሲባል በየእሩብ ዓመቱ ከአንድ በላይ የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባ ሊካሄድ ይችላል። (ማስታወሻ፦ እንደአስፈላጊነቱ፣ የመጀመሪያ ክፍል አመራሮች ተተኪ አስተማሪዎችን ይመድባሉ፣ ክፍሎችን ያቀላቅላሉ ወይም የመጀመሪያ ክፍል አስተማሪዎች የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎችን እንዲሳተፉ ለመፍቀድ ሌላ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ።)
-
የወላጆች የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎች በአጥቢያ ምክር ቤት እንደተወሰነው በማንኛውም እሁድ ሊካሄዱ ይችላሉ።
ማን መካፈል ይኖርበታ?
ቢያንስ በእነዚያ ቡድኖች ወይም ክፍሎች ላይ ሃላፊነት ካለባቸው የክህነት ወይም የድርጅት መሪዎች ውስጥ አንዱን ጨምሮ ማንኛውም በአጥቢያ ውስጥ ወይም በክፍል ውስጥ የሚያስተምር ሰው መሳተፍ አለበት። አስፈላጊ ከሆነ፣ የሚያስተምሯቸውን ሰዎች ፍላጎት ባማከለ ሁኔታ ተሳታፊዎች በቡድኖች ሊከፈሉ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ የወጣቶች ወይም የልጆች አስተማሪዎች አልፎ አልፎ ወጣቶችን እና ልጆችን በማስተማር የተለዩ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ተለይተው በመሰብሰብ ሊጠቀሙ ይችላሉ።
ለወላጆች የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎች የአጥቢያ ምክር ቤቱ የተለዩ ወላጆችን ለመጋበዝ ወይም መሳተፍ ለሚፈልጉት ሁሉ ክፍት ለማድረግ ይወስናል።
እነዚህን ስብሰባዎች የሚመራው ማን ነው?
የአጥቢያ ምክር ቤቱ በሰንበት ትምህርት ቤት አመራር እርዳታ የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎችን ይመራል። በክፍሎች እና በስብሰባዎች ውስጥ በተመለከቱት ነገር ላይ በመመርኮዝ ስለአስተማሪዎች እና ስለተማሪዎች ፍላጎቶች በጋራ ይማከራሉ። ከ በአዳኝ መንገድ ማስተማር መርሆዎች እና ልምዶች ውስጥ የትኞቹ የለዩትን ፍላጎቶች የበለጠ እንደሚያሳኩ ለመወሰን በጋራ ይሰራሉ።
አብዛኛውን ጊዜ የሰንበት ትምህርት ቤት አመራር አባል የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎችን ይመራል። ይሁን እንጂ፣ የሌላ አጥቢያ አባላት አልፎ አልፎ ስብሰባዎችን እንዲመሩ ሊመደቡ ይችላሉ። የቡድኖች እና የድርጅት አመራሮች በስብሰባ ላይ ውይይት በተደረገባቸው መርሆዎች እና ተግባሮች አስተማሪዎቻቸውን ያጠናክራሉ።
በአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባ ውስጥ ምን ይካሄዳል?
የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባ ይህንን መልክ መያዝ ይኖርበታል፦
-
አካፍሉ እንዲሁም በጋራ ተማከሩ። አስተማሪዎች የቅርብ ጊዜ የትምህርት ልምዶችን እንዲያካፍሉ ጋብዙ፣ ከትምህርት ጋር የሚዛመዱ ጥያቄዎችን ጠይቁ እንዲሁም ተግዳሮቶችን የማሸነፍ ሃሳቦችን አካፍሉ። ይህ የስብሰባ ክፍል ባለፈው ስብሰባዎች ላይ ውይይት የተደረገባቸው መርሆዎች ክለሳን ማካተት ይችላል።
-
በጋራ ተማሩ። በዚህ ግብአት ውስጥ ከቀረቡት የሚከተሉት መርሆዎች ውስጥ አንዱን እንዲወያዩ አስተማሪዎችን ጋብዙ፦ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አተኩሩ፣ የምታስተምሯቸውን ሰዎች ውደዱ፣ በመንፈስ አስተምሩ፣ ትምህርቱን አስተምሩ እና በትጋት መማርን ጋብዙ። በአጥቢያ ምክር ቤት ካልተወሰነ በስተቀር መርሆዎቹ በማንኛውም ቅድመ ተከተል መሰጠት ይችላሉ፣ የስብሰባው ተሳታፊዎች ቀጣዩን መርህ ለውይይት መምረጥ ይችላሉ። አስፈላጊ ከሆነ በአንድ መርህ ላይ ከአንድ በላይ ስብሰባን ማድረግ ትችላላችሁ።
-
አቅዱ እና ጋብዙ። አስተማሪዎች የተወያዩበትን መርሆ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ እንዲያቅዱ እርዱ። እንደተገቢነቱ፣ የተወያያችሁበትን ክህሎት በጋራ መለማመድም ትችላላችሁ። በሚያስተምሩት ውስጥ መርሆውን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ የሚቀበሉትን ማንኛውንም መነሳሳቶች እንዲመዝግቡ እና እንዲተገብሩ ጋብዟቸው። ውይይት የሚደረግበትን የሚቀጥለውን መርህ ማጥናት እንዲጀምሩ አበረታቷቸው።
በተቻለ አቅም፣ የአስተማሪ ምክር ቤት ስብሰባዎች ወይይት እየተደገረባቸው ያሉትን መርሆዎች አርአያ ያደረጉ መሆን ይኖርባቸዋል።
አዲስ የተጠሩ አስተማሪዎችን ማሰልጠን
እንደመሪ፣ በድርጅታችሁ ውስጥ “አዲስ ከተጠሩ አስተማሪዎች ጋር የመገናኘት” እና “ለጥሪያቸው እንዲዘጋጁ እነሱን የመርዳት” ሃላፊነት አለባችሁ (የአጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፣ 17.3፣ ChurchofJesusChrist.org)። እነዚህ ስብሰባዎች አዲስ አስተማሪዎችን ከቅዱስ ጥሪዎቻቸው ጋር የማስተዋወቂያ እና በአዳኙ መንገድ ማስተማር ምን ማለት እንደሆነ በራዕይ የማነሳሳት እድል ናቸው። እንደመሪ፣ የሚከተሉትን በማድረግ አዲስ አስተማሪዎችን ለማገልገል እንዲዘጋጁ መርዳት ትችላላችሁ።
-
አዳኙ በጥሪያቸው ውስጥ እንደሚረዳቸው ያላችሁን ልበ ሙሉነት ግለፁ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥78 ይመልከቱ)።
-
የዚህን የመረጃ ምንጭ ቅጂ ለአዲስ አስተማሪዎች ስጡ እንዲሁም መርሆዎቹን በትምህርታቸው ውስጥ ለመተግበር መንገዶች እንዲፈልጉ አበረታቷቸው።
-
እነሱ ስለድርጅታችሁ ቢያውቋቸው የሚረዷቸውን ነገሮች ለአዲስ አስተማሪዎች አካፍሉ።
-
እንደአስፈላጊነቱ፣ አዲስ አስተማሪዎች በየትኛው ክፍል ውስጥ እንደሚያስተምሩ እና ከየትኛው ትምህርት እንደሚጀምሩ ንገሯቸው። ስለክፍላቸው እና የክፍል አባሎች የሚፈልጉትን ማንኛውንም መረጃ ስጡ።
-
በጥሪያቸው መርዳት እንደምትችሉ ለአዲስ አስተማሪዎች ግለፁ። አስፈላጊ ከሆነ በክፍል ውስጥ እና የትምህርት ግብዓቶችን በማግኘት ላይ ደጋፍ ስጡ።
-
የአስተማሪ ክፍሎችን አልፎ አልፎ እንደምትመለከቱ እና በመንፈስ በመነሳሳት አስተያየቶችን እንደምታቀርቡ ግለፁ።
-
በእሩብ ዓመታዊ የአስተማሪዎች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ አስተማሪዎችን ጋብዙ።