“በትጋት መማርን ጋብዙ፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር፦ በቤት እና በቤተክርስቲያን ለሚያስተምሩ ሁሉ [2022 (እ.አ.አ)]
“በትጋት መማርን ጋብዙ፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር
በትጋት መማርን ጋብዙ
በእርግጥ አዳኙ በውኃ ላይ ሲራመድ መመልከት በጣም የሚያነሳሳ ነበር። ነገር ግን ያ ለጴጥሮስ በቂ አልነበረም። አዳኙ ያደረገውን ለማድረግ፣ የነበረበት ቦታ ለመሆን እና ራሱ ተመሳሳይ ልምድ ለማግኘት ፈለገ። “በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ሲል ተናገረ። አዳኙ “ና” ብሎ ቀላል ግብዣ በማቅረብ መልስ ሰጠ። በዚያም ጴጥሮስ ከጀልባው ምቾት ወጣ እናም ደቀመዝሙርነት የተግባር ልምድ እንደሆነ አሳየን (ማቴዎስ 14፥24–33 ይመልከቱ)። በክርስቶስ እምነትን እና ያላሰለሰ ጥረትን ይጠይቃል። ነገር ግን ከአዳኙ ጋር የመጓዝን የካበተ በረከት ያመጣል።
“ኑ።” “ኑ እና ተመልከቱ።” “ኑ፣ ተከተሉኝ።” “ሂድ አንተም እንዲህ አድርግ” (ማቴዎስ 14፥29፤ ዮሐንስ 1፥39፤ ሉቃስ 18፥22፤ 10፥37)። ከአገልግሎቱ መጀመሪያ ጀምሮ አዳኙ ለተከታዮቹ የሰጣቸውን እውነቶች፣ ኃይል እና ፍቅር ለግላቸው እንዲለማመዱ ጋበዘ። ይህን ያደረገው መማር ማለት በእርግጥ ይሄ ስለሆነ ነው። ማዳመጥ ወይም ማንበብ ብቻ ሳይሆን መለወጥ፣ ንስሃ መግባት እና እድገት ማሳየት ማለትም ነው። በአዳኙ አገላለጽ መማር የሚመጣው “በማጥናት እንዲሁም በእምነት” ነው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥118፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል)። እምነት ደግሞ በሌላው ተጽዕኖ እንዲደርስ ሳይሆን በራሳችን ምርጫ መተግበርን ያካትታል (2 ኛ ኔፊ 2፥26ይመልከቱ)።
የአዳኙን ምሳሌ ስንከተል የምናስተምራቸው ሰዎች እንዲጠይቁ፣ እንዲሹ እና እንዲያንኳንኩ ከዚያም እንዲያገኙ እንጋብዛለን ( ማቴዎስ 7፥7–8)። ያንንም ግብዣ እራሳችን እንቀበላለን። በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት እና ያላሰለሰ ጥረት ከእርሱ ጋር መራመድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ራሳችን እናውቃለን።
አዳኙ ሌሎች ለትምህርታቸው ሃላፊነትን እንዲወስዱ አገዘ
ውቅያኖሶችን በደህና ማቋረጥ የሚችል ጀልባ መገንባት ለማንም ሰው ከባድ ነው። የያሬድ ወንድም ስለጀልባዎቹ ቅርፅ እና እንዴት እንደሚናፈሱ መመሪያዎችን በመቀበል “ያለማቋረጥ በጌታ እጅ ተመራ” (ኤተር 2፥6)። ነገር ግን የያሬድ ወንድም በጀልባ ውስጥ ብርሃንን እንዲሰጠው ጌታን ሲጠይቅ ጌታ ከመለሰበት መንገድ ምን አስተዋላችሁ? ( ኤተር 2፥22–25)። የያሬድ ወንድም በዚህ መልኩ እምነቱን እንዲለማመድ በቀረበለት ግብዣ እንዴት ነው የተባረከው? (ኤተር 3፥1–16)።
ተማሪዎች ማወቅ አለባቸው ብላቸችሁ የምታስቧቸውን ነገሮች ሁሉ መንገር ቀላል ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ፣ ሽማግሌ ዴቪድ ኤ.ቤድናር እንዲህ መክረዋል፦ “የእኛ ዓላማ ‘ምን ልንገራቸው’ መሆ የለበትም። ከዚያ ይልቅ፣ እራሳችንን መጠየቅ ያለብን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ነው፣ ‘ምን እንዲያደርጉ ልጋብዛቸው? ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ከሆኑ፣ መንፈስ ቅዱስን ወደ ሕይወታቸው መጋበዝ የሚጀምር ምን ዓይነት የተነሳሳ ጥያቄዎች ልጠይቅ?’” (evening with a General Authority፣ የካቲት 7፣ 2020 (እ.አ.አ)፣ broadcasts.ChurchofJesusChrist.org)።
ተማሪዎች ለትምህርታቸው ሀላፊነት እንዲወስዱ እንዴት እንደምትጋብዙ አስቡ። ለምሳሌ፣ የራሳቸውን ጥያቄዎች ለመጠየቅ እንዲችሉ፣ መልሶችን እንዲፈልጉ፣ እንዲያሰላስሉ እንዲሁም ሃሳባቸውን እና ስሜታቸውን እንዲያካፍሉ ወይም እንዲመዘግቡ መጋበዝ ትችላላችሁ። ይህን ሲያደርጉ እምነታቸውን ያጠነክራሉ፣ በእግዚአብሔር ቃላት ውስጥ እውነቶችን ያገኛሉ እንዲሁም ከእነዚህ እውነቶች የራሳቸውን ልምዶች ያገኛሉ። ለትምህርታችን ሃላፊነትን ስንወስድ፣ ጆሴፍ ስሚዝ “በራሴ ተማርኩኝ” እንዳለው ማለት እንችላለን (የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ 1፥20)።
የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ተማሪዎች በትምህርታቸው ረገድ ምላሽ የማይሰጡ ከመሆን ይልቅ ንቁ መሆን ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? ተማሪዎች ለትምህርታቸው ሀላፊነት እንዲወስዱ እንዴት መርዳት ትችላላችሁ? አስማሪዎች ይህን እንድታደርጉ ያገዟችሁ እንዴት ነው? ከቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ሰዎች በራሳቸው እንዲማሩ የተጋበዙበትነን ምን ምሳሌ ማሰብ ትችላላችሁ? እነዚህ ምሳሌዎች በምታስተምሩበት መንገድ ላይ ተፅዕኖ ያደረጉት እንዴት ነው?
ከቅዱሳት መጻህፍት፦ 1 ኛ ኔፊ 11፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 9፥7–8፤ 58፥26–28፤ 88፥118–125፤ የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ 1፥11–20
አዳኙ ሌሎች የእርሱን ቃል በማጥናት እርሱን ወደማወቅ እንዲመጡ አበረታቷል
በኋለኛው ቀናት ውስጥ አዳኙ ቤተክርስቲያኑን በይፋ የሚያቋቁምበት ጊዜ በመጣ ጊዜ፣ አገልጋዮቹን “በተፃፉ ነገሮች ላይ ተመኩ” ብሎ ነገራቸው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 18፥3)። በእርግጥ ተርጉመው ለመጨረስ ትንሽ ቀርቷቸው የነበረው መጽሐፈ ሞርሞን፣ ጥምቀት እንዴት እንደሚከናወን፣ ቅዱስ ቁርባንን የማካፈል ስራ እንዴት እንደሚሰራ እና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን ጨምሮ ለስራው ጠቃሚ መመሪያን ይዟል። ነገር ግን አዳኙ አገልጋዮቹ የእርሱን ራዕዮች እርሱን ለመስማት እና እርሱን ይበልጥ በጥልቅ ለማወቅ እንደሚያስችል እድል እንዲያዩም ፈለገ። በዚያው ራዕይ ውስጥ እንዲህ ነገራቸው፣ “ለእናንተ እነዚህን የሚናገራችሁ ድምፄ ነው፤ … ስለዚህ ድምፄን እንደሰማችሁ እና ቃላቴን እንደምታውቁ መመስከር ትችላላችሁ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 18፥35–36)።
ስለምታስተምሯቸው ሰዎች አስቡ። የቅዱሳት መጻህፍት ጥናትን እንዴት ይመለከቱታል? እናንተስ እንዴት ታዩታላችሁ? ከዕለት ተዕለት ግዴታ በላይ ነው? ቅዱሳት መጻህፍትን ስታጠኑ አዳኙ በቀጥታ ለእናንተ ሲናገር ይሰማችኋል? ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፦ “እርሱን ለመስማት የት መሄድ እንችላለን? ወደ ቅዱሳት መጻህፍት ለመሄድ እንችላለን።… በእነዚህ ረብሻ በሚበዛባቸው ቀናት፣ ለመንፈሳዊ ደህንነት በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ በየቀኑ መጥለቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የክርስቶስን ቃላት በየዕለቱ በምንመገብበት ጊዜ፣ ያጋጥሙናል ብለን ላላሰብናቸው ችግሮች እንዴት ምላሽ እንደምንሰጥ የክርስቶስ ቃሎች ይነግሩናል (“Hear Him፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2020 (እ.አ.አ)፣ 89)። ስታስተምሩ ተማሪዎች አዳኙን በማግኘት ዓላማ ማለትም ስለ እርሱ እውነቶችን ወይም ጥቅሶችን ለማግኘት ብቻ ሳሆይን ነገር ግን እርሱን ለማግኘት ቅዱሳት መጻህፍትን እንዲያጠኑ አበረታቱ። በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ የጌታን ድምፅ በየቀኑ መስማት ለእድሜ ልክ የትጋት፣ የግል የወንጌል ጥናት መሰረታዊ ነገር ነው።
የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ የግላችሁን የቅዱስ ጽሁፍ ጥናት ልምድ አስቡ። የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት ከእርሱ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ያጠነከረው እንዴት ነው? ጥናታችሁን ለማሻሻል ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ሌሎች የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት እና በየወቅቱ እንዲያጠኑ ማነሳሳት የምትችሉት እንዴትነው? ይህን ሲያደርጉ ምን ዓይነት በረከቶችን መቀበል ይችላሉ?
ከቅዱሳት መጻህፍት፦ ኢያሱ 1፥8፤ 2 ኛ ጢሞቴዎስ 3፥15–17፤ 2 ኛ ኔፊ 32፥3፤ ያዕቆብ 2፥8፤ 4፥6፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 33፥16
አዳኙ፣ ሌሎች ለመማር እንዲዘጋጁ ጋበዘ
ምርጥ የሆነው ዘርም እንኳን እራሱ በጠንካራ፣ በድንጋያማ ወይም በእሾኻማ መሬት ላይ አይበቅልም። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በጣም ድንቅ እና እምነትን የሚጭር ትምህርት ለመቀበል ዝግጁ ያልሆነን ልብ ሊቀይር አይችልም። ያ ስለዘሪ፣ ስለዘር እና የተለያየ ሁኔታ ስላለው የአፈር አይነት አዳኙ የተናገረው ምሳሌ መልዕክት አካል ነው። “በመልካም መሬት” ውስጥ ማለትም ከመንፈሳዊ ድንጋዮች እና እሾኮች በለሰለሰ እና በጠራ ልብ ውስጥ ነው የእግዚአብሔር ቃል ሕይወት የሚሰጥ ፍሬ የሚያፈራው (ማቴዎስ 13፥1–9፣ 18–23)።
መንፈሳዊ ዝግጁነት ለእናንተ እና ለምታስተምሯቸው ሰዎች ዋጋ አለው። ስለዚህ ልቦቻችን ለእግዚአብሔር ቃል “መልካም መሬት” እንዲሆኑ ለማዘጋጀት የምንረዳው እንዴት ነው ? በሕይወታችሁ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የምትችሏቸው እና በምታስተምሯቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ልታበረታቱ የምትችሏቸውን የሚከተሉትን የዝግጅት መርሆዎች አስቡ። ጌታ እንድትማሩ የሚፈልገውን ነገር ለማወቅ ጸልዩ። በሕይወታችሁ ውስጥ የእርሱን መገኘት በሚጋብዝ መልኩ ኑሩ። በየቀኑ ንሥሃ ግቡ። ከልብ የሆኑ ጥያቄዎችን በመጠየቅ የመማር ፍላጎታችሁን መግቡ። እርሱ ወደ መልሶች እንደሚመራችሁ በማመን የእግዚአብሔርን ቃል አጥኑ። እርሱ ለሚያስተምራችሁ ለማንኛውም ነገር ልባችሁን ክፈቱ።
ተማሪዎች በዚህ መልኩ ለመማር ሲዘጋጁ፣ ጌታ እንዲያውቁ የሚፈልገውን ነገር ለማየት እና ለመስማት መንፈሳዊ አይኖች እና ጆሮዎች ይኖራቸዋል (ማቴዎስ 13፥16 ይመልከቱ)።
የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ራሳችሁን ለመማር ለማዘጋጀት ምን ታደርጋላችሁ? ዝግጅታችሁ የእግዚአብሔርን ቃል በምትመለከቱበት፣ በምትሰሙበት እና በምትረዱበት መንገድ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ሌሎች ለመማር እንዲዘጋጁ የምታነሷሷቸው እንዴት ነው? ያ የወንጌልን እውነታዎች በሚቀበሉበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?
ከቅዱሳት መጻህፍት፦ ኢኖስ 1፥1–8፤ አልማ 16፥16–17፤ 32፥6፣ 27–43፤ 3 ኛ ኔፊ 17፥3
አዳኙ ሌሎችን የተማሩትን እውነቶች እንዲያካፍሉ አበረታታ
ጌታ ሔኖክን ወንጌል እንዲሰብክ ሲጠራው “አፌ ኮልታፋ ነው” በማለት አዘነ። ነገር ግን አንደበተ ርዕቱነት የጌታ አገልጋይ ለመሆን መስፈርት ሆኖ አያውቅም። ከዚያ ይልቅ፣ አንደበቱን ለመክፈት በቂ እምነት ካለው ቃላቶች እንደሚመጡ ጌታ ለሔኖክ ቃል ገባለት። “እኔም የምትናገረውን እሰጥሃለሁ፣” አለው (ሙሴ 6፥31–32)። ሔኖክ እምነቱን ተለማመደ እናም ጌታ በእርግጥ በእሱ አማካኝነት ሰዎቹ እንዲንቀጠቀጡ ያደረጋቸውን ኃይለኛ ቃላትን ተናገረ (ሙሴ 6፥47 ይመልከቱ)። በእርግጥ መሬት እራሷ እንድትንቀጠቀጥ አደረጓት። “የሔኖክም ቃላት በጣም ሀይለኛ ስለነበሩና እግዚአብሔር የሰጠው ቋንቋ በጣም ሀይለኛ ስለነበር” ተራሮች ጠፉ፣ ወንዞች መስመራቸውን ቀየሩ እናም አገራት የእግዚአብሔርን ሰዎች ፈሩ (ሙሴ 7፥13)።
ጌታ ነቢያቱ ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም የእርሱን ቃል ለመናገር ኃይል እንዲኖረን ይፈልጋል። የምታስተምሯቸውን ሰዎች ጨምሮ ሁላችንም ያ እንዲኖረን ይፈልጋል ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥-20–21ይመልከቱ)። ቃላችን ተራራዎችን ላያንቀሳቅሱ ወይም የወንዞችን መስመር ላያስቀይሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ልብን ለመቀየር መርዳት ይችላሉ። ለዚያ ነው ተማሪዎች ስለአዳኙ እና ስለ ወንጌሉ የሚማሩትን ነገር አንዳቸው ለሌላቸው እንዲያካፍሉ ዕድል መስጠት በጣም አስፈላጊ የሆነው። ይህን ማድረግ የሚማሩትን እውነቶቸ የራሳቸው እንዲያደርጓቸው እና እንዲገልጿቸው ይረዳቸዋል። በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ እውነቶችን በማካፈል ችሎታቸው ረገድ ድፍረት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።
የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ስለአንድ የወንጌል እውነት ከሆነ ሰው ጋር የተነጋገራችሁበትን ጊዜ አስቡ። ከዚህ ልምድ ምን ተማራችሁ? የሆነ ሰው ሃሳቡን እና እምነቱን ለማካፈል ድፍረት በማግኘቱ አመስጋኝ የሆናችሁት መቼ ነበር? የምታስተምሯቸው ሰዎች ስለሚማሯቸው ነገሮች ለማውራት በሚያገኟቸው ዕድሎች ተጠቃሚ የሚሆኑት እንዴት ነው? ምን ዓይነት ዕድሎችን ልትፈጥሩላቸው ትችላላችሁ?
ከቅዱሳት መጻህፍት፦ አልማ 17፥2–3፤ ሞሮኒ 6፥4–6፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥85፤ 88፥122፤ 100፥5–8
አዳኙ ሌሎች ያስተማራቸውን እንዲኖሩ ጋበዘ
“ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።” “ጠላታችሁን ወደዱ።” “ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል።” “በቀጥታው ደጅ ግቡ።” (ማቴዎስ 5፥16፣ 44፤ 7፥7፣ 13።) በአዳኙ መላ ምድራዊ አገልግሎቱ ውስጥ የተወሰኑት እጅግ ግልጽ የሚታወሱ ግብዣዎች የተነገሩት የገሊላን ባሕር ቁልቁል በሚያሳየው ተራራ ላይ ደቀመዛሙርቱን ሲያስተምር ነበር። የአዳኙ ዓላማ በመጨረሻ ግብዣው ግልፅ እንደተደረገው ሕይወትን መቀየር ነበር፦ “ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው፣ ሁሉ፣ ቤቱን በአለት ላይ እንደሰራ እንደ ጠቢብ ሰው አመሳስለዋለሁ” (ማቴዎስ 7፥24፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል)።
ዝናብ ይዘንባል ፤ ጎርፍ ይመጣል እንዲሁም ንፋስ በእያንዳንዱ ሕይወት ውስጥ ይነፍሳል። ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በሙሉ መቋቋም ቢችሉ ስለወንጌል መማር በቂ አይሆንም። ለዚህ ነው ተማሪዎች የሚማሩትን ነገር እንዴት መኖር እንደሚችሉ እንዲያስቡ ለመጋበዝ ማቅማማት የሌለብን። የሌሎችን ምርጫ ለማክበር ሲባል ብዙዎቹ ግብዣዎቻችን ጠቅለል ያሉ ይሆናሉ፦ “ምን ለማድረግ ትነሳሳላችሁ?” አልፎ አልፎ ግብዣዎቻችን የበለጠ ግልፅ መሆን ሊኖርባቸው ይችላል፦ “መለማመድ የምትፈልጉትን የአዳኙን አንድ ባህሪ ትመርጣላችሁን?” ተማሪዎች ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጡትን መነሳሳቶች እንዲሰሙ፣ እንዲገነዘቡ እና እንዲያካፍሉ ዕድሎችን ስትሰጡ፣ ምን ዓይነት የግል ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው እርሱ ያስተምራቸዋል። ተማሪዎች የተማሩትን ነገር ሲተገብሩ የሚከተሉትን በረከቶች እንዲያስቡ አግዙ እንዲሁም ከባድ በሚሆንበት ሰዓት እንዲጠነክሩ አበረታቱ። እውነትን መኖር ለታላቅ እምነት፣ ለምስክርነት እና ለመለወጥ ፈጣኑ መንገድ ነው። አዳኙ እንዳለው፣ የአብን ትምህርት መኖር ለሁላችንም ትምህርቱ በእርግጥ እውነት እንደሆነ የምናውቅበት መንገድ ነው (ዮሐንስ 7፥17 ይመልከቱ)።
የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ የሆነ ሰው ባቀረበው ግብዣ ምክንያት ለመተግበር የተነሳሳችሁት መቼ ነው? በዚያ ምክንያት ሕይወታችሁ የተለወጠው እንዴት ነው? በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ እና በቤተክርስቲያን መሪዎች የተሰጡትን ግብዣዎች ልብ በሉ። ሌሎች እንዲተገብሩ ስትጋብዙ የሚረዳችሁን ምን ነገር ትማራላችሁ? በምን ዓይነት መንገድ ግብዣችሁን መከታተል ትችላላችሁ?
ከቅዱሳት መጻህፍት፦ ሉቃስ 10፥36–37፤ ዮሐንስ 7፥17፤ ያዕቆብ 1፥22፤ ሞዛያ 4፥9–10፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 43፥8–10፤ 82፥10